መጋቢት 18 ፣ 2013

ከኢትዮጵያ ጋር ድርድር እንዲደረግ የቀረበላቸውን ጥያቄ ተከትሎ የሱዳን ልዑካን ዛሬ ወደ ሳውዲ ያቀናሉ

ፖለቲካወቅታዊ ጉዳዮች

ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የድንበር ውዝግብ ለመፍታት እና በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከስምምነት ለመድረስ በኤሚሬት አነሳሽነት ለሚደረገው ንግግር ባለሥልጣናቷ ወደ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ትላንት አቅንትዋል።

ከኢትዮጵያ ጋር ድርድር እንዲደረግ የቀረበላቸውን ጥያቄ ተከትሎ የሱዳን ልዑካን ዛሬ ወደ ሳውዲ ያቀናሉ

የሳውዲ አረቢያ መንግስት በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል የተፈጠረውን የግዛት ይገባኛል ውዝግብ በድርድር ለመፍታት ጥሪ ማቅረቡን ተከትሎ የሱዳን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ወደ ሳውዲ አረቢያ፤ አቡዳቢ ዛሬ እንደሚያቀኑ ተነግሯል።
 

ሱዳን ትሪቡን የአገሪቱን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ የሱዳን ከፍተኛ ባለሥልጣናት በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር ወደ ሳውዲ አረቢያ ያቀናሉ።
 

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሯ ማሪያም አል-ማሃዲ፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ ያሲን ኢብራሂም፣ የፍትህ ሚኒስትሩ ናስር አል-ዲን አብደል ባሪ፣ የደህንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተሩ አህመድ ኢብራሂም ሙፋዳል እና የድንበር ኮሚሽን ኮሚሽነሩ ሙአዝ ታንጎ ወደ ሳውዲ አረቢያ ከሚያቀኑት የሱዳን ልዑክ አባላት መካከል ናቸው ተብሏል።
 

ሳውዲ አረቢያ አሁን ኢትዮጵያ እና ሱዳን በይገባኛል ጥያቄ በሚወዛገቡበት ስፍራ በግብርናው መስክ የመሰማራት ፍላጎት እንዳላትና ከሁለቱም አገራት ለስራው የሚያስፈልጉ በግብርና ላይ የተሰማሩ ሰዎችን ለመቅጠር ሃሳብ እንዳላት ተረድቻለሁ ሲል ሱዳን ትሪቡን ዘግቧል።
 

በሌላ በኩል ደግሞ የአቡዳቢው ልዑል ሞሐመድ ቢን ዛይድ የደህንነት አማካሪ ሞሐመድ ዳህላን የሱዳን ጦር አካባቢውን ከለቀቀ በኋላ ሁለቱ አገራት በሚወዛገቡበት ስፍራ ዓለምአቀፍ ኃይሎች እንዲሰፍሩ ማድረግ እንደሚቻል ሃሳብ እንዳላቸው ተነግሯል።
 

ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር የገባችውን የግዛት ይገባኛል ውዝግብ ለመፍታት በሳውዲ በኩል የቀረበውን ጥያቄ እንደምትቀበለው ማስታወቋ የሚታወስ ነው። የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ከካቢኒያቸው ጋር በነበራቸው ስብሰባም ጉዳዩን በተመለከተ ገለፃ ያደረጉ ሲሆን እናደራድራችሁ የሚለውን የሳውዲ ሃሳብ ይመረምራል የተባለ የቴክኒክ ኮሚቴ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ከሚባሉ የተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ተውጣጥቷል።
 

በቴክኒክ ኮሚቴው የቀረበውን ሃሳብ መርምሮ ያፀደቀው ካቢኔ በኤሜሬቶች በኩል የቀረበውን ሃሳብ በመርህ ደረጃ እንደተቀበለውና ድርድሩ ግን የሱዳንን ብሔራዊ ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ እንዲሆን ከውሳኔ ላይ እንደደረሰ መነገሩ የሚታወስ ነው።
 

ኢትዮጵያ የግዛት ይገባኛል ጥያቄውን በተመለከተ ወደ ድርድር የምታመራው ሱዳን ከያዘቻቸው ቦታዎች መጀመሪያ ለቃ ስትወጣ እንደሆነ በተደጋጋሚ አፅዕኖት ሰጥታ ስትናገር ቆይታለች። ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የያዘው አቋም ምን እንደሆነ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ግዜ ድረስ በይፋ የታወቀ ነገር የለም።
 

በተያያዘ የሕዳሴውን ግድብ በተመለከተ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ እዛው ሳውዲ ውስጥ ንግግር እንዲያደርጉ ጥያቄ እንደቀረበላቸው እየተነገረ ነው።
 

ጉዳዩን በተመለከተ ጥያቄ ያቀረብንለት የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ለአዲስ ዘይቤ በሰጠው ምላሽ “በጉዳዩ ዙሪያ የተጣራ ነገር ስለሌለ ይሄ ነው ማለት አይቻልም፤ ይሄ ነው ብለን የምናረጋግጠው ነገር የለም” ማለቱ ይታወሳል።

አስተያየት