የሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ከመገንባቱ በፊት፤ ከቻይኖቹ ጋር የበቆሎ ቅቅል ከመካፈላችን ቀድሞ፤ ከህንዶቹ ጋር ራሷቸው በሰሯት ባጃጅ ወንበር ለመያዝ ሳንጋፋ ድሮ፣ ከማሌዥያኖቹ ጋር አቡካዶ በዳጣ ሳንቋደስ ገና ገና… እንዳልክ እያለከለከ መጥቶ፤ ደግሞ ያችን አምስት ቦታ ተንፍሳ በተውሶ ማስቲሽ (ጫማ ሰፊው ዳኜ "ለመጨረሻ ጊዜ ነው" ብሎ አስፈራርቶ የሰጠን) አስር ቦታ የተለበጠች ባለኒ ኳስ እያነጠረ በር በራችንን ሲያይ፤ ሳይጠይቀኝ እሺ እለዋለሁ፤ ሳይለምንኝ እከተለዋለሁ፤ ቢጥም ሳይለኝ ፈቃዴን እሰጠዋለሁ። አብረሃም ላስቲኳ ብቻ የቀረች ጀላቲውን እየመጠጠ፤ ኪያ ሸፋፋ ሸራ ጫማውን እየጎተተ፣ ጴጥሮስ የቤት መጥረጊያ ከሚያክለው ሸንኮራ ጋር እየተላፋ፤ የበኃይሉ እናት ትንሹ ልጃቸው ጠፍቷቸው "ያንን ሰላቢ አያችሁት?" እያሉን፤ እኛ ልባችን ተሰቅሎ፤ ልክ እንዳረፈደ ተማሪ ተግተልትለን ወደ አውሮፕላን ሜዳ እንበራለን።
የውቅሮ ሰፈር ልጆች ቀድመውን መጥተዋል። የዋርካ ሰፈር ልጆችማ እዚሁ ማደር ነው የቀራቸው። የፒያሳ፣. የቄራ፣ የ05 እና የደቡብ እዝ ወጣቶችም ሜዳዋ ላይ ሰፍረውባታል። ጥቃቅንና አነስተኛ አውሮፕላን እንዲያሳርፍ የታቀደው ሜዳ ኳስ መጠለዣ ሆኗል። ተስፋ ቆርጠን፤ የጨዋታ ሞራላችን ሙሽሽ ስትል ሸንኮራውን ያልጨረሰው ጴጥሮስ ወደ በቆሎ እርሻ ይጠቁመናል። እንስማማለን፤ በርግጥ አማራጭ አልነበረንም። ያ አሁን ፓርኩ ያረፈበት ቦታ፤ 16 ሺህ ወጣት ጨርቅ ቀዶ ሸሚዝ የሚሰፋበት ግቢ የቫንዳምን (የሆሊውድ አክትር) ክንድ የሚያክል በቆሎ ያፈራ ነበር። አይተው የማይለዩን፣ ረግመው የማይጠግቡን፣ ሮጠው የማይደርሱብን ዘበኞች ትዝ ይሉኛል። የእርሻውን መስመር ተከትልን የሩጫ ሀራራችንን እንወጣለን፤ ከዚያም ያቅማችነን ያህል ለጋ በቆሎ መንትፈን እብስ።
ጀንበሯ በፍቅር ሀይቅ ታዝላ፤ በታቦር ተራራ ሽኮኮ ተብላ፤ በሀዋሳ ለስላሳ ነፋስ እሹሩሩ እየተባለች ወደ ማደሪያዋ ስታዘግም እኛም ነጭ ላበታችንን ለማስለቀቅ ወደሀይቅ እንሄዳለን። በ01 በኩል አድርገን፤ በማራናታ ቤተክርስቲያን ታጥፈን፤ ወሎ መንደርን ዘይረን (መግሪብን ለመስገድ በጊዜ ወደ መስጊድ የሚያመሩት ሸህ ሰይድ ገና ሲያዩን "እንዲህ ከጉድጓድ የወጣች አይጥ መስላችሁ ወዴት ነው?" ይሉናል። አነጋጋረቻው የሆነ ቃና አለው፣ ቃላቸው ለዛ አለው፣ ፈገግታው ውበት አለው። የኪያን ጸጉር እያሻሹ "ምን ያለኸው ጅላንፎ ሁነኸልሳ፤ በቃ ኪታቡን ርግፍ አርገህ ተውከውም አይደል?") ሀይቃችን ጋ ከተፍ።
ጊዜ ሄደ… ሰው ሄደ…ጊዜ መጣ… ሰውም መጣ። በቅርቡ የሸህ ሰይድንና የመንደራቸውን ሰዎች ሁለንተናው ባህል የሚያስተዋውቀኝ፤ ከተማ የሚለግሰውን ገጸ-በረከትና ጦስ የሚያስታውሰኝ ሸጋ (የአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ደባሌ ተመስገን በገባሁ በወጣሁ ቁጥር 'ሸጋዋ' ይልኝ ነበር። ቅላጼው አሁንም ጆሮየ ስር እንደተሰነቀረች ነው። የሆነ ቅርበት ነገር አላት፤ አለሁልህ፣ ከጎንህ ነኝ የምትል) መጸሀፍ አገኘሁ።
ስሄድ አገኘኃት ስመለስ አጣኃት
የቦርከና ውሀ እባብ ያንሻልላል
ያንቺ ልብ እንዴት ነው የኔ ይዋልላል
(የህዝብ ስነ-ቃል)
ባለፈው ወር፤ ወደ ደሴ ለስራ ጉዳይ ስሄድ የሙሉጌታ አለባቸውን 'መሀረቤን ያያችሁ' መጸሀፍ በሻንጣየ ይዤ እንዲሁም የማዲቱ ወዳይን "እሽክም" ሙዚቃን በፍላሼ ጭኜ ነበር። የስነ-ሰብዕ (Anthropology) ተማሪ እንደመሆኔ መጠን መጓዝ እወዳለሁ፤ ስበር ውየ ስበር ባድር የማየት ክንፎቼ አይደክሙም። ስሮጥ ነግቶ ስሮጥ ቢመሽ የማየት እግሮቼ አይዝሉም። መንፈሴ ክፍት ነው! ወደ ላይ ብወጣ የሀገሬ ሰዎች ርጥብ ልባቸውን ጎዝጉዘው እንደሚቀበሉኝ አምናለሁ፤ ተደርጎልኝም ያውቃል። ወደ ታች ብወርድ የሀገሬ ሰዎች ለስላሳ ፈገግታቸውን ነስነሰው እንደሚያቅፉኝ አውቃለሁ፤ ተደርጎልኝም ያውቃል። ወደ ጎን ብሄድም የሀገሬ ሰዎች ቡቡ አንጀታቸውን ዘርግተው እንደሚያሳርፉኝ አይቻለሁ፤ ተደርጎልኝም ያውቃል። ውስጤ ለአዲስ ባህል ቀና ነው! ለዚያም ነው የኢትኖግራፊክ ስራዎች የሚስቡኝ።
(John Brewer noted that Ethnography is the study of people in naturally occurring settings or 'fields' by means of methods which capture their social meanings and ordinary activities, involving the researcher participating directly in the setting, if not also the activities, in order to collect data in a systematic manner but without meaning being imposed on them externally).
John Brewer
በእኔ እድሜ የፍቅረማርቆስ ስራዎች ጥም ቆራጭ ናቸው። በእኔ ዘመን የአዳም ረታ ጥልፍልፍ ትረካዎች አንጀት አርስ ናቸው (እህቴ እንደ ጦር የምፈራውን ኪሮሽ ሰድራ ዳንቴል ስትሰራ አበሽቃታለሁ። ክር መተብተብ ምን የሚሉት ሙያ ነው? ሞክረው ብላ ስትጠኝ ውትፍትፍ፣ ውሽልሽል አደርገዋለሁ) አዳም ታሪክን፣ ባህልንና ጊዜን አሰናስሎ ሞሰብ ላይ ጣል የሚደረግ የልቦለድ ዳንቴል የሚጠልፍ እንቁ፣ ድንቁ፣ ብረቁ (ቤት ስለመታልኝ እንጂ ሰውየው ከዚህም ይከብዳል) ነው።
ሙሉጌታ አለባቸው “መሀረቤን ያየ” ብሎ የዘመን ጥያቄ፣ የከተማ እንቆቅልሽ ሲጠይቅኝ ‘አላየሁም እባካችሁ’ ብየ ማለፍ አልፈለኩም፤ እቃቃው ፈረሰ ዳቦው ተቆረሰ ብየም መተው አልሻትኩም። ሙሌ Benedict Anderosn፣ Frederic Barth፣ Frank Webister፣ Sinisa Maleseviç፣ Mark Haugaard እና መሰል የስነሰብዕ ሊቃውንት ሲቦካ የነበረውን የማንነት፣ እንዴትነት፣ ለምንነትና ወዴትነት ምርምሮች በራሱ ሊጥ የጋገረልን ደራሲ ነው። መሀረቤን ያያችሁ የየጁ ገነት ትዝታ የሚላመጥበት ድርሳን ነው። ትላንት አልጨበጥ፣ ዛሬ አልያዝ ነገም አልነካ ያለው ስብክብክ (ታሞ ህመሙን የማይናገር አራስ ልጅ ወይም ንጭንጭ የተቀላቀለብት ለቅሶ እያቋረጠ የሚቀጥል) ጉብል ትርክት ነው። መሀረቤን ያያችሁ ፍቅር በዘመን አመጣሽ ቦለቲካ፣ እምነት ውሸት ወለድ በሆነ እውቀት ሲሸረሸር፣ ሲናድ፣ ሲንኮታኮት የሚያሳይ መድብል ነው። ልጅነቱን ባደራ አስቀሞጦ ወጥቶ ሆኖም ሲመለስ እንደ ጤዛ የተነነችበት (የሀይሌ ገሪማ ጤዛ ፊልምን ልብ ይሏል)፤ ታዳጊነቱን በጥቁር መሀረብ ሙጋድ አደባባይ ላይ በውሰት ሰጥቶ ሄዶ፣ ሄዶ፣ ሄዶ እንደገና ሲመለስ አጣት።
ሙሌ ደገኞቹን ከሳንቃና ዋድላ፤ ቆለኞቹን ከቆቦኖ ራያ ከነ ሽርጣቸው፣ ከነ ጅብ አይበላሽ ጫማቸው፣ ከነ ክትክታ መሟጫቸው፤ ገነቴ ማክሰኞ ገበያ ሸክፎ የጁ የተዋቀረብትን ካስማ፣ ወሎ የተቀየጠበትን ቀለም፣ ሀገሬ ኢትዮጵያ የተገመደችበትን የባህልና የታሪክ ሀረግ እንደ ፋፎ ቆሎ፣ እንደ ባኒ ዳቦ ደግሞም እንደ ሶፍያ ቁርቁራ በሚጣፍጡ ዓረፍተ ነገሮቹ ያቃምሰናል። ይህቺን ልዋሰው...
ከጋራው ስር እንደ ነዳይ ልብስ እዚህና እዚያ የተቦተረፈ ባዘቶ ደመና የለበሰች፤ ከደመናውም ስር ለጋስ ክረምት አረንጓዴ የውስጥ ልብስ ያቆናጸፋት ገነቴ፤ ያልበሰለች የጳጉሜ ጸሀይ ላይዋ ላይ እንደ ወርቅ ውሀ ፈስሳባት፤ ለመሳል እንደተዘጋጀች ቆንጆ በጥልቅ ጸጥታና በርግታ ተቀምጣለች፡፡ (ገጽ-1).
ይቺ ረጋ ያለች ከተማ፣ ይቺ ረጋ ያለች ህይወት የተገነባችው በመልክ ብዙ ቋሚዎች እና በቁመተ ልዩ ማገሮች ነው። ከምዕራብ ሳንቃና ቃሊምን ተሻግሮ እስከ ዋድላ ደላንታ ድረስ ያሉ ደገኞች፤ ከሰሜን ቆቦና ራያ የሚኖሩ ጠምበለል ቆሎኞች፤ ከምስራቅ ከአፋር የግራ ጎን ከሀራና ከሚሌ ሽርጣቸውን ያገለደሙ የበርሀ ሰዎች፤ የቅርቦቹ ከወውድመንና ከመቻሬ በረባሶ ጫማቸውን ደንቅረው ገነቴ ገበያ ከች።
ገነቴ በዘመን ኩሽና ውስጥ በእልፍ አይነት ወጥ ቤት የተሰራች የሆነ አይነት ልዩ ምግብ ሆናለች። የሆነ የአረበኛ አሰል (ማር)፤ ጠብ ብሎበት የኦሮምኛ አሳቦ (ጨው) የላሰ፤ በትግረኛ ባኒ (ዳቦ) የታጀበ፤ በጣልያን ደንብ በሹካ የሚበላ በአማርኛ ሳህን የቀረበ፤ የአፋር የበክል ጥብስ
(ገጽ-197).
ይህ የሚያጓጓ ሚስቶ ምን ገጠመው? በ2009 ዓ.ም ለህትመትየበቃው መሐረቤን ያያችሁ 12 አጫጭር ታሪኮችን በ215 ገጽ አቅፏል። እኔ የድርሰቱ ዓይና ጆሮ በሆኑት ሁለት ትረካዎች ላይ አተኩራለሁ። በለስ አልባ ገነት 1 እና 2። መነጸሬም ስነ ጽሁፍ ሳትሆን የከተማ ስነሰብ (UrbanAnthropology) ነው።
ከውስጥ ወደ ውጭ
ባቲ ላይ ሰው (ያው ቆንጆ መሆን አለበት) አይቶ አበደ ሰውየው
ደሴ ላይ ቆንጆ አይቶ አበደ ሰውየው
ከሚሴ ቆንጆ አይቶ አበደ ሰውየው
መቼ እመለሳለሁ የጁን ሳላሳየው።
(የህዝብ ስነ-ቃል)
የሰውን ልጅ እንዴትነትና ባህል ምንነት በመመርመር ፍቅር የተለከፈው ስነሰብዕ የረጅም ታሪክ ባለቤት ነው። እንደ E.A.Oke (1984) ያሉ ወግ አጥባቂ ሙህራን አጀማመሩን ወደ ፈላስፋው Xenophanes (570-475 BC) እና ጸሀፊው Herodotus ofHalicarnassus (c. 484–425 BC) ጋር ይወስዱታል።ከ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት የነበሩ የስነሰብዕ ሊቃውንት ትኩረታቸው ከምዕራቡ አለም በርቀት ላይና ተገለው በሚኖሩት ማህበረሰቦች ላይ ነበር። ህዝቦቹ ከመረጃ፣ ከእውቀት እና ከመሰረተ ልማት የራቁ በመሆናቸው ያልተበረዘውን ባህል ለማጥናት አመቺ ሆኗል። በዚህም Bronislaw Malinowsk, Lewis Henry Morgan, Edward B. Taylor እና የመሳሰሉቀደምት ተመራማሪዎች ተሳታፊ ነበሩ። ይሁን እንጂ ከኢንዱስትሪ አብዮት መስፋፋት ጋር ተያይዞ ቅኝ ግዛት ሲጧጧፍ፤ መሰረተ ልማት ሲዘረጋ፤ ከተሞች መስፋፋትና ብዛት ያለውን የህዝብ ቁጥር ማስተናገድ ጀመሩ። ይህም የማህበራዊ ሳይንስ አጥኒዎችን ቀልብ ሰረቀ። እኤአ በ1930ዎቹ የችካጎ ሶሾሎጅካል ት/ቤት የከተማን ጥናት የምር ያዘው። በተለይም Urbanism as aWay of Life የተሰኘውየLouis-Wirth(1938) የምርምር ወረቀት አይን ገላጭ ነበር። በአሁኑ ወቅት የከተማ ስነሰብ የሚባለው የጥናት ዘርፍ የከተማ ህይወትን ቅርጽ፣ መልክ፣ ባህሪ፣ ታሪክ እና መሰል ጉደዮች ላይ ትኩረቱን አድርጓል።
ሙሉጌታ በዘመን ሂደት ስሟና ለዛዋ እየተለወጠ ስለመጣችው የቀድሞዋ ገነቴ፣ ከዚያም የጁ፣ ዛሬ ደግሞ ወልድያ (መገናኛ) ተብላ ስለምትጠራው አድባር በቁጭት እስክርቢቶ አሪፍ እውነት ቀመስ ልቦለድ አዘጋጅቷል። በተለይም በመጽሐፉ መግቢያና መውጫ በር ላይ የተሸጎጡት ታሪኮች አንጀት ይበላሉ። በቃ የጋራ እሴቶቻችን(sharedvalues) ብጥስጥሳቸው ሲወጣ ማኀበረሰባዊ ትውስታችን (collective memory) ስብርብር ሲሉ ያሳይሃል። ስነ-ቃሉ ዞሮ ዞሮ ማህበራዊ ለውጡን ያስተጋባሉ፣ ግጥሙ ሄዶ ሄዶ ትላንትና ዛሬን ያነጻጽራል፣ ባለቃና ንግግሮቹ እንዲሁም ምስል ከሳች ገለጻዎች በገነቴ ፍቅር ወድቀን ትዝታዋን እንድንጋራ፣ ጨዋታዋን እንድንቋደስ በህመሟም ምጥ እንደረዘመባት እርጉዝ እህህህ…… እንድንል ያስገድደናል።
ሙሉጌታ ገነቴ ላይ እትብቱ የተቀበረ፣ ትውስታው የተዳፈነ፣ እንቆቅልሹ የተሸሸገ ይመስለኛል። እናም መሀረቤን ያያችሁ ከውስጥ ወደ ውጭ የተተኮሰ የቃርያ ጥፊ ነው። ይህቺን ልቀንጭብ...
እዚህ ሰፈር በጥቁር ዐይነ ርግብ ሸፍነው መሀል ላይ ቢጥሉኝ፤ በኮቴያቸው ድምጽ ለይቼ አብሮ አደጎቼ ሰላም እያልኩ...ታድያስ ሰረቀ...አዲስ ስዕል አልሰራህም?... ርቦኝ ሳፋሽክ ስታየኝ ቁራሽ የማትነፍገኝ የሀጂ እንድሪስ ልጅ ሀውለትን እያመሰገንኩ...እግዚሃር ይስጥልኝ ሀውለትዋ..." (ገጽ-198). ይህ ገለጻ እንደ እውር አሞራ መሀል መንደሬ ላይ ቢጥሉኝ የሚያነሳኝ አላጣም መሆኑ ነው። ይሁን እንጂ ብዙም ሳንርቅ ገጽ-200 ላይ እንዲህ ይላል "ከዩንቨርስቲ ተባርሬ ድብርቴን ለማረገፍ፤ የናፈቀኝን የሰፈሬን አየር በመስገብገብ ልተነፍስ የሳንባየን ክንፎች ዘርግቼ ስወጣ፤ አብሮ አደጎቼ የነበሩ የሰፈሬ ልጆች ዘር እየቆጠሩ እንደ ካርታ ስራዎች ድርጅት ድንበር ሲያበጁ ደረስኩ።
ሙሉጌታ ለውጡ መቼ ተጋግሮ መቼ ለምሳ እንደደረሰ በግልጽ አይናገርም። ማኀበራዊ ህይወታችን እንዴት እንደተከረባበተ በማስረጃ አይተነትንም። በርግጥ በፈጠራእና በትዝታ መኃል ላይ ከቆመ መጽሐፍ መልስ ፍለጋ መኳተን ብዙም ስሜት ላይሰጥ ይችላል። ሆኖም ብዙ ጸሐፊያን ባህልና ማንነት እንደሚለወጥ ይረሱታል። ቤነዴክት አንደርሰን (1983) ማንነት የምናብ ፈጠራ ስለሆነ በጊዜ፣ በቦታና በሁኔታዎች መሻሻላቸው ወይም መቀነሱ አይቀርም ይላል። አቶ የሱፍ ያስን "ኢትዮጵያዊነት፣ አሳባሳቢ ማንነት በአንድ ሀገር ልጅነት" (2009) በተሰኘ መጽሐፋቸው የማንነት ድንበሮች ቋሚ ሳይሆን ተለዋዋጭና በየጊዜው የሚታደሱ ናቸው፤ የሚታደሱት ደግሞ በማኀበራዊ መስተጋብሮቻችን ነው ሲሉ ያስረዱናል። በዚህ በየቀኑ አዳዲስ ፈጠራ አለምን በሚያጨናንቅበት ወቅት በራስ አጥር ተከልሎ መኖር የዋህነት ነው፤ ወደ ለውጡ ላለመሄድ ወስነን በራችንን ብንቆልፍ እንኳ አንችልም፤ ቴክኖሎጂው ነፋስ ለብሶ እሳት ጎርሶ ይመጣብናል። የትምህርትና የመሰረተ ልማት መስፋፋት ሲጨመርበት ደግሞ ለአዳዲስ ባህሎች ተጋላጭ እየሆንን እንመጣለን።
ታዲያ የራስ አስጥሎ በልካችን ያልተሰፋ ልብስ እንዴት ለብሰን ቁጭ አልን? የት ጋ ተሸወድን፣ ለምንወደ ተሳሳተው መንገድ ተሸቀዳደምን፤ እረ እንዴት ሀይ የሚለን አጣን፣ እንደዚያ ለመራራቅ የተጣደፍነውስ እዚህ ለመድረስ ነበር?
ኑ አብረን እንሽሽ
ይሄው አሁን እንቅልፋችን በነነ
ጎህ ቀደደ፤ ህልማችን ተነነ
ደረቅ ረፋድ ሆነና መለያያት ዘለቀ
ቀትር በህዋው ሰፈነ፤ አዚማችን ለቀቀ።
(ካህላል ጅብራን - ትርጉም ጌታነህ አንተነህ)
ሙሉጌታ የፈራ ይመስላል። ከመጽሐፉ ሽፋን ጀምሮ (ከጥቁረቱ መሞጫጨሩ) ጭንቀት፣ ብስጭትና ሀዘን ተሸክሞ የሚዞር የከሰረ ነጋዴ ዓይነት ሆኖብኛል። ለምሳሌ፤ በእውንና በህልም ዓለም እመላለሰለሁ (ገጽ- 6) ሰውነቴ ዝሏል (ገጽ-8) የተቀመጥኩበት ኩርሲ ይቆረቁረኛል (ገጽ-15) እህሳ ጆንትራው! አበባችን በሞሳነታችን አልረገፈም? (ገጽ-200) መለመላዋን በቀረች ልቤ ሳቁ (ገጽ-200) ከዘመን መቅሰፍት ለመሰወርስ አልታደልንም (ገጽ-201) ሰው መሆንን የሚያስረሳ፣ ወንድማማችነት ቆርጦ የሚጥል፣ ምን አይነት ሰይጣን የሞረደው፣ እንዴት የተባ ካራ ነው ፖለቲካ? (ገጽ-201)...ዝርዝሩ ብዙ ነው።
ማፈግፈግ መፍትሄ አይሆንም፤ ቀለል አድርጎ ዳገቱን መውጣት ይሻላል። በርግጥ የሚታየው፣ የሚሰማው፣ የሚነበበው ሊያስበረገግ ይችላል። ሆኖም አዋጩ ጉዳይ ዛሬን ማሳመር ፣ ለነገ ደግሞመሰረት መጣል። ሁላችንም በለውጥ ውስጥ ነን። ባህል በቴክኖሎጂ መስፋፋት፣ በመሰረተ ልማት መጎልበት እና በድንበር ዘለል ንግድ ቅጣንባሩ እየወጣ ነው። አሁን በርና መስኮት ዘግቶ ቅርሴ፤ ታሪኬ ምናምኔ የምንልበት ጊዜ አልፏል። የለውጡ ጎርፍ ጠራርጎን ከመድፈቁ በፊት ለውጡን በጥሞና መረዳት፣ መተንተን፣ መከራከር እና የማርያም መንገድ መፈለግ አለብን። (አለበለዚያ የፖለቲካ ሳይንቲስቱ Samuel P. Huntington በThe Clash of Civilizations and theRemaking of World Order (1997) አረቦቹ ላይያሟረተው በኛም ስላለመደገሙ ዋስትና የለም) ። ሙሌ መውጫ ቀዳዳውን ይጠቁመናል ብየ ስጠበቅ ራሱ ሲደናገር ታዝቤዋለሁ ወይም ምን አገባኝ ብሎ ትቶታል።
ፍቃዱ ቀነኒሳ የፕሮፌሰር መሳይ ከበደ "Africa’sQuest for a Philosophy of Decolonization" የተባለ መጽሐፉ በመጥቀስ መፍትሄውን ለማሳየት ይሞክራል፡፡ በድህረ ቅኝ ግዛት አፍሪካ ያሉትን ነባራዊ ሁነታዎች በድጋሚ በማጥናት፣ ከእኛ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የማይሄዱና የተዛባ አስተሳሰብ የሚታይባቸውን እንደ ዘመናዊነት የመሰሉ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ፍልስፍናዊ ጽንሰ ሃሳቦች ትርጉም በመሻር (deconstruction) እንደ አዲስ ከእኛ አውድ ጋር አስታርቆ መበየን (reconstruction) ነው ይላል። ሌላው አፍሪካዊ ፈላስፋ ፀናይ ሰረቀብርሃን "The Critique of Eurocentrismand the Practice of African Philosophy" በተባለ ጽሑፉ፣ አፍሪካውያን በዘመናዊነትና በሉላዊነት ሳቢያ በአውሮፓውያን እየደረሰባቸው ስላለው የባህል ተጽዕኖና ስለማምለጫ መንገዶቹ ሲጽፍ፣ የአፍሪካውያን ፍልስፍና Historico-Hermeunitical የተባለውን መንገድ በመከተል የአፍሪካውያንን ችግሮች ከታሪካዊ ዳራ ትንታኔ በመነሳት እንደገና ማሰብና የተጣመመውን ማቃናት፤ የጎደለውን መሙላት ያስፈልጋል ይላል"። እንደዚያ ካልሆነ ግን የሙሉጌታን ሀሳብ መውሳችን አይቀሬ ነው፡፡ "ይህንን ያልተረዳች እንጭጭ ነፍሴ ግን፤ ቅጠልያ ደም ባላቸው ለጋ ወንድሞቼ መካካል...በቂመሀ ቤት ተረብ ተሸፋፍና ፈዋሾቿን ትክድ ነበር::”(ገጽ-206).
ጎዲን
ቀጥተኛውን መንገድ ምራን
የነዘያን በነርሱን ላይ በጎ
የዋልክላቸውን፣ በነርሱ ላይ
ያልተቆጣህባቸውንና
ያልተሳሳቱትንም ሰዋች መንገድ...
(ቅዱስ ቁራአን)
ዱኒያ፣ ሙላቃ፣ ሙጌራ፣ ባኒ ዳቦ፣ ካሳፉርት፣ ላነቲካ፣ ቅዋ፣ ፋጡማ ቆሪ፣ ፌርኔሎ፣ ነአል ዲነክ፣ ሙስበክ፣ ሀለዋ፣ ራሄሎ፣ ወዳጃ፣ ማሟጫ፣ አንጋሬ፣ ጥልቆ፣ ፎሌ፣ ሱቢህ፣ አድሩስ፣ ሳርጢስ፣ ቡቅሬ፣ ተርቲበኛ፣ አሻቦ...። ሙሉጌታ ወሎተኮርና እየጠፉ ያሉ ቃላትን ከያሉበት ለቃቅሞ ወደ ገበያ ይዟቸው ከች ብሏል። ለልብ-ወለዱ ማርና ቅቤ ሆነውታል። ምንጫቸውንና አመጣጣቸው በግርጌ ማስታወሻ መተንተኑም ደራሲውን የሚያስመሰግነው ነው። ለተጨማሪ የኢትኖግራፊክ ጥናት በር እንደሚከፍት ተስፋ አለኝ። በአጠቃላይ ግን ውስጥን ኮርኳሪ ስራ ነው።
በመጨረሻም ሙሌን እንዲህ ብለው እወዳለሁ...ከናፍቆት ጥላ ራቅ በል፣ ከጨለማ ዳስ ወጣ በል፣ ከትዝታ እስር ፈቀቅ በል (ሺ አመት አይኖርወንድሜ! አለበለዚያ ወደ ተማርክባት ሀዋሳ ናና ሽር ብትን በል)።