ነሐሴ 5 ፣ 2014

የድሬዳዋ ቻርተር መሻሻል ለከተማዋ ነዋሪ ፋይዳ ይኖረው ይሆን?

City: Dire Dawaፖለቲካማህበራዊ ጉዳዮችወቅታዊ ጉዳዮችከተማ

የድሬዳዋ ቻርተር ዘላቂ መፍትሔ እስኪገኝ ድረስ የተቀመጠ እንጂ በራሱ ለረጅም ጊዜ ሊያገለግል ታስቦ የተዘጋጀ አዋጅ አይደለም: የህግ ባለሙያ

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራው

ዝናሽ ሽፈራው በድሬዳዋ የሚትገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነች።

የድሬዳዋ ቻርተር መሻሻል ለከተማዋ ነዋሪ ፋይዳ ይኖረው ይሆን?
Camera Icon

ፎቶ፡ ዝናሽ ሽፈራው (ከአዲስ ዘይቤ)

የኢህአዴግ አስተዳደር ከሽግግር መንግስቱ ምስረታ በኋላ አስራ አራቱን የክልል መስተዳደሮች ወደ ዘጠኝ ክልላዊ መንግስታት እና ወደ ሁለት የከተማ አስተዳደሮች ስር አዋቀረ። ዘጠኙ ክልሎች የየራሳቸውን ህገ መንግስት ሲያዘጋጁ ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ማለትም የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተሞች ደግሞ የየራሳቸው መተዳደሪያ 'ቻርተር' ተዘጋጀላቸው።

በሂደት በህገ መንገስቱም ሆነ በቻርተሮቹ ውስጥ በተቀመጡ አንዳንድ አንቀጾች በህዝብ ዘንድ ቅሬታን አስከትለዋል። በተለይም የድሬዳዋ ቻርተር በአብዛኛው የከተማዋ ነዋሪ ዘንድ ውስጥ ውስጡን ቅሬታዎች ቢቀርቡበትም፤ በአደባባይ ትችት ሲሰነዘርበት ለረጅም ጊዜ አልታየም። ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህዝቡ በድሬዳዋ ቻርተር ዙሪያ ጥያቄዎችን በተለያዩ ጊዜያት በይፋ ማንሳት ጀምሯል። ጥቂት የማይባሉ ነዋሪዎችም “ድሬዳዋን ወደኋላ እንድትቀር ያደረጋት ቻርተሩ ነው” በማለት ቅሬታቸውን ሲገልጹ ይሰማል። 

ይህን በተመለከተ ከሰሞኑ የድሬዳዋን ቻርተር ለማሻሻል አዲስ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የድሬዳዋ ነዋሪዎች ለውይይት ቀርቧል። ረቂቅ አዋጁ 68 አንቀፆችና 186 ንኡስ አንቀፆች ያሉት ሲሆን በ10 ክፍሎች ተዘጋጅቶ የቀረበ ነው።

ለመሆኑ ቻርተር ማለት ምን ማለት ነው? የድሬዳዋ የቀድሞ ቻርተርስ ምን ጉድለት ነበረበት? እንዲሁም አዲስ የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅስ ምን ጥቅም ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል ? የሚሉትን ጥያቄዎች በማንሳት አዲስ ዘይቤ የተለያዩ አካላትን አነጋግራ የሚከተለውን ይዛለች።

አቶ ጌቱ ደርቤ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ሳቢያን ሁለተኛና መሰናዶ ት/ቤት የስነ ዜጋና ስነምግባር መምህር ናቸው። በፌዴራል የመንግስት አስተዳደር ስርዓት የሚተዳደሩ ሀገሮች የሚመሩበት ህጎች ሁሉ የበላይ ህግ የፌዴራል ህገ መንግስት መሆኑን አንስተው፤ “በፌዴራል ሥርዓት በሚተዳደሩ ሀገሮች ውስጥ ከአንድ በላይ ህገ መንግስት ይኖራል” በማለት ሃሳባቸውን  ይሰጣሉ። 

“ይህም ማለት ፌዴራል መንግስቱን የመሰረቱት ክልላዊ መንግስታት የየራሳቸው ህገ መንግስት ሲኖራቸው ማዕከላዊ ወይም ፌዴራል መንግስት ተብሎ የሚጠራው ደግሞ የራሱ ህገ መንግስት ይኖረዋል። የክልል ህገ መንግስቶችና ሌሎች ልክ እንደ ቻርተር ያሉ ህጎችና ደንቦች የፌዴራል መንግስቱን ህገ መንግስት መነሻ አድርገው የሚዘጋጁ ናቸው” ሲሉ አቶ ጌቱ ይገልጻሉ። 

እንደ መምህሩ ማብራሪያ “ክልሎች የራሳቸውን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ያዘጋጁት ህገ መንግስት አላቸው። ድሬዳዋም ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዋን ባማከለ መልኩ የምትተዳደርበት ቻርተር ተዘጋጅቷል። ይህ ቻርተር የሚያገለግለውም ለወጣበት አካባቢ ብቻ ነው” ሲሉ ይናገራሉ።

ፎቶ፡ ዝናሽ ሽፈራው (ከአዲስ ዘይቤ)

የድሬዳዋ ቻርተር ሐምሌ 23/1996 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 416/1996 የወጣና ድሬዳዋ እራሷን በራሷ እንድታስተዳድር ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ አቶ ዑመር ሁሴን በድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት የህግ ፍትህና መልካም አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ናቸው።

አቶ ዑመር ሁሴን እንደሚሉት “ቻርተሩ ድሬዳዋ እራሷን በራሷ እንድታስተዳድር አግዟል። በወቅቱ የነበሩ ችግሮችን በአንፃራዊነት ያስወገደ ቢሆንም በቻርተሩ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ድንጋጌዎች በአስተዳደሩ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ የማያመላክቱ በመሆኑ በአሰራር ላይ ችግሮችን አስከትሏል” ይላሉ። 

“ይህም በመሆኑ ችግሮችን በማስወገድ አሰራርና የአደረጃጀትን፣ እንዲሁም ዲሞክራሲና መልካም አስተዳደርን በላቀ ደረጃ በሚያሰፍን፤ ከወቅታዊ እድገትና ልማት አቅጣጫ ጋር በሚጣጣም መልኩ ቻርተሩ እንዲሻሻል ማድረግ አስፈልጓል” በማለት አቶ ዑመር ገልፀዋል። 

ቻርተሩን የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁን ያዘጋጁት ከተለያዩ አካላት የተውጣጡ ባለሙያዎች ናቸው። ይህ ቡድን ከአስተዳደር ምክር ቤቱ የህግ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ ከከንቲባ ፅ/ቤት የህግ ባለሙያ (በግል)፣ ከእንባ ጠባቂ ተቋም፣ ከፌዴራል አቃቤ ህግ እና ከፍትህ ቢሮ የተወጣጣ ነው። ረቂቁንም ከአለም አቀፍ ህጎች ጋር በማመሳከር የድሬዳዋን ነባራዊ ሁኔታን ያገናዘበ ሆኖ መዘጋጀቱን አቶ ዑመር ጨምረው ያስረዳሉ።

ይህን ረቂቅ አዋጅ ለማዘጋጀት የተለያዩ ህጎች ተጣቅሰዋል። ከነዚህም ውስጥ የቀድሞው የድሬዳዋ ቻርተር አዋጅ 416/1996 ዓ.ም፣ የክስና ተዛማጅ ህጎች፣ የቤተሰብ ህግ፣ በ1955 የወጣው የፍትሃ ብሔር ህግ፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አዋጅ ቁጥር 720/2004 ዓ.ም፣ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አዋጅ እንዲሁም የትራንስፖርት ህግን ለመቆጣጠር የወጡ አዋጆች ጋር ተገናዝቦ መቅረቡ ተነግሯል።

ከዚህ በፊት የነበረው አዋጅ በአስተዳደሩ የሚገኙ 38 የገጠር ቀበሌዎችን ያላማከለ እና ቀጥተኛ የህዝብ ተሳትፎን ያላረጋገጠ ማለትም ህዝብ ያልተወያየበት ነበር። በተጨማሪም በገጠርና በከተማ መካከል ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል አለመኖሩ፣ ቀልጣፋ የፍትህ ስርዓት አለማግኘት፣ የስልጣን እርከኑ በማዕከልና በቀበሌ ብቻ መወሰኑ፣ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የተሰጣቸው የዳኝነት ስልጣን ውስን መሆኑ፤ እንዲሁም የአስተዳደሩ የስራ ቋንቋዎች በድሬዳዋ ያለውን ብዝሀነት መሰረት ያላደረገ እንደነበር ያነጋገርናቸው ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

ከአዲስ ዘይቤ ጋር ቆይታ ያደረጉት የህግ ባለሞያ አቶ አቤል ልዑልሰገድ እንደሚሉት “የድሬዳዋ ቻርተር ዘላቂ መፍትሔ እስኪገኝ ድረስ የተቀመጠ እንጂ በራሱ ለረጅም ጊዜ ሊያገለግል ታስቦ የተዘጋጀ አዋጅ አይደለም” ይላሉ።

አቶ አቤል የድሬዳዋን ቻርተር ጊዜያዊነት ሲያስረዱም “በ1994 እ.አ.አ የሶማሌ ክልል ጅግጅጋን የክልሉ ዋና ከተማ ከማድረጉ በፊት ድሬዳዋን ዋና ከተማ ለማድረግ ይጠይቃል። በወቅቱ ደግሞ ድሬዳዋ የተነቃቃች የንግድ ማዕከል እና እያደገች ያለች ከተማ ነበረች። በዚህ ጊዜ የኦሮሚያ ክልልም ድሬዳዋ ላይ የይገባኛል ጥያቄ በማንሳቱ ምክንያት ቻርተሩን የፌዴራል መንግስት እንደ መፍትሔነት ያስቀመጠው የህግ ማዕቀፍ ነው” በማለት ያብራራሉ። 

ቻርተሩ በጊዜው በነበረው የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ሁኔታ ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀ በመሆኑና አዘገጃጀቱም ጊዜያዊ በመሆኑ ምክንያት መቀየሩ ለድሬዳዋ በጣም አስፈላጊ መሆኑን የሚያምኑበት የሕግ ባለሞያው፤ አሁን ላይ ብዙ ነገሮች ስለተቀያየሩ በጊዜው ያስማማሉ ተብለው የተዘጋጁ ህጎች በአሁን ሰዓት እንደማይሰሩ ይናገራሉ። 

እንደ የሕግ ባለሙያው ኃሳብ ከኢኮኖሚ አንፃር ድሬዳዋን ወደኋላ እንድትቀር ያደረጋት ቻርተሩ ነው ማለት ባይቻልም አንደ አንድ ምክንያት ግን መጠቀስ እንደሚችል ያስረዳሉ።

አዲስ ዘይቤ አሁን ከሚሻሻለው ቻርተር ድሬዳዋ ምን ትጠብቃለች ? ብላ ለጠየቀችው ጥያቄ  የሕግ ባለሙያው አቶ አቤል ሲመልሱ “በአብዛኛው ተሻሻሉ የሚባሉ ህጎች ህዝቡ ላይ ለውጥ ሲያመጡ አላይም። ምክንያቱም ወረቀት ላይ ብቻ ይቀሩና ወደታች ወርደው አይፈፀሙም። ይህ በተለያዩ ምክንያቶች ሊፈጠር ይችላል። ለማህበረሰቡ በተገቢው መልኩ ግንዛቤ ያለመፍጠርና የአስፈፃሚ አካላት ግዴለሽነት ወይም የራስ ፍላጎትን ማስቀደም ሊጠቀሱ የሚችሉ ምክንያቶች ናቸው” በማለት ገልጸዋል።

“በግሌ ይህ ቻርተር ድሬዳዋ ላይ ለውጥ የሚያመጣና ተግባር ላይ ሊውል የሚችል መሆን አለበት ባይ ነኝ” ሲሉ ይናገራሉ። “ቻርተሩ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታና ከትውልዱ ፍላጎት ጋር የሚጣጣም መሆን ይኖርበታል። በተጨማሪም ስልጣን እንዴት እንደሚሰጥና እንደሚቀማ በግልፅ ያስቀመጠ ቢሆን ይመረጣል” በማለት አቶ አቤል አስረድተዋል።

ነባሩ ቻርተር ለድሬዳዋ እድገት ወሳኝ የሆኑ ገቢዎችን ለፌዴራል መንግስት በማድረጉ በኢኮኖሚው ላይ ጫና አሳድሯል። ይህንንም ጫና ማሻሻል የሚያስችሉ ድንጋጌዎችን ባለመያዙ እና በከተማ አስተዳደሩ የሚመራ ቀጥተኛ የፖሊስ ኃይል አለመኖር በዋነኝነት በአዋጁ የተጠቀሱ ክፍተቶች እንደሆኑ ባለሙያዎቹ ጨምረው ይገልጻሉ።

የባንክ ባለሞያው አቶ ተሻገር ተሾመ ደግሞ በቻርተሩ መሻሻል ላይ ሙሉ በሙሉ እንደሚስማሙ ይናገራል። “ድሬዳዋ ለልማት ፈር ቀዳጅ የሆነች ከተማ ነበረች። እንደ አነሳሷ እድገቷ በዛው ልክ አልሆነም። ለዚህ በዋነኝነት አስተዳደሩ ልክ እንደ አንድ ተቋም በተመደበለት በጀት ብቻ እንዲንቀሳቀስና የግብር ተካፋይ አለመሆኑ ኢኮኖሚው ላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል። አዲስ የሚሻሻለው ህግም ይህን ችግር ይፈታል ብዬ አስባለሁ” ይላሉ።

በተጨማሪም የድሬዳዋ ነዋሪዎችን ጥቅም የሚያስጠብቁ ህጎች፤ ለምሳሌ የከተማው ነዋሪዎች ቅድሚያ የአመራር እድል ማግኘት እንዲሁም ኢኮኖሚው ተስተካክሎ ሰፊ የስራ ዕድል የሚፈጠርበት ይሆናል የሚል ተስፋ እንዳላቸው አቶ ተሻገር ገልጸዋል። 

ረቂቅ አዋጁ በመሰረታዊነት ያስፈለገበት ምክንያት የአስተዳደሩን አደረጃጀትና አሰራር ከዲሞክራሲ መርሆዎችና ከመልካም አስተዳደር ስርዓት እንዲሁም ከወቅታዊ የእድገትና የልማት አቅጣጫ ጋር በሚጣጣም መልኩ በህግ መወሰን በማስፈለጉ እንደሆነ ተነግሯል። 

አዲስ ስለሚሻሻለው የድሬዳዋ ቻርተር አስተያየቱን የጠየቅነው ወጣት “ይህ ቻርተር 40. 40. 20 የአመራር ዕድል ክፍፍል አለው። ይህም ማለት 40 እጅ ለሶማሌ፣ 40 እጅ ደግሞ ለኦሮሞ ቀሪው 20ው እጅ ደግሞ ለተቀሩት ብሔሮች የሚል ነው። አዲስ የሚፀድቀው ቻርተር በዚህ ዙሪያ የተሻለ ነገር ይዞ እንደሚመጣ እጠብቃለው” ሲል ያለውን ተስፋ የገለጸልን አቶ ብስራት ነጋ በድሬዳዋ ከተማ ነዋሪ ነው።

ለውይይት የቀረበው የተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ መሰረታዊ ማሻሻያ ከተደረገባቸው መካከል ከስያሜ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች እና የአስተዳደሩ የስራ ቋንቋ አማርኛ፣ ኦሮምኛ እና ሶማሊኛ ሆነው መወሰናቸው ተገልጿል። 

በተሻሻለው ቻርተር የአስተዳደሩ ስልጣን አደረጃጀት በማዕከል፣ በወረዳ እና በቀበሌ የስልጣን አካላት የሚከፋፈል ይሆናል።

የአስተዳደሩ ፖሊስ ኮሚሽንን በተመለከተ በተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ መሰረት በአስተዳደሩ በሚወጣው ህግ የሚቋቋም እንደሚሆን ተጠቁሟል። 

የፍትሃ ብሔር ጉዳዮችን የመዳኘት ስልጣን፣ የፌዴራል ቤቶች በባለቤትነት የሚያስተዳድራቸውን ቤቶች፣ ውርስን፣ የወንጀል ዳኝነትን፣ በፋይናንስ የሚነሱ ወንጀሎችን በሚመለከት፣ የወንጀል ዳኝነትን በሚመለከት፣ የትራፊክ ደንብ መተላለፍ፣ የታክስ ይግባኝ ኮሚሽን እንዲሁም የቀበሌ ማህበራዊ ፍርድ ቤቶችን አቅም ማሳደግን በተመለከተ በአዲሱ ቻርተር ፍርድ ቤቶች የመዳኘት ስልጣን ተሰጥቷቸዋል።

አስተያየት