ጥር 15 ፣ 2011

ስለ ከተማዬ ያገባኛል! ዝም አልልም! እናንተስ - የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም

ወቅታዊ ጉዳዮችኹነቶች

ስምንተኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ከየካቲት 9 እስከ 14 2011 ዓ.ም በጅግጅጋ ከተማ እንደሚካሄድ ዛሬ በከተማ ልማት እና ስነ ሕንጻ ሚኒስቴር መ/ቤት…

ስለ ከተማዬ ያገባኛል! ዝም አልልም! እናንተስ - የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም
ስምንተኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ከየካቲት 9 እስከ 14 2011 ዓ.ም በጅግጅጋ ከተማ እንደሚካሄድ ዛሬ በከተማ ልማት እና ስነ ሕንጻ ሚኒስቴር መ/ቤት በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ተገለጸ፡፡“መደመር ለኢትዮጵያ ከተሞች ብልጽግና” በሚል መርህ የሚካሄደውን ዝግጅት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፣ የሶማሌ ክልላዊ መንግስትና በጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር በትብብር አሰናድተውታል፡፡  በዚህ ፎረም ከሁለት መቶ በላይ ከተሞች እንደሚሳተፉ የሚጠበቅ ሲሆን እስካሁን ድረስ 109 ከተሞች ተመዝግበዋል፡፡ በሚደረገው አውደ ጥናት ላይ 23 ፅሑፎች በባለሙያዎች እንደሚቀርቡም ለማወቅ ተችሏል፡፡ከተሞች የእርስ በርስ የሚተዋወቁበትና የመማማር እድልን የሚፈጥሩበት እንዲሁም ያላቸውን በጎ ገጽታ ለማስተዋወቅ እንደሚረዳ የገለፁት የከተማ ልማትና ስነ ሕንጻ ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ካሳሁን ጎፌ ‘ትብብርን መሰረት ያደረገው የከተሞች ውድድር’ እንደሚካሄድም አስታውቀዋል፡፡ አያይዘውም ውድድሩ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ መሆን እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ዝግጅቱ ዘጠና አምስት በመቶ መጠናቀቁንና ቀሪው ደግሞ በሚቀጥሉት ሳምንታት እንደሚገባደድ የገለጹት የሶማሌ ክልላዊ መንግስት የከተማ ልማትና ስነ ሕንጻ ቢሮ ሀላፊ አብዱልፈታህ ሼህ ቢሂ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ “ሀገርን የሚያኮራ ዝግጅት አድርገናል፤ የጸጥታ ሁኔታው አስተማማኝ ነው፤ ህብረተሰቡም እንግዶችን ለመቀበል ከምንግዜውም በተሻለ ሁኔታ ተዘጋጅቷል” በማለት ተናግረዋል፡፡ሚኒስቴር ዴኤታው አቶ ካሳሁን በበኩላቸው በርካታ ተሳታፊዎች በሚታደሙበት በዚህ ዝግጅት የአጎራባች ሀገራት ከተሞች ናይሮቢ፣ ኪጋሊ፣ ሀርጌሳ፣ ሞቃድሾና አስመራ እንዲሳተፉ ከውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በመተባበር ኦፊሴላዊ ጥሪ እንደተደረገላቸው ገልጸዋል፡፡በሀገሪቱ የከተማ ልማት ፖሊሲ መሰረት ዐበይት የኢትዮጵያ ከተሞች ችግር ድህነትና የመልካም አስተዳደር እጦት እንደሆነ የተናገሩት አቶ ካሳሁን በከተሞች የሚታየው አብዛኛው ችግር የከተማ ነዋሪው የባለቤትነት ስሜት እንደሌለው በመንግስት በኩልም ይህንን ለመፍጠር አለመቻሉን እንደ ድክመት ገልጸው አሁን በሀገሪቱ እየተካሄደ ካለው ፖለቲካዊ ሪፎርም ጋር ተያይዞ ሁሉን ባሳተፈ መልኩ የከተማ አጀንዳን ወደፊት ለማራመድ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡አዲስ ዘይቤ ፖሊሲው ከለያቸው ድህነትና የመልካም አስተዳደር እጦት በተጨማሪ ሀገሪቷ የዘር ፌዴራሊዝም መከተሏ የከተሞችን ህልውና አደጋ ላይ ጥሎታል የሚል ጥያቄ ለሚኒስቴር ዴኤታው አቅርባለች፡፡ ከተሞች በባህሪያቸው በርካታ የተለያዩ ማኀበረሰቦች የውጭ ዜጎች ሳይቀር የሚገነቧቸው እና የሚኖሩባቸው ናቸው፡፡ ለምሳሌ ሀረር ላይ በርካታ የውጪ ሀገር ዜጎች አሻራ ያረፈበት ከተማ ነው፡፡ ባለፉት ጥቂት አመታት ግን ይህንን ፎረም የምታዘጋጀው ጅግጅጋን ጨምሮ ድሬዳዋ፣ ሀረር፣ ሀዋሳ፣ ቡራዩ፣ አዲስ አበባ፣ ወልዲያ፣ ጎንደርና  በርካታ ከተሞች ይህንን መልካቸውን የሚፈታተኑ ችግሮች አጋጥሟቸዋል፡፡ ከዚህ በመነሳት እና የስምንተኛው የከተሞች ፎረም መሪ ቃል “መደመር ለኢትዮጵያ ከተሞች ብልጽግና” ከመሆኑ አንጻር በዝግጅቱ ይህንን ችግር ለመፍታት የሚያግዝ ነገር የታሰበ ነገር እንዳለ አዲስ ዘይቤ ጠይቃለች፡፡አቶ ካሳሁን “በተለያዩ አካባቢዎች የሚታየው የፀጥታ ችግር ውስጡ የዘር ፌዴራሊዝም የሚመስል ቢሆንም የነዚህ ችግሮች መንስኤ የዘር ፌዴራሊዝም አይደለም፡፡ ዋናው ጉዳይ ከጊዜ ወደ ጊዜ የመጣው አቃፊነት እየተውን አግላይነት ላይ ማተኮራችን ነው፡፡  መደመር ሲባል እነዚህን ያጣናቸውን እሴቶች የምናገኝበትና የከተማውን ነዋሪ የባለቤትነት ጸጋን እንዲጎናፀፍ ማድረግ ነው፡፡” ሲሉ ገልጸዋል፡፡በወርሃ ታህሳስ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረገው ጉባኤ ራስን በራስ ማስተዳደር፣ ከማንነት ጥያቄ እና ከሌሎች ተመሳሳይ ክስተቶች ጋር ተያይዞ የሚነሱ ግጭቶች ከፍተኛ ለሆነ አለመረጋጋት መንስዔ በመሆናቸው አስተዳደራዊ ወሰኖች በቀጣይነት የሚወሰኑበትንና የሚለወጡበትን መንገድ ለማጥናት የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ለማቋቋም መወሰኑ ይታወሳል፡፡

አስተያየት