ነሐሴ 6 ፣ 2014

ለ 28 ዓመታት የተጓተተው የደብረታቦር ከተማ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ

City: Gonderወቅታዊ ጉዳዮችከተማ

አገልግሎቱን ያቋረጠው ይህ የአውሮፕላን ማረፊያ በአጼ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ተገንብቶ ለ 39 አመታት አገልግሎት ሲሰጥ የነበረ ሲሆን፤ ከ 1986 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ ቆሞ ቀርቷል።

Avatar: Getahun Asnake
ጌታሁን አስናቀ

ጌታሁን አስናቀ በጎንደር የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ለ 28 ዓመታት የተጓተተው የደብረታቦር ከተማ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ
Camera Icon

Credit: Social Media

በየዓመቱ ብዙ ሺህ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ቱሪስቶች የሚጎበኟት የደብረታቦር ከተማ፤ የሰው ሰራሽ እና የታሪካዊ መስኅቦች ባለቤት ናት። ይሁንና የደብረታቦር የአውሮፕላን ማረፊያ አገልግሎት ባለመስጠቱ ጎብኚዎች  ከአዲስ አበባ 667 ኪ.ሜ ወይንም ከባህርዳር ከተማ 97 ኪ.ሜ አልያም ከጎንደር ከተማ 143 ኪ.ሜ በመኪና ከመጓዝ ውጭ ሌላ አማራጭ የላቸውም።

ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ በ 1867 እ.ኤ.አ ላይ ያሰሩት 'ሴባስቶፖል' የተሰኘ መድፍ የተሰራበት የጋፋት መንደር የደብረታቦር አንዱ ታሪካዊ ስፍራ ነው። ይህን ቦታ ብዙ የቱሪዝም ባለሙያዎች “በኢትዮጵያ የመጀመርያው  ኢንዱስትሪ መንደር” እያሉ ይጠሩታል። በተጨማሪም በኢትዮጵያ በርዝመቱ 3ኛ ደረጃ የያዘው ጉና ተራራ እንዲሁም በ 50 ዓመታት ጉዞ የራሱን ባህል የፈጠረው የአውራ አምባ ማኅበረሰብ መገኛ ናት የደብረታቦር ከተማ። 

እነዚህንና ሌሎች የቱሪዝም መስኅቦችን አቅፋ በምትገኘው ደብረታቦር፤ የአውሮፕላን ማረፊያ ባለመኖሩ ጎብኚዎች ወደ አካባቢው ሂደው ለመጎብኘት እንደሚቸገሩ የሚናገሩት አቶ ገደፋው ወርቁ የደቡብ ጎንደር ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ ናቸው። 

ከዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው በ 2011 ዓ.ም 4ሺህ 361 የውጭ ሃገር ዜጎችን ጨምሮ 9ሺህ 884 ቱሪስቶች ከተማዋን ጎብኝተዋል። በተመሳሳይ በ 2012 ዓ.ም ደግሞ 13ሺ 3594 ቱሪስቶች የመጡ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ 4ሺህ 848 የውጭ ሃገር ጎብኘዎች ነበሩ። 

አቶ ባሻ እንግዳው የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ከንቲባ ናቸው። አቶ ባሻ  ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት “አውሮፕላን ማረፊያው ከ 1929 ዓ.ም ጀምሮ ከደብረታቦር አዲስ አበባ የመደበኛ በረራ እየሰጠ ቆይቷል። በ 1968 ዓ.ም በደርግ ዘመን በነበረው ጦርነት ተቋርጦ፤ እንደገና ከ 1984 እስከ 1985 ዓ.ም አንድ አመት ያክል መደበኛ ስራውን ቀጥሎ ነበር። ይሁንና ከ 1986 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠ አይደለም” ብለውናል።

በቀድሞ አጠራሯ 'ጁራ' በሚል ስያሜ የምትታወቀው ደብረታቦር፤ በአፄ ሰይፈ አርእድ ዘመነ መንድስት በ 1327 ዓ.ም ነበር የተቆረቆረችው። በአሁኑ ወቅት ደብረታቦር የደቡብ ጎንደር ዞን አስተዳደር መዲና ሆና እያገለገለች ትገኛለች።

በ 1925 ዓ.ም የተገነባው የደብረታቦር የአውሮፕላን ማረፊያ በአማራ ክልል ካሉ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያዎች ቀዳሚ እንደሆነ ይነገርለታል። የአውሮፕላን ማረፊያው ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የመደበኛ በረራ ታሪፍ የወጣለት በ 1929 ዓ.ም እንደነበር ተመዝግቦ ይገኛል።

የደብረታቦር ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ አበበ እምቢያለ “የከተማ አስተዳደሩ ይህን የህዝብ ጥያቄ ለአማራ ክልል ምክር ቤት አቅርቦ ተቀባይነት አግኝቶ፤ ክልሉም ለኢትዮጵያ ሲቪል አቬሽን ባለስልጣን ያቀረበውን ጥያቄ አቬሽኑ ተቀብሎ ቦታው ለአገልግሎት ብቁ መሆኑን በባለሙያ ካረጋገጠ በኋላ ግንባታው ተፈቅዷል” ሲሉ ተናግረዋል። 

ቦታው ለሌላ አገልግሎት ሳይተላለፍ ተጠብቆ መቆየቱ እንደገና ለመፈቀዱ ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳለው የሚገልጹት የደብረታቦር ምክትል ከንቲባ አቶ ባሻ እንግዳው በበኩላቸው “ለአውሮፕላን ማኮብኮቢያ የሚያስፈልገውን የተመረጠ ጋረጋንቲ፣ ማሽን እና የነዳጅ ወጭን በመሸፈን በተገባው ቃል መሰረት የድርሻችንን ስራ አጠናቀናል። ቀሪውን 80 በመቶ የሚሆነውን ስራ የፌደራል መንግስት እንዲሰራልን ኮሚቴ አዋቅረን እየጠየቅን ነው” በማለት ነግረውናል።

እንደ አቶ ባሻ ገለጻ ከሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ “20 በመቶ የሚሆነውን ሰርታችሁ ጠይቁ” ባለው መሰረት 4.5 ኪሎሜትር ርዝመትና 30 ሜትር ስፋት ያለው የአውሮፕላን ማረፊያና ማኮብኮቢያ ሰርተው ሪፖርት ማድረጋቸውን ያስረዳሉ።

የቀድሞው የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ተመስገን ጥሩነህ በ 2012 ዓ.ም 'አውሮፕላን ማረፊያውን ስራ ለማስጀመር' በሚል ወደ ደብረታቦር አምርተው ነበር። በወቅቱም 20 በመቶ የሚሆነውን ግንባታ በከተማ አስተዳደሩ በኩል እንዲሰራ ተወሰነ። 80 በመቶ የሚሆነውን በፌደራል መንግስት በኩል ሊያሰሩ ቃል ገብተው ነበር። ይህን ተከትሎ በአፋጣኝ አገልግሎት እንደሚጀምር ተስፋ የሰነቁት የከተማዋ ነዋሪዎች እና የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር የታቀደላቸውን 20 በመቶ ስራ አጠናቀው መጪውን እየተጠባበቁ ነው።

የከተማዋ ነዋሪዎች “ስራው ሊጀምር ነው” የሚል ዜና ሲሰሙ ትልቅ ደስታ ተሰምቷቸው እንደነበር፤ ነገር ግን ድጋሚ ስራ ማቆሙ እንዳሳዘናቸው ገልጸውልናል። ኢንቨስተሮች ወደ ከተማዋ እንዳይመጡ፣ የቱሪዝም ዘርፉ እንዳይስፋፋ፣ ኢንዱስትሪዎች እንዳይገነቡና ከተማዋ እንዳትለማ አድርጓል ይላሉ። 

አቶ ሸጋው (ስማቸው የተቀየረ) በደብረታቦር ከተማ ከ 54 አመት በላይ የኖሩ ናቸው። ጉዳዩን ከትግራይ ክልል አውሮፕላን ማረፊያዎች ጋር እያነጻጸሩ ሲናገሩ “በአክሱም እና በሽሬ ከተሞች መካከል ያለው ረቀት 60 ኪ.ሜ ቢሆንም በሁለቱም ከተሞች ላይ አውሮፕላን ማረፊያ ተገንብቶ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። ደብረታቦር ያለው አውሮፕላን ማረፊያ ግን አገልግሎት እንዲጀምር ህዝቡ ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርብም ሰሚ አቷል” ይላሉ አቶ ሸጋው።

አዲስ ዘይቤ ያናገረችው ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ናትናኤል እባቡ፤ ከደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በመካኒካል ኢንጅነሪንግ ተመርቆ ስራ በማፈላለግ ላይ ይገኛል። ደብረታቦር ከተማ በ 14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ተመስርታ ዕድገቷ ግን ከዕድሜዋ በእጅጉ ወደኋላ የቀረች መሆኗ እንዳስቆጨው የሚናገረው አቶ ናትናኤል “የቱሪስት መዳረሻ የነበረች ቦታ ተቀብራ ቀረች” ይላል በምሬት። አውሮፕላን ማረፊያው እንደገና ስራ መጀመር ለሌሎችም ፕሮጀክቶች መምጣት በር እንደሚከፍትና የስራ እድልም ይፈጥር እንደነበር ይገልጻል። “ጉዳዩ ትኩረት ቢያገኝ ተመርቀው እቤታቸው ለተቀመጡ ስራ ፈላጊዎች ብዙ እድል ይፈጥር ነበር” ብሏል።

ፎቶ፡ ጌታሁን አስናቀ (ከአዲስ ዘይቤ)

በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና በሰሜን ኢትዮጵያ በተከሰተው ጦርነት ምክንያት የደብረታቦር የቱሪዝም ዘርፉ ቢዳከምም፤ ከ 2011 እስከ 2014 ዓ.ም ድረስ ባሉት የአራት አመታት ጊዜ ውስጥ 10,655 የውጭ ሀገር ዜጎች እና ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች እንደጎበኟት ከደብረታቦር ከተማ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ጥቂት ስለ ጋፋት

በጎንደር እና በአካባቢዊ የሚገኙ ቅርሶችን በማስጎብኘት ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ ማንደፍሮ ተሻለ “ጋፋት በኢትዮጵያ የመጀመርያው ኢንዱስትሪ መንደር ሊባል ይችላል” ይላሉ። እንደ አስጎብኚው አባባል ነገሩ ጥናት የሚጠይቅ ቢሆንም በኢትዮጵያ በሎም በአፍሪካ የመጀመርያው ኢንዱስሪ መንደር ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል። 

ንጉሡ አጼ ቴዎድሮስ የውጭ ሀገር ሰዎችን አስረው ለወደፊቱ የኢትዮጵያ ሥልጣኔ እና እድገት ያግዛል ያሉትን የተለያዩ የቴክኖሎጂ ስራዎችን ጋፋት ላይ አሰርተዋል። ከሴፓስቶፖል መድፍ በተጨማሪ ሌሎች መድፎች እና መድፉ የተጓጓዘበት ጋሪ የተሰሩት በእዚሁ በጋፋት መንደር ነበር።

ፎቶ፡ ጌታሁን አስናቀ (ከአዲስ ዘይቤ)

ጥቂት ስለ ጉና ተራራ

በከፍታው ከአፍሪካ 9ኛ፤ ከኢትዮጵያ ደግሞ 3ኛ ደረጃን የያዘው የጉና ተራራ በደብረታቦር ከተማ አቅራቢያ የሚገኝ እና 41 ወንዞች እንዲሁም 77 ምንጮች የሚገኙበት ውብ ስፍራ እንደሆነ ከዞኑ የቱሪዝም መምሪያ የተገኘው መረጃ ያስረዳል። ጉና ተራራ ከባህር ጠለል በላይ 4ሺህ 231 ሜትር ከፍታ ያለው ሲሆን በአጠቃላይ 9ሺህ 192 ሄክታር መሬት ይሸፍናል። 

ጉና ተራራ የበርካታ የዱር እንስሳትም መገኛ ነው። ከእነዚህም መካከል በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኘውን ቀይ ቀበሮን ጨምሮ ሚዳቋና ቀበሮ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው። በተጨማሪም በርካታ የተፈጥሮ ሃብቶች፣ አዋፋት እና ዓይነተ ብዙ እጽዋት መገኛም ነው።

ጥቂት ስለ አውራ አምባ ማህበረሰብ

አውራ አምባ በአማራ ክልል በደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ ወረዳ ከወረታ ከተማ ወደ ደብረታቦር በሚወስደው ጎዳና በ 8 ኪ.ሜ ርቀት ላይ፤ በ18 ሄክታር በማይበልጥ መሬት ላይ ያረፈ የመኖርያ መንደር ነው። ከ 50 ዓመታት በላይ ባስቆጠረ ሂደት የራሱን ባህል የፈጠረው የአውራ አምባ ማኅበረሰብ መገኛ ከተማ ነች ደብረታቦር።

የአውራ አምባ ማኅበረሰቡ የተመሰረተው በ1964 ዓ.ም አቶ ዙምራ ኑሩ በተባሉ ግለሰብ ነው። አውራምባዎች ከሌላው የኢትዮጵያም ሆነ የአማር ህዝብ በተለየ የአኗኗር ዘይቤአቸው ይታወቃሉ። ከአማር ክልል ነዋሪዎች ለየት ባለ መልኩ የፆታ እኩልነትን በተግባር ያሳየ፣ ስራን የማኅበረሰቡ እምነት ያደረገ፣ እንደ ማኅበረሰብ የሚተዳደሩበት የራሳቸው የሆነ መተዳደሪያ መርሆዎችን በማስቀመጥ የሚኖር ማኅበረሰብ መሆኑ ይነገራል።

መስራቹ አቶ ዙምራ ኑሩ (የክቡር ዶክተር) የአውራ አምባ ማኅበረሰብን በመመስረት እና በመምራት የላበረከቱት አስተዋጽኦ የጅማ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ድግሪ ተሰጥቷቸዋል።

ፎቶ፡ ጌታሁን አስናቀ (ከአዲስ ዘይቤ)

በመጨረሻም የደቡብ ጎንደር ዞን ባህልና ቱሪዝም ባለሙያ አቶ ገደፋው ወርቁ እንደሚሉት “ደብረታቦር ከተማ ዋና የቱሪስት ፍሰት መስመር ነች” ይላሉ። ቱሪስቶች ወደ ጨጨሆ መድሃኒያለም እና ወደ ግሼን ደብረከርቤ ለመጓዝ፤ እንዲሁም 'ደብረታቦርን በደብረታቦር' የሚባልለትን የቡሄ ባህል በድምቀት የሚከበርለትን ደብረታቦር እየሱስ ለመታደም እና ሌሎች በዞኑ ያሉ ቦታዎችን ለመጎብኘት ሲፈልጉ ደብረታቦር ዋነኛ የቱሪስት መዳረሻቸው እንደሆነች ያስረዳሉ።  

በመጋቢት ወር  2014 ዓ.ም ላይ የብልጽግና ፓርቲ ስብሰባ ላይ የአውሮፕላን ማረፊያውን በተመለከተ ጥያቂያው ቀርቦ ነበር። የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት በሰኔ ወር 2014 ዓ.ም ምላሽ እንደሚሰጣቸው ቃል የገባ ቢሆንም የአማራ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት 6ኛ ዙር ስብሰባውን ሰኔ 26 ቀን 2014 ዓ.ም ሲያካሂድ የደብረታቦርን ከተማ ወደ ሪጅዮ-ፖሊታንት እንድታድግ ሲወስን ስለ አውሮፕላን ማረፊያው ጉዳይ ምንም የተነሳ ነገር እንደሌለ ሰምተናል።

አስተያየት