መጋቢት 10 ፣ 2013

“መካለል ያለብን ወደ ማረቆ ነው” ያሉ ዜጎች ሠላም ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ሰልፍ አካሄዱ

ወቅታዊ ጉዳዮች

የደቡብ ክልል መንግስት ልዩ ኃይል ሕገ-መንግስታዊ ጥያቄ በመጠየቃችን ምክንያት ሊገድለንና ከቤት ንብረታችን ሊያፈናቅለን አይገባውም

“መካለል ያለብን ወደ ማረቆ ነው” ያሉ ዜጎች ሠላም ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ሰልፍ አካሄዱ

“እኛ ወደ ማረቆ የመካለል እንጂ በመስቃን ወረዳ ስር የመደራጀት ፍላጎት የለንም” ያሉ ሰልፈኞች አዲስ አበባ በሚገኘው የሠላም ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ሕንፃ “ቅሬታችንን ስሙን” በማለት ሰልፍ አካሄደዋል።
 

ሰልፈኞቹ “ወደ ማረቆ መካለል ያለባቸው ዘጠኝ ቀበሌዎች ወደ መስቃን እንዲካለሉ መደረጉ አግባብነት የለውም በሚል ተቃውሞ በማሰማታችን ምክንያት የደቡብ ክልል ባሰማራቸው ልዩ ኃይሎች ጥቃት እየደረሰብን ነው” ሲሉ አማረዋል።
 

የደቡብ ክልል መንግስት ልዩ ኃይል ሕገ-መንግስታዊ ጥያቄ በመጠየቃችን ምክንያት ሊገድለንና ከቤት ንብረታችን ሊያፈናቅለን አይገባውም ያሉት ሰልፈኞቹ በስፍራው የመጀመሪያው ግጭት መስከረም 3 እና 4 ቀን 2011 ዓ.ም እንደተከሰተና ሁለተኛው ግጭት ደግሞ በዚያው ዓመት ህዳር 5 እንደተነሳ በዚህም ሰዎች መገደላቸውን ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።
 

ወደ ማረቆ ሊካለሉ ይገባቸዋል የተባሉት ዘጠኙ ቀበሌዎች ኢንሲኖ፣ ኢንሲኖ ኡስሜ፣ በቼ ቡልቻኖ፣ ባቴ  ፉጦ፣ ባቴሌጃኖ፣ ኤምር ዋጮ ሶስት፣ ባሞ፣ ዲዳ እና ኦቻ ገነሜ የሚባሉ እንደሆኑ የነገሩን ቅሬታ አቅራቢ ሰልፈኞች “የፌደራሉ መንግስት በጉዳዩ ጣልቃ ገብቶ አንድ ይበለን” ሲሉ ጥሪያቸውን አሰምተዋል።
 

“የጉራጌ ከፍተኛ አመራሮች ጫና ከማረቆ ብሔረሰብ ላይ ሊነሳ ይገባል” ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎች “እኛ ከደቡብ ክልል መንግስትና ከጉራጌ ዞን መስተዳድር ቀና ምላሽ ስላጣን የፌደራል መንግስት ይስማን” ብለዋል።
 

“ይህንን ቅሬታችንን ለተለያዩ የፌደራል ተቋማት ከዚህ ቀደም ብናሰማም ሁሉም ጆሮ ዳባ ልበስ በማለታቸው አዝነናል” ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎች “በግጭት ምክንያት የሰው ህይወት እያለፈ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
 

አዲስ አበባ በሚገኘው የሠላም ሚኒስቴር እና በኢትጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መስሪያ ቤቶች ቅሬታቸውን ለማሰማት ሰልፍ የወጡትን ዜጎች የመስሪያ ቤቶቹ የስራ ባልደረቦች እንዳነጋገሯቸውና ለሚመለከተው አካል ቅሬታቸውን በማቅረብ ለመፍታት የተቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ እንደነገሯቸው አዲስ ዘይቤ ከምንጮቹ ሰምቷል።

አስተያየት