_ሞሴ በምዕራብ ጎጃም በአንድ የገጠር ቀበሌ ውስጥ ጥናት ሳደርግ ካጋጠሙኝ አርሶአደሮች አንዱ ነው። ተንቀሳቃሽ ስልኬን ቻርጅ የማደርገው እሱ ጋር ስለነበር በተደጋጋሚ አገኘው ነበር። 20ዎቹን ያላለፈ ወጣት ነው። ሆኖም ቤተሰብየሚያስተዳድር አባወራ ነው። ያርሳል፣ በጓሮው አትክልት ያለማል፣በተጨማሪም አነስተኛ ሱቅ አለው። ወደ ገጠር ማእከሉ ገብቶ መኖር ከጀመረ ከሦስት ዓመት በላይ ሆኖታል። በወረዳ በተዘጋጀ የሽንሽን ፕላን አማካኝነት ያለበት አርሶአደሩን ወደ ቀበሌውንማእከል ለማሰባሰብ እየተሞከረ ነው። ይህም ማእከሉ ላይ መጠነኛ እንቅስቃሴያለበት እንዲሆን አድርጎታል። በዋናው መንገድ ላይ ለሚያልፍ ሰው ከመጋዘንእህል የሚያወርዱና የሚጭኑ ሰዎች ይታያሉ፡፡ ጭነት መኪኖች የፒስታ መንገዱን አቧራ እያቦነኑየተመረተውን ምርት ጭነው ይተማሉ። ሳይክል የሚጠግኑ ወጣቶች፣ ጸጉር የሚቆረጥበት ሱቅ፣ የምግብ ቤቶች፣ አረቄ መጠጫዎች ወደ ውስጥትንሽ ገባ ብሎ ደግሞ የሚሸምኑ ወጣቶች፣ ብረት ቀጥቅጠው ማረሻ እና ቢላዋየሚያመርቱ ሰዎች፣ እንደ ሞሴ አይነት ሱቆች ይመለከታሉ። ይህን ሁሉ ለሚመለከት ሰው ከገጠርወደ ከተማ ሊቀየር ነው የሚል ጮክ ያለ መልዕክትያስተላልፋል።
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ እጅግ ዝቅተኛ ከትሜነት ካለባቸው ሃገሮች አንዷ ናት። ይህን ለመረዳት ከሳሃራ በታች ባሉት አገሮች ካለው 37 በመቶ አማካይ የከተሜነት ምጣኔ ጋር ማነጻጸር በቂ ነው። የሀገሪቱ ከተማ በመቶኛ ሲስላ 20 እንኳን አይሞላም፡፡ መጠኑ አነስተኛ ይሁን እንጂ ይህ በዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ያልዳበረው ከተሜነት ለሀገሪቱ ጥቅል ምጣኔ ሃብት 38 በመቶውን ያበረክታል። ይህም ከተሜነት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ያለውን አስፈላጊነት እና አንገባግቢነት በግርድፉ ይጠቁመናል።
ለነገሩ ወደ ከተማነት መሸጋገሩንተወደደም ተጠላም በከፍተኛ ፍጥነት እየሆነ ያለ እውነታ ነው። ከገጠር ወደ ከተማ፣ ከተሞቹ ሊቀበሉከተዘጋጁበት ፍጥነት በላይ የሚፈልሰውን ነዋሪ ትተን በዛው በሚኖሩበት የገጠር ቀዬ በሚገኙ የገጠር ማእከላት የሚታየውን ወደ አንድቦታ የመሰባሰብ፣ ቤት የመስራትና ከግብርና ውጪ ባለ እንቅስቃሴ የመሳተፍ ሁኔታ፤ የከተሜነት ፍላጎት በገጠር ነዋሪውም ዘንድ ስርመስደዱን ያስረዳናል። ለዚህ እጅግ ብዙ ምክንያቶች መጠቀስ ይችላሉ። ከነኚህ መካከል ለመደምደሚያዬ የሚያግዙኝንና በጣም ወሳኝ ናቸውያልኳቸውን ሁለቱን ብቻ ላንሳ።
ጥግግት ለመሰረተ ልማት
አብዛኞቹ መሰረተ ልማቶች ለዜጎች በዝቅተኛ ወጪ በቀላሉ ሊቀርቡ የሚችሉት ነዋሪዎች በተቻለ መጠን ተጠጋግተውበአንድ ቦታ ሲሰባሰቡ ነው። በደርግ ጊዜ አርሶ አደሮችን በአንድ ቦታ አሰባስቦ ለዚህ የሚያመቻች ጎጥ በመባል የሚታወቅ ስርዓትየነበረ ሲሆን ዛሬም በአብዛኛው የኢትዮጵያ የገጠር ቀበሌዎች ከ600 እስከ 1000 አካባቢ የሚሆኑ ነዋሪዎችን በመያዝ በየቀበሌውከስድስት እስከ አስር ሆነው እናገኛቸዋለን። ሆኖም ይህም ቢሆን ከላይ የጠቀስኩትንውጤት ለማስገኘት እዚህ ግባ የሚባል ጥግግትና ብዛት ባለመሆኑና ጎጦችም አንዳቸው ከአንዳቸው ተራርቀው ስለሚገኙ ዛሬም ድረስ ልማትንእና መሰረተ ልማትን ማዳረስ ውድ እና ከባድ አድርጎታል። ከላይ የጠቀስኩላችሁ የቀበሌ ማእከል ጎጥ እንኳን ያለው የአባወራ ብዛትከ300 አይበልጥም፣ በዚያ ላይ የአንድ ሰው ይዞታ 1000 ካሬ ሜትር አካባቢ እንደመሆኑ ጥግግቱ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።ስለዚህም ከዚህ የተሻለ የህዝብ ብዛትና ጥግግት ያላቸው የወረዳ፣ የዞን እና የክልል ከተሞች መሰረተ ልማትን በተሻለ ሁኔታ የሚያገኙበመሆኑ፣ ከገጠር ወደነኚ ከተሞች የተሻለን ኑሮ ፍለጋ ይሰደዳሉ።
አማራጭ የስራ እና የኢኮኖሚ መስክ ፍለጋ፣ የእርሻ መሬት እጦት
ማእከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ በ2001ከወጣው መረጃ መረዳት እንደሚቻለው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ገበሬ ያለው አማካይ መሬት 1.2 ሄክታር ሲሆን ይህም አሁን ባለው ነባራዊየምርታማነት መመዘኛ ስንወስደው አንድን ቤተሰብ ለመመገብ የማያስችል ነው።ከዚህ በላይ ለማምረት ወይም ምርታማነትን በተሻሉ የአስተራረስ ዘዴዎች ለመጨመር የሚያስፈልገውን የማዳበሪያ እና የመካናይዜሽን ወጪለመሸፈን ደግሞ በዚች የመሬት ስፋት የማይደፈር ነው። እንግዲህ ይህን ሁሉ የምናወራው ይቺን መሬት በአማካይ 4-6 ወደሚሆኑ ልጆቹማስተላለፍ እንደሚጠበቅበት ከግምት ሳናስገባ ነው።
የአማካይ ገበሬ ሁኔታ ይህን ሲመስል፣ልጁ ደግሞ የትምህርት ተዳራሽነት መጨመሩን ተከትሎ ከተግባረ-እድም ሆነ ከከፍተኛ የትምህርትተቋማት ከተመረቀ በኋላ ተመልሶ ወደገጠር ሄዶ የመስራት ፍላጎት ማጣት፣ በእርሻ መሰማራት ቢፈልግ እንኳን የአስተራረስ ዘዴውን ማሻሻልይቅርና በተለምዶው መንገድ እንኳን ለማረስ መቸገር ግብርናን በመተው ወደሌላ የስራ መስክ እንዲያማትር ያደርገዋል።
ምርታማ እየሆነ የመጣው፣ ሰፊ መሬትያለውና በየገጠር ቀበሌው የኑሮ መሻሻል እያሳየ የመጣው ሞዴል አርሶ አደር ደግሞ የቆጠበውን ገንዘብ ተጠቅሞ ሌላ የስራ መስክ ላይላይ እንኳን ባያውለው ከተማ ሄዶ ቤት መስራቱ አይቀርም። በአጠቃላይገበሬው ኑሮ ሲከዳውም ሆነ ኑሮው ሲሻሻል የሚታየው ቀጣይ እርምጃ ከተማ ነው ማለት እንችላለን።
በእነኚህና በሌሎችም ምክንያቶች ከተማነት እያደገ መሆኑ እውነታ ነው። ሆኖም አብዛኛው ውይይት እና ጥናት ያተኮረው ከገጠር ወደተመሰረቱ ከተሞች የሚደረገው ፍልሰት ላይ እንጂ፣ በገጠር ቀበሌ ማእከላት እየታየ ያለው የመሰባብሰብ ቦታ የመመራት፣ መሬት የመግዛት እና ቤት የመስራት ሁኔታ አይደለም። እነኚህ ላይ በትኩረት መስራት ለኢትዮጵያ በአጠቃላይም ሆነ ለአርሶ አደሩ በየግል የሚያመጣው አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ ነው ብዬ እሞግታለሁ። በጣም ዋና የምላቸውን ልጥቀስ
- የኢኮኖሚ ሽግግር በአነስተኛ ስጋት
የአሜሪካንን 300 ሚሊየን አካባቢህዝብ የሚመግበው 2 ሚሊየን የማይሞላው ገበሬዋ ነው። ከ አንድ ፐርሰንት ያነሰ ማለት ነው። ኢትዮጵያ ግን100 ሚሊየኑን በ80 ሚሊየን አርሶ አደር መመገብ ተስኗት ብዙ ስትቸገር እናያለን። እያንዳንዱ ገበሬ በነፍስ ወከፍ የያዘው መሬትአነስተኛ በመሆኑ ከዚያ የሚያገኘው ገቢ ከለት ጉርሱ አልፎ ወደሌላ የሚያሰራ ገንዘብ መቀየር ከባድ ያደርገዋል። ስለዚህ ከግብርናውጪ ወዳለ የኢኮኖሚ አማራጭ መሸጋገር ይኖርበታል። እዚህ ጋር ሁለት አማራጭ ይኖረዋል። አንደኛው ወደ ተመሰረቱት/የሚመሰረቱት ከተሞችመፍለስ ነው። ይህ ብዙ ፈተናዎችን ያዘለ አማራጭ ነው። ምክንያቱም የሚሄድበት ከተማ የማያቀው እንደመሆኑ የስጋት risk መጠኑንከፍ ያደርገዋል። የኔ የሚለውን ንብረት እና ማህበረሰብ ጥሎ እንደመሄዱ እንግዳ በሆነበት ማህበረሰብ ውስጥ ዝቅተኛ ኀብረተሰባዊ ደረጃ(social status) ይዞ መቀላቀል የሚፈጥረው ስነልቦናዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖበቀላሉ የሚታይ አይደለም። ወደ ማኀበረሰቤ ልመለስ ብሎ ቢያስብ እንኳንከስሮ መመለስ የሚያስከትለውን የምን ይሉኛል ዱላ መቋቋም ይጠበቅበታል። በአቅራቢያ የሚካሄድ የመከተም ስርአት ግን ከላይ የጠቀስኳቸውንስጋቶች በመቀነስ እንደ ሞሴ ያለው አርሶ አደር የእርሻ ተግባሩን ሳይለቅ ከተሜነትን በአንድ እግሩ እየሞከረ በመቀጠልም ትርፋማነቱንሲያይ ሙሉ በሙሉ እየገባ ይመጣል። የእርሻ መሬቱንም እርሻው ላይውጤታማ እየሆነ ላለው ገበሬ በመልቀቅ ከግብርና ወደ ንግድና ኢንዱስትሪ የሚካሄደውን ሽግግር ያፋጥነዋል።
- ለኢንቨስትመንት የተረጋጋ የሰውኃይል
በማምረት ዘርፍ ላይ መሰማራት የሚፈልጉኢንቨስተሮች በዚያው በገጠር ማእከል እየተፈጠሩ ባሉ ከተሞች ቢገነቡ ይህንን የመክተም ሂደት ከማገዛቸው በተጨማሪ፤ በማምረቻው ለሚቀጠሩሰራተኞች ቦታው ቀዬአቸው እንደመሆኑ መጠን የመኖሪያና መሰል ወጪዎችን ያስቀርላቸዋል። ለኢንቨስትመንቱም በተነጻጻሪነት ለረጅም ጊዜየሚቆዩለትን ሰራተኞች ያገኛል።
- የባለቤትነት ስሜት፣ የእችላለኹ ስነልቦና
በአሁኑ ጊዜ የገጠሩ ማህበረሰብ ሳያውቀው ነገር ግን ከውስጥ እንደ ነቀዝ እየበላው ያለ ነገር ቢኖር በተደጋጋሚ ችግር ላይ ሲወድቅ በመንግስትም ሆነ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የሚመጣለት መፍትሄ የጥገኝነት እና የተመጽዋችነት ስነልቦና እንዲያዳብር እያደረገው መምጣቱ ነው። ይህም ለሚመጣበት ተግዳሮት አይበገሬ ሆኖ በራሱ የፈጠራ ክህሎት መፍትሄ እንዳያበጅ አድርጎታል። እራሱ የገጠሩ ማህበረሰብ እያየው በተካሄደ ሽግግርና የራሱ የማህበረሰብ ተፈጣሪ የሆነችን ከተማ በማየት የሚፈጠረው፤ በስራ እንደሚለወጡ የማመን፣ የፈጠራ ዝንባሌና የእችላለኹ ስነልቦና ለሃገሪቱ ያለው ፋይዳ እጅግ ትልቅ ነው።
- የመሰረተ ልማት አቅርቦትን በቀላሉባልተለመዱ አማራጮች
የመሰረተ ልማትን ማቅረብ ተጠጋግተውበሚኖሩ ነዋሪዎች መካከል ቀላል እና ቀልጣፋ እንደሆነ ከላይ በመጠኑ አይተናል። አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የገጠር ነዋሪውተጠጋግቶ ቢሰፍር የመሰረተ ልማቶችን ያለ መንግስት ድጎማ በራሱመዋጮ እንኳን ሳይቀር መሸፈን እንደሚችል ነው። ይህንን በመንግስት ቸርነት ብቻ የሚታሰብ ዘርፍ እንደ ህብረት ስራ ማኀበር ወይም የመንግስትና ግል አጋርነት ያሉ መንገዶችን በመጠቀም ዘላቂና ግልጽ በሆነሂደት ማዳረስ ይቻላል።
- ትንፋሽ ለትልልቅ ከተሞች
ከገጠር ወደ ከተማ የሚፈልሰው ህዝብአሁን ያሉት ትላልቅ ከተሞች በተለይም አዲስ አበባ ሊሸከሙት ከሚችሉት በላይ ነው። ይህ በአቅራቢያ የመክተም ሂደትን ማሳካት ከተቻለግን ለትልልቆቹ ከተሞች የተወሰነ ትንፋሽ ይፈጥርላቸው ይሆናል።
በአጠቃላይ የአነስተኛ ከተሞች ሂደትበጥንቃቄ ከተመራ የሚፈጠሩትን አዳዲስ ከተሞች የሃገሪቱን ዋና ዋና ችግሮች መፍቻ ቁልፍ አድርጎ መጠቀም ይቻላል። የኢኮኖሚ ሽግግሩን፣የአርሶ አደሩን ምርታማነት፣ የአርሶ አደሩን ስነልቦና እና የመሰረተ ልማት አቅርቦት ጥያቄዎች ለመመለስ አይነተኛ መግቢያ በሮችመሆን ይችላሉ። ይህን ሂደት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና በአዳዲስ የከተሜነት እሳቤዎች ከመራነው ደግሞ በተቀሩት ከተሞቻችን የሚስተዋሉትንችግሮች ቀድመን መከላከል ብሎም ለሌላው አለም ምሳሌ የሚሆን የአከታተም አማራጭን ልናስተዋውቅ እንችላለን።