ታህሣሥ 30 ፣ 2011

ዓለም ዓቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት ቅርንጫፉን በኢትዮጵያ ሊከፍት ነው

ወቅታዊ ጉዳዮችዜናዎች

በአርቲስት ታማኝ በየነ የሚመራው ዓለም ዓቀፍ ትብብር ለኢትጵያውያን መብት (Global Alliance for the Right of Ethiopian) በኢትዮጵያ…

ዓለም ዓቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት ቅርንጫፉን በኢትዮጵያ ሊከፍት ነው
በአርቲስት ታማኝ በየነ የሚመራው ዓለም ዓቀፍ ትብብር ለኢትጵያውያን መብት (Global Alliance for the Right of Ethiopian) በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ ለማገዝና በሀገር ውስጥ ቅርንጫፍ ከፍቶ ለመንቀሳቀስ ማቀዱን ገለጸ፡፡ተቋሙ እስካሁን ከሚያደርጋቸው የገንዘብና የቁሳቁስ እርዳታዎች በተጨማሪ ከሀገር ውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ያላቸውን እውቀትና ክህሎት ለሀገር በማዋል በጎ ፍቃድ አገልግሎትንም እንዲሰጡ ያለመ እንደሆነ የድርጅቱ ተወካይ አቶ በትሩ ገ/ እግዚአብሄር ዛሬ በካፒታል ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል፡፡ይሕንንም እውን ለማድረግ ከሁለት ሳምንት በፊት የልኡካን ቡድን ወደ ሀገር ውስጥ ተልኳል፡፡ በህዝቡና በውጪ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ የሚያገናኝ ድልድይ በመፍጠር እንደ አንድ አማራጭ ሆኖ ለመስራት መታሰቡንም ተወካዩ ገልፀዋል ፡፡የህብረተሰቡን አቅም ለመጨመር የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ የውይይት መድረኮችን በመፍጠር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ሌላኛው የትብብሩ ተወካይ ፕሮፌሰር አቻምለህ ደበላ ናቸው፡፡ግሎባል አሊያን በኢትዮጵያውያን የሚደርሱትን ማንኛውንም የሰብአዊ መብት ጥሰቶችንና መሰል ችግሮችን በመቃወም ለአሜሪካ ኮንግረስ እንዲሁም ለተባበሩት መንግስታት ደብዳቤ በመፃፍ ተጽእኖ በመፍጠር ላይ እንደሚገኝም ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል፡፡በኢትዮጵያ የሚከፈተው ቅርንጫፍ ራሱን ችሎ ሀገር አቀፍ ስራዎችን የሚሰራ አሊያም የአለም አቀፉ ትብብር ቅርንጫፍ ለማድረግ በጥናት ላይ መሆናቸውንም በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት ተገልጿል፡፡በ2013 (እ.አ.አ) በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሳውዲ አረቢያ እንዲወጡ የሚያደርግ እንቅስቃሴ በተጀመረበት ወቅት ነው ድርጅቱ የተመሰረተው፡፡ በየትኛውም ዓለም ያሉ ኢትዮጵያውያን ላይ ለሚደርሱ የሰብዐዊ መብቶች ጥቃቶችን ለመከላከል እና ለሚደርሱ ማንኛውም አደጋዎችና የሰብአዊ ጥሰቶች እርዳታ ማድረግ ዓለማ አድርጎ የተነሳ ድርጅት ነው፡፡ 

አስተያየት