ግንቦት 4 ፣ 2014

ከጥገና ቡድኑ 400 ኪ.ሜ ርቆ የሚገኘው የአሚባራ የኤሌክትሪክ ማሰራጫ ሰብስቴሽን

City: Adamaወቅታዊ ጉዳዮች

በሰብስቴሽኑ ላይ ብልሽት ሲከሰት የጥገና ቡድኑ ከሻሸመኔ 400 ኪ.ሜ ተጉዞ እስኪደርስ ለቀናት የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ ስለሚፈጠር ከፍተኛ የደንበኞችን ቅሬታና ግጭት አስከትሏል

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ከጥገና ቡድኑ 400 ኪ.ሜ ርቆ የሚገኘው የአሚባራ የኤሌክትሪክ ማሰራጫ ሰብስቴሽን
Camera Icon

Credit: Ethiopia Electric Power

ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ የቀድሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ፈርሶ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተብሎ በሁለት ተከፍሏል። እንደባለሞያዎች ቴክኒካዊ ገለጻ ከ66 ኪሎ ቮልት በላይ ያሉ ኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች፣ ሰብስቴሽኖች እና የኃይል ማመንጫ ግድቦች በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ስር ሲተዳደሩ፤ ከ66 ኪሎ ቮልት በታች ያሉ ኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች፣ ሰብ ስቴሽኖች እና የኤሌክትሪክ ኃይል ስርጭት እና ሽያጭ ስራን ደግሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያከናውናል።  

የቀድሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ለሁለት ከተከፈለ ወዲህ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተብሎ የተቋቋመው እና ለደንበኞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት መስጠትን ዋነኛ ተግባሩ ያደረገው ተቋም በብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት ወሰን አከላለልን መሠረት ባደረገ የአሰራር መዋቅር አገልግሎቱን እየሰጠ ይገኛል።

በአሁን ወቅት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት 11 የኤሌክትሪክ አገልግሎት ቅርንጫፎች አሉት። ከእነዚህ አንዱ የአፋር ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ቅርንጫፍ ነው። ከግማሽ በታች የኤሌክትሪክ ሽፋን ያለው አፋር ክልል በስሩ ከ15 እስከ 66 ኪሎ ቮልት አቅም ያላቸው 3  ሰብስቴሽኖች ይገኙበታል። ከእነዚህ ሌላ 66 ኪሎ ቮልት አቅም ያለው አፍዴራ ሰብስቴሽን በግንባታ ላይ ይገኛል። በክልሉ በአሁን ወቅት በስራ ላይ የሚገኘው ብቸኛ የ66 ኪሎ ቮልት አቅም ያለው ሰብስቴሽን የአሚባራ ሰብስቴሽን ብቻ ነው። 

የአሚባራ ሰብስቴሽን በ1980 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ጥገና ይፈልጋል። ይህ ሰብስቴሽን የኤሌክትሪክ ሃይል የሚቀበለው ከአዋሽ 7 ሰብስቴሽን ነው። የመልካ-ወረር ከተማን ፣ የሶዳሞ ጥጥ መዳመጫን፣ የከሰም ስኳር ፋብሪካን ጨምሮ ከአሚባራ እስከ ገዋኔ እና ሳጉሬ ላሉ እስከ 200 ኪሜ ርቀት ላይ ላሉ ቦታዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ያከፋፍላል።

ሰብስቴሽኑ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መደበኛ አሰራር በተቃራኒ በአፋር ኤሌክትሪክ አገልግሎት ስር መሆን ሲገባው በኦሮሚያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በሻሸመኔ ዲስትሪክት ስር ይገኛል። ለሰብስቴሽኑ ማስተዳደደር፣ ድጋፍ እና ጥገና የሚሰጠው ቡድንም ከአሚባራ ከ400 ኪ.ሜ. በላይ ርቀት ላይ ሻሸመኔ ከተማ ውስጥ ይገኛል። ይህ የሆነበት ምክንያት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሰብትራንስሚሽን አሰራር ምክንያት እንደሆነ ባለሞያዎቹ እና ኃላፊዎቹ ይናገራሉ።

የአሚባራ ሰብስቴሽን በማርጀቱ እና የእድሳት ስራም ባለመሰራቱ፣ መስመሩ ባለበት የኃይል ጫና ምክንያት በሚደርስበት ተደጋጋሚ ብልሽት በተደጋጋሚ የኃይል መቆራረጥን ያስከትላል። የጥገና ሰራተኞቹ ከአሚባራ 400 ኪ.ሜ. ርቀው ሻሸመኔ ከተማ ውስጥ በመገኘታቸውና ባለው ርቀት ምክንያት ፈጣን የጥገና አገልግሎት መስጠት ባለመቻላቸው በስፍራው የሚገኙ የአፋር ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት የአሚባራ ደንበኞች አገልግሎት ቅርንጫፍ ሰራተኞች ከአካባቢው ህብተረሰብ እንዲሁም የአስተዳደር አካላት ጋር ተደጋጋሚ ግጭት ውስጥ እየገቡ እንደሆነ ይናገራሉ። 

ያለመግባባቱን መንስኤ ሲገልጹም 'ኤሌክትሪክ ተቋርጦ እናንተ ግን የጥገና ኃላፊነታችሁን እየተወጣችሁ' አይደለም የሚል እንደሆነ ይናገራሉ። ባስ ሲልም እስከ መታሰር ድረስ የሚዘልቅ ጫና ውስጥ እየከተታቸው እንደሆነ ይናገራሉ።

አሚባራ ሰብስቴሽን ላይ ያለው እና እየተፈጠረ ያለው ችግር ምንድን ነው የሚለውን አዲስ ዘይቤ የሚመለከታቸውን አካላት አነጋግራ የሚከተለውን ዘገባ አዘጋጅታለች።

መሐመድ አደም በአፋር ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት የመልካ-ወረር ከተማ ደንበኞች አገልግሎት ጽ/ቤት ስርጭት ቴክኒሻን ነው። መስመሩ በሚቋረጥበት ጊዜ ኃላፊነታቸው ባይሆንም ስራውን እየሰሩ ያሉት እርሱን ጨምሮ በስፍራው ያሉት የመልካ-ወረር ደንበኞች አገልግሎት ቴክኒሻኖች እንደሆኑ ይናገራል። 

“መስመሩ በሚቋረጥበት ሰዓት የጥገና ሰራተኞች ከሻሸመኔ ዲስትሪክት ነው የሚመጡት” የሚለው መሀመድ በስፍራው ርቀት ምክንያት የኃይል መቋረጡ ረጅም ጊዜ እንደሚቆይ ገልጿል። የአካባቢው ህብረተሰብም ጉዳዩ የመልካ-ወረር ደንበኞች አገልግሎት ቅርንጫፍን እንደሚመለከት በማሰብ ወደዚያው ቅሬታ ለማሰማት ቢመጣም መፍትሄ እንደማያገኝ ያስረዳል። 

“ብልሽት ሲገጥም የሻሸመኔ ሰራተኞች እንደሚዘገዩ ስለሚታወቅ በመልካ ወረር ዲስትሪክት ጫና አድርጎ ወደ ስራ እንድንገባ ያደርገናል” የሚለው የመልካ-ወረር ደንበኞች አገልግሎት ባልደረባ እና ቴክኒሻን መሀመድ አደም “በስራ ሂደቱ ላይ አደጋ ቢደርስ ኃላፊነት የሚወስድ አካል የለም። የደንበኞችን ጥያቄ ለመመለስ በሚል ብቻ ተፋጥነን ወደ ስራ እንድንገባ ይደረጋል” ይላል። 

ለመልካ-ወረር አካባቢ ኤሌክትሪክ ደንበኞች አገልግሎት መስሪያ ቤት ፈታኝ የስራ ጫና እየፈጠረ እና ከስራ ድርሻቸው ውጪ ተጨማሪ ልፋት እየፈጠረባቸው የሚገኘው የአሚባራ ሰብስቴሽን እጅግ ያረጀ እንደሆነ ይናገራሉ።

ከአዋሽ 7 ሰብስቴሽን 66 ኪሎ ቮልት ኃይል የሚቀበለው አሚባራ ሰብስቴሽን፣ ኃይል ተቀብለው ወደ አሚባራ ሰብስቴሽን የሚወስዱት መስመሮቹ በእንጨት ምሰሶዎች የተሰሩና ያረጁ ሲሆኑ የኤሌክትሪክ አስተላላፊ መስመሮቹም እንዲሁ በአገልግሎት ብዛት የደከሙ ናቸው። 

የአካባቢው አቀማመጥ ገደላማ እና ሸለቆ የሚበዛው መሆኑ፣ በትልልቅ ዛፎች መሸፈኑ እንዲሁም የአየር ንብረቱ በብዛት ነፋሳማ መሆኑ ከመስመሩ ማርጀት ጋር ተደምሮ የጥገና ሂደቱን ከድጡ ወደ ማጡ አድርጎታል።

“የተቋረጠ መስመር ሲኖር የተቋረጠበትን ቦታ እንኳን ለማወቅ ከዋና የአስፖልት መንገድ ርቀን በጫካ እና በገደል ውስጥ ከሰባት እስከ ስምንት ኪሎ ሜትሮች ድረስ በእግራችን እንጓዛለን” ሲል የስራውን አድካሚ ጫና የሚናገረው መሃመድ አሮጌዎቹ የእንጨት ምሰሶዎች ወደ ታወር ወይም ወደ ኮንክሪት ምሰሶ ካልተቀየሩ እንዲሁም የኤሌክትሪክ አስተላላፊ መስመሮቹም በአዲስ ካልተተኩ ዘላቂ መፍትሔ አይኖረውም ይላል።

“የጥገና ቡድኑ ቀድሞ በአዳማ ዲስትሪክት ስር ነበር። አሁን የባሰ ርቆ በሻሸመኔ ዲስትሪክት ስር ሆኗል። ቢቻል ቅርብ ባሉ ዲስትሪክቶች ስር ሆኖ ቢተዳዳር የተሻለ ነው” በማለት መሃመድ አስተያየቱን ይሰጣል።

ያለፉትን ስድስት ዓመታት በአሚባራ ሰብስቴሽን ውስጥ በስራ እንዳሳለፉ የነገሩን አቶ አብዲሳ ገመቹ በአሁን ወቅት የሰብስቴሽኑ ኃላፊ ናቸው። የሚያስተዳድሩት ሰብስቴሽን አቅሙ 8.4 ሜጋ ዋት እንደሆነና እስከ 200 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ድረስ ላሉ የአፋር ክልል አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት እንደሚሰጥ ነግረውናል።

የአሚባራ ሰብስቴሽን መልካ ወረር ለሚገኘው ለሶዳሞ ለጥጥ መዳመጫ እና ለመልካ- ወረር ከተማ እና አካባቢዋ ለእያንዳንዳቸው 15 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ኃይል ሲሰጥ በ200 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ለምትገኘው ገዋኔ ከተማ እና አካባቢዋ እንዲሁም በ100 ኪ.ሜ. ላይ ለምትገኘው ሳቡሬ ከተማ ለእያንዳንዳቸው 33 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ኃይል ያቀርባል።

የሚያስተዳድሩት ሰብስቴሽን በየትኛው ክልል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ስር እንዳለ የጠየቅናቸው አቶ አብዲሳ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተውናል። “አደረጃጀት ሲሰራ ሰብስቴሽኑ በኦሮሚያ ስር ነው የተሰራው። የአፋር ሪጅን በእኛ ስር ይሁን ብለው ጥያቄ ማቅረባቸውን አውቃለሁ። አሁን ምን ላይ እንደደረሰ አላውቅም” የሚሉት ኃላፊው የጥገና ቡድኑ መራቅ የጥገና ስራውን አስቸጋሪ እንዳደረገው ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ  ኤሌክትሪክ ኃይል እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለሁለት ከተከፈለ ወዲህ በሁለቱ መሃከል የጥገና ውል እንደነበር አቶ አብዲሳ አስታውሰው በአሁኑ ወቅት ግን ውሉ መቋረጡን ነግረውናል። ውሉ በመቋረጡም ምክንያት የጥገና ሰራተኞቹ ከሻሸመኔ መጥተው ለመስራት መገደዳቸውን ይናገራሉ።

“ወደ ሰብስቴሽኑ ገቢ 66 ኪሎ ቮልት መስመሮች ሲወድቁ  ምንም እንኳን ግዴታቸው ባይሆንም የአፋር ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሰራተኞች ለህዝብ ጥቅም ሲሉ ጥገና ያደርጋሉ” የሚሉት አቶ አብዲሳ እነሱም የስራ ድርሻችው ባይሆንም ለደንበኞች ፈጣን አገልግሎት ሲባል በቻሉት አቅም ከአፋር ክልል ቴክኒሻኖች ጋር የጥገና ስራውን እንደሚሰሩ አስረድተዋል። 

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አሰራር መሠረት የጥገና ባለሞያዎች እንደየስራ ክፍላቸው የተለያየ ኃላፊነት እና ደረጃ አላቸው። የደንበኞች አገልግሎት ላይ የሚገኙ የጥገና ሰራተኞች ከ45 ኪሎ ቮልት በላይ የሆነ የኃይል መስመር የመጠገን ኃላፊነትም ሆነ ግዴታ የለባቸውም። በዚህም ምክንያት ሰራተኞቹ ግዴታቸው እና ኃላፊነታቸው አለመሆኑን ይናገራሉ።

የአሚባራ ሰብስቴሽን ኃላፊው አቶ አብዲሳ የሰብስቴሽኑ ማርጀት ከመጪው የክረምት ወቅት እና አካባቢው ካለው ንፋሳማ የአየር ንብረት አንጻር ሰብስቴሽኑ የከፋ ችግር ላይ እንዳይወድቅ ስጋት እንዳሳደረባቸው ይናገራሉ። በቅርብ ጊዜ የተፈጠረውን ሁኔታ እንዲህ ያስታውሱታል። 

“ሰብስቴሽኑ በማርጀቱ ጣሪያው በንፋስ ተወሰደ። የስራ ድርሻችን ባይሆንም ዝናብ ከዘነበ ሰብስቴሽኑ እስከመቃጠል የሚደርስ ጉዳት ሊያጋጥመው ስለሚችል ይህንን ለመከላከል በራሳችን ቆርቆሮ ገዝተን ጠግነናል” ሲሉ ሰብስቴሽኑ ያለበትን ሁኔታ ያስረዳሉ።

ሰብስቴሽኑ እንዲጠገን በባለፈው ዓመት ማለትም በ2013 ዓ.ም በጀት መያዙን ያስረዱን አቶ አብዲሳ እስካሁን ግን ምንም የተደረገ ነገር እንደሌለ ገልጸዋል። በተጨማሪም ካለፈው አመት ጀምሮ በደብዳቤ እንዲሁም በአካልም ቀርበው ለሻሸመኔ ዲስትሪክት ያለውን ችግር ቢያስረዱም መልስ አለማግኘታቸውን ነግረውናል።  

ከ2013 ዓ.ም ክረምት በፊት ሰብስቴሽኑ በኦሮሚያ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት አዳማ ዲስትሪክት ስር እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ። ከ2013 ዓ/ም  ወዲህ ግን ሰብስቴሸኑ ተጠሪነቱ ወደ ሻሸመኔ ዲስትሪክት ተዘዋውሯል። ይህም የሆነበትን ምክንያት ሲያስረዱ ሻሸመኔ ከአዳማ ይልቅ በሰብትራንስሚሽን ስር ለሚተዳደደሩ ከ45 እስከ 66 ኪሎ ቮልት አቅም ላላቸው ሰብስቴሽኖች አማካኝ በመሆኑ እንደሆነ ይገልጻሉ። ይህም በ 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የነበረውን የጥገና ቡድን ተጨማሪ 200 ኪሎ ሜትሮች እንዲርቅ ምክንያት ሆኗል።

ሻሸመኔ ከአሚባራ በ400 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ትገኛለች። በወቅቱ ይህ ውሳኔ ሲወሰን የአሚባራ ሰብስቴሽን ሰራተኞች እና ኃላፊዎች ጥያቄ አንስተው ነበር። 

“አዳማ ቢሆን ለድንገተኛ ጉዳዮችም ምላሽ ለመስጠት ቅርብ ነው ብለን ብንጠይቅም ሻሸመኔ ለተለያዩ ሰብስቴሽኖች አማካይ ነው በሚል ወደ ሻሸመኔ ዲስትሪክት ተዘዋውሯል” ሲሉ አቶ አብዲሳ በወቅቱ የተሰጣቸውን ምላሽ ነግረውናል።

በኦሮሚያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ስር የሚገኘው በሻሸመኔ ዲስትሪክት በኦሮሚያ ክልል ስር የሚገኙትን ሞጆ፣ ጎቤሳ ፣ ኑራኤራ ሰብስቴሽኖችን እንዲሁም በአፋር ክልል ስር የሚገኘውን አሚባራ ሰብስቴሽኖችን ያስተዳድራል።

ከሻሸመኔ ሞጆ 180፣ ኑራኤራ 337፣ ጎቤሳ 170 እና አሚባራ 400 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ይገኛሉ::

የአፋር ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና መስሪያ ቤት መቀመጫው በክልሉ ርዕሰ መዲና ሠመራ ነው። አቶ መሃመድ አብዱ የአፋር ክልል ኤኤሌክትሪክ አገልግሎት አውቶሜሽን ም/ስራ አስኪያጅ እና የዋና ስራ አስኪያጅ ተወካይ ሲሆኑ ይህ የአወቃቀር ችግር የተፈጠረው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከ45 ኪሎ ቮልት እስከ 66 ኪሎ ቮልት ያሉ ሰብስቴሽኖችን ለማስተዳደር እና ለመጠገን የሚጠቀምበት አደረጃጀት ሲዘረጋ እንደሆነ ነግረውናል። 

“የአዋጭነት ጥናት ተሰርቶ አንድ ሰብስቴሼንን ብቻ የሚከታተል የጥገና ቡድን ማቋቋም አዋጭ አይደለም በሚል ነበር በኦሮሚያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አዳማ ዲስትሪክት ስር አሚባራ እንዲተዳደር የተወሰነው” ይላሉ። 

በዚህ ምክንያት በአዳማ ዲስትሪክት ስር ሲተዳደር የነበረው የአሚባራ ሰብስቴሽን ከባለፈው 2013 ዓ.ም ክረምት ጀምሮ በተቋሙ ውሳኔ ወደ ሻሸመኔ ዲስትሪክት ተዘዋውሯል። አዳማም ሆነ ሻሸመኔ ከተሞች ከአሚባራ ረጅም ርቀት ላይ የሚገኙ ቦታዎች መሆናቸው የጥገና ጊዜውን በማራዘሙ ከፍተኛ የህዝብ ቅሬታ እና የሰራተኞች እንግልት መንስዔ እንደሆነ ም/ስራ አስኪያጁ ይገልጻሉ።  

“እንደዘላቂ መፍትሔ እዚሁ በአፋር ክልል ውስጥ ሆኖ የሚጠግን ቡድን መቋቋም አለበት እንዲሁም መስመሮች መጠገን እና ሰብስቴሽኑም እድሳት ሊደረግለት ይገባል ብለን ጥያቄ አቅርበናል” የሚሉት ም/ስራ አስኪያጁ አቶ መሃመድ አብዱ ወደፊትም ጥያቄው ምላሽ እስከሚያገኝ ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉ ነግረውናል።

በአሚባራ ሰብስቴሽን ላይ በረመዳን ጾም ፍቺ ወቅት ገጥሞ የነበረን ብልሽት ከሻሸመኔ የጥገና ቡድን እና መለዋወጫ ተልኮ ተጠግኖ ወደ አገልግሎት መመለሱን አስታውሰው ያም ሆኖ ጥገናው ግዜያዊ እንጂ ዘላቂ መፍትሔ እንዳላመጣ ይናገራሉ።

አቶ መሃመድ በዘላቂነት መፍትሔ ያሉትን ሀሳብ ሲያስቀምጡ “አንደኛ ያረጁት ፖሎች መቀየር አለባቸው፣ ሁለተኛ አስፈላጊው የሰው ኃይል እና በጀት ተመድቦ ሰብስቴሽኑ ሙሉ በሙሉ በክልሉ ስር መተዳዳር አለበት አለበለዚያ ዘላቂ መፍትሔ ይኖራል ብለን አናስብም” ይላሉ። ምክንያቱንም ሲያስረዱ መስመር ሲቋረጥ የጥገና ቡድኑ እስኪመጣ ከአንድ ቀን እስከ ሁለት ቀን በመፍጀቱና ይህም ደግሞ ከፍተኛ የደንበኞችን ቅሬታ እያስከተለ በመሆኑ ነው። 

ኤሌክትሪክ ኃይል ተቋርጦ በሚቆይበት ሰዓት ከፍተኛ የህዝብ ቅሬታ እና ጫና ስለሚኖር የአካባቢው መንግስት አስተዳደር አካላት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሰራተኞችን እስከማሰር የሚደርስ እርምጃ እንደሚወስዱ ገልጸው ይህም በሰራተኞቹ ላይ ከፍተኛ የስነ-ልቦና ጫና እንደፈጠረባቸው ይናገራሉ። 

“እኛ መልካ-ወረር ላይ ያሉን 15 ሺህ ኪሎ ቮልት እና 33 ሺህ ኪሎ ቮልት ማዕከላትን የመጠገን አቅም እና ኃላፊነት ያላቸው እንጂ የ66 ሺህ ኪሎ ቮልት ጠጋኝ ባለሞያዎች የሉንም” ይላሉ አቶ መሃመድ። 

ሻሸመኔ የሚገኘው የጥገና ቡድን ብልሽት እንደገጠመ ሪፖርት ተደርጎለት ለጥገና ተጉዞ እስኪደርስ የአካባቢው አስተዳደር አካላት በአፋር ክልል ስር የሚገኙት ሰራተኞችን 'የመስሪያ ቤቱ አባላት ሆናችሁ እንዴት ጥገናው ዘገየ'  በሚል ምክንያት  እስር እና መሠል ችግሮች ይፈጥሩባቸዋል የሚሉት አቶ መሐመድ ጉዳዩን ለማስተካከል ከመንግስት አስተዳደር አካላት ጋር እንደሚሰሩ ነግረውናል።

በኦሮሚያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሻሸመኔ ሰብትራንስሚሽን ኃላፊ የሆኑት አቶ ፉሪ ገመቹን በጉዳዩ ዙሪያ አነጋግረናቸው ነበር። ሰብትራንስሚሽን ማዕከሉ ከ45 እስከ 66 ኪሎ ቮልት አቅም ያላቸው 6 ሰብስቴሽኖች በስሩ እንዳሉ ይናገራሉ፤ እነሱም ሞጆ፣ ኑራኤራ፣ ጎቤሳ፣ ባሌ ሮቤ፣ ነጌሌ ቦረና እንዲሁም አሚባራ ሰብስቴሽኖች ናቸው።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አሰራር ሰብስቴሽኖች ከከፍተኛ ከኃይል ተሸካሚ የኤሌክትሪክ መስመሮች የተቀበሉትን የኤሌክትሪከ ኃይል አጎልብተው ወይም አሳንሰው ለተጠቃሚ የሚያደርሱ ጣቢያዎች ናቸው። በሌላ መልኩ ደግሞ ሰብትራንስሚሽን ደግሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በስሩ የሚገኙ ከ45 እስከ 66 ኪሎ ቮልት አቅም ያላቸው ሰብስቴሽኖችን የሚያስተዳድርበት መዋቅር ነው

“የሰብትራንስሚሽኑ ቢሮ ሻሸመኔ የተደረገው ለሌሎችም ሰብስቴሽኖች አማካኝ እንዲሆን በማሰብ ነው” ያሉት ሃላፊው አሚባራ ከሻሸመኔ 400 ኪ.ሜ.፣ ነገሌ ቦረና ደግሞ በ500 ኪ.ሜ. ርቀት የሚገኙ ሲሆን ማዕከሉ አዳማ በነበረ ግዜ ግን ነገሌ ቦረና ለጥገና ለመሄድ ከ700 ኪ.ሜ. በላይ ይፈጅ እንደነበር አስታውሰዋል። 

ሰብትራንስሚሽኑ በስሩ የሰብስቴሽን እና የትራንስሚሽን ጥገና ክፍሎች አሉት፤ እነኚህ እያንዳንዳቸው 8 ሰራተኛ አላቸው። እንደኃላፊው ገለጻ እነዚህን ሁሉ ለጥገና ስራ ብቻ የሚንቀሳቀሱ ሰራተኞች ለአንድ ሰብስቴሽን ብሎ መመደብ አስቸጋሪ እንደሆነ ተጠንቶ መወሰኑን ነግረውናል።

ሰብስቴሽኑን ማስተዳደር የኢትዮጵያን ኤሌክትሪክ አገልግሎት ኃላፊነት እንደሆነ ገልጸው “እኛ አስተዳድሩ እስከተባለ ድረስ እናስተዳድራን የውሳኔ ለውጥም ካለ እናስተላልፋለን” ይላሉ አቶ ፉሪ።

ሰብስቴሽኑ እና የኤሌክትሪክ አስተላላፊ መስመሮቹ ስለማርጀታቸው የሚስማሙት ኃላፊው ወደ ኮንክሪት ምሰሶ እንዲቀየሩ ለሚመለከተው ክፍል አመልክተናል ብለዋል። በተጨማሪም ለጥገና የተያዘው በጀት እንዴት ስራ ላይ ሳይውል ቀረ ብለን የጠየቅናቸው አቶ ፉሪ ሰብስቴሽኑ በእነርሱ ስር ከሆነ ገና 6 ወሩ እንደሆነ ይናገራሉ።

“የአሚባራ ሰብስቴሽን በአዳማ ዲስትሪክት ስር በነበረ ጊዜ ለጥገና የተያዘው በጀት በአፋር እና አዳማ ዲስትሪክት አለመግባባት መመለሱን አውቃለሁ” የሚሉት አቶ ፉሪ ከክረምቱ በፊት ሰብስቴሽኑን ለማደስ እያስጠኑ መሆኑን ነግረውናል። 

“ለመጪው ክረምት የእንጨት ፖሎች እና ሲኒዎች እንዲቀየሩ አድርገናል” ሲሉ ለመጪው ክረምት የተደረገውን ቅድመ-ዝግጅት ገልጸዋል።

ከኃይል ማመንጫዎች የሚመረተውን የኤሌክትሪክ ኃይል በመላው ሀገሪቱ ባሉ የስርጭት መስመሮችና ለማስተላለፍ እንዲሁም ለተጠቃሚዎች ለማድረስ ከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ መስመሮችና ሰብስቴሽኖች እጅግ አስፈላጊ ናቸው። በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መረጃ መሰረት በአሁኑ ወቅት ከ132-500 ኪሎ ቮልት ተሸክመው የሚያስተላልፉ መስመሮች ከ 17,000 ኪ.ሜ በላይ የተዘረጉ ናቸው። ከ132-500 ኪሎ ቮልት የሚያስተናግዱ ሰብስቴሽኖችም 163 ደርሰዋል።

አስተያየት