መጋቢት 21 ፣ 2013

በአረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) የሚመራው ትዴፓ ከትግራይ ውጪ በሌሎች አካባቢዎች በሚደረገው ምርጫ አልወዳደርም አለ

ወቅታዊ ጉዳዮች

በአረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) የሚመራው ትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) በዘንድሮው ብሔራዊ ምርጫ በሌሎች አካባቢዎች ላይ እንደማይወዳደር ለአዲስ ዘይቤ አስታውቋል።

በአረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) የሚመራው ትዴፓ ከትግራይ ውጪ በሌሎች አካባቢዎች በሚደረገው ምርጫ አልወዳደርም አለ

በቅርቡ ሥያሜውን ከትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር ወደ ትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) የቀየረውና በአረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) የሚመራው ፓርቲ በዘንድሮው ብሔራዊ ምርጫ በሌሎች አካባቢዎች ላይ እንደማይወዳደር ለአዲስ ዘይቤ አስታውቋል።

መንግስት “የሕግ ማስከበር ዘመቻ” ሲል የጠራውን የትግራይ ጦርነት ተከትሎ በተፈጠረው አለመረጋጋት ምክንያት በተከሰተው የፀጥታ ችግር አሁን ላይ በክልሉ ምርጫ ማድረግ እንደማይቻል መነገሩን ተከትሎ የትግራይ ዴሞክራስያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) በተቀረው የአገሪቱ ክፍል በሚካሄው ምርጫ ላይ ይሳተፍ እንደሆነ የጠየቅናቸው የፓርቲው ሊቀ-መንበር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) በተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል ፓርቲያቸው እንደማይወዳደር ነግረውናል።

ሊቀ-መንበሩ ለአዲስ ዘይቤ ሲናገሩ “ዋናው መሰረታችን ትግራይ ነው፤ ሌላ አካባቢ መወዳደሩ ብዙ ጥቅም የለውም” ብለዋል። “ብዙ ጥቅም የለውም” ለምን እንዳሉ የጠየቅናቸው አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) “ዋናው መሰረትህ ላይ ካልተወዳደርክ ቅርንጫፎቹ ላይ መወዳደሩ የትም አያደርስም” ሲሉ መልሰዋል።

በትግራይ የኤርትራ ወታደሮች መግባታቸውን በተመለከተ የፓርቲያቸውን አቋም ያስረዱት ሊቀ-መንበሩ ጦሩ ለምን እንደገባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል ካሉ በኋላ በኤርትራ ጦር ከገባ በኋላ በሰራዊቱ አማካኝነት በሕዝቡ ላይ የሚያደርሰውን ግፍ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ የንብረት ማውደም እና ዝርፊያን በግልፅ ተቃውመናል አሁንም እንቃወማለን ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ አስረድተዋል።

ጥቅምት 04 ቀን 2013 ዓ.ም የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ሆነው መሾማቸውን ተከትሎ እርሳቸው የሚመሩት ፓርቲ በሥልጣን ላይ ካለው የብልፅግና ፓርቲ ጋር ለመዋሃድ አልያም ጥምረት ለመፍጠር በመስራት ላይ እንደሆነ መነገሩን በተመለከተ ጥያቄ ያቀረብንላቸው አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ምንም አይነት ንግግር እያደረጉ እንዳልሆነና ውሕደት አልያም ጥምረት አለመፍጠራቸውን ተናግረዋል።

በጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙት የትዴፓ ሊቀ-መንበር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ጽህፈት ቤቱን በዋና ዳይሬክተርነት ሲያገለግሉ የነበሩና በጡረታ የተሰናበቱትን ወ/ሮ ሮማን ገብረሥላሴን መተካታቸው የሚታወስ ነው።

በህወሓት የሥልጣን ዘመን በትግራይ ያለው የፖለቲካ ምህዳር ጠባብ በመሆኑ በክልሉ የሚያደርገው እንቅስቃሴ የተገደበ እንደነበረ ሲናገር የቆየው ትዴፓ በአዲስ አበባ ከከፈተው ጽ/ቤቱ በተጨማሪ የመጀመሪያ ማስተባበርያ ቢሮው በመቐለ ከፍቶ እንደነበረ የሚታወስ ነው።

አስተያየት