ወለቃ ከጎንደር ወደ ደባርቅ በሚወስደው መንገድ ላይ ከአጼ ፋሲል ግቢ በሰሜን አቅጣጫ 3 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኝ ከጎንደር ቀደምት መንደሮች አንዷ ነች። ወለቃ በምታቀርበው በዘመናዊ እና ባህላዊ መንገድ በተሰሩ የሸክላ ምርት ውጤቶች በስፋት ትታወቃለች። በተለምዶ የፈላሻ መንደር እየተባለች የምትጠራው ወለቃ የቀደምት ቤተ እስራኤላውያን መንደር ናት።
ለመንደሯ መመስረት በአካባቢው ይኖሩ የነበሩት ቤተ እስራኤላውያን የጎላ ድርሻ አላቸው። ቤተ እስራኤላውያኑ በወርቅና ብር ማንጠር፣ በሽመና፣ በሸክላ፣ በእንጨትና ብረታ ብረት ስራ ሙያዎች ይታወቁ ስለነበር የከተማዋ ህዝብና ነገስታቱ ሩቅ ሳይሄዱ በመንደሯ የሚፈልጉትን ለማግኘት አስችሏቸው ነበር።
በሚያመርቷቸው የዕደ ጥበብ ስራዎችም ከሃገሪቱ ታሪክ የቆየውን ባህልና እሴት በማገናዘብ ታሪክንና ባህልን ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፍ አድርገዋል። በዚህም ስፍራ ጥንት ቤተ እስራኤላዊውያን ይጠቀሙበት የነበረ ምኩራብ ቤተ መቅደስን ጨምሮ ይኖሩባቸው የነበሩ ቤቶችም ይገኛሉ። በወለቃ ባሉ ቤቶች የተለያዩ የዕደ ጥበብ ውጤቶች የሚገኙ ሲሆን በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ፎቶግራፎችም በቤቶቹ ግድግዳ ላይ ተሰቅለው ይታያሉ።
የመንደሩ ቤተ እስራኤላዊያን መተዳደሪያ ሞያ እንደጾታቸው እና እድሜያቸው የተለያየ ነው። ወንዶቹ በብረት ስራ፣ ሽመና፣ አናጢነትና ግንበኝነት ሙያዎች የተሰማሩ ሲሆን ሴቶቹ ደግሞ የቤት ውስጥ መገልገያዎችን ከሸክላ ያመርታሉ። ወለቃ በዋናነት የቱሪስት ቀልብ የሚስቡና አይንን የሚያማልሉ የሸክላ ስራዎች በማምረት ትታወቃለች። ከ1985 ዓ.ም ጀምሮም በቦታዋ ፕላውሸር የተሰኘ የሴቶች ዕደ ጥበብ ማሰልጠኛ ማዕከል ቻርልስ ሻርሎክ በሚባል ኢንግሊዛዊ ግለሰብ ነው ድጋፍ ተቋቁሟል።
ፕላውሸር የሴቶች ዕደ ጥበብ ማሰልጠኛ ተቋም ባህላዊ እና ዘመናዊ የዕደ ጥበብ ስራዎች የበለጠ እንዲጎለብቱ እና በዘመናዊ መልኩ ተሻሽለው እንዲቀርቡ አድርጓል። የጃፓን ተራድዖ ድርጅትም ባደረገው እገዛና ስልጠና ወደ አካባቢው የሚመጣውን የቱሪስት ቁጥር ከፍ እንዲልና አካባቢውን ህብረተሰብም ተጠቃሚ እንዲሆን አስችሏል።
የፕላውሸር የሴቶች የእደጥበብ ማሰልጠኛ ማዕከል መስራች ቻርልስ ሻርሎክ የተቋሙ አላማ ገቢ የሌላቸው ሴቶችን (ባሎቻቸው የሞቱባቸው ወይም የተፋቱ አልያም ልጆችን ብቻቸውን እያሳደጉ ያሉ እናቶችን) መርዳት ነው። ከተቋቋመ 27 አመታትን ያስቆጠረው ማዕከል እገዛ የሚሹ እናቶች ሞያ ተምረው በሚያገኙት ገንዘብ ራሳቸውን ማስተዳደር እንዲችሉ የስራ እድል የመፍጠር እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው።
ወ/ሮ ተስፋለም አበራ የፕላውሸር የሴቶች እደጥበብ ማሰልጠኛ ማዕከል ስራ አስኪያጅ ናቸው። ወ/ሮ ተስፋለም እንደሚናገሩት ማዕከሉ ባሳለፋቸው አመታት ከ2500 በላይ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍል የመጡ እናቶችን በተቋሙ በማኖር በተለያዩ ሙያዎች አሰልጥነው ባለሙያ አድርገዋል። ሴቶቹ ስልጠናቸውን ሲጨርሱም በሚኖሩበት አካባቢ የስራ ቦታ እንዲሰጣቸውና በሙያቸው እንዲተዳደሩ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
በባህላዊ የሸክላ አሰራር ስራ የጀመረው ማዕከል በአሁኑ ወቅት በዘመናዊ የሸክላ አሰራር ጥበብ የተለያዩ አይነት የሸክላ አሰራር ዘይቤዎችን ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል። ማዕከሉ በብርጭቆ ዱቄት፣ በሲሚንቶ ዱቄት እና በአካባቢው በሚገኙ የቀይ አፈር አይነቶችን በኤሌክትሪክ ምድጃ (ኪሊን) በማቃጠል ሸክላዎችን ያመርታል። በዚህ ማሰልጠኛ ማዕከል ከሸክላ ስራ በተጨማሪ የሽመና፣ የስፌት እንዲሁም የህትመት ስራ ይከናወናል።
የ37 አመቷ ወ/ሮ ፈንታ መኮነን በማሰልጠኛ ማዕከሉ ሸክላዎችን እና ሽመናዎችን እየሠራች እንደምትኖር ነግራናለች። ሸክላውን ሲሰሩ የተለያዩ ማጌጫዎችን እየሳሉ ያሳምሯቸዋል። ለአብነት ያክል የዋሊያ ምስል፣ ዝሆን፣ ጎንደር የሚል ቅርጽ፣ ወለቃ የሚል ጹሁፍ፣ ጀበና የሚሉ ቅርጾች ተጠቃሽ ናቸው።
ከእነዚህ የእደ ጥበብ ውጤቶች በተጨማሪ ቤተ እስራኤላዊያን ምግብ ለማብሰል እና ለጸሎት ይጠቀሙባቸው የነበሩ ቤቶችም በቱሪስቶች ይጎበኛሉ። እነዚህ ቤቶች አሁን የሸክላ ምርቶች መደርደሪያ ወይም ማስቀመጫ ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ።
እንደ ወ/ሮ ፈንታ መኮነን ገለጻ በ2014 ዓ.ም ከእሷ ጋር ሃምሳ ያክል እናቶች በስልጠና ላይ መሆናቸውን ገልጻ ከጃፓን የመጣላቸው ዘመናዊ የሸክላ ማቅለጫ ማሽናቸው ስራ ማቆሙን እንዲሁም በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ሶስት የሸክላ ማቅለጫ ማሽኖች የእሳት ነበልባሉን ወደ ውጭ እያወጡ ሸክላው ጠንካራነቱን እየቀነሰባቸው እንደሆነ ነግራናለች። ማሽን ሲበላሽ የሚጠግንላቸው ባለመኖሩ በሙሉ አቅማቸውን እንዳይሰሩ እክል ሆኖባቸዋል።
ሸክላዎቹ ለአይን ማራኪ ገጽታ ያላቸው ሲሆኑ ከሸክላ ስራዎቹ ውስጥ በብዛት የሚመረተው ጀበና ነው። ሌሎች ቦታዎች ከሚዘጋጁ ጀበናዎች እነዚህን ለየት የሚያደርጋቸው በሲሚንቶ እና ብርጭቆ ዱቄት መሰራቱ እና በሽያጭ ደረጃም ከአፈር (ከሸክላ) ከሚሰሩት ጀበናዎች ላቅ ባለ ገንዘብ እንደመጠናቸው ከ45 ብር ጀምሮ እስከ 150 ብር ድረስ ይሸጣሉ።
በማዕከሉ የሽመና ስራዎችም የሚከናወኑ ሲሆን ከስራዎቻቸው ውስጥ የሴቶች ቀሚስ ተጠቃሽ ነው። ቀሚሶቹ ከጥጥ የተሰሩ እና ሲያዩዋቸው ለአይን የሚስቡ በመሆናቸው አብዛኛው ማህበረሰብ ይጠቀማቸዋል። በዋጋ ደረጃ እስከ 6000 ብር ይሸጣሉ።
በታሪክ እንደሚነገረው ቤተ እስራኤላውያን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የንግስተ ሳባና የንጉስ ሰለሞን ልጅ በሆነው በአጼ ሚኒሊክ ቀዳማዊ ዘመነ መንግስት ከ982~957 ዓመተ ዓለም ነው። ቀዳማዊ ሚኒሊክ በተወለደ በ22ኛ ዓመቱ አባቱን ለማየት ወደ እስራኤል አመራ፤ በዚያም ለሶስት ዓመታት ያክል ቆይቶ ወደ ኢትዮጵያ በተመለሰ ጊዜ ታቦተ ጺዮንን እና ከ22ቱ ነገደ እስራኤል 12 ሺህ እብራዊያን የበኩር ወንድ ልጆች ውስጥ አንድ ሺህ ልጆች ይዞ መጣ ይላል በ2013 የታተመው የሃይለማሪያም ኤፍሬም “ድብ አንበሳ” ከተሰኘው መጽሃፍ የተገኘው መረጃ።
ሁለተኛው የቤተ እስራኤላውያን ወደ ኢትዮጵያ ፍልሰት ደግሞ ከመጀመሪያው ጉዞ ከ500 ዓመታት በኋላ የሆነ ነው። የባቢሎን ወይም የዛሬው ኢራቅ ንጉስ ናቡከደናጾር እስራኤልን ወርሮ የሰለሞንን ቤተ መቅደስ ካፈረሰ በኋላና እየሩሳሌምን አውድሞ ህዝቡን ባሪያ አድርጎ በግዞት ሲወሰድ ከጥፋቱ ያመለጡ የተወሰኑ ሰዎች ግብጽ ገቡ። እነዚህ ሰዎች በግብጽ ፈረኦን አፍራህ ሲጨፈጨፉ የተወሰኑት አምልጠው ወደ ኢትዮጵያ መጡ በማለት ይተርካል መጽሃፍ።
በሌላ ጎን “ፈላሻ” የተባሉት ቤተ እስራኤላውያን በደቡብ አረቢያ ሰፍረው ከነበሩት የአይሁድ ነጋዴዎችና ነዋሪዎች ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ናቸው የሚሉም አሉ።
የታሪክ ድርሳናቱ እንደሚያስረዱት እስራኤላዊያኑ ከዓጼ ሚኒሊክ ቀዳማዊ ጋር ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ በኋላ መጀመሪያ የተቀመጡት በአክሱም ነበር። በኋላም አጼ ኢዛና በ4ኛው ክፍለዘመን ክርስትናን ከተቀበለና ክርስትና በ325 ዓ.ም የአገሪቱ ብሄራዊ ሃይማኖት ሆኖ ከታወጀ በኋላ የተወሰኑት ሲቀበሉ አብዛኞቹ አንቀበልም ብለው አክሱምን ለቀው መጀመሪያ መቀመጫቸውን በሰሜን ተራሮች አደረጉ የራሳቸውንም መሪ አዘጋጁ ስሙም "ፊናስ" ይባላል። ከዛም ቀስ በቀስ በወገራ ፣ በወልቃይት ፣ በደንብያ ፣ በቋራ ፣ በኮሶየ፣ በሽሬ፣ በጭልጋ፣ በወለቃና በጎንደር አንዳንድ አካባቢዎች መኖር ጀመሩ።
ቤተ እስራኤላዊያን በጎንደርና አካባቢዋ ሲኖሩ የእደ ጥበብ ስራዎቻቸውን አጠናክረው ይሰሩ ነበር። በዚህ ጥበበኝነታቸው በጎንደር ከተማ ምስረታ ወቅት በተለይም በአብያተ መንግስታት ፣ በአድባራትና በድልድዮች ግንባታ ላይ ቀዳሚዎቹ አናጺዎችና ጠባቂዎች ነበሩ በማለት በጎንደር ከተማ መቆርቆር ላይ የቤተ እስራኤላዊያንን አሻራ ክሌን የተባሉ ሰው እ.ኤ.አ በ2007 በጻፉት የዶክትሬት ድግሪ ማሟያ ጥናታቸው ላይ አመላክተዋል።
እስራኤላውያን ሃገራቸውን በ1948 እ.ኤ.አ ከመሰረቱ በኋላ በተለያዩ ጊዜያት በተካሄዱ ዘመቻዎች ቤተ እስራኤላውያንን ከኢትዮጵያ ወደ አዲሲቱ እስራኤል ወስደዋቸዋል። እነዚህ ዘመቻዎች በ1976 ዓ.ም. የተካሄደው ዘመቻ ሙሴ፣ በ1977 የተካሄደው ዘመቻ ኢያሱ እንዲሁም በ1983 የተካሄደው ዘመቻ ሰለሞን ነበሩ።
በእነዚህ ዘመቻዎች በኢትዮጵያ ይኖሩ የነበሩ አብዛኞቹ ቤተ እስራኤላውያን የተወሰዱ ቢሆንም በጎንደር ዙሪያ በኖሩበት ጊዜ እስካሁን ድረስ ያሉ ማህበረሰቦች እየተጠቀሙበት ያለ የእደ ጥበብና የሸክላ ስራዎች ሙያን አስተምረዋል። ይህን ሞያ እየሰሩ የኖሩባትና ያስተማሩባት ቦታ ወለቃ ደግሞ አሁንም በእደ ጥበብ ስራዎቿ ታዋቂ እንደሆነች ቀጥላለች።