ታህሣሥ 19 ፣ 2011

ኢትዮጵያና የ’ብሔርተኝነት’ ተስቦ

መጽሓፍት

አብራክ በእያንዳንዳችን ቤት ገብቶ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ስር ሰዶ የምናየውን ማኀበረሰባዊ አለመተማመንና በጥርጣሬ መተያየት በእያንዳንዱ ግለሰብ…

ኢትዮጵያና የ’ብሔርተኝነት’ ተስቦ

አብራክ በእያንዳንዳችን ቤት ገብቶ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ስር ሰዶ የምናየውን ማኀበረሰባዊ አለመተማመንና በጥርጣሬ መተያየት በእያንዳንዱ ግለሰብ መድሏዊ አስተሳሰብ ( ስነ - ልቦና ) ላይ የተመሰረተ መሆኑን ያሳየናል። ይሄንን ክፍተት በማጋለጥ መፅሀፉ በብሔር ክፍፍል የተፋጠጠውን ኀብረተሰብ መፍትሔ ጠቋሚ ወደሆነ ግልፅ ውይይት ይመራዋል።

አብራክ፥ ሁላችን ጋር ያለ እውነታ

አብራክ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ  በህገ-መንግስት አስተማሪነታቸው እውቅናን በተቸሩት መምህር ፥ ሙሉጌታ አረጋዊ ፥ የተፃፈ የፖለቲካ ይዘት ያለው ልብ-ወለድ ነው። የመፅሀፉ አጠቃላይ ይዘት ኢትዮጵያ ተግባራዊ ባደረገችው ብሔርን መሰረት ያደረገ ፌደራሊዝም ጥቅምና ጉዳት ዙሪያ ግልፅ ኅብረተሰባዊ ውይይትን ከመጀመርና ከማበረታታት ጋር ተያይዞ መፅሀፉ ጊዜውን የጠበቀ  የሚባል ነው። ይህንን ሊያሳካ ያሰበውን ራዕይ እያንዳንዳችንን በሚመስሉ ገፀ-ባህርያት እያዋዛና የተወሳሰበና የምሁራን ይመስለን የነበረን ጉዳይ ዐለት ተዕለት በምንወስዳቸው እንቅስቃሴዎች በማሳየት ቁም ነገሩን ያስጨብጠናል። ዋና ባለታሪኮቹ አርካኒ ጫላና ዋልታ ሀጎስ የተባሉ ሁለት ፍቅረኛሞች ናቸው። እነዚህ ሁለት ሰዎች ፥ እሷ ከኦሮሞ ፥ እሱ ከትግሬ ቤተሰቦች ፥ መምጣታቸው ሳይገድባቸው በፍቅር ይወድቃሉ። ሁለቱ የህግ ምሁሮች ከጀመሩት ፍቅር ጋር ተያይዞ በሚገጥማቸው የተለያዩ ችግሮች እንዲሁም በአካባቢያቸው ባሉ ሰዎች የህይወት እንቅስቃሴ ውስጥ አብራክ እኛ ኢትዮጵያውያን በጋራ የገባንበትን የሞራል አዘቅት ጥልቀት ያስገነዝበናል። ከዚህ አዘቅት ለመውጣት አብራክ መፍትሄው እያንዳንዱ ሰው የራሱን መድሏዊ አስተሳሰብ ለመቅረፍ ከራሱ ጋር የሚያደርገው ውጊያና ትግል መሆኑን ያመለክተናል።

አርካኒና ዋልታ የተዋወቁት በአ.አ.ዩ. የህግ ት/ቤት ነው። እነዚህ ፍቅረኛሞች ከተገናኙባት ደቂቃ ጀምሮ አለምን የሚያዩበት መነጽር ከመመሳሰሉ የተነሳ በምናብ አንድ ለመሆን ጊዜ አልፈጀባቸውም። ሁለቱም ጠንካራ ሰብዕና ያላቸው ሲሆኑ እውነታቸውን በገሐድ የመንገር ፣ በፍትህን መጓደል ከሚሰቃይ ማንም ሰው ጋር አብሮ የመጨነቅ ልምድ አላቸው። ነገር ግን ይሄ የማንነታቸው መመሳሰል ካለማንም ጣልቃ ገብነት የሚቀጣጠል ፍቅራቸውን ለማጣጣም በቂ ሆኖ አልተገኘም። ግንኙነታቸው ስር እየሰደደ በመጣ ጊዜ የፍቅራቸው ጉዳይ የቤተሰብ የፖለቲካ ፓርቲና የብሄር ክፍፍል ውጥንቅጥ ማማሰያ ሆነ።

የአርካኒ ቤተሰቦች ልጃቸው በራሷ የምትተማመንና ምክንያታዊ እንድትሆን አድርገው ነው ያሳደጉዋት። በቤተሰቡ ውስጥ ከአጎቶቿ አንዱ በህወሓት(ህዝበዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ) በበላይነት በሚተዳድረው ኢህአዴግ የግዛት ጊዜ ባልተገባ ሁኔታ በልጅነቱ ተገድሏል። በዚህም የተወሰኑት የቤተሰቡ አካላት ለህወሓትና ለትግራይ ህዝብ ኃላፊነት በመስጠት ቂም ቋጥረዋል። በተለይ የሟቹ ታላቅ ወንድም የሆነው ታዬ የተባለ አጎቷ እራሱን ከ27 ዓመት በላይ በኢህአዲግ  አገዛዝ አሳሩን ያየው የኦሮሞ ህዝብ መብት ተሟጋች አድርጎ ከመሰየሙም በላይ በማያወላውል መልኩ  “ሁሉም ትግሬ የህውሀት ደጋፊ ነው ፣ በመሆኑም ህውሀት ለሰራው እያንዳንዱ ስራ ከድርጅቱ እኩል ተጠያቂ ነው” የሚል አቋሙን እዚም እዛም ያሳያል። “ወገኖቼ” እያለ ለሚጠራው የኦሮሞ ህዝብ ላይ ለደረሰው ግፍ ትግሬዎችን በሙሉ በደፈናው ይረግማል።

በዋልታ ቤተሰብ ውስጥ የታዬ አይነት ቦታ የሚይዘው ክብረት የሚባለው የህወሓት ታማኝ አገልጋይ የሆነ ታላቅ ወንድሙ ነው።  አባታቸው ደርግን በመጣል ትግል ጊዜ በሞት የተለያቸው ክብረት ፣ ዋልታና መብራት እናታቸው ወ/ሮ ፅጌ ናቸው እንደ እናትም እንደ አባትም ሆነው ያሳደጉዋቸው። ወ/ሮ ፅጌ ራሳቸው በሞት ካጡዋቸው ባለቤታቸው ጋር ታጋይ የነበሩ ፣ ጠንካራ የፍትህ ስሜት ያላቸው ቆፍጣና ሴት ሲሆኑ ልጆቻቸውንም በዚህ በራሳቸው መርህ ለማሳደግ ጥረዋል። ዋልታ የመርህ ሰው ሲሆን የማይነቀነቅ ሰብዕና አለው ፤ በዚህ ከእናቱ ጋር ይመሳሰላል።  ከዚህ በተቃራኒው ክብረት “የእናት ሆድ ዥንጉርጉር ነው እንደሚሉት” የህወሓት አምላኪና አሜን ባይ ሆኖ ነገሮችን የማያመዛዝን የፓርቲና  የፖለቲካ ተልዕኮ ማስፈፀሚያ መሣሪያ ነው። ህወሓት የትግራይ፣ እንዲሁም የኢትያጵያ ነጻ አውጪ ነው የሚል ፅኑ እምነት አለው። በዚህም እምነቱ ምክንያት የኦሮሞን ህዝብ ባጠቃላይ ውለታ ቢስ ፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር(ኦነግ) ደቀመዝሙርና ያጎረሰውን እጅ ነካሽ አድርጎ ያያል።

ታዬና ክብረት ሁለቱም ባሉበት የየራሳቸው ጠባብ ዓለም ውስጥ ሆነው አርካኒን እና ዋልታን ለማለያየት እንቅልፍ ያጣሉ። ታዬ የወንድሙ ልጅ በራሷና በቤተሰቡ ላይ ችግር እየጋበዘች ነው ፣ “ወገኖቿንም” እየከዳች ነው ብሎ ይበሳጫል። ክብረት በበኩሉ ወንድሙ ዋልታ ከአርካኒ ጋር የጀመረው ጓደኝነት የትግራይ ህዝብና ህውሓት እሱንና አጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብን ነፃ ለማውጣት የከፈሉትን መሰዋዕትነት አፈር ማልበስ ነው ይላል። በዚህም ታዬና ክብረት ያላቸውን ኃይልና አቅም ተጠቅመው የፍቅረኛሞቹን ጓደኝነት ለማቋረጥ ይሮጣሉ። በተለይም ክብረት በፓርቲው እንዲሁም በመንግስት ውስጥ ባለው ስልጣን በመጠቀም ፍቅረኛሞቹ የተለያዩ ችግሮች እንዲጋረድባቸው ያደርጋል ፤ ከዩንቨርስቲ አስተዳደር የቃል ማስጠንቀቂያ ከመቀበል ጀምሮ ከስራ እስከ መባረር ፣ መታሰርና ሰርተው እንዳያድሩ ፈቃድ መከልከልንና ሌሎችም ችግሮች ይገጥሟቸዋል። አብራክ በልብ አንጠልጣይ አወራረዱ እስከ ታሪኩ ፍፃሜ ይዞዎት ይዘልቃል።

እራስን መታዘብ?

ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ታሪካዊ በሚባል የሽግግር ጊዜ ላይ ትገኛለች ፤ ፖለቲከኞቻችንና የተለያዩ ምሁራን በብሔር ተኮር ፌደራሊዝም ጥቅምና ጉዳት ላይ የተጋጋለ ክርክር እያደረጉም ነው። አብራክ ከዚህ አንፃር በትክክለኛው ጊዜ ተገኝቶ ኑሯችንን በሚያንፃባርቅ ታሪክ ውስጥ እያንዳንዳችን እራሳችንን እንድንመለከት ያደርገናል። የመፅሐፉ ገፀ-ባህርያት በሚያደርጉት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴና ምሁራዊ ውይይት የተወሳሰቡና መሰረታዊ ጥያቄዎች ይዳሰሳሉ። “ብሔርተኝነት ምንድን ነው” ፤ “ኦሮሞ ፣ ትግሬ ፣ አማራ ፣ ሲዳማ ወይም ጋምቤላ መሆን ምን ማለት ነው”፤ እነዚህን  የመሳሰሉት ጥያቄዎች በአርካኒ ፣ በዋልታና በጓደኞቻቸው የማያልቅ ክርክር ውስጥ ይፈተሻሉ።  

አርካኒ ያደገችበት ቤተሰብ በነፃ ውይይት በሚያምን፣ ለጥያቄ የማይቀር ሀሳብ በሌለበትና በተማረ ቤተሰብ ነበር። አንድ ቀን ፍቅሬ የምትለውን ዋልታን ይዛ ቤቴና ቤተሰቤ ወደምትለው ነገር ስትሄድ የገጠማት ልብ የሚሰብር አቀባበል ነበር። ዋልታ ትግሬ በመሆኑ ብቻ የጥላቻ አቀባበል ሲገጥመው ስታይ የምታውቃቸውና ያሳደጓት ቤተሰቦቿ የማታውቃቸው ሰዎች ሆኑባት። በተማሪዎቹ የተከበረ ምሁር ፣ ለሷ ልዩ ፍቅርና አክብሮት ያለው ዋልታ እሱ ባላጠፋውና በራሳቸው የኖረ መድሏዊ አስተሳሰብ ተጠቂ ሲሆን ማየት ማሰብ ከምትችለው በላይ አሳመማት። የዋልታ ወንድም ክብረት በበኩሉ ለአርካኒ ያለውን ንቀትና ጥላቻ ፍቅረኛሞቹ ባንድ ላይ ባገኙት ጊዜ በግልፅ አሳይቷታል።

ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ኢትዮጵያውያን በተለየም ፤ በዚህ ስርዓተ መንግሥት ያደገው፣ የተማረው ትውልድ አባላት ፤ በብሔር ማንነት እንዲያስቡ፣ ሰዎች ውስጥ ሰውነታቸውን ሳይሆን ብሔር እንዲመለከቱ፣ እንዲሁም እራሳቸውን ጨምሮ እያንዳንዱን ሰው የብሔር ሳጥን ውስጥ ዘግተው እንዲቀመጡ ሆነዋል። አብራክን ስናነብ ጭንቅላታችን ውስጥ ደጋግመው የሚያቃጭሉ ጥያቄዎች አሉ ፤ በእያንዳንዳችን ቤተሰብ ውስጥ ታዬ-ዎችና ክብረት-ዎች የሉም ወይ ፧ ስናድግ ዘመዶቻችንና ጎረቤቶቻችን ተበደልኩ ብሎ የሚያለቅስ ኦሮሞ ሁሉ የኦነግ ደጋፊ ፤ ትግሬ የሆነ ሁሉ የህውሓት አቀንቃኝ ወይም የሚጮህ አማራ ሁሉ አሐዳዊ ስርዓት ናፋቂ ነው አላሉንምን ፤ ጓደኞቻችንን ለቤተሰብ ስናስተዋውቅ ብሔሩ/ሯ ምንድን ነው አልተባልንምን?

ከዚህም ባሻገር አብራክ “እኛና እነሱ” በሚባለው የፖለቲካ ነጋዴዎች ጨዋታ ውስጥ የዛኛውን ወገን ገመና ያሳየናል። ታዬን የመሳሰሉ ገፀ-ባህርያት ትግሬንና ህወሓትን በአንድ ላይ የመደመርና የመጨፍለቅ የተሣሣተ አስተሳሰብን ያጋልጣሉ። አብራክ በትግሬዎችና በህወሀት መካከል ያለውን የተወሳሰበ ግንኙነት በማሳየት ያልተለመዱና የተዘነጉ ጥያቄዎችን ያጭራል። “ኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች በማያባራ አመፅና ሰላማዊ ሰልፍ ስትናጥ ለምንድን ነው ምንም ጩኸት ከትግራይ ሲመጣ የማንሰማው” ፤ “ትግራይ ውስጥ ብዙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሌሉት ለምንድን ነው” ፤ “ለምንድን ነው አንዳንድ የትግራይ ተወላጆች ህወሓትን ያለምንም ጥያቄ የሚከላከሉለት”፤ እነዚህና ተመሳሳይ ጥያቄዎች ለጠየቀ ሰው አብራክ ጥሩ መነጽር ያስታጥቃል።

መጪው ጊዜ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ ከአዲሱ አስተዳደር ጋር ሁሉም ሰላም የሆነ ይመስላል። ነገር ግን ከኛ ጋር ለብዙ ዘመናት የቆዩ ችግሮቻችን በአንድ ቀን አይቀረፉም ፤ በተለይም ደግሞ አገር በብሔርተኝነት ሱስ በጦዘበት ጊዜ። በዚህ ወሳኝ ሰዓት አብራክ ብሔርተኝነትን የሚመለከቱ ጥያቄዎችን በጥሞና አጢነን እራሳችንን እንድንመረምር ያግዘናል። ብሔርተኝነት የሌሎች ችግር እንደሆነ አድርገን ጣት ከመጠቆም ባለፈ እያንዳንዳችን በራሳችን መድሏዊ አስተሳሰብ ከታወርንበት እንድንነቃም ይረዳናል። ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን እየመጣ ያለውን ለውጥ ለማገዝና ወደፊት ለመጓዝ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ከብሔርተኝነት ስካር መንቃት ያስፈልገዋል። ይሔን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ አብራክን የመሳሰሉ የስነ-ጥበብ ውጤቶች የሚፈጥሩልንን ዕድል ተጠቅመን ልባዊ የሆነ ውይይትና ክርክር ማድረግ ስንችል ብቻ ነው ፤ ችግራችን ማወቅ ወደመፍትሄ ለመሄድ ብቸኛው ጓዳና ነውና። የአገራችን ተስፋ ለሚመጣው ትውልድ የምናስተምረው ቅንነት ፣ እንዲሁም ከእናትና ከአባቶቻችን የምንወርሰው ደግነትና አንድነት ነው። አብራክ እያንዳንዳችንን እንደ ግለሰብ ያከግቸነውን መድሏዊ አስተሳሰብ አጋልጦ ፣ በዘመናችን ልናየው ወደምንናፈቅነው ተስፋ እና አንድነት ያመራናል። አብራክ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሊያነበው የሚገባ አስተማሪ መፅሐፍ ነው።

አስተያየት