የብሔራዊ የህግ ማሻሻያ ካውንስል የሕግ ማሻሻያ ሥራዎችን ከሚያካሄድባቸው ጉዳዮች ውስጥ የሚዲያ ነጻነት እና ሐሳብን በነጻነት የመግለፅ መብቶች ይገኙበታል፡፡ ለማሻሻያ ሥራዎች ግብዓት የሚሆኑ ውይይቶች በመካሄድ ላይ ናቸው፡፡ በእነዚህ ውይይቶች ሐሳባቸውን ካቀረቡ ምሑራን መካከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምሕር የሆኑት መሰንበት አሠፋ(ዶ/ር) ይገኙበታል፡፡ ይህንን የግል የመፍትሔ ሐሳብ ብዙዎች እንዲመለከቱት በማሰብ እዚህ በድጋሚ ታትሟል፡፡
መግቢያ
የመናገር ነፃነት እና የሚዲያ ነፃነት ለማንኛውም በዲሞክሪያሳlዊ ስርአት መርሆች ለሚመራ የፖለቲካ ማህበረሰብ ወሳኝ እና መሰረታዊ የሆነ ጉዳይ ነው፡፡የመናገር ነፃነት እና የሚዲያ ነፃነት ለዲሞክራሲያዊ ሰርአት ግነባታ ወሳኝ እና መሰረታዊ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡ ዲሞክራያሲያዊ ስርአት ሁለት መሰረታዊ ሃሳቦችን የያዘ ሲሆን እነዚህም የህዝብ ልእልና (popular sovereignty) እና የህዝብ ተሳትፎን (participation) የሚጠይቅ የፖለቲካ ስርአት ነው፡፡
ብዙ የህግ እና የፖለቲካ ሳይንስ ጠበብቶች እንደሚያስረዱት እነዚህ ሁለት መሰረታዊ የዲክራሲያዊ ስርአት መለኪያዎች ለማረጋገጥ የመናገር ነፃነት የማይተካ ሚና አለው፡፡ በመሆኑም ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት ለአንድ ሃገር የዲሞክራሲም ይሁን ሁለንተናዊ እድገት እጅግ በጣም አስፈላጊ እና ተገቢ የሆነ የህግ ከለላ ሊሰጠው የሚገባ መሰረታዊ የሆነ የሰው ልጆች ነፃነት ነው፡፡
ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት በአለም አቀፍ የስብአዊ መብት ስምምነቶች ፈር ቀዳጅ በመሆን እውቅና የተሰጠው ሲሆን በበርካታ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች እውቅና የተሰጠው መብት ነው፡፡ ለምሳሌ ለመጥቀስ ያክል ሁለንተናዊ የሆነውን የአለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነት፡ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን እና የአፍሪካ የሰብአዊ መብቶች ቻርተር ሃሳብ የመግለፅ ነፃነትን በግልፅ ያስቀምጣሉ፡፡ ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው እነዚህ አለም አቀፍ እና ህጉራዊ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች በግልፅ እነደሚያሰቀምጡት ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት መሰረታዊ የሆነ የሰብአዊ መብት ሲሆን ለዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ወሳኝ ከሚባሉ ነፃነቶችም አንኳር የሆነ ነው፡፡
ነገር ግን በሰፊው እንደሚታወቀው ማንኛውም የሰብአዊ መብት በህግ የተቀመጡ አግባብ ያላቸው ገደቦች መቀመጣቸው ተገቢ ነው፡፡ በተመሳሳይ ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት ከሌሎች በተለየ ሁኔታ ጥበቃ የሚደረግለት መሰረታዊ የሆነ የሰው ልጀች ነፃነት ቢሆንም አግባብነት ያላቸው ገደቦች ሊቀመጡ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም አንድ ሃገር ፀጥታን ለማስጠበቅ፣ የሰዎችን መልካም ስም ለመጠበቅ፣ የህዝብን ሞራል እና ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል በህግ የተደነገጉ ገደቦችን ማስቀመጥ ተገቢ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ገደቦች ሃሳብ የመግለፅ ነፃነት ሊኖረው የሚችለውን ማህበራዊ፣ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች በተለይም ደግሞ በዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ላይ ያለውን የማይተካ ሚና ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆን ይኖርበታል፡፡
በመሆኑም በሃገራችን ኢትዮጵያ ያለውን ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት ገደቦች ስናይ በርካታ የሆኑ ገደቦች ያሉት ሲሆን ኢትዮጵያ ካፀደቀቻቸው ስምምነቶች፤ ከህገ መንግስቱ ድንጋጌዎችም ይሁን አሁን ካለው የብዙ ሃገሮች ልምድ እና ተሞክሮ ሲታይ ብዙ መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ በተለይም አሁን ካለው የሃገራችን የፖለቲካ ሪፎርም ፕሮግራም ጋር ተያይዞ ከሚጠይቀው የተሻለ የፖለቲካ ተሳትፎ፤ ኢትዮጵያ ካፀደቀቻቸው የሰብአዊ ስምነቶች ከሚጠይቁት ሃላፊነት አንፃር እና አሁን ካለው የብዙ ሃገራት አለም አቀፋዊ ልምድ ብዙ መሻሻል ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ ያሳያል፡፡ በመሆኑም የዚህ ፅሁፍ ዋና አላማም ሃሳብን የመግለፅ ነፃነትን አስመልክቶ በወንጀል ህጉ የተቀመጡ ገደቦች አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር በሚጣጣም መልኩ እና የዲሞክሪያሲ ግንባታ ሂደቱ ላይ የራሱን አስተዋፅኦ እንዲኖረው ለማድርግ ይችላል በሚል መሰረታዊ ሃሳብ የቀረበ ነው፡፡
ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት በህገ-መንግስቱ ያለው ይዘት
እንደሚታወቀው አስከፊው የደርግ ወታደራዊ ስርአት ወድቆ የዲሞክራሲያዊ እና የመድብለ ፓርቲ የፖለቲካ ስርአት ህገ መነግስታዊ መሰረት ካገኘበት ከ1987 ዓ/ም ጀምሮ አንኳር ከሚባሉት ጉዳዮች አንዱ የሰብአዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ህገመንግስታዊ እውቅና የተሰጣቸው መሆኑ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት ለሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ትኩረት እንደሰጠው ማሳያ ከሚሆኑትመ ጉዳዮች አንዱ 1/3ኛ የሚሆነው የህገመንግስቱ ድንጋጌዎች የሰብአዊ መብት እና የዴሞክራሲያዊ መብቶች ላይ መዋላቸው ነው፡፡ ህገ-መንግስቱ በርካታ የሰብአዊ እና የዲሞክራሲያ መብቶችን የሚሸፍን ሲሆን ሃሳብን በነፃ የመግለፅ መብት በህገ መንግስቱ አንቀጽ 29 ተደንግጎ እናገኘዋለን፡፡ አነቀፅ 29 ሃሳብ መግለፅ ነፃነትን እና የሚዲያ ነፃነትን በዝርዘር የሚያሰቀምጥ ሲሆን የመብቱን ገደብም በተመለከተ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ነጥቦችን ይዘረዝራል፡፡
ከላይ እንደተቀመጠው ለሃሳብ መግለፅ ነፃነት የተሰጠውን ከፍተኛ ቦታ የሚያሳይ ሲሆን በማንኛውም መመዘኛ ሲታይ ህገ-መንግስቱ አበረታች በሆነ መልኩ ጠንካራ ድንጋጌዎችን አስቀምጧል፡፡ ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት እና የሚዲያ ነፃነት ለዲሞክሪያሲ ስርኣት ግንባታ ያላቸውን ልዩ ቦታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ህገ-መንግስቱ የተለየ ከለላ እንደሚደረግለት ያስቀምጣል፡፡ ህገ- መንግስቱ በግልፅ እነደሚያስቀምጠው ማንኛውም ሰው ያለምንም ጣልቃ ገብነት ሃሳቡን የመግለፅ ነፃነት አለው፡፡ በተጨማሪም ህገ-መንግስቱ ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት እና የሚዲያ ነፃነትን አስመልክቶ ዝርዝር ጉዳዮችን የያዘ ሲሆን በተለይም ደግሞ የቅድሚያ ምርመራ (Prior Censorship) በማንኛውም መልኩ የተከለከለ እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡
የቅድመ ምርመራ በተለየ ሁኔታ በህገ-መንግስቱ አጽንኦት ተሰጥቶት የተቀመጠው በደርግ ወታደራዊ ስርአት የነበረው ሁኔታ ሲሆን የደርግ የሳንሱር መስሪያ ቤት ማንኛውም አይነት ህትመትን በጽህፈት ቤቱ ይሁኝታን ሳያገኝ እንደማይታተም የሚደረግበት ጊዜ እንደነበር የቅርብ ጊዜ የፖለቲካ ታሪካችን ነው፡፡ በመሆኑም ማንኛውም የህትመት ስራም ይሁን በሌላ መልኩ የሚወጣ ሃሳብ መንግስት ምንም አይነት ቅድመ ምርመራ እንደማይደረግበት እና ምንም አይነት ክልከላ እንደማየኖረው ያስቀምጣል፡፡
በመሆኑም የዚህ ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌ የሚያመለክተው በመርህ ደረጃ አንድ ሰው ወይም የሚዲያ ተቋም ምንም እንኳ የወንጀል ህጉን የሚተላለፍ ሀሳብ ቢያስተላልፍ በህግ ሊጠየቅ የሚችለው አቃቤ ህግ በሚያቀርበው የወንጀል ክስ ነው፡፡ ነገር ግን እጅግ በጣም በተለየ ሁኔታ አንድ የህትመት ወይም ሌላ ስራ የህዝብ ደህንነትን አደጋ ውስጥ የሚጥል እና ግልፅ እና ቅፅበታዊ አደጋ (Clear and Imminent danger) የሚያመጣ ሲሆን ክልከላው ተገቢ ይሆናል ብለው የሚከራከሩ የህግ ምሁራንም አሉ፡፡ በዚህ ረገድ የህገ-መንግስቱ ረቂቅ ግልፅ የሆነ አቋም እንደሌለ የሚያሳይ ቢሆንም የበርካታ የዲሞክሪያሳዊ ስርአትን የሚከተሉ ሃገራትንም ይሁን የአለም አቀፍ ሰብአዊ መብት መርሆዎችን ስናይ የቅድመ ክልከላ ከሃሳብ መግለፅ ነፃነት መሰረታዊ መርህ ጋር አብሮ የማይሄድ በመሆኑ ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት ላይ የሚደረጉ ገደቦች በወንጀል ህጉ በተቀመጡ ገደቦች ሰዎች ለሚያጠፏቸው ጥፋቶች እንዲጠየቁ ማድረጉ የተሻለ ይሆናል፡፡
የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት ከዚህ በተጨማሪ ዜጎች የህዝብን ጥቅም የሚመለከት መረጃን የማግኘት መብት እና በተለይ ደግሞ ሚዲያን በሚመለከት ለዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ የሚያበረክተውን ልዩ የሆነ አስተዋፅኦ ከግምት ውስጥ በማስገባት የተለየ የህግ ጥበቃ እንደሚደረግለት ያስቀምጣል፡፡ ከሁለም በላይ ደግሞ ብዙ ምሁራን የማያስተውሉት እና ለሃሳብ መግለፅ ነፃነት ከፍተኛ ቦታ መሰጠቱን የሚያሳየው የህገ መንግስቱ አንቀፅ 29 (6) እንደሚያስቀምጠው ሃሳብ የመግለፅ ነፃነት ገደብ ሊጣልበት የሚቸለው ሃሳብ የመግለፅ ነፃነት በአስተሳሰባዊ ይዘቱና ሊያስከትለው በሚችለው አስተሳሰባዊ ውጤት ሊገታ አይገባውም በሚል መርህ ላይ ተመስርተው በሚወጡ ህጎች ነው የሚለው ድንጋጌ ነው፡፡
ይህ ድንጋጌ እንደሚያስቀምጠው በመርህ ደረጃ ይዘትን መሰረት ያደረገ ክልከላ (content-based limitation) እንደማያስፈልግ እና በዋናነት ይዘትን መሰረት ያላደረጉ ክልከላዎች (content-neutral restrictions) መሆን እንዳለባቸው ያመለክታል፡፡ በመሆኑም ሃሳብን የመገለፅ ነፃነት ለዲሞክሪያሳዊ ስርአት ግንባታ ካለው የማይተካ ሚና አንፃር ይህ ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ እንደሚያሳየው እጅግ በጣም አስፈላጊ በሆነ ሁኔታ ካልሆነ በስተቀር በመርህ ደረጃ ገደብ ሊቀመጥበት እንደማይገባ ያስቀምጣል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሃሳብ ነፃነትን ለመገደብ የሚወጡ ህጎች ማለትም፣ አመፅ ማነሳሳት፡ ስም ማጥፋት፤ ዘርን ወይም ሃይማኖትን አስመልክቶ የሚደረጉ የጥላቻ ንግግሮች (hate speech) እና ሌሎችም ገደቦች በጠባቡ መተርጎም እንዳለባቸው ያመለክታል፡፡
ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት እና በወንጀል ህጉ ያላቸው ገደብና የማሻሻያ ሃሳቦች
- የሃገርን መልካም ስም እና የተቋማትን መልካም ስም ማጥፋት (Seditious Libel)
የተሻሻለው የወንጀል ህግ ትኩረት ሰጥቶ ካላያቸው ጉዳዮችና ሃሳብን የመግለፅ ነፃነትን በከፍተኛ ሁኔታ ከሚጎዱ ጉዳዮች አንዱ በወንጀል ህጉ አንቀፅ 244 የተቀመጠው ነው፡፡ የወንጀል ህጉ አንቀፅ 244 እንደሚያስቀምጠው ማንኛውም ሰው የመንግስትን ስም ያጠፋ፤ ያዋረደ እና የሰደበ ከሶስት ወር በማያንስ ቀላል እስራት እንደሚያስቀጣ ያስቀምጣል፡፡ ይህ ድንጋጌ በብዙ ሃገሮች የቀረና በህግ ቢኖርም እንኳ ተግባራዊ የማይደረግ ከአለም አቀፍም ይሁን ከአህጉራዊ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች እንዲሁም ከህገ-መንግስቱ አንቀፅ 29 መሰረታዊ ሃሳብ ጋር የሚጋጭ ድንጋጌ ነው፡፡ ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት ለዲሞክራሲያዊ ስርአት የማይተካ ሚና የሚጫወት በመሆኑ አንደዚህ አይነት ከጊዜው ጋር ያልተቃኙ የህግ ድንጋጌዎች እና አስተሳሰቦች መወገድ ይኖርባቸዋል፡፡
አንቀፅ 244 በተለይም እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው የሚባለውን የፖለቲካ ንግግርን (political speech) በከፍተኛ ሁኔታ የሚጎዳ ሲሆን አሁን ካለው አለም አቀፋዊ የህግ ተሞክሮ እንደሚያሳያው በርካታ ሃገሮች ከህግ ማእቀፋቸው ያስወጡት ገደብ ነው፡፡ የወንጀል ህጉ አንቀጽ 244 በመሰረተ ሃሳቡ እጅግ በጣም ግልፅነት የጎደለውና ትርጉሙ የሚያሻማ በመሆኑ መሰረታዊ የወንጀል ህግ መርህንም ይፃረራል፡፡ አንድ ሰው መቼ ነው የሃገርን ስም አጠፋ የሚባለው ብለን ብንጠይቅ ግልጽ የሆነ ትርጉም ማስቀመጥ አንችልም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የፍርድ ቤት መዝገቦች እንደሚያሳዩት የወንጀል ድርጊቱ አንድ ሃገር ላይ ያተኮረ ብቻ ሳይሆን የመንግስት ተቋሞችንም ያካትታል፡፡ ይህ ማለትም አንድን የመንግስት መስሪያ ቤት ወይም የህግ አውጭው፣ የህግ አስፈፃሚውም ይሁን የህግ ተርጓሚው በንግግር ተብጠልጥያለሁ ብሎ የህግ እርምጃ እንዲወሰድ ይፈቅዳል፡፡
ይህ በመሰረተ ሃሳቡ ዘውዳዊ ስርአቱ ጋር ቁርኝት ያለውና የዘውዱ ስርአት ወይም ንጉሱና የንጉሱ ቤተሰቦች መተቸት እንደሌለባቸው ከሚደነግገው የቀድሞው የወንጀል ህግ ጋር ቁርኝት ያለው ነው፡፡ የሃሳብ ነጻነትና ነፃ ሚዲያ አራተኛ የመንግስት አካል (fourth estate of government) ከሚያደርጉት ጉዳዮች ዋነኛው የመንግስት ብልሹ አሰራርና ሙስናን በማጋለጥ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለውን ህዝባዊ አገልግሎቱን እንዲወጣ ካስፈለገ የወንጀል ህጉ አንቀፅ 244 ሊወገድ ይገባል፡፡ በዲሞክራሲያዊ ስርአት የሚመራና የሃሳብ ነፃነት ገዢ የሆነበት ህገ-መንግስታዊ ስርአት መሰረት እንዲኖረው ካስፈለገ አላስፈላጊ እንደዚህ አይነት በዲሞክራሲያዊ ስርአት ተቀባይነት የሌላቸው ገደቦችም ሊወገዱ የገባል፡
1 አመፅ ማነሳሳት (Incitemnet)
ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት የሚገባውን ህገ-መንግስታዊ መሰረት በከፍተኛ ሁኔታ ከሚሸረሽሩ የወንጀል ድንጋጌዎች አንዱና በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት አመፅ ማነሳሳት የሚለው የወንጀል ድንጋጌ ነው፡፡ ይህ ድንጋጌ በወንጀል ህጉ እና በፀረ-ሽብር ህጉ የተቀመጠ ሲሆን በተለይ በቅርብ ጊዜ ከተፈፀሙት የፖለቲካ አፈናዎች ለመጠቀሚያ ካገለገሉ የህግ ማዕቀፎች አንደኛውና የሚዲያ ነፃነትን በከፍተኛ ደረጃ ከጎዱት ወንጀሎች አንዱ ነው፡፡
በተለይ ደግሞ የፀረ-ሽብር ህጉ በአንቀፅ 4 እና በአንቀፅ 6 ሽብር ማነሳሳትን እንደ ወንጀል ማስቀመጡ የሃሳብን ነፃነትና የሚዲያ ነፃነት እንዳይኖር ካደረጉት የህግ ተግዳሮቶች ዋነኛው ነው፡፡አመፅ ማነሳሳት ለሃሳብ መግለፅ ነፃነት አስቸጋሪና ውስብስ ከሚያደርጉት ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው ምክንያት በባህሪው ንግግርን ብቻ መሰረት በማድረግ የሚደረግ ወንጀል (Inchoate crime) በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ማለት አንድ ሰው በተግባር ምንም አይነት ይሁን የወንጀል ድርጊት ባይፈፅምም ሃሳቡ አመፅ ያነሳሳል በሚል ብቻ ለወንጀልና ለፍርድ በቂ ሊሆን ይችላል ማለት ነው፡፡ በመሆኑም አመፅ ማነሳሳት ከሌሎች የወንጀል አይነቶች ጋር ሲነፃፀር ሃሳብን የመገልለፅ ነፃነት በከፍተኛ ሁኔታ ሊጎዳ ስለሚችል እጅግ በጣም ጠባብ በሆነ የህግ ትርጉም ሊፈፀም የሚገባው ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አሁን ያለው የወንጀል ህግና የፀረ-ሽብር ህጉ መሻሻል ያለባቸውን ነጥቦች ቀጥሎ ለማቀረብ እሞራለሁ፡፡
የወንጀል ህጉን ስናይ በርካታ የሚባሉ አንቀፆች አመፅ ማነሳሳት እንደ ወንጀል የሚያስቀመጡ ሲሆን እነዚህም አንቀፅ 36 (ወንጀል እንዲፈፅም ማነሳሳት በሚል ጥቅል ድንጋጌውን የሚያስቀምጥ ሲሆን) ፡ አንቀፅ 269 እና አንቀፅ 274 የዘር ማጥፋት ወንጀልን ማነሳሳት (Incitement to genocide) ፡ አንቀፅ 332 ወታደራዊ ትእዛዞች እንዳይፈፀሙ ማነሳሳት እንዲሁም በአጠቃላይ የወንጀል ድርጊት እንዲፈፀም ማነሳሳት የሚከለክለውን የወንጀል ህጉ አንቀፅ 480 ማየት ተገቢ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የፀረ-ሽብር ህጉ አንቀፅ 4 እና አንቀፅ 6 ሽብር ማነሳሳት እንደ ወንጀል የሚያስቀምጥ ሲሆን ቅጣቱም ከፍተኛ የሚባል እና እስከ 20 አመት የሚያስፈርድ ወንጀል ነው፡፡ ንግግር በባህሪው ከሌሎች ወንጀሎች ተለይቶ የሚታይና ብዙ የእስራት ቅጣት ሊጣልበት የማይገባ ሆኖ እያለ እስከ 20 አመት የእስር ቅጣትን ማስቀመጥ ህጉ ለፖለቲካ ፍጆታ በከፍተኛ እንደዋለ የሚያሳይ ነው፡፡ ለምሳሌ የፀረ-ሽብር ህጉ የተወሰደበትን የእንግሊዝ የፀረ-ሽብር ህግ ስናይ ሽብር ማነሳሳት ከ 7 አመት በላይ የማያስቀጣ ወንጀል ነው፡፡
ከፍ ብለው የተቀመጡት አንቀፆች በግልፅ እንደሚያስቀምጡት አንድ የወንጀል ድርጊት በተግባር ሳይፈፀም ንግግርን ብቻ በማድረግ አንድ ሰው ወንጀለኛ ሊባል እንደሚችል ነው፡፡ ነገር ግን ህጎቹ በምን አይነት ሁኔታ አንድ ንግግር አመፅ አነሳሳ የሚባለው መቸ እና ምን ምን የህግ መስፈርቶች ሲሟሉ ነው የሚለውን ጉዳይ በገልፅ አያስቀምጥም፡፡ ፍርድ ቤቶችም ቢሆን ውሳኔወቻውን ሲያስተላልፉ ምንም አይነት የህግ መመዘኛወችን ስለማያስቀምጡ ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት በተገቢው ሁኔታ ከለላ አድይኖረው አድርገዋል፡፡
በተለይ ደግሞ የፀረ ሽብር ህጉ ሽብር ማነሳሳትን እንደ ወንጀል መቁጠሩና የዚህ ፅንስ ሃሳብና አለም አቀፋዊ ተሞክሮ እጅገ አዲስ እና ያልዳበረ በመሆኑ ህጉ ያለ አግባብ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን፤ ጋዜጠኞችንና የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲታሰሩና የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲጠብ ካደረጉ ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡፡ እነዚህ ህጎች መስተካከል የሚገባቸውና አሁን ካለው አለም አቀፍ ተሞክሮ እና የህግ እድገት አንፃር ተቃኘተው በሚዲያ ህጉ መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡ ይህን በማደረግ ረገድ አንዳንድ የማሻሻያ ነጥቦችን እንደማሳያ ማንሳት ይቻላል፡፡
ሀ) የፖለቲካ ንግግሮችንን በተለየ ሁኔታ ጥበቃ ማድረግ
በዲሞክራሲያዊ ስርአት የሚመራ ማንኛውም አይነት የፖለቲካ ስርአት የተለየ ትኩረት አድርጎ ጥበቃ የሚያደርግለት ተቋም ሚዲያና ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት ነው፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ በመቻቻል ላይ እና በሃሳብ ፉክክር የሚመራ ስርአት በመሆኑ በተለይ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን ንግግሮች ትኩረት ሰጥቶ ጥበቃ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ለ) የተናጋሪውን አላማ ለይቶ ማወቅ
ወንጀል በባህሪው ሰዎች አስበውና አቅደው የሚፈፅሙት ተግባር በመሆኑ ንግግሮች አመፅ ያነሳሳል ብሎ ለመወሰን ተናጋሪው ንግሩን ወይም ፅሁፉን ያስተላፈበት ሁኔታ አመፅን ለማነሳሳት አውቆ እና አስቦ መሆኑን ከንግግሩና ከአጠቃላይ ሁኔታ መረዳት የሚቻል መሆኑን ማወቅ አስፈላጊ ነው፡፡
ለ) የንግግሩን ባህሪ እና አጠቃለይ ሁኔታ (Context) ማየት
ንግግሮች አመጽ ያነሳሳሉ ብሎ ለመወሰን ተናጋሪው ንግሩን ወይም ፅሁፉን ያሰተላፈበት ሁኔታ ከንግግሩም ይሁን ከንግገሩ ጋር የሚያያዙ ሌሎች ጉዳዮች ለምሳሌ የነበረው የፀጥታ ሁኔታ፤ ንግግሩ ለየትኛው ኦዴንስ የተላለፈ መሆኑን፡ ተናጋሪው በማህበረሰቡ ያለው ተቀባይነት ወይም ታዋቂነትና የመሳሰሉትን ጉዳዮች ማየት ተገቢ ነው፡፡
ሐ) የንግግሩ ይዘት
አንድ ንግግር አመፅ ያነሳሳል ብሎ እንደ ወንጀል ለመቁጠር የንግሩን ይዘት በተገቢው መመርመር አስፈላጊ ነው፡፡ በመሆኑም በተለይ ንግግሩ ቀጥተኛ በሆነ ሁኔታ አመፅ ያነሳሳል ወይስ አያነሳሳም የሚለው ነጥብ አስፈላጊ ነው፡፡
ለምሳሌ ብዙ ይዘት የሌለው አይነት ንግግር እንደ ግደለው፡፣ ስበረው እና የመሳሰሉት አይነት በባህሪያቸው ድርጊት-መሪ ንግሮች (directive speech) መሆናቸውን ማየት አንድ ንግግር አመፅ ያነሳሳል ወይስ አያነሳሳም የሚለውን ፍሬ ነገር ለማወቅ ያስቸላል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ መታየት ያለበት ንግግሩ በቀጥታ አመፅና ብጥብጥ አንዲነሳ የሚያደርግ ሲሆን በተሻለ ሁኔታ መወሰን የሚቻል ሲሆን አስቸጋሪ የሚያደርገው ግን ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ አንድ ንግግር አመፅ የሚያስነሳ አይነት ንግግር ነው አይደለም የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ረገድ በተለይ እጅግ በጣም አስቸጋሪ የሆነው የሽብር ማነሳሳት (Incitemnt to terrorism) ወንጀል ሲሆን አለም አቀፋዊ ልምዱ እንደሚያሳየው ይህ ወንጅል ሊያስቀጣ የሚችለው ማነሳሰቱ በቀጥተኛ መንገድ የተላለፈ ሲሆን ነው፡፡
መ) አመፅ የመከሰቱ ሁኔታን ማየትና በምን ያህል ጊዜ እንደሚከሰት ማየት (Likelihood and Imminence of Harm)
አመፅ ማነሳሳት እንደወንጀል የተቀጠረው ንግግር ብቻውን በባህሪው ወንጀል ስለሆነ ሳይሆን ሊያመጣ በሚችለው ሰላምንና ፅጥታን የማደፍረስ አደጋን ነው፡፡ በመሆኑም አንድ ንግግር አመፅ ያነሳሳል ወይስ አያነሳሳም ብሎ ለመወሰን ንግግሩ ሊከሰት የሚችልበትን ሁኔታ ማየት ብቻ ሳይሆን ይህ ደግሞ በአጭር ጊዜ ሊከሰት የሚችል ፀጥታና ሰላም ማደፈረስ መኖሩን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ያለው ሚዛን የሚደፋው ተሞክሮ እንደሚያሳየው የተጋረጠው አደጋ ግልፅና የሚታይ (clear and present daneger) ከሆነ ብቻ አንድ ንግግር ወንጀል ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባው እነደሆነ ነው፡፡
በአጠቃላይ የኛ ፍርድ ቤቶች እነዚህን ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ ባለማስገባት በርካታ ፍርዶችን ያስተላለፉ ከመሆናቸው አንፃር የህግ ማአቀፉ በተወሰነ ደረጃ እነዚህን ነጥቦች ማካተቱ ህጉ አላግባብ እንዳይተረጎም ከማድረግ አኳያ አስፈላጊ ነው፡፡
3) ስም ማጥፋት
ስም ማጥፋት የዲሞክራሲያዊውን ስርአት በሚከተሉ ብዙ ሀገሮች ከወንጀል ህግ እየተወገደ ያለበት ሁኔታ ቢኖርም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሃገሮች አሁንም በወንጀል ህጋቸው ውስጥ አስቀምጠውት ይገኛል፡፡ አሁን ባለው አለም አቀፍ አሰራርም ይሁን የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎች ስም ማጥፋት እንደ ወንጀል መቆጠር የለበትም የሚለው ሃሳብ ሚዛን ይደፋል፡፡ በመሆኑም በሃገራችን ያለው የህግ ማእቀፍም ስም ማጥፋት ከወንጀል ህጉ በማስወጣት ሃሳብ የመግለፅ ነፃነትና የሚዲያ ነፃነት በተሻለ ሁኔታ ጥበቃ እንዲደረግልት የሚስችል ሁኔታን መፍጠር አንዱ አማራጭ ነው፡፡ በሃገራችን የወንጀል ህግ አንቀፅ 613 የስም ማጥፋት ወንጀልን ያስቀምጣል፡፡
በተለይ ህጉ እውነትን የሚያይበት እይታ ጠበቅ ያለ በመሆኑ ሰዎች የተሻለ ጥረት አድርገው እንኳ እወነተኛ ያልሆነ ሪፖርት ቢያወጡ ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ በመሆኑም የአለም አቀፋዊ ልምድ እንደሚያሳየው አንድ ጋዜጠኛ እውነቱን ለማረጋገጥ በቂ የሚባል ጥረት ካደረገ በህግ ተጠያቂ መሆን የለበትም የሚለው ነው፡፡ በመሆኑም የህግ መለኪያችን መሆን ያለበት አንድ ሰው የተናገረውን ነገር እውነተኛነት ለማወቅ ከፍተኛ ቸልተኝነትን (reckless disregard for the truth) ካላሳየ በስተቀር በህግ መጠየቅ የለበትም የሚል ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የፖለቲካ ንግሮችን አስምልክቶ የተለየ ጥበቃ መደረግ ያለበት መሆኑን በብዙ የዲሞክራሲያዊ ስርአትን የሚከተሉ ሃገራትና በአለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ሰነዶች ተቀባይነት ያገኘ ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ረገድ የተለይ ጥበቃ እንዲኖር የሚያስችል ህግ ሊኖር ይገባል፡፡
በተለይ ደግሞ የህዝብ ሃላፊነትን የሚወጡ የመንግስት ባለስልጣናት ህዝባዊ አገልግሎት እስከሰጡ ድረስ ለትችት መቅረብ እንዳለባቸው ግልፅ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ሊወሰድ የሚገባው ነጥብ አንድ ሰው በመንግስት ባለስልጣናት ላይ የሚሰነዝረው ትችት ሌላ መንግስታዊ ሃላፊነትን ከማይወጣ ሰው ጋር እኩል መታየት እንደሌለበት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ብዙ የፖለቲካ ንግግሮችና በአጠቃላይ በህዝባዊ ውይት የሚቀርቡ ሃሳቦች የአንድን ሰው አስተያየት (opinion) የሚያመለክቱ እንጂ አንድን ተጨባጭ የሆነ እውነታን በማስመለከት አይደልም፡፡ በመሆኑም እውነትን የምናየበት እይታ ከስም መጥፋት ጋር ተያዞ የሚያስፈለገው የህግ እይታ ሰፋ ማለት እንዳለበት ያሳያል፡፡
4) የሃሰት ወሬወችን ማሰራጨት
ከፍ ብለው ከተጠቀሱት የህግ ጉዳዮች በተጫማሪ በከፍተኛ ሁኔታ መታየት ያለበት ጉዳይ በወንጀል ህጉ አንቀፅ 43 (1) (ሀ) እና አንቀፅ 486 ሃሳተኛ ወሬዎችን ማሰራጨት ወንጀል ነው፡፡ ይህ የወንጀል ድንጋጌ በከፍተኛ ሁኔታ በርካታ ሰዎችን ለክስና ለእስራት ከዳረጉ ህጎች አንዱ ሲሆን የህግ ትርጉሙም በውሉ የማይታወቅ ነው፡፡ ከፍ ብሎ ለመግለፅ እንደተሞከረው በመጀመሪያ ሃሰትና እውነትን የምናይበት እይታ ተገቢ ስላልሆነ ሰዎች በመንግስትና በህዝብ አስተዳደር እንዲሁም በአጠቃላይ የሃገሪቱ የፖለቲካ ሂደት ላይ በሚሰጡት አስተያየት ምክንያት ብቻ በዚህ የወንጀል ህግ ተጠያቂ ተደርገዋል፡፡
በመሆኑም ብዙ የፖለቲካ ንግግሮች የሰዎችን አስተያት እንጂ ሃሰት ወይም እውነት ለማለት አስቸጋሪ ስለሚደረግ ገደቡ እጅግ በጣም ጠባብ በሆነ መልክ ሊተረጎም ይገባል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሃሰተኛ ወሬዎችን ማሰራጭት ለብቻው እንደወንጀል መታየት አለበት ወይ የሚለው በጣም አስፈላጊ ጥያቄ ነው፡፡ የብዙ ሃገራት ልምድ እንደሚያሳየው የሃሰት ወሬዎችን ማሰራጭት እንደወንጀል ሊያስቀጣ የሚችለው በአንድ ሃገር ላይ የፀጥታን መደፍረስ ወይም በግልፅ ሚታይ የህዝብን ሰላም የሚያውክና አመፅን የመቀስቀስ አቅም ሲኖር ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ የህግ ማእቀፍ ሃሰተኛ ወሬን ማሰራጭት እንደወንጀል መቆጠር ያለበት በዚህ የህግ አግባብ መሆን እንዳለበት በግልፅ ሊቀመጥ ይገባል፡፡ ይህ የህግ መሻሻል እጅጉን በጣም አስፈላጊ የሚያደርገው ደግሞ በርካታ የመብት ተሟጋቾችና የፖለቲካ አክቲቪሰቶች በዚህ የወንጀል ድንጋጌ አላግባብ በመታሰራቸው ነው፡፡
5 የጥላቻን ወሬ መሰራጨት
የህገ መንግስታዊ ስርአቱ የብሄር ብሄረሰቦችን መብት እንዲሁም ደግሞ በአጠቃላይ በበቂ ሁኔታ በፖለቲካ ስርአቱ በተገቢው ያልተወከሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን መብት መጠበቅ ፍላጎት ስላለ በብሄር ወይመ በሃይማኖት ላይ የሚደረግ የጥላቻ ንግግር ገደብ ማስቀመጡ ተገቢ ነው፡፡ በሃገራችን የወንጀል ህግ ከፍ ብሎ የተገለፀው አንቀፅ 486 እና አንቀፅ 816 አንድን ዘር ወይም ሃይማኖት አስመልክቶ የጥላቻ ንግግር ማድረግን ይከለክላል፡፡ ይህ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ በርካታ ብሄሮችና ብሄረሰቦች እንዲሁም ሃይማኖቶች ባሉበት ሃገር ላይ አስፈላጊ ቢሆንም ዝርዝር ጉዳዮችን ያልያዙ ድንጋጌዎች ባለመኖራቸው የጥላቻ ንግግር ምንና ምን ጉዳችን ያካትታል የሚለው መሰረታዊ ጥያቄ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ህጉ ግልፅነት ስለሌው እንደ መፍትሄ መወሰድ ያለበት የተለየ ህግ በዚህ ጉዳይ ላይ ቢወጣ ነው፡፡ የተለያዩ ሃገሮች ልምድ እንደሚያሳየው በዘር ወይም በሃይማኖት ላይ የሚደረግ የጥላቻ ንግግር በርካታ ውስብስ ጉዳዮች ስላሉበት እና በዚህ ጉዳይ ላይም ከፍተኛ ሃገራዊ ፋይዳ ያለው ጉዳይ በመሆኑ አንድ የተለየ ህግ ቢወጣ የተሻለ ያደርገዋል፡፡