ጥር 15 ፣ 2011

የመሶብ ህንጻ ንድፍ/ግንባታ በባለሙያዎች እይታ

ወቅታዊ ጉዳዮችፊቸር

The 46-storey CBE HQ Bldg. under construction has a project cost of 6.1 billion birr & imagine the…

የመሶብ ህንጻ ንድፍ/ግንባታ በባለሙያዎች እይታ
በዓለም ላይ የዘመኑን ቴክኖሎጂና የራስ ፈጠራን ተከትሎ በርካታ ለማመን የሚከብዱና አስደናቂ ህንጻዎችን መመልከት እየተለመደ መጥቷል። የህንጻዎችን ቅርጽ ለመወሰን የኪነ ህንጻ ባለሙያዎች የሚከተሏቸው የተለያዩ ዘዬዎች ሲኖሩ፤ አንዳንዶቹ አንድን ነገር የሚወክሉ (replica) ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ በአርክቴክቶቹ ፈጠራ የሚሰሩ (imagination) ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ህንጻዎቹ ከሚሰጡት አገልግሎት በመነሳት (form follows function) የሚሰሩም እንዳሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።እንደ ህንጻ ንድፍ ባለሙያዎች አገላለፅ አንድ ህንጻ ከመሰራቱ በፊት በዲዛይን መስክ ሊያሟላቸው የሚገቡ ቅድመ ሁኔታዎች፣ ሙያዊ ሂደቱንና መስፈርቱን ተከትሎ መስራት አለበት። ምንም እንኳ የዲዛይን ስራ ወጥ የሆነ አካሄድ ባይኖረውና የጥበብ አካል እንደመሆኑ በንድፍ አድራጊው ይሁንታ ላይ ቢወድቅም አጠቃላይ የመሆነ መግባቢያ መስፈርቶች አሉት።ከሰሞኑ የባህልና ቱሪዝም ሚንስቴር 250 ሜትር ከፍታ እና በ20 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ የሚሰፍር  የተለያዩ ደረጃቸውን የጠበቁ ባህላዊና ዘመናዊ ሆቴሎች፣ የገበያ በዕከል፣ ሁሉንም ክልሎች የሚወክል የባህል ማእከል፣ የጎልፍ ሜዳ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ እና የቱሪዝም እና ሆቴል እንዳለው የተነገረለት የመሶብ ቅርጽ ያለው ኪነ ህንጻ ለማነጽ ማለሙን የሚገልጽ ዜና ከተነገረ ጀምሮ የብዙኃኑ መነጋገሪያ ሆኗል። በተለይ የኪነ ህንጻ ባለሙያዎች የተለያየ አስተያየት ሲሰነዝሩ ተስለውሏል።የመሶብ ህንፃን ዲዛይን እንደነዱፉ የተነገረላቸው አብርሃም ታንቶ “ህንፃው የመሶብ ቅርፅ የያዘበት ምክንያትን ኢትዮጵያውያን ከቤታችን የማይጠፋው መሶብ፤ ተምሳሌትነቱ አብሮ የመሰባሰብ፣ የአንድነት፣ የደስታና የጋራ ቃልኪዳን የሚታሰርበት ድርና ማጋችን ስለሆነ ነው” በማለት ገልፀዋል።የኪነ-ሕንጻና የአዳዲስ ከተሞች ልማት ባለሙያ የሆኑት ኤርሚያስ ተሰማ እንደሚሉት “ህንጻዎች በተለያዩ መንገዶች ዲዛይን ይደረጋሉ፤ አንድም የታሰበላቸውን አገልግሎት በሚገባ እንዲሰጡ ከመፈለግ ወይም ደግሞ የማይጨበጥ ስነ-ውበታዊ ግብን ለማሳካት በማሰብ ይሰራሉ።” ለምሳሌ ህንፃው ለቢሮ አገልግሎት ከሆነ የሚያስፈልገው መሰረታዊ ነገሮችን ማሟላት አለበት። የመጠቀሚያ ስፍራዎቹ ማሰራት መቻላቸው፣ በቂና ትክክለኛ ብርሃን ማግኘቱ፣ የመንቀሳቀሻ ቦታዎቹ፣ ህንጻው መቆም መቻሉ፣ ከአረንጋዴ ልማት ጋር በተያያዘ ያሉ ነገሮች እና፣ ወጪ ከመቆጠብ ወዘተ… አኳያ እንደ ዋና የዲዛይን መወሰኛ ተደርጎ እንደሚሰራ ሁሉ በባለሙያው ይሁንታ ወይም ፈጠራ የሆነ መልእክትን ለማስተላለፍ ወይም ደግሞ ስነውበታዊ ግብን አልሞም መስራት ይችላል። በዓለም የስነ ህንፃ ታሪክ ውስጥ ሁለቱንም አይነት የሚወክሉ በርካታ ህንፃዎች ቢሰሩም በአመዛኙ በመሃል ላይ ያሉት ሁለቱንም ግብ ለማመጣጠን የሚሰሩት አብላጫውን ቁጥር ይይዛሉ።በዚህ ውስጥ የደንበኛው ፍላጎት አብዛኛውን ነገር የሚወስን ሲሆን፤ የህንጻው ባለቤቶች ግለሰቦች ከሆኑ ፍላጎታቸውን መሰረት አድርጎ ሲሰራ፣ ሙያዊ ምዘናዎችን ባያከብር እንኳን የግለሰቡ ፍላጎት ነውና የከተማ ህጉን እስካልጣሰ ድረስ ብዙ ማለት አይቻል ይሆናል። ነገር ግን የሚያስተዳድረው መንግስት ከሆነ ግን ደንበኛው ህዝብ እንደመሆኑ መጠን አገራዊ አንድምታ ስለሚኖረው ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ባለሙያዎች ይናገራሉ።እነዚህን ሙያዊ ሐሳቦች የሚሰነዝሩበት ባለሙያዎች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ከዚህ በታች ባሉት አራት ዋና ጉዳዮች ዙሪያ ያጠነጥናሉ፡፡
  1.  የአካሄድ ቅደም ተከተል
እንደዚህ አይነት ሀገር በቀል ወይም በመንግስት አስተዳዳሪነት የሚሰሩ ህንጻዎች ከመሰራታቸው አስቀድሞ ገና በንድፍ ሂደት ላይ መከናወን ከሚገባቸው ነገሮች መካከል ግልፅ ጨረታ ማካሄድ፣ የንድፍ ውድድር ማድረግ የተመረጡትን ደግሞ ህንፃው ከሚሰጠው አገልግሎት ጋር መስማማቱን መለየት ያስፈልጋል። ከዚህ በተጨማሪ ይሄን ለማሰራት ኋላፊነት የወሰደው የባህልና ቱሪዝም ሚንስቴር በዚህ ጉዳይ ላይ የሚመለከታቸውን፤ የከተማ ልማት ሚኒስቴር መ/ቤት፣ ከኪነ ሕንጻ ባለሙያዎች ማህበር ጋር መወያየት ያስፈልገዋል።የመጀመሪያው ጥያቄ እንዲህ አይነት ህንጻ ለማሰራት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ካስጠናው ጥናት ወይም በሌላ ምክንያት እቅዱ ውስጥ አካቶት የነበረ ነገር ነው?  የሚለው ነው። ከዚህ አንጻር ሚንስቴር መ/ቤቱ ከእቅድ ውጪ የሆነ አካሄድን የተከተለ ነው ማለት ይቻላል።ሌላው አንድ የህንጻ ዲዛይን፣ ያውም በሌላ አካል ተሰርቶ የቀረበን፣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለህዝብ ከገለጸ በኋላ ‘ከህጉ ጋር እንዲሄድ አድርገን እንሰራለን’ ማለት ብዙ አደጋ ያለውና ህንጻው ለህጉ ሳይሆን ህጉ ለህንጻው እንዲገዛ የሚያደርግ ትልቅ ስህተት ነው። ስለዚህ መሶብ ህንጻ ከላይ የተገለፁትን አካሄዶች የሚያሟላ አይደለም በማለት የዘርፉ ባለሙያዎች ይከራከራሉ።ቅድስት አመዴ የኪነ ሕንጻና የህንፃ ንድፍ አማካሪ ናቸው። “ዲዛይኑ ከመሰራቱ በፊትም ሆነ ከተሰራ በኃላ የባለሙያዎች ተሳትፎ እንደሚጎድለው ያስታውቃል። እንደዚህ አይነት ዲዛይን በት/ቤት ደረጃም እንዲሰራ አይፈቀድም።” በማለት የተነሳውን ሀሳብ ይደግፋሉ።
  1.  የንድፍ(Design) ችግር
ቢኒያም ሀይሉ በህንፃ ኮሌጅ መምህር ሲሆኑ በቤልጂየም ሀገር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን እየተማሩ ይገኛሉ። ቢኒያም በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ትችት የኢትዮጵያ የህንፃ ዲዛይን ባለሙያዎች ባህላዊ የእደ ጥበባትን ፣ የአልባሳትን ቅርፅ ፣ የሙዚቃ መሳሪያዎችንና የመሳሰሉትን በመውሰድና በመኮረጅ መጠቀም አግባብ አይደለም በማለት ይከራከራሉ:: ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርሶች ጋር መመሳሰል በራሱ ኢትዮጵያዊ እንደማያስብለው ይናገራሉ።“…It is also not snatching elements from Axum, Lalibela...etc and ill-fitting them to our current architectural works, for those had their own merit and we should be crafting ours.”  “(ኢትዮጵያዊ ስነህንጻ) ... ማለት ከአክሱምና ከላሊበላ ወይም ከሌሎች ቅርሶች ላይ አንዳንድ ነገሮችን ወስዶ የአሁኑ ስራችን ላይ መለጠፍ ማለት አይደለም። እነሱ የራሳቸው መስህብነት እና ጥበብ አላቸው፤ ይህም ትውልድ የራሱን ሊነድፍ ይገባዋል።”“እንደ አርክቴክት ስመለከተው” ይላሉ ኤርሚያስ ተሰማ ደግሞ “ይሄ ህንጻ የበሰለ ስራ ነው ማለት ይከብደኛል። ህንጻ ነገሮችን እንዲመስል የማድረግ ሂደት ለተለየ አላማ ካልሆነ በስተቀር የሚበረታታ የህንጻ አነዳደፍ አይደለም። በመሰረታዊነት ህንጻ መምሰል ያለበት ህንጻ እንጂ ሌላ ነገር አይደለም። መሶብ ያንን ቅርጽ የያዘበት የራሱ አላማ አለው። ህንጻ እናድርገው ካልን ብዙ ጉድ ይዞ ይመጣል። ለምሳሌ፤ በህንጻ ቅርጽ መሶብ መስራት ያስኬዳል ወይ? ወይስ በጀበና ቅርጽ ጫማ ወይ ኮፍያ ብሰራ የሚገዛኝ አለወይ? ህንጻ ላይ ሲመጣም ተመሳሳይ ነው። ቅርጹ በዋናነት መመንጨት ያለበት ከሌላ ባእድ ነገር ሳይሆን በህንጻው ማግኘት ከምንፈልገው ግብ፣ ከውስጣዊው ግልጋሎት፣ እና ከአካባቢያዊ ወይም ከዙሪያው ከተማዊ ባህሪ ሊሆን ይገባል። ዋና ጽንሰ ሃሳቡ መሶብ ቢሆን እራሱ፣ መሆን ያለበት በቀጥታ መሶቡን መገልበጥ ሳይሆን፣ ለህንጻው የሚሆኑ ሃሳቦችን ብቻ በጥንቃቄ ከሌሎች የስነ-ህንጻ መሰረታዊያን ጋር በማዋደድ ብቻ ሊሆን ይገባል ባይ ነኝ።”በኤርሚያስ ሐሳብ የሚስማሙት ቅድስት አመዴ እንደዚህ አይነት ህንጻዎችን በተለያዩ ሀገራት መመልከት በአጠቃላይ የዚህ ህንጻ ንድፍ የፈጠራ ችሎታ የሚያንሰውና በቂ ጊዜ ያልተሰጠው እንዲሁም ጥልቅ ጥረት ያልተደረገበት ነው ማለት ይቻላል። በዚህና ከላይ በተነሱት ነጥቦች ምክንያት ይገነባል የሚል እምነት የለኝም ።  ከተገነባ እንኳ ለሚሰጠው አገልግሎት በበቂ ሁኔታ መሰራት ይችላል? የሚለውን ጥያቄ መመለስ የሚችል አይደለም።” በማለት ጥርጣሪያቸውን ያጋራሉ።በባለሙያዎቹም ዘንድ ትክክለኛ ትችት መስጠት አለመለመድም ሌላኛው ችግር እንደሆነ ቢኒያም ሃይሉ ይናገራሉ። ህዝቡ ስለ ህንፃ ንድፍ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑ የኪነ ህንጻ ባለሙያው ይህን ሀላፊነት ወስዶ መስራት ሲያስረዱ “… በእኛ በባለሙያዎቹ ዘንድ ቸልተኝነት፣ በዘርፉ ያለው የቴክኖሎጂ መራቀቅና ቅሳቁሶችን ወደሀገር ማስገባት መቻላችን ፤ መደረግ የሚገባውን በመስራት ፈንታ ቀላሉን መንገድ እንድንመርጥ እድል ፈጥረዋል።” ይላሉ።በተጨማሪም የኪነ ሕንጻ ባለሙያዎች በኋላፊነትና በጥንቃቄ መስራት አለባቸው ሲያመላክቱ “የኪነ ህንጻ ባለሙያ አንድን ነገር ለማስተላለፍ በማሰብ ከሆነ ነገር ተውሶ መስራት የለበትም። ምክንያቱም አርክቴክቸር በራሱ ከፍ ያለና የተከበረ ዓላማ አለውና።’’ በተጨማሪም ራሱ ባለሙያው እንዲናገር ከማድረግ ይልቅ የሌሎች እሳቤዎች ጥገኛ እንዲሆን እንዳደረገው ጠቁመዋል። እንዲሁም ከተማዋ ከምትፈልገው ጋር አብሮ የሚሄድ ቅርጽ እንደሚስፈልጋት ይናገራሉ።
  1.  የከተማ ፕላን አክብሮና ደረጃ ጠብቆ መስራት ላይ
በመጀመሪያ ይሄ ህንጻ የት አካባቢ እንደሚሰራ ግልፅ የሆነ መረጃ አለመኖሩ በራሱ ለብዙዎቹ ባለሙያዎች ግራ መጋባትን ፈጥሮባቸዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የከተማውን ህግ ተከትሎ ይሰራል? ዋነኛው እንደ መስፈርት መቀመጥ ያለበት ጉዳይ ደግሞ ከአዲስ አበባ ፍላጎት እና የእስከ ዛሬው አከታተም ሂደት ጋር አብሮ መሄድ ይችላል?  የሚሉ ጥያቄዎችን የሚመልስ ሆኖ እንዳላገኘው የሚነገረው ደግሞ ኤርሚያስ ተሰማ ነው።ያነጋገርናቸው ባለሙያዎች እንደሚስማሙት ከሆነ ይሄ ህንጻ በትክክል የት አካባቢ እንደሚሰራ በውል አልታወቀም ፤ በተጨማሪም በአዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙት አካባቢዎች የራሳቸው የሆነ ቅርፅ አላቸው ስለዚህም ይህን ህንፃ የሚስተካከል ስፍራ ማግኘት በራሱ ከባድ መሆኑን ያስረዳሉ።
  1.  ከወጪ አኳያ
በባለሙያዎች እይታ የህንጻ ግንባታውን አስፋላጊነትን እና ቀደሚ አጀንዳነት ጥያቄ ውስጥ የሚከተው የሚፈጀው ከፍተኛ ገንዘብ ነው፡፡ ከላይ የተገለፁትን ሶስት ነገሮች በአግባቡ ያልመለሰ ህንፃ፤ ይሁን እንኳን ተብሎ ቢሰራ የሚያወጣው ወጪ ከፍተኛ ነው። እርግጠኛ በሌለው ነገር ላይ ከፍተኛ ወጪ ማውጣት ደግሞ የተገቢነት ጥያቄ የሚያነሱት ባለሙያዎች የሚሰራው ህንፃ ለቱሪስት አገልግሎት ይውላል ቢባልም፣ እንኳን አዲስ ቱሪስት ሊያመጣ የሚችልበት እድል ይጠራጠራሉ፡፡ “ይህ ሲገነባ ከተማዋ እስከዛሬ ያዳበረችውን በቱሪስትም ሊጎበኝ የሚችለውን ልዩ ገጽታ እና እሴት የሚፎካከር እና ምናልባትም የሚያመክን እንደመሆኑ፤ ሊመጣ ያለውንም እንዳያስቀር ስጋት አለኝ። ለሰማይ ጠቀስና አስደማሚ ግንባታ ብቻ የተፈጠሩ እንደ ዱባይ ያሉ ከተሞች ባሉበት ያለን ሃብት ላይ እንደመስራት፣ ይህንን ባእድ ነገር ሰርተን ቱሪስት መጠበቅ የዋህነት ነው።” ሲሉ ኤርሚያስ ያላቸውን ጥርጣሬ ያስቀምጣሉ።“ውበቱን በርካታ ሰዎች ሲያደንቁት ለማስተዋል ችያለሁ፤” በማለት የሚናገሩት ቅድስት አመዴ  “ነገር ግን በባለሙያዎች ዘንድ በርካታ ትችቶን አስተናግዷል። በበኩሌ ይሄ ህንጻ በምንም መልኩ መስፈርቱን አያሟላም እላለሁ። በተገቢው መንገድ ጥናት የተደረገበትም አይመስልም እንጂ እንደዚህ አይነት ህንጻ ገንብቶ ለቱሪስት መስህብ ይሆናል ማለት ዘበት ነው። ምክንያቱም በዓለም ላይ በርካታ ሀገራት መሰል ህንጻዎች ይገኛሉ። እንዲያውም በዚህ አሰራር የሚታወቁት ቻይና(በህግ ድንጋጌ) እና ዱባይ (በምጣኔ ሀብት ቀውስ ምክንያት) ተጨማሪ እንዳይገነባ ከልክለዋል።” ሲሉ ይናገራሉ።በተጨማሪም ”በዓለም ላይ ለግንባታ የሚሆኑ ግብአቶች እጥረት እየተከሰተ ባለበት በዚህ ወቅት እንደዚህ አይነት ግዙፍ ህንጻ ከመስራት ይልቅ መዋእለ ነዋዩን ትምህርት መስክ ላይ በማዋል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ማግኘት ይቻላል።” በማለት ሀሳባቸውን ያጠናክራሉ።እንደ አብነት አሁን በመገንባት ላይ ካለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መ/ቤት ግንባታ ወጪ ጋር የመሶብ ታወርን ወጪ ያወዳደሩት የኪነ ሕንጻ ባለሙያው እና በሸገር ሬድዮ የ`ከቤት እስከ ከተማ` መርሐ ግብር አዘጋጅ የሆኑት ማህደር ገብረ መድህን በበኩላቸው የመሰራት እድሉ አነስተኛ እንደሆነ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ 46 ወለል ያለው የንግድ ባንክ 6.1 ቢሊዮን ብር ያወጣል፤ ባለ 70 ወለሉ መሶብ ህንጻ ባለው የውጪ ምዛሬ አማካይነት ወደ 10 ቢሊዮን ሊያስወጣ ይችልል፡፡ ስለዚህ የመሰራት እድሉ ዝቅተኛ ነው፡፡ በአጠቃላይ አንድ ህንፃ ለህዝብ ይፋ አድርጎ ለመቅረብ ከላይ የተገለፁትን ቅደም ተከተሎች አሟልቶ መገኘት አለበት። የመሶብ ህንፃ ደግሞ እነዚህን መስፈርቶች ወይም ቅድመ ሁኔታዎች ባለማሟላቱ ምክንያት ተግባራዊ ቢደረግ ውጤታማ አያደርግም በማለት ሀሳባቸውን ያጠቃልላሉ።በዚህ ጉዳይ ላይ ንድፉን የሰሩትን ባለሙያም ሆነ ህንጻውን በኋላፊነት አስገንብቶ በባለቤትነት እንደሚስተዳድረው የተገለጸው ሚንስቴር መ/ቤት ኋላፊዎች መረጃ ለመስጠት ፈቃደኞች አልሆኑም። የመ/ቤቱ ሀላፊዎች “ከአፍሪካ አንደኛ የሆነ ህንጻ እንደሆነ እንዲሁም ከከተማዋ ፍላጎት ጋር አይሄድም ለሚለው ጥያቄ አዲስ አበባ ወጥ ሆነ ቅርፅ የላትም፤ ይሄ አያሳስብም ።” በማለት በደፈናው አስተያታቸውን ሰጥተዋል። 

አስተያየት