ሐምሌ 7 ፣ 2014

ናፍቆት የድሬዳዋ ሳምንት

City: Dire Dawaባህል ወቅታዊ ጉዳዮች

“ከተማችንን በእውቀት፣ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂና በኢንቨስትመንት ለማሳደግ ግዜው አሁን ነው” አንጋፋው የፖለቲካ ሰው አምባሳደር ማሃሙድ ዲሪር

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራው

ዝናሽ ሽፈራው በድሬዳዋ የሚትገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነች።

ናፍቆት የድሬዳዋ ሳምንት
Camera Icon

Credit: Social Media

ናፍቆት የድሬዳዋ ሳምንት በውጭ ሀገርና በሀገር ቤት ያሉ የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆችን በማገናኝት ጠንካራ ማህበራዊ ትስስር ለመፍጠርና ድሬዳዋን መልካም ገፅታ ለማስተዋወቅ ዓላማ አድርጎ የሚከበር ሳምንት ነው። ይህ አመታዊ በዓል ለመጀመሪያ ጊዜ ከሐምሌ 11 እስከ 16፤2014 ዓ.ም በድሬዳዋ ይከበራል። የፍቅር ቀን፣ የባህልና ስፖርት ቀን፣ የንግድ ቀን፣ የቤተሰብ ቀን እና የምስጋና ቀን በሚሉ ስያሜዎች ለአምስት ተከታታይ ቅናት ይከበራል። ከስያሜውም መረዳት እንደሚቻለው የድሬዳዋ ተወላጆች የድሮዋን ድሬዳዋ በመመለስ ናፍቆታቸውን የሚወጡበት ዝግጅት ይሆናል።

ናፍቆት የድሬዳዋ ሳምንት ፕሮግራም ሃምሌ 6 ቀን 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሸራተን ሆቴል በገቢ ማሰባሰቢያ የእራት ግብዣ በይፋ ተጀምሯል። በዝግጅቱ የተገኙት አንጋፋው የፖለቲካ ሰው አምባሳደር ማሃሙድ ዲሪር “ከተማችንን በእውቀት፣ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂና በኢንቨስትመንት ለማሳደግ ግዜው አሁን ነው” ብለዋል። በመክፈቻው ፕሮግራም በርካታ የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች የሆኑ የሃይማኖት አባቶች፤ ታዋቂ መሁራን፤ ፖለቲከኞችና አርቲስቶች ታድመዋል። ተሳታፊዎቹም ናፍቆት የድሬዳዋ ሳምንት በስኬት እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ቃል ገብተዋል።  

በናፍቆት የድሬዳዋ ሳምንት የሚኖሩት መርሀ ግብሮችም ከለገሀር እስከ ለገሀሬ የእግር ጉዞ፣ ነባር ትምህርት ቤቶችን መጎብኘት፣ የባህል አልባሳት ትዕይንት፣ የፎቶ ኤግዚቢሺን፣ የመንገድ ዳር ምግቦች ትዕይንት፣ የስፖርት ፌስቲቫል፤ በድሬዳዋ እንነግድ (የንግድ ትስስር የሚፈጥር) ሲምፖዚየም፣ እንግዶች ከህፃናት ጋር የችግኝ ተከላ ፕሮግራም፣ በዲያስፖራ ምሁራን የሚከናወኑ ጥናታዊ ፅሁፎች የሚቀርቡበትና ውይይቶች የሚካሄዱበት ሲምፖዝየም፣ የፅዳትና የበጎ ፈቃድ ስራዎች በመርሀ ግብሩ ውስጥ ተካተዋል፡

በበዓሉ ላይ የከተማ አስተዳድሩም የአቀባበል፣ የሁነት ዝግጅት፣ የማስታወቂያና የኮምኒኬሽን፣ የስፖርት ዝግጅት፣ የበጎ ፈቃድ ስራዎችና የባለድርሻ አካላትን ማስተባበር፣ የፋይናንስ፣ የሎጂስቲክ እንዲሁም የሰላምና ፀጥታ ንዑስ ኮሚቴ ተዋቅሮ የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ ይገኛሉ።

የዝግጅቱ የአስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሳራ ሀሰን በሽር “ናፍቆት የድሬዳዋ ሳምንት” በመላው ዓለም የሚገኙ የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች በናፈቋት ከተማ ተሰብስበው የተለያዩ በጎ ተግባራትን በመሳተፍ በፍቅርና በአብሮነት የሚያሳልፉበት እንዲሆን መታሰቡን ገልፀዋል።

የድሬዳዋ ዲያስፖራ ጉዳዮች ዳሬክቶሬት ዳሬክተር አቶ አቤል አሸብር እንደነገሩን ለናፍቆት የድሬዳዋ ሳምንት የተለያዩ ዝግጅቶች እየተከወኑ እንደሚገኙና ለበዓሉም በሺዎች የሚቆጠሩ እንግዶች እንደሚመጡ ይጠበቃል። በድሬዳዋ አስተዳደር በኩል ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ለእንግዶች የእንኳን ደህና መጣችሁ ዝግጅቶችን ያዘጋጃል፣ እንግዶች የሚያርፉበትን ሆቴልና ተሽከርካሪ ያዘጋጃል፣ሲሉ አቶ አቤል ገልፀዋል።

“በነበረው የፖለቲካ ሽኩቻና በተለያዩ ነገሮች ምክንያት ያጣነውን እሴት መልሰን የምንገነባበት እንዲሁም የመሀበራዊ እሴት ግንባታውን የሚያጠናክርልን ይሆናል” ሲሉም አቶ አቤል አሸብር ተናግረዋል። እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ከዝግጅቱ የሚገኙ ገቢዎች በአስተዳደሩ ለሚከናወኑ ማህበራዊ አገልግሎቶች ማስፈፀሚያ ይውላሉ።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር በበኩላቸው የሰላም፤ የፍቅርና የአብሮነት ከተማ በሆነችው ድሬዳዋ በአሉ እንዲከበር ሀሳቡን ያመነጩና ወደ ተግባር የገቡ ቅን ዜጎችን ከልብ አመሰግነው ለዝግጅቱ ስኬትም “አስተዳደሩ የድርሻውን እንደሚወጣም አረጋግጣለሁ” ብለዋል። “አብሮነትን የሚያጠናክሩ ይህን መሰል ዝግጅቶችም በቀጣይም ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል” ሲሉም አሳስበዋል።

ለፕሮግራሙ በአስተዳደር ደረጃ ከተቋቋሙት ኮሚቴዎች መካከል አንዱ የማስታወቂያና የኮምኒኬሽን ንዑስ ኮሚቴ ነው።

የኮሚቴው ሰብሳቢ የድሬዳዋ የኮምኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ አቶ ብሩክ ፈለቀ እንደሚናገሩት የተደራጀ መረጃ ለማዳረስና በተገቢው ሁኔታ ፕሮግራሙን ለማስተዋወቅ ሂደቱን እንደ ጀመሩ ነገር ግን እስካሁን የተቀናጀ መረጃ እየተሰራጨ እንዳልሆነ ገልፀዋል። “በግለሰብ ደረጃ የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም በማስታዋወቅ ላይ ይገኛል። ይህ ጥሩ ሆኖ ሳለ የመረጃ መዛባት እንዳይፈጠር በእኛ በኩል መረጃዎችን ስለምንለቅ የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች የእኛን ገፆች እንዲመለከቱ” ሲሉ ጋብዘዋል።

የአቢሲኒያ ባንክ ባልደረባ የሆኑት አቶ ተሻገር እንዳልካቸው እንደዚህ አይነት ዝግጅቶች የከተማዋን ኢኮኖሚ ከመደገፍ አንፃር ትልቅ አስተዋፆ እንዳላቸው ይናገራሉ። ትልቅ የንግድ ትስስር ከመፍጠር ባሻገር ከተማዋ ያላትን ባህል ታሪክ ከማስተዋወቅ አንፃር ጉልህ ፋይዳ አለው ብለዋል። ድሬዳዋ ከተማ የምትታወቅባቸው ነገሮች እንደ ጣፋጭ ምግቦችና የኤሌክትሮኒስ እቃዎች የመሳሰሉትን ለገበያ በማቅረብ የከተማዋ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ጠበቃል።

አስተያየት