ሰኔ 3 ፣ 2013

በሽሬ ከተማ ያሉ ተፈናቃዮች ፈተና

ትግራይወቅታዊ ጉዳዮች

በሽሬ ከተማ በአንድ የመጠለያ ጣቢያ ዉስጥ በእርዳታ አስተባባሪነት የሚሰሩ ግለሰብን አዲስ ዘይቤ አነጋግራለች፡፡

በሽሬ ከተማ ያሉ ተፈናቃዮች ፈተና

'የሕግ ማስከበር ዘመቻ'ዉን ተከትሎ በሽሬ ከተማ የመጠለያ ጣቢያዎች የተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ በስፍራዉ ተጠልለዉ የሚገኙ ተፈናቃዮች አሳሳቢ ሁኔታ ላይ አንደሚገኙ በከተማዉ በአንድ የመጠለያ ጣቢያ ዉስጥ በእርዳታ አስተባባሪነት የሚሰሩ ስሜ አይጠቀስ ያሉ ግለሰብ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል፡፡

ከሁመራ፣ ማይፀብሪ፣ ሸራሮ፣ አድአሮ፣ አድመብርኢት እና ሌሎች ትናንሽ ከተሞች በየጊዜዉ ወደ ከተማዋ የሚገቡ ተፈናቃዮቹ  ቁጥር በየጊዜዉ እየጨመረ መሄዱንና ምዝገባ የሚካሄደዉ በተለየዩ የምግባረ ሠናይ ድርጅቶች በተናጠል በመሆኑ የተፈናቃዮችን ትክክለኛ ቁጥር ለማወቅ አስቸጋሪ መሆኑን የሚገልጹት አስተባባሪዋ በአሁኑ ሰዓት በሽሬ የመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች ቁጥር ከ5 መቶ ሺ በላይ ሊሆን አንደሚችል ይናገራሉ፡፡   

"በከተማዉ የሚንቀሳቀሱ ቁጥራቸዉ ከ12 በላይ የሚደርሱ የእርዳታ ድርጅቶች ቢኖሩም ተፈናቃዮቹ በቂ እርዳታ እያገኙ አይደለም፡፡   አሁን ባለኝ መረጃ መሰረት የምግብ እና ሌሎች ቁሳቁሶች ድጋፍ እያገኙ ያሉት ተፈናቃዮች ቁጥር ከ100ሺ አይበልጥም ሲሉ አስተባባሪዋ ይናገራሉ፡፡ በተጨማሪም በአሁኑ ሰዓት አንዳንድ የከተማዉ ነዋሪዎች ጭምር ከተፈናቃዮች ጋር እየተቀላቀሉ እርዳታ ስለሚወስዱ በመጠለያ ጣቢያዎቹ ዉስጥ ከፍተኛ የሆነ የምግብ እጥረት እየገጠመ እንደሚገኙም ያነሳሉ፡፡

"እርዳታ ያላገኙ ተፈናቃዮች በአውራ ጎዳናዎች ላይ እስከመለመን አንደደረሱና አንዳንዶቹን የከተማው ነዋሪ አቅሙ በፈቀደ መጠን እየረዳቸዉ ነዉ የሚገኘዉ። እርዳታ የደረሳቸውም ቢሆኑ የተሰጣቸውን ስንዴ የሚያስፈጩበት ገንዘብ እየቸገራቸዉ ይሸጡታል። ገንዘብ ለማግኘት ቡና አፍልቶ ከመሸጥ ጀምሮ የተለያዩ ስራዎችን የሚሠሩ ብዙ ናቸው" ይላሉ። 

ከምግብ እጥረት በተጨማሪ ሌላዉ የተፈናቃዮቹ ፈተና ደግሞ የመጠለያ ቦታ ያለማግኘት እንደሆነ የሚናገሩት የእርዳታ መስጫ አስተባባሪዋ በስፍራዉ የሚገኘዉ መጠለያ በቂ ባለመሆኑ ተፈናቃዮቹ እየተቸገሩ አንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ "መጀመሪያ አከባቢ ተፈናቃዮች ሲመጡ መንገድ ላይ ይተኙ ነበር፤ ከዛ መጠለያ (ድንኳን) አንዲዘዋወሩ ተደረገ፤ አሁን ላይ ደግሞ ቁጥራቸዉ እየጨመረ በመምጣቱ በየት/ቤቶች ዉስጥ አንዲጠለሉ ተደርጓል ነገር ግን ሊበቃቸው አልቻለም። ብዙዎች በድንኳን ይገኛሉ ቀጣይ ክረምት ሲመጣ እንዴት እንደሚሆኑ እንዲሁም ከመጡበት ቦታ ተዘርፈው እና ቤታቸው ተቃጥሎ የመጡት ሰዎች ቀጣይ እጣፈንታቸው ያሳስበኛል" ብለዋል።

የብሄራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ በሽሬ ከተማ ተፈናቃዮች ስላሉበት ሁኔታና እየተደረገ ስላለዉ ድጋፍ ተጠይቀዉ በሽሬ ከተማ በርካታ ተፈናቃዮች ቢኖሩም ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ አስፈላጊዉን ድጋፍ እየሰጠን ነዉ ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል፡፡  

እሳቸው እንደሚሉት በትግራይ ክልል ከግጭቱ በፊት 1ሚሊዮን ህዝብ በቋሚነት የሚረዳ610ሺ ተፈናቃይ የነበረ ሲሆን ህግ ከማስከበሩ በኃላ 7መቶ 46ሺ 5መቶ 82 ተፈናቃዮች ተጨምረው 2.5ሚሊዮን ህዝብ ይረዳል።

 "በትግራይ ክልል ካለው ተረጂ ቁጥር የበለጠ ለ4.2 ሚሊዮን ህዝብ ነው እርዳታ እየሠጠን ነው ይህም ትግራይ ካላት የህዝብ ቁጥር ጋር ሲነፃፀር ከግማሽ በላይ ነው። ሽረ ከተማ በእዚህ ቁጥር ውስጥ የሚካተት ይሆናል" የሚሉት ዳይሬክተሩ "ተረድቶ አልተረዳሁም የሚል ሠው ካልሆነ በስተቀር ሙሉ በሙሉ  አስፈላጊ የሆነውን ምግብ እና መጠለያ እያቀረብን እንገኛለን ለተፈናቃዮቹ መድረሡንም እንከታተላለን" ይላሉ። ተፈናቃዮቹ ለቀጣይ ሊደርግላቸው የሚገቡ ጉዳዮችን በተመለከተ መንግስት እየሰራበት መሆኑንም አክለዋል።

አስተያየት