ሐምሌ 11 ፣ 2014

በአዳማ የሲሚንቶ እጥረት በባለሞያዎች ላይ እያስከተለው ያለው ጫና

City: Adamaኢኮኖሚወቅታዊ ጉዳዮች

የአዳማ ከተማ አስተዳደር የኮንስትራክሽን ባለስልጣን እንደሚለው በከተማው የ2014 ዓ/ም የዘርፉ የስራ እድል ፈጠራ እቅድ የተሳካው 57 በመቶ ብቻ ነው።

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

በአዳማ የሲሚንቶ እጥረት በባለሞያዎች ላይ እያስከተለው ያለው ጫና
Camera Icon

ፎቶ፡ ተስፋልደት ብዙወርቅ

ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት የሚታየው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት የግንባታ ስራዎችን እያስተጓጎለ ይገኛል። የግብዓቶች ውድነት እና እጥረት ከፍተኛ የስራ እድል የሚፈጥረው የግንባታው ዘርፍ ላይ ጫና እያሳደረ እንደሆነ የዘርፉ ተዋንያን ይገልጻሉ። በአዳማ ከተማ ያለውን ሁኔታ በግንባታ እና ተያያዥ ስራዎች ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ባለሞያዎችን በማናገር ለመረዳት ሞክረናል።  

በአሁን ወቅት ከፍተኛ የሲሚንቶ እጥረት አለ የሚለው ናሆም የአዳማ ከተማ ነዋሪ ሲሆን በግሉ የሚሰራ የሲቪል መሃንዲስ ነው። የወቅቱ የውጪ ምንዛሪ እጥረት ለሲሚንቶ መጥፋት አንዱ ምክንያት ነው የሚለው ናሆም ሲሚንቶ በማከማቸት ዋጋው እንዲወደድ ጥረት የሚያደርጉ ህገ ወጥ ነጋዴዎችም እንዳሉ ገልጾልናል። 

“የተፈጠረው የሲሚንቶ እጥረት ብዙ የስራ እድል ዘግቷል፤ አንድ የግንባታ ሳይት ብቻውን ከ20 እስከ 30 ሰዎች ቀጥሮ ያሰራ ነበር” የሚለው ናሆም አሁን አብዛኛዎቹ ስራ ማቆማቸውን ነግሮናል። እርሱም ኮንትራክተር ሆኖ ከያዛቸው አራት ፕሮጀክቶች ሶስቱ በሲሚንቶ እጥረት የተነሳ የቆሙ ሲሆን ቀሪው አንድ ግንባታው ያልተቋረጠው ከዓመታት በፊት ተከፍሎበት በመጣ ሲሚንቶ እንደሆነ አብራርቷል። 

የውጭ ምንዛሪ እጥረት የግንባታ ወጪን ከእቅድ በላይ በማድረግ ባለሀብቶችን ከፍተኛ ጫና ውስጥ እየከተተ እንደሆነ ይህም ስራዎችን በማጓተት ላይ መሆኑን ነግሮናል። “ማቴሪያል የለም ማለት ስራ የለም ነው” የሚለው ናሆም ሲሚንቶ መወደዱና መጥፋቱ ከህጋዊ የገበያ መስመር ወጥቶ ኮንትሮባንድ ውስጥ እየገባ መሆኑን ያሳያል ይላል።

“መንግስት በአምራች ፋብሪካዎች እና በተጠቃሚው መሀል ላይ ያለውን የአቅርቦት ሰንሰለት በመቁረጥ መፍትሔ ሊሰጥ ይገባል” በማለት ሃሳቡን ይደመድማል።

ደሳለኝ ተሾመ በአዳማ ከተማ ደካ አዲ አካባቢ በብሎኬት ማውጣት ስራ ላይ ተሰማርቶ ይገኛል። በስፍራው በአማካኝ በቀን ከ100 እስከ 150 ብር ደሞዝ የሚከፍላቸው ስምንት ሰራተኞች እንደነበሩት ይናገራል። “ከስምንቱ ልጆች አምስቱን ቀንሻለሁ፣ አሁን እየሰሩ ያሉት ሶስቱ ብቻ ናቸው” የሚለው ደሳለኝ ሰራተኛ ለመቀነስ ምክንያት የሆነው ጉዳይ የሲሚንቶ መወደድ እና መጥፋት እንደሆነና በስራቸው ላይም ከፍተኛ የገቢ ቅናሽ እንዳስከተለ ገልጿል።  

ነጋልኝ ተሾመ የፊኒሺንግ ባለሞያ ነው። የፊኒሺንግ እቃዎች እንደሌሎቹ የግንባታ እቃዎች አልጠፉም፣ ነገር ግን ዋጋቸው በእጥፍ ጨምሯል የሚለው ነጋልኝ ጄሶ ከ90 ብር ወደ 150 እና 180 ብር መግባቱን ተናግሯል።  ሽቦ ከ80 ብር ወደ 250 ብር ሲጨምር ቃጫ 10 ኪ.ግ  ከ400 እስከ 600 ብር እንገዛው የነበረው አሁን ከ1300 ብር በላይ ሆኗል ሲል ልዩነቱን ያስረዳል። ነጋልኝ እንደሚለው ይህ የተጋነነ ጭማሪ የተስተዋለው ከገና በዓል በኋላ ነው። 

የእቃዎቹ ከልክ በላይ መወደድ አስገንቢዎች እያረፉ እንዲሰሩ ከማስገደድ አልፎ እነነጋልኝን ስራ አልባ አድርጓቸዋል። “ከዚህ በፊት አንድ ስራ ሲያልቅ ሌላ ወዲያው እናገኝ ነበር፤ አንዳንዴም ሶስት አራት ሳይቶች በአንድ ጊዜ ይዘን እንሰራ ነበር። አሁን ግን ስራ ካቆምን ሁለት ወራት አልፏል” የሚለው ነጋልኝ “ይህ የሆነው በሲሚንቶ እጥረት ነው፤ የሁሉ ነገር የልብ ትርታ ሲሚንቶ ነው” ሲል ይናገራል። 

ነጋልኝ እና የስራ አጋሮቹን ችግር ላይ የጣላቸው ሲሚንቶ መወደዱ ብቻ ሳይሆን ጭራሽ ገበያው ላይ አለመገኘቱ ነው። “ተወዶ እንኳን ቢኖር ስራ አንፈታም ነበር” ያለ ሲሆን በስሩ ባለሞያዎችን ሲያሰራ ለዋና ባለሞያ 250 ብር እንዲሁም ለረዳት 150 ብር አንዳንዴም የምሳ አበል እና የትራንስፖርት ይከፍል የነበረው ሁሉ ቀርቶ እሱ ራሱ ገቢውን አጥቷል።

ከአዲስ ዘይቤ ጋር ቆይታ ያደረገው በግንበኝነት ስራ ላይ የተሰማራው አማኑኤል ዘነበ በሚያገኘው ገቢ ቤተሰቡን ያስተዳድራል። “የምኖረው በኪራይ ቤት ነው፤ እናቴንም የምጦረው እኔ ነኝ” የሚለው አማኑኤል የስራው ጉዳይ መዋዠቅ ኑሮውን ከጊዜ ወደ ጊዜ ፈታኝ አድርጎበታል። 

“ሶሰት ሳምንት ገደማ ስራ አልሰራሁም፤ ኮንትራት ይዤ የጀመርኩት ስራም ሲሚንቶ ባለመኖሩ ከቆመ ወር አልፎታል” ያለ ሲሆን የቤት ኪራይ፣ የምግብ እና ሌሎች መሠረታዊ ፍጆታዎችን ማሟላት እያቃተው እንደሆነና ይህን ችግር እንደሱ ያሉ ሌሎች ብዙ ግንበኞችም እንደሚጋሩት አጫውቶናል። “ቤተሰቡን ማብላት ያልቻለ ሰው ብዙ አማራጭ ሊያስብ ይችላል” በማለት ይህ ችግር ተባብሶ ሀገራዊ ቀውስ እንዳይፈጥር ያለውንም ስጋት አልሸሸገም።

አማኑኤል እንደሚለው ሲሚንቶ ገበያ ላይ ቢጠፋም አንዳንድ ሰዎች ይዘውት ይገኛሉ፤ ከየት እንደሚያመጡትም አይናገሩም። “መፍትሔው ምርቱንና አቅርቦቱን መጨመር እንዲሁም በህገ-ወጥ መንገድ የሚዘዋወረውን ሲሚንቶ መቆጣጠር ነው” ያለ ሲሆን የህገ-ወጥ ዝውውሩን ደረጃ ሲያስረዳ በከተማው አንዳንድ አካባቢዎች በሬሳ ሳጥን ውስጥ ደብቆ እስከማዟዟር መደረሱን እና በዚህ መንገድ ሲሚንቶ መጥቶለት ግንባታ የሰራ የሙያ አጋር እንዳለው አጫውቶናል።  

በግንባታ ዘርፉ ውስጥ ከግንበኞች በተጨማሪ አናጺዎች እንዲሁም የብረት፣ የፊኒሺንግ፣ የኤሌክትሪክ ዝርጋታ፣ የእንጨት ስራ እና ሌሎችም ባለሞያዎች ይሳተፋሉ። 

የአዳማ ከተማ አስተዳደር ኮንስትራክሽን ባለስልጣንን ወክለው ከአዲስ ዘይቤ ጋር ቆይታ ያደረጉት አቶ እንደሻው ተፈራ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ውስጥ የቁጥጥር ባለሞያ ናቸው። የኮንስትራክሽን ባለስልጣኑ የ2014 ዓ/ም የስራ እድል ፈጠራ እቅዱ አፈጻጸም ከ57 በመቶ እንዳልዘለለ ከቢሮው ተወካይ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ባለስልጣኑ የግንባታ ስራዎችን ደረጃ ሀ ፣ ለ እና ሐ በማለት እንደሚከፍላቸው የነገሩን የቁጥጥር ባለሞያው ደረጃ "ሀ"  ከሁለት ፎቆ በታች ያሉ ህንጻዎች ሲሆኑ ፣ ደረጃ "ለ" ከሁለት ፎቅ በላይ ያሉ ህንጻዎች እና ሪል-ስቴቶችን ያጠቃልላል። ደረጃ "ሐ" ደግሞ ለህዝብ አገልግሎት የሚውሉ የገበያ ህንጻዎችን እንዲሁም የማምረቻ ቦታዎች ስራ የሚሸፍን ነው። 

በደረጃ ሀ በዚህ ዓመት ውስጥ 3840 ግንባታዎች ለመስራት ታቅዶ 2195 (57 በመቶ)፣ በደረጃ ለ 445 ታቅዶ 227 (51 በመቶ) እና በደረጃ ሐ 240 ግንባታ ለመስራት ታስቦ 131 (55 በመቶ ) ብቻ መሳካቱን አቶ እንደሻው ተፈራ ለአዲስ ዘይቤ ገልጸዋል። 

ባለሞያው እንደሚሉት እነዚህ ቁጥሮች በተለያዩ ምክንያቶች ከፍ ዝቅ የማለት እድል ይኖራቸዋል። ይህም የሚሆነው የተለያየ ደረጃ ያላቸው ግንባታዎች እንደእቅዳቸው፣ አሰራራቸው እና አፈጻጸማቸው የተለየያዩ የግንባታ ባለሞያዎችን ስለሚያሳትፉ ነው።

ለአብነትም አንድ የቪላ ቤትን አሰራር ጠቅሰው ቤቱ ተገንብቶ እስከሚጠናቀቅ ድረስ የቁፋሮ ባለሞያዎች፣ ግንበኞች እና ረዳቶቻቸው፣ የአርማታ ባለሞያዎች፣ የኤሌክትሪክ ስራ፣ የባንቧና፣ የፊኒሺንግ ባለሞያዎችን ጨምሮ እስከ 36 ሰዎች ያሳትፋል ይላሉ።

ይህንንም የስራ እድል በደረጃ ሀ ከተቀመጠው ቁጥር ጋር ሲያነጻጽሩት ይገነባሉ ተብለው የታቀዱት 3840 ግንባታዎች 36 ባለሞያዎችን ቢያሳትፉ እስከ 138,240 የስራ እድሎችን ይፈጥሩ እንደነበር ገልጸዋል። ነገር ግን ስራ የተፈጠረው ለ79,000 ሰራተኞች ብቻ ነው። ይህም ማለት ከ59,000 በላይ ስራዎች ሳያገኙ ቀርተዋል።

ይህ ቁጥር ወደ ደረጃ ለ ሲሄድ የግንባታ ስራው ከፍ ስለሚል የፕሮጀክት ማናጀር፣ የዲዛይን እና ግንባታ መሀንዲስ እንዲሁም ሌሎች ባለሞያዎችን ጨምሮ እስከ 150 ሰዎችን በአንድ የግንባታ ሳይት በተለያየ የስራ ዘርፍ ሊያሳትፍ ይችላል ይላሉ።

“በአዳማ ከተማ ከፍተኛ የሆነ የግንባታ ግብዓቶች አጥረት አለ” የሚሉት አቶ እንደሻው ተፈራ የግብዓት እጥረቱ በዘርፉ ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን ይናገራሉ። አሁን ባለው የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ 65 በመቶ የሀገሪቱ የግንባታ እቃዎች ከውጭ የሚገቡ በመሆናቸው በውጪ ምንዛሪ እጥረት እየዘገዩ መሆናቸው ዋናው ችግር እንደሆነ ገልጸው ሌላው ደግሞ በገበያ ላይ የሚገኙ ግብዓቶች ውድነት እንደሆነ ይገልጻሉ።

“የእኛ መስሪያ ቤት የቁጥጥር ተቋም ነው፤ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች በከፍተኛ ደረጃ እንዲመረቱና ያሉ የግዢ ሰንሰለቶች እንዲያጥሩ ለሚመለከታቸው አካላት ሀሳብ እናቀርባለን” የሚሉት አቶ እንደሻው ተፈራ ከዚህ በፊት ለተደራጁ ወጣቶች እና ለቤት ገንቢዎች በቀጥታ ሲሚንቶ ለመስጠት የተደረገ ሙከራ መኖሩን አስታውሰው ይህ ሙከራ ቅሬታ እንደቀረበበት ይናገራሉ። ቅሬታው የመጣው ለቤት ሰሪም ለህንጻ ገንቢዎችም እኩል ኮታ በመቀመጡ ነበር። 

ከገበያ የጠፋው ሲሚንቶ በአሁኑ ወቅት አዳማ ከተማ ውስጥ በኩንታል ከ1300 እስከ 1500 ብር በህገ-ወጥ መንገድ እየተሸጠ እንደሚገኝ ያነጋገርናቸው የግንባታ ባለሞያዎች ገልጸውልናል።

አስተያየት