ሐምሌ 12 ፣ 2014

የሴት አስተናጋጆችን ሰውነት የሚያጋልጠው አለባበስ ያስነሳው ውዝግብና ውይይት

City: Addis Ababaማህበራዊ ጉዳዮች

በምግብና መጠጥ አገልግሎት ሰጪዎች የሚዘወተረው እና ሴት አስተናጋጆች የሚለብሱት ሰውነትን የሚያሳይ ልብስ በባለቤቶቹ ትዕዛዝ ቢሆንም አብዛኛው ተጠቃሚ ደግሞ ጉርሻ የሚሰጠው አለባበሳቸው አይቶ ነው

Avatar: Nigist Berta
ንግስት በርታ

ንግስት የአዲስ ዘይቤ ከፍተኛ ዘጋቢ እና የይዘት ፈጣሪ ስትሆን ፅሁፎችን የማጠናቀር ልምዷን በመጠቀም ተነባቢ ይዘት ያላቸውን ጽሁፎች ታሰናዳለች

የሴት አስተናጋጆችን ሰውነት የሚያጋልጠው አለባበስ ያስነሳው ውዝግብና ውይይት
Camera Icon

Credit: Facebook

የሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪው ዘርፍ (Hospitality Industry) ከሚመራባቸው መርሆዎች ዋነኛው የደንበኞችን ምቾትን ማረጋገጥ ነው። በዚህም በኢንደስትሪው ውስጥ ጥቅም ላይ ከሚውሉ ቁሳቁሶችና አገልግሎቶች ጀምሮ እስከ የአሰራር ስነ ምግባር ድረስ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ይመጥናል ተብሎ በሚታሰብ ከፍተኛ ጥራትና ደረጃ የተቃኙ ናቸው። የሆቴል አገልግሎት ዘርፍ የአሰራር መርሆና ስነምግባር አንደኛው መገለጫ ደግሞ የአለባበስ ዘይቤ ሲሆን ከዚህም የአስተናጋጆች አለባበስ ዋነኛ ትኩረት የሚሰጠው ነው። 

የአስተናጋጆች አለባበስን በተመለከተ በሆቴል ኢንደስትሪ ሙያ የተቀመጡ የአልባሳቱን አይነት፣ ቅርፅ፣ እንዲሁም ቀለምና ሌሎች ተዛማጅ አጠቃላይ መመሪያዎች አሉ። ኮርባራ የተባለውና ከ70 አመታት በላይ ለሆቴል ኢንደስትሪው ዩኒፎርም ዲዛይን በማድረግና በማምረት የታወቀው የጣሊያን ድርጅት ባስቀመጠው መመሪያ መሰረት የሆቴል ዩኒፎርም ዲዛይን የሚሰጠውን ተግባር፣ ድርጅታዊ መለያነቱን፣ የሰራተኞች ምቾትን እንዲሁም ለስራ ቡድኑ የሚሰጠውን በራስ መተማመን ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት ይላል። 

“አንድ በሆቴልና ተመሳሳይ ዘርፍ ላይ የተሰማራ ድርጅት ለሰራተኞቹ ዩኒፎርም ሲያዘጋጅ የመጀመሪያ አላማው የድርጅቱን ገፅታ መገንባትና የሰራተኞቹን እርካታ መጨመር መሆን ይኖርበታል። በዚህም መሰረት ዩኒፎርሙ ስለድርጅቱ ማንነት የሚሰጠው መልዕክት በደንበኞችና ሰራተኞቹ ዘንድ ከበሬታና ተቀባይነት የሚያስገኙለት ሲሆን አግባብ ያለው ዩኒፎርም አለመምረጡ ደግሞ ተቃራኒው ውጤት ይኖረዋል” ይላል ኮርባራ በድረ ገፁ ስለ ዩኒፎርም ባስቀመጠው መመሪያ። 

በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞች በተለይ ደግሞ በአዲስ አበባ ይህ ከፍተኛ ጥንቃቄና እይታ እንዲኖረው የሚጠበቀው በተለይ ደግሞ የሴት አስተናጋጆች ዩኒፎርም ለየት ባለ ሁኔታ በሚለበሱ ዩኒፎርሞች እየተተካ ይታያል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ አበባ በሚገኙ ስጋ ቤቶች፣ ባርና ሬስቶራንቶች ከጉልበት በላይ የሆኑና ሰውነት የሚያጋልጡ ዩኒፎርሞችን የለበሱ ሴት አስተናጋጆችን ማየት የተለመደ ሆኗል። ይህ አዲስ ልምድ ሆቴሎቹና ሬስቶራንቶቹ ገበያ ለመሳብ እየተገበሩት እንደሆነ በቀላሉ መረዳት ይቻላል። 

ሆኖም ይህ ያልተለመደ የሴት አስተናጋጆች አለባበስ ከአግባብነት፣ ከሞራል እሴትና የሴቶች መብት አንፃር ጥያቄዎችና ሂሶች እየተሰነዘሩበት ይገኛል። 

በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ተጽዕኖ መፍጠር ከቻሉ ግለሰቦች መካከል አንዱ የሆነው ተስፋ ነዳ የተባለ ወጣት “ግልጽ ደብዳቤ ለአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ለክብርት ወይዘሮ አዳነች አቤቤ” በሚል ርዕስ በሴት አስተናጋጆች አለባበስ ላይ ያለውን ስጋት የሚገልጽ ጽሁፍ አጋርቶ ብዙዎች ተቀባብለውት ጉዳዩ ጆሮ አግኝቶ ነበር።

ተስፋ ነዳ ደብዳቤውን እንዲጽፍ ያስገደደውን ገጠመኝ አብሮ አካፍሏል። “...ከባድ ዝናብ እየዘነበ ዝናቡን ሽሽት አንድ መንደር ውስጥ ያለ ስጋ ቤት ተጠልዬ ነበረ። የስጋ ቤቱ አስተናጋጆች በመላው አዲስ አበባ እየተለመደ የመጣውን ከፓንት ትንሽ የረዘመ ቀሚስ ልብሰዋል። ብርዱ እንኳን በዚህ አለባበስ ይቅርና ጋቢ ለለበሰም ይከብዳል። በዚህ መሃል አንዷ አስተናጋጅ ከስር ታይት አድርጋ ስትመጣ ከባለቤቱ ጋር ተጣሉ። ባለቤቱ ታይቷን እንድታወልቅ ሲያዛት እሷም ማህፀኗን እንደሚያማትና ዝናቡ እስኪያልፍ ድረስ ታይቱን እንድትለብስ እያለቀሰች ብትለምነውም በጄ ሊላት አልፈቀደም። ታይቱን እንድታወልቅ ካልሆነ ስራውን እንድትለቅ ነገራት…” ይላል ተስፋ አንዳንድ ሴት አስተናጋጆች ያሉበትን አስቸጋሪ ሁኔታ በግልጽ የሚያሳየውን ምስክርነቱን ሲገልጽ።  

ተስፋ ደብዳቤውን ሲጽፍ ይህን ገጠመኙን ካስተዋለ በኋላ በከተማዋ ውስጥ እንዲህ ያለ የሴቶችን መብት የሚጋፋ አሰራር መስፋፋቱ አስጊ መሆኑን በመገንዘብ “...ክብርት ከንቲባ እርስዎ በሚመሯት በአዲስ አበባ ከተማ ሴት እህቶቻችን ሰውነታቸው ደረጃ እየወጣለት ለትልቅ ሆቴል፣ ለስጋ ቤት፣ እና ለትናንሽ ቤት እየተባለ እየተመደበ ነው። የመንደር ምግብ ቤቶች ሳይቀሩ በዚህ ተግባር ተጥለቅልቀው የሴሰኝነት መናኸሪያ ሆነዋል…” በማለት በወረቀት ላይ የሰፈረው የሰራተኞች ህግ እንዲተገበር ጠይቋል።

ይህን ተከትሎ አዲስ ዘይቤ በአንዳንድ የከተማዋ የምግብ እና የመጠጥ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥ ተዘዋውራ ከላይ በተጠቀሰው መልኩ ስራ ላይ የተሰማሩ ሴት አስተናጋጆችን ስላሉበት ሁኔታ አነጋግራለች። እንደዚህ ባለ አለባበስ በስራ ላይ መሆናቸው ምቾት ይሰጣቸው እንደሆነ የተጠየቁት አስተናጋጆች በአብዛኛው ምላሻቸው “ባለቤቶቹ እንዲህ እንድለብስ ስለሚያዝዙን ነው፣ ይህን አንፈጽምም ብንል ዳፋው ለኛው ነው፣ ስራ ከየት ይመጣል” የሚል ነው። አንዳንዶቹ ደግሞ “በደሞዝ ብቻ ይሄ ኑሮ አይገፋም፣ አብዛኛው ተጠቃሚ ደግሞ ጉርሻ የሚሰጠን አለባበሳችንንም አይቶ ነው” ይላሉ።   

አንዳንዶች እንደሚሉት የሴት አስተናጋጆች ሰውነት በአለባበስ በተጋለጠባቸው ቦታዎች ላይ ገበያተኛ ይበዛል። እንደአስተያየት ሰጪዎቹ ምልከታ ይህ ጉዳይ በማህበረሰቡም ሆነ በአሰሪዎች ዘንድ እየተለመደ ከሄደ አስተናጋጆቹን ሌላ አማራጭ እንዳይፈልጉ መንገዱን ይዘጋባቸዋል። 

በአስተናጋጆች አለባበስ የተሻሉ ናቸው የሚባሉት ኬክ እና ጣፋጭ መሸጫ ካፌዎች እና መደበኛ የመስተንግዶ የደንብ ልብስ የሚለበስባቸው አንዳንድ መለስተኛ እና ከፍተኛ ሆቴሎች ናቸው። በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እየሰሩ የሚገኙትን ሴት አስተናጋጆች እነዚህን አማራጮች መሞከር ይችሉ እንደሆነ ጥያቄ አቅርበንላቸው ነበር። አብዛኞቹ የሚናገሩት አነስተኛ ካፌዎች እና ሆቴሎች ደሞዛቸው ለእለት ጉርስም የማይበቃ እንደሆነና ትልልቅና ታዋቂ ካፊዎች እና ሆቴሎች ደግሞ የሚጠይቋቸው መስፈርቶች ለማሟላት ከባድ እንደሆኑ ነው። 

አሰሪዎች ምንጊዜም ለሰራተኞቻቸው ምቹ የሆነ የስራ ሁኔታን (አካባቢን) የመፍጠር ግዴታ እንዳለባቸው የኢትዮጵያ አሰሪና ሰራተኛ ህግ ይደነግጋል። በአሰሪ እና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ  ቁጥር 1156/2019 አንቀፅ 12 ስር ከተዘረዘሩት የአሰሪዎች ግዴታዎች ውስጥ በንዑስ አንቀፅ 4 ስር የተቀመጠው ህግ "ሰራተኛው የሚገባውን ሰብዓዊ ክብር ስለመጠበቅ" ያብራራል። በዚህ አንቀፅ መሰረት አሰሪ የሰራተኞቹን ክብር የመጠበቅ ግዴታ እንዳለበት በግልፅ በህግ ተደንግጓል። 

ሴቶች ብዙ ጊዜ በስራ ወቅት የሚያደርጓቸው ሰውነታቸውን አጋልጠው የሚያሳዩ አልባሳት ፆታዊ ጥቃት እንዲደርስባቸው ፣ ሰብዓዊ መብቶቻቸው እንዲጣሱ እንዲሁም ክብራቸው በሚነካ ሁኔታ ውስጥ እንዲሰሩ ያስገድዳቸዋል። በማህበራዊ ሚዲያ ላይ መልዕክቱ እንዲዘዋወር ያደረገው ተስፋ፣ ከገጠመኙ ተነስቶ እንደገለጸው አንዲት ሴት ከሌሎች የስራ ባልደረቦቿ ተነጥላ በእንደዚህ አይነት አለባበስ አልሰራም ብትል (ለዛውም የጤና ሁኔታዋን በግልጽ ተናግራ) ከስራ ገበታዋ የመባረር እጣ ይገጥማታል። 

የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህን ጉዳይ በተመለከተ ምን እንደሚል ጥያቄ ያነሳንላቸው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የህግ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደረጄ ተክይበሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ህጎች እስካሁን የየትኛውንም ፆታ የአለባበስ ሁኔታን የሚደነግጉ ድንጋጌዎች ባለመኖራቸው በህግ አግባብ ትክክል ወይም ትክክል ያልሆነ አለባበስ ተብሎ ለመፈረጅ አስቸጋሪ እንደሚሆን ይገልጻሉ። “ይሁን እንጂ ልብሱን ተገደው እንዲለብሱ የሚደረጉ ከሆነ እና የሴት አስተናጋጆችን አለባበስ ተከትሎ የሚፈፀምባቸው ወሲባዊ ትንኮሳ እንዲሁም ሌሎች ፆታዊ ጥቃቶች ካሉ እነዚህ በህግ የተከለከሉ ድርጊቶች ናቸው” ሲሉ ህጉን አብራርተዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ የሴቶችን መብት የሚጋፋ እና በስራ ገበታ ላይ ለሚደርስ የጤና ጉዳት የሚዳርግ ከሆነ ቀጣሪዎች ላይ የሚጣለው ቅጣት የጉዳት ካሳ ጨምረው እንዲከፍሉም ያስገድዳል። “የሴት አስተናጋጆች ልብስ ማጠሩ ጤናቸውንም ሆነ ሞራላቸውን የሚነካ ከሆነ ቀሚሱን ማስረዘምም ሆነ በሱሪ መልክ እንዲጠቀሙ አሰሪዎች ሊያመቻቹ ይገባል” ሲሉ አክለዋል። 

በመሆኑም ሴት አስተናጋጆች ራሳቸውም ሆኑ ሌሎች ይመለከተናል የሚሉ የማህበረሰባችን ክፍሎች ሁሉ ሴቶች በስራ ቦታቸው ላይ ለሚደርስባቸው ወሲባዊ ትንኮሳም ሆነ ማንኛውም ፆታዊ ጥቃት በህግ የሚያስጠይቅ ወንጀል መሆኑን በማወቅ እንደዚህ ያለ ድርጊት ሲያጋጥማቸው ለህግ አካላት በአካል በመሄድ እንዲጠቁሙ ወይም ካሉበት ሆነው በነፃ የስልክ መስመር 991 ሪፖርት እንዲያደርጉ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አሳስቧል።

አስተያየት