መጋቢት 20 ፣ 2013

በጥብቅ ተፈፃሚ ይሆናል የተባለው የኮቪድ መመሪያ

ኮቪድ 19ወቅታዊ ጉዳዮች

ከ20 መጋቢት 2013 ዓ.ም ጀምሮ በጥብቅ ተፈፃሚ ይሆናል የተባለው የኮቪድ መመሪያ...

በጥብቅ ተፈፃሚ ይሆናል የተባለው የኮቪድ መመሪያ

መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ስርጭቱንም ለመግታት ያግዛል በሚል መመሪያ ቁጥር 30 መውጣቱ የሚታወስ ነው። በአተገባበሩ ላይ ከፍተኛ የሆነ ክፍተት ታይቶበታል የተባለው ይህ መመሪያ ከዛሬ መጋቢት 20 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በሚመለከታቸው አካላት ጥብቅ ቁጥጥር በማካሄድ ወደ ተግባር እንዲገባ ይደረጋል ተብሏል።

በዚህ መመሪያ የተደነገጉ ክልከላዎችን እና ግዴታዎችን የተላለፈ ማንኛውም ሰው አግባብነት ባለው የወንጀል ሕግ አንቀጽ መሰረት እንደሚቀጣ የሚደነግገው ይህ መመሪያ በመላው አገሪቱ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ ሁሉ ተፈፃሚ ይሆናል።

የጤና ሚኒስትሯ ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) በይፋዊ የፌስ ቡክ ገፃቸው ላይ እንዳስታወቁት ከሆነ “የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ስርጭቱንም ለመግታት የሚያግዘው መመሪያ ቁጥር 30 ቢወጣም አተገባበሩ ላይ ግን ከፍተኛ ክፍተት በመኖሩ የሚደረጉ ማናቸውንም እንቅስቃሴዎች መመሪያው ላይ በተቀመጠው መስፈርት ስለመሆኑ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋል፣ በሚመለከታቸው አካላትም አስፈላጊዉ እርምጃ ይወሰዳል” ሲሉ ተናግረዋል።

በመመሪያው ላይ ማንኛውም አስክሬን ከውጭ አገር ወደ ኢትዮጵያ በሚላክበት ጊዜ የሞት ምክንያትን የሚገልጽ የሞት ሰርትፍኬት አብሮ መላክ እንዳለበት የሚደነግገው ይህ መመሪያ ማንኛውም ኮቪድ-19 ያለበት ሰው ቫይረሱ እንዳለበት እያወቀ ወደ አገር ውስጥ መግባት፣ ከማህበረሰቡ ጋር መቀላቀል ወይም ቫይረሱ ወደ ሌሎች ሰዎች ሊተላለፍ በሚችልበት ሁኔታ ከሌሎች ሰዎች ጋር መገናኘትን ይከለክላል።

በትላንትናው ዕለት ብቻ በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት 17 ሰዎች የሞቱ ሲሆን 805 ሰዎች ደግሞ በፅኑ መታመማቸው ተነግሯል። እስካሁን ድረስ 2801 ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል።

ከወራት በፊት ተግባራዊ እንዲደረግ ወጥቶ ነገር ግን እስካሁን ድረስ በሚፈለገው መጠን ተግባራዊ አልተደረገም በተባለው መመሪያ ላይ ማንኛውም ሰው ለሰላምታና ሌላ ለማንኛውም አላማ በእጅ መጨባበጥ፣ ሆነ ብሎ የእርስ በእርስ አካላዊ ንክኪ ማድረግን ይከለክላል።

ከዚህ በተጨማሪ ማንኛውም ሰው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ቀሪ መሆኑ እስከሚወሰንበት ጊዜ ድረስ ከመኖርያ ቤት ውጪ በማንኛውም ቦታ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርግ መገኘት ወይም መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው የሚለው መመሪያው ሆኖም ዕድሜያቸው ከስድስት አመት በታች የሆኑ ህጻናት ወይም በማስረጃ የተረጋገጠ የመተንፈሻ አካላት ወይም መሰል ችግር ያለባቸው ሰዎች ይህ ድንጋጌ ተፈፃሚ አይሆንባቸውም ሲል ያስቀምጣል።

በማንኛውም መንግስታዊ እና የግል ተቋም ሰራተኞች ከሁለት የአዋቂ እርምጃ በታች ተጠጋግተው እና የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ፣ ተገልጋዮች በሚቀመጡበት ጊዜም ይሁን በማንኛዉም አኳኋን አገልግሎቱ ሲያገኙ ከሁለት የአዋቂ እርምጃ በታች ተጠጋግተው እና የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ወይም በአንድ ጠረጴዛ ከሶስት ተገልጋዮች በላይ እንዲቀመጡ ማድረግ በመመሪያው የተከለከለ ተግባር ነው።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን መመሪያ ማስፈንጠሪያውን በመጫን ያገኙታል። እዚህ ይጫኑ

አስተያየት