ግንቦት 3 ፣ 2014

ኢድ አልፈጥርን የሚከተለው ደማቁ ሸዋል ኢድ

City: Dire Dawaባህል ወቅታዊ ጉዳዮች

ሀይማኖታዊ፣ ባህላዊና ማህበራዊ አውዶች ያሉት ሸዋል ኢድ በተለይ በሃረሪ ክልል በድምቀት ይከበራል

ኢድ አልፈጥርን የሚከተለው ደማቁ ሸዋል ኢድ
Camera Icon

Credit: Zenashi Shiferaw

ይህ በዓል በሂጅራ የዘመን አቆጣጠር በሸዋል ወር የረመዳን ፆም ተጠናቆ ኢድ አልፈጥር በዋለበት በስምንተኛው ቀን ይከበራል። በዓሉ በሐረሪ ክልላዊ መንግስት ህዝባዊ እና ባህላዊ በዓል ሆኖ እንዲከበር ጥቅምት 8 1999 ዓ.ም በአዋጅ ተደንግጓል።  

የሸዋል ኢድ በዓል አከባበር ሀይማኖታዊ፣ ባህላዊና ማህበራዊ አውዶች አሉት። ሀረሪዎች ይህን በዓል የሚያከብሩት ኢድ አልፈጥር ከተከበረ በኋላ በተከታታይ ስድስት ቀናት ከተፆመ በኋላ ነው። ፆሙ የሚፆመው ሴቶች በተፈጥሮ  ምክንያት የወር አበባ ወቅት እንዲፆሙ ስለማይፈቀድ ያንን ለማካካስ ወንዶችም እነዚህን ቀናት ጨምረው በመፆም ተጨማሪ ምንዳ ያገኛሉ በሚል እምነት ነው።

በዓሉ በሀረሪዎች ዕድሜና ፆታ ሳይወስነው ሁሉም የየራሳቸውን ሚና እየተወጡ የሚያከብሩት፣ ሁሉም ከዋኝ ሁሉም ተሳታፊ የሚሆኑበት በዓል ነው። ሊቃውንትና አባቶች ዱዓ በማድረስ፣ እናቶች በዜማ ዝማሬና ለበዓሉ የሚያስፈልገውን ድግስ በማዘጋጀት እና የወደፊት የትዳር አጋራቸውን ለመፈለግ ወጣቶች ንቁ ተሳታፊ የሚሆኑበት በዓል ነው።

የሸዋል ኢድ ክብረ በዓል አከባበር የሚጀመረው ከዋናው በዓል ሁለት ቀን ቀደም ብሎ ነው። በየቤቱ እንዲሁም ‘አው አቅበራ’ እና ‘አው ሹሉም አህመድ’ በተባሉ ኃይማኖታዊ አዋቂዎች ከምሽቱ ሶስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋት ድረስ ድቤ እየተመታ በታዳሚዎች ጭብጨባ በሚታጀብና በአዋቂዎች በሚከወን ዝክሪ (መንዙማ) ፈጣን በማመስገን ይከወናል።

በሐረሪዎች ሸዋል ኢድ የሚከበረው ተያይዘው በሚመጡ ሰፊ ትርጉም ባላቸው ማህበራዊ ክንዋኔዎች ታጅቦ ነው። ልጃገረዶች በዓሉን ተከትሎ በሚኖሩ ሶስት ተከታታይ ቀናት ከስራ ነፃ ሆነው የገንዘብ መዋጮ (መሐለቅ መታጫ) በማድረግ ድግስ አዘጋጅተው በመመገብና በመጨፈር በዓሉን ያከብራሉ። ባህላዊ ምግብና መጠጥ የበዓሉ አንዱ አካል ነው። በዓሉ በሚከወንባቸው አካባቢ የሚኖሩ ማህበረሰቦች “አቅሌል” (በቀይ ወጥ የተዘጋጀ ፍትፍት) ፣ “ሐሸር ቃሕዋ” (ከወተት ጋር የተፈላ ትኩስ የቡና ገለፈት)፣ “ቁጢ ቃሕዋ” (ደርቆ የታመሰ የቡና ቅጠል እንደሻይ ተፈልቶና ከወተት ጋር ተቀላቅሎ የሚጠጣ) የመሳሰሉትን  አዘጋጅተው ለበዓሉ ተሳታፊዎች ያቀርባሉ።

የሸዋል ኢድ እየተከበረ በነበረበት አደባባይ ላይ ሲሳተፍ ያገኘነው ሙራድ አብዲ ለሸዋል ትልቅ ፍቅር እንዳለው ይናገራል። በሸዋል ኢድ ሁሉም በባህላዊ አልባሳት አሸብርቆ የሚወጣ በመሆኑአዲሱ ትውልድ አልባሳቱን እንዲወድና እንዲለብስ አዎንታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራል። ባህሉንም በማስተዋወቅ የላቀ ፋይዳ አለው። በዓሉ የሀረሪ ተወላጆች ወደ ሀረር የሚጎርፉበትን እድል ከመፍጠር ባሻገር መስህብ ያለው በመሆኑ የሚፈጥረው የቱሪዝም እንቅስቃሴ ከፍተኛ  እንደሆነና ሀረር በዚህ መጠቀም እንዳለባት በዓሉ ሊኖረው ስለሚችለው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታም ሙራድ አስተያየቱን ይሰጣል።

ሌላኛዋ የበዓሉ ተሳታፊ አሚና ሁሴን ነች። አሚና የዛሬ አመት በዚሁ ሸዋል ኢድ በዓል ላይ እንደተጫጨች ገልፃለች። ከባለቤቷ ጋር ኑሯቸውን በአዲስ አበባ ቢያደርጉም በዓሉን ለማሳለፍ ግን ወደ ሀረር ለመምጣት እንዳልቦዘኑ ተናግራለች። ከዚህ በኋላም የሸዋልን በዓል ለማክበር እንደምትመጣ ገልፃ አሁን አሁን ግን ወጣቶች በባህላዊው የሸዋል ዒድ በዓል ላይ ብዙም እየተጫጩ እንዳልሆነ ተናግራለች። አሚና ምክንያቱን ስታስረዳ “አሁን ከቴክኖሎጂ መስፋፋት ጋር ተያይዞ የአሁኑ ወጣት ጉዳዩን በፌስቡክና በቴሌግራም ይጨርሰዋል፤ እንደነዚህ አይነት ቴክኖሎጂዎች ባህልን የመሸርሸር ጠባይ አላቸው” ስትል ገልፃለች። 

ካለፉት ሁለት አመታት ወዲህ በዓሉን በዩኔስኮ ቅርስነት ለማስመዝገብ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ።  የዘንድሮ በዓል እስካሁን ከነበሩት ይበልጥ የደመቀ እንደነበር የከተማዋ ነዋሪዎችም ይናገራሉ። በአሁኑ አመት ከሚያዝያ 28 እስከ ግንቦት 5 ቀን በተለያዩ ፕሮግራሞች እየተከበረ ይገኛል።

የበአሉ አከባበር የተለያዩ ሁነቶች የነበሩት ሲሆን የሐረሪን ክልል ባህልና አልባሳት የሚያንፀባርቅ ኤግዚቢሽን፣ የተሰሩ ፕሮጀክቶችን ማስመረቅ፣ ሲምፖዝየም፣ ወጣቶች ባህላዊ ጭፈራዎችን ያካተተ ዝግጅቶች፣ ባህላዊ አልባሳትን የሚያስተዋውቅ የፋሽን ሾው፣ የተለያዩ ታሪካዊ ቦታዎች እና ሙዚየሞችን የመጎብኘት ፕሮግራም እንዲሁም ወጣቶች በጉጉት የሚጠብቁት በሸዋል ፆም ስድስተኛው ቀን ማምሻውን የሚከበረው የሸዋል ኢድ የአደባባይ በዓል ይጠቀሳሉ። ይህ የሸዋል ኢድ የአደባባይ በዓል በሀረር ከተማ በፈላና በርና ኤረር በር ተከብሯል።

የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ የ 1443ኛውን ሸዋል ኢድ በዓል በይፋ ያስጀመሩት የሸዋል ዒድ ባህልን የሚዳስስ ጥናታዊ ፅሁፍ በቀረበበት መድረክ ላይ ነው። ሸዋል ኢድ በዘንድሮው አመት ከኢድ እስከ ኢድ ወደሀገር ቤት ጥሪ መርሀግብር አካል በመሆን በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።

አስተያየት