የጎንደር ከተማ እንደጥንታዊ መናገሻነቷ እና አሁን እንዳላት የህዝብ ቁጥር እድገትገት አንጻር በበቂ ሁኔታ ንጹህ የመጠጥ ውሃ እያገኘች አይደለም። ለጎንደር ከተማ ዋነኛ የውሃ መሰረት የሆነው የአንገረብ ግድብ በደለል በመሞላቱ እና ከአገልግሎት እድሜው በላይ የቆየ በመሆኑ በቂ የመጠጥ ውሃ ማቅረብ አልተቻለም። እንዲሁም በቅርቡ ለከተማዋ ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች ይውላል ተብሎ የተገነባው የቆላድባ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በውሃ እጥረት ምክንያት አገልግሎቱ በተደጋጋሚ መቆራረጡ ለችግሩ ዋነኛ ምክንያት ሆኗል።
አሁን ላይ በከተማዋ ያለው የውሃ ስርጭት ከ25 ቀናት በላይ ቆይቶ የሚመጣ ነው። የውሃ እጥረቱ ዘላቂ መፍትሄ ማግኘት ባለመቻሉ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦቱን ብቻ ሳይሆን የከተማዋን የቱሪዝም፣ ኢንዱስትሪዎች፣ ሆቴሎች፣ የጤና እና ሌሎች ተቋማትን የውሃ ፍላጎት ለማዳረስ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሷል።
አቶ እንግዳ (ስሙ የተቀየረ) የጎንደር ከተማ ነዋሪ ነው። 6 ልጆቹን ዳቦ እየጋገረ በማከፋፈል ያስተዳድራል። እንደ እሱ ገለጻ “ጎንደር ክረምት ከበጋ የዉሃ ጥም እያቃጠላት ይገኛል”። ለሳምታትና ለወራት ዉሃ ባለመኖሩ ጀሪካን ይዞ መዞር የነዋሪዉ ቀዳሚ ስራ እንደሆነና በክረምቱ ዝናብ ከቆርቆሮ ላይ በሚወርደው ውሃ እየተጠቀሙ መሆናቸውን ያስረዳል።
ባለሆቴሎችም በቦቲ መኪና እስከ 1200 ብር እየገዙም እንደሚገኙ ይናገራሉ።
ከተመሰረተች 400 አመታትን ያስቆጠረችው ታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ ዘመናዊ ንጹህ የመጠጥ ውሃ በቧንቧ መስመር ማግኘት የጀመረችው በኢጣሊያን ወረራ ጊዜ በ1934 ዓ.ም ነበር። በኋላም በተለያዩ ቦታዎች የውሃ ጉድጓዶች ተቆፍረው አገልግሎት ሲሰጡ ቢቆዩም በቂ ባለመሆናቸው የከተማዋ የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር እየተባባሰ ሄዷል።
የአንገረብ ግድብ ግንባታ በ1978 ዓ.ም ተጀምሮ በ1986 ዓ.ም የተጠናቀቀ ቢሆንም የውሃ ማጣሪያ ጣቢያ ባለመኖሩ፣ በከተማዋ ውስጥ የሚዘረጋ ከባድ የውሃ መስመር እና የማጠራቀሚያ ታንከሮች ባለመሰራታቸው አገልግሎት ሳይሰጥ ለረጅም ጊዜ ቆይቷል። በ1990 ዓ.ም የክልሉ መንግስት በጀት በመመደብ የውሃ ማጣሪያ ጣቢያና ሌሎች ግንባታዎችን በማስጀመሩ በ1994 ዓ.ም ስራ መጀመሩን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ይህ ግድብ የአገልግሎት ጊዜውን የጨረሰ ቢሆንም እስካሁን ከ10 ሺህ ሜትር ኩብ በላይ ውሃ እያመረተ እንደሚገኝ የጎንደር ከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ወርቅነህ አያል ነግረውናል።
አቶ ወርቅነህ ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራቸው ቆይታ በከተማው ውስጥ ካለው ፈጣን የህዝብ ቁጥር እድገትና ከፍተኛ የውሃ ተጠቃሚ ኢንዳስትሪዎች እንዲሁም ህዝባዊና መንግስታዊ ተቋማት መስፋፋት ምክንያት የውሃ አቅርቦቱን በሚፈለገው መጠን ማዳረስ እንዳልተቻለ ያስረዳሉ።
ሆኖም ችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ባለማግኘቱ የህዝቡ ጥያቄ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ሲመጣ የውሃ እጥረቱን በዘላቂነት ለመፍታት ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ የፕሮጀክት ጥናት ሲደረግ ቆይቷል። በዚህም ከአለም ባንክ በተገኘ ብድርና ከክልሉ መንግስት እንዲሁም ከከተማ አስተዳደሩና ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተገኘ የተቀናጀ ድጋፍ በ561 ሚሊዮን ብር በጀት በቀን 17ሺህ ሜትር ኩብ ውሃ የሚሰጥ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ተደርጎ ነበር። ነገር ግን ከጎንደር ከተማ በቅርብ ርቀት በምትገኘው ቆላድባ ከተማ የተቆፈሩት ስምንት ጥልቅ ጉድጓዶችን ወደ ስራ ቢገቡም ከ3500 ሜትር ኩብ ውሃ በላይ መስጠት አልቻሉም ብለውናል።
እየተሰሩ ያሉት ስራዎች የከተማዋን የውሃ ችግር ከመሰረቱ ሊቀርፉ ባለመቻላቸው ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመሄድ ላይ ነው። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ለከተማዋ የሚያስፈልገውን የንጹህ መጠጥ የውሃ አቅርቦት ከጣና ሃይቅ በማምጣት የውሃ ሽፋኑን ከ18 በመቶ ወደ 80 በመቶ ለማሳደግ የሚያስችል አዲስ የንጹህ መጠጥ ውሃ ማሻሻያ ፕሮጀክት መጠናቱን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው አቶ ዘመነ ሃብቱ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱን ገንብቶ ለማጠናቀቅ 2.6 ቢሊየን ብር እንደሚያስፈልግ ተገልጿል። ይሄንንም ከጎንደር ከተማ ህዝብ 100 ሚሊዮን ብር፣ ከከተማ አስተዳደር 200 ሚሊዮን ብር፣ ከረጂ ድርጅቶች 200 ሚሊዮን ብር፣ ከክልሉ መንግስት 500 ሚሊዮን ብር፣ በክልል ደረጃ 600 ሚሊዮን ብር፣ ከፌደራል መንግስት 1.6 ቢሊዮን ብር፣ ውጭ ከሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆችና የልማት ደጋፊዎች 100 ሚሊዮን ብር እንደሚፈለግ ነግረውናል።
የንጹህ መጠጥ ውሃ ማሻሻያ ፕሮጀክቱ ተግባራዊ እስኪደረግ ድረስ የመጠጥ ውሃ እጥረቱን ለመፍታት እየተወሰዱ የሚገኙ የመፍትሄ እርምጃዎች ምንድናቸው ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ፥ በደንቢያ ሮቢት ቀበሌ አካባቢ ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ተቆፍሯል። የመስመር ዝርጋታ በማከናወን አገልግሎት ላይ የማዋል ስራ እየጀመሩ መሆናቸውን እና የአንገረብ ግድብ ደለልን በማስወገድ ተጨማሪ የመያዝ አቅሙን የማሳደግ እተየሰራ መሆኑን አቶ ዘመነ ነግረውናል።
በተጨማሪም በተለያዩ ጊዚያት ተቆፍረው አገልግሎት የማይሰጡ 10 ያክል የውሃ ጉድጓዶችንና ምንጮችን እንደገና በማጎልበት ወደ ስራ እንደሚያስገቡ አቶ ዘመነ ሃብቱ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ መናገሻ ከተማ በመሆን ለረጅም አመታት ስታገለግል የነበረችው ጎንደር፥ በስነጥበብ እና በኪነህንጻ ታሪክ ካላቸው ጥቂት ታሪካዊ ከተማች ውስጥ አንዷ ናት። በ16ኛው ክ/ዘመን የነበሩ ነገስታት የውሃን ጠቀሜታ ተረድተው በጎንደር ከተማ መካከል የሚፈሰውን ቃሃ ወንዝን ጠልፈው ለመዝናኛት ይጠቀሙ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል።