መጋቢት 10 ፣ 2013

ኢትዮጵያውያንን ያማረረው የኑሮ ውድነት - “ደቡብ ውስጥ ገዢ አጥቶ ጦጣ የሚበላው ማንጎ አዲስ አበባ ላይ በውድ ዋጋ ይሸጣል”

ወቅታዊ ጉዳዮችምጣኔ ሀብት

የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት በየካቲት ወር የተመዘገበው የዋጋ ግሽበት 20.6 በመቶ መድረሱን አስታውቋል።

ኢትዮጵያውያንን ያማረረው የኑሮ ውድነት - “ደቡብ ውስጥ ገዢ አጥቶ ጦጣ የሚበላው ማንጎ አዲስ አበባ ላይ በውድ ዋጋ ይሸጣል”

በየግዜው መጨመር እንጂ መቀነስ የማያሳየው የኢትዮጵያ ኑሮ ዉድነት ማማረሩን ከጀመረ ሰነባብቷል በሚል ንግግራቸውን የሚያሟሹት አስተያየታቸውን የሰጡን ሰዎች የኑሮ ውድነቱ ክፉኛ ያማርራሉ።
 

አዲስ አበባ ውስጥ ጫማ በመጥረግ እና መኪና በመጠበቅ ሥራ የሚተዳደረው ሌንዳሞ ደስታ ከወላይታ ወደ መዲናይቱ ከመጣ ሁለት አመት ሊሞላው የቀረው ጥቂት ሳምንታት ብቻ ነው።
 

“ኑሮ እሳት ሆነ” የሚለው ሌንዳሞ ከአንድ ወር ገደማ በፊት በ40 ብር የሚገዛው የጫማ ቀለም ከሰሞኑ አንድ መቶ ብር መሻገሩን ይናገራል። “ምነው ተወደደ” ብዬ ብጠይቅ “እኛም ከምናስመጣበት ቦታ ስለተወደደብን ነው፤ ምን እናድርግ” የሚል ምላሽ አገኘሁ የሚለው ሌንዳሞ “ደንበኛዬ ጋር በ35 ብር አገኛት የነበረችው ሽሮ እንኳ 50 ብር መግባቷን የተረዳሁት በድንገት ለመመገብ በሄድኩበት ነው” ይላል።
 

“ያላቸው ናቸው ኑሮውን የሚያሳብዱት” የሚለው ሌላኛው አስተያየት ሰጪ በለጠ ንጋቱ “ሐብታሞቹ የተጠየቁትን ገንዘብ ላጥ አድርገው ይከፍላሉ፤ እኛ የሌለንስ” ሲል ይጠይቃል።
 

ጥሩ ነገር መመገብ ቀርቶ ሆድ ሊሞላ የሚችል ምግብ ለማግኘት እንኳን ዋጋው አላላውስ እያለ መምጣቱን የሚያወሳው በለጠ ከሰሞኑ በነዳጅ ምርቶች ላይ የተከሰተውን የዋጋ ጭማሪ ተከትሎ የትራንስፖርት ታሪፍ ላይ ማሻሻያ መደረጉ የሸቀጣሸቀጦች ዋጋ እንዲያሻቅብ ሳያደርግ እንዳልቀረ ግምቱን ያስቀምጣል።
 

በርግጥ ከጥቅምት 1 ቀን ጀምሮ አዲስ ተመን እስከወጣለት መጋቢት ወር 2013 ዓ.ም ድረስ ባሉት ግዜያት ውስጥ ብቻ በነዳጅ ዋጋ ላይ ማለትም በቤንዚን፣ ኢታኖል ድብልቅ ቤንዚን፣ ኬሮሲን፣ ነጭ ናፍታ፣ ቀላል ጥቁር እና ከባድ ጥቁር ናፍታ ላይ በጠቅላላው በእያንዳንዳቸው ላይ በአንድ ሊትር የተደረገው የዋጋ ጭማሪ ሲደመር የ35 ብር ከ46 ሳንቲም የዋጋ ንረት ታይቷል።
 

በጥቅምት የነበረው ዋጋ ከያዝነው መጋቢት ወር ጋር ሲወዳደር በተነፃፃሪ በአንድ ሊትር የ3 ብር ከ27 ሳንቲም አነስተኛ ጭማሪ ካሳየው ከባድ ጥቁር ናፍታ ጀምሮ የ14 ብር ከ28 ሳንቲም ከፍተኛ ጭማሪ እስከታየበት የአውሮፕላን ነዳጅ ድረስ በሁሉም የነዳጅ ምርቶች ላይ የኑሮ ውድነቱን በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ሊያባብስ የሚችል የዋጋ ጭማሪ ስለመደረጉ የወሩን መገባደጃ ቀናት ጠብቆ የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ ክለሳ ከሚያደርገው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መግለጫ በቀላሉ መረዳት ይቻላል።

 

ላለፉት 12 ዓመታት ከተለያዩ አገራት ምግብ ነክ እና የተለያዩ ሸቀጣሸቀጦችን አስመጥተው በማከፋፈል ሥራ ላይ የተሰማሩት ወ/ሮ ሳባ ማርቆስ የነዳጅ ዋጋ መናር ለኑሮ መወደድ እንደ ምክንያት ሊቀመጥ የሚችል እንደሆነ ቢስማሙም ብር ከዶላር አኳያ ያለው ዋጋ ከግዜ ወደ ግዜ እየተዳከመ መምጣቱም ሌላኛው ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ያምናሉ።
 

ካለፉት አምስት አመታት ወዲህ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት እየተመለከቱ እንደሆነ የሚናገሩት ወ/ሮ ሳባ አሁን ላለው የኑሮ ውድነት ግን ከመንግስት ጀምሮ ነጋዴውና ሕብረተሰቡ ሁሉም በየደረጃው ተጠያቂ ነው ይላሉ።
 

“ዕቃ የምንረከባቸው አከፋፋዮች ትላንት በሸጡልን ዋጋ ዛሬ አይሸጡልንም፤ ብዙ ትርፍ ለማጋበስ ሲሉ ጭማሪያቸው የተጋነነ ነው፤ እኛም ይህንኑ ተከትለን ጭማሪ ስናደርግ ሕብረተሰቡ እኛ ጋር መጥቶ ይጮሃል እንጂ ለምን ይህ ሆነ ብሎ ለመንግስት እና ለመገናኛ ብዙሃን አቤት አይልም” ያሉን ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የሸቀጣሸቀጥ መደብር ባለቤት የሆኑት አቶ ሙራድ ሙስጠፋ ናቸው።
 

ወ/ሮ ሳባም ሆኑ አቶ ሙራድ ግን የኑሮ ውድነት ስለመኖሩ ልዩነት የላቸውም።
 

ብዙሃኑ ሸማች የሚገዛው ነገር ከሚያገኘው ገቢ በላይ ዋጋ ከተጠየቀበት የኑሮ ውድነት አለ ለማለት ያስደፍራል የሚሉት የምጣኔ ኃብት ባለሙያው አቶ ጌትነት ወርቁ አሁን በአገሪቱ ያለውን የኑሮ ውድነት ችግር ለመፍታት ግን በዋናነት መፍትሄው በመንግስት ዕጅ ስለመሆኑ ይናገራሉ።
 

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ሊቀ-መንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ የአገሪቱ የፖለቲካ ብልሽት ያመጣው ዳፋ ወጪው በየግዜው እየናረ ገቢው ግን ባለበት የሚረግጥ ዜጋ እና ኢኮኖሚ እንዲፈጠር አድርጓል፤ ይህንን ችግር ለመፍታት ደግሞ መጀመሪያ ፖለቲካው መቃናት አለበት በማለት ያስረዳሉ።
 

የምርት ማነስ አሁን ላለው የኑሮ ውድነት ትልቅ ሚና አለው የሚሉት ሌላኛው ፖለቲከኛና የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊዉ አቶ ገለታው ዘለቀ ግብርናው የተሻለ ምርት እንዲያመርት የፖሊሲ ለውጥ ሊደረግ ያስፈልጋል ባይ ናቸው።
 

“መንግስት የባልትና ንግድ ውስጥ ጭምር ሊገባ አይገባውም” የሚሉት አቶ ገለታው “የግሉ ዘርፍ መበረታታት ይገባዋል” ሲሉ ይሞግታሉ። “አሁን ያለውን ችግር ግን ለግዜው ለማለፍ መንግስት የተለያዩ ምርቶች ላይ ድጎማ ቢያደርግ ሳይሻል አይቀርም” ይላሉ።
 

በእርግጥ ለኑሮ መወደድ የነዳጅ ዘይት ዋጋ ላይ ጭማሪ መኖሩ እንደ አንድ ምክንያት ሊቆጠር ቢችልም በሌላ በኩል ግን መጨመር እንጂ መቀነስ የማያሳየው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት፣ የምርት አቅርቦት መቀነስ፣ የሰላም መታጣት እና ሌሎችም ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች እንደ ምክንያት ሊቀርቡ የሚችሉ መሆናቸውን የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ ጌትነት ወርቁ ነግረውናል።
 

እንደ ምጣኔ ኃብት ባለሙያው አቶ ጌትነት ገለፃ ከሆነ አሁን ያለውን የኑሮ ውድነት ችግር ለመፍታት መንግስት እና ነጋዴው ከሌሎች ባለድረሻ አካላት ጋር በመቀራረብ ሊሰሩ  ያስፈልጋል።
 

“ደቡብ ክልል ውስጥ ገዢ አጥቶ ጦጣ የሚበላው ማንጎ አዲስ አበባ ላይ በውድ ዋጋ ይሸጣል” የሚሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው “ይህንን መሰል ችግር ለመፍታት ገዢ እና ሻጭ ያለማንም ደላላ ጣልቃ ገብነት በቀጥታ መገናኘት እንዳለባቸው” አፅዕኖት ሰጥተው ተናግረዋል።
 

የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት በየካቲት ወር የተመዘገበው የዋጋ ግሽበት 20.6 በመቶ መድረሱን አስታውቋል።
 

የተመዘገበው የዋጋ ግሽበት ባለፉት ስድስት ወራት ከተመዘገቡት ውስጥ በጣም ትልቁ ሲሆን፣ ጭማሪው ምርቶች ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አኳያ ያሳዩት ለውጥ ማሳያ መሆኑ ተጠቁሟል።
 

በተመሳሳይ የምግብ ዋጋ ግሽበት 22.8 በመቶ ሲደርስ፣ ምግብ ነክ ባልሆኑ ምርቶች ላይ 18 በመቶ የሚደርስ ጭማሪ መታየቱን ኤጀንሲው ጠቁሟል።
 

በተለይም በእህሎች ላይ የታየው ጭማሪ ለምግብ ዋጋ ግሽበት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረገ ሲሆን የስኳር፣ የምግብ ዘይት፣ በርበሬ፣ ድንችና ቡና ዋጋዎች መጨመሩ ግሽበቱን እንዳባባሰው የኤጀንሲው ሪፖርት አመላክቷል።
 

የማዕከላዊ ስታስቲክስ ሪፖርት እንዳሳየው ከፍተኛ የምግብ ዋጋ ግሽበት የተመዘገበው በትግራይ ክልል ሲሆን 31.6 በመቶ ደርሷል። 14.1 በመቶ አነስተኛ የምግብ ዋጋ ግሽበት የተመዘገበው በአማራ ክልል ነው። የአዲስ አበባ የምግብ ዋጋ ግሽበት ደግሞ 25.7 በመቶ መድረሱ ተሰምቷል።
 

የገንዘብ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ በተከሰተው የኑሮ ውድነት ዙሪያ ያለው ምልከታ ምን ይመስላል የሚለውን ጉዳይ ለመጠየቅ ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመስሪያ ቤቱ ባልደረቦች ጉባዔ ተቀምጠዋል በሚል ምክንያት ጥረታችን ሳይሳካ ቀርቷል።

አስተያየት