You can paste your entire post in here, and yes it can get really really long.
አዲስ አበባ ትንሽዋ ኢትዮጵያ ነች፡፡ ለዚህም ነው በሰፈር ስያሜ እንኳን ወሎ ሰፈር፤ አደሬ ሰፈር፤ ጎጃም በረንዳ፤ ጅማ በር፤ ሱማሌ ተራ…ሲባል የምንሰማው፡፡ አዲስ አበባ የተለያዩ የኢትዮጵያውያን ባሕሎች ቤት ነች፡፡ ነገር ግን አዲስ አበባ እነዚህን የትዬሌሌ ባሕሎች ተቀብላ የምታስጎበኝ ሙዚየም አይደለችም፡፡ አዲስ አበባ የተለያዩ የኢትዮጵያን ባሕሎችን አገናኝታ፤ አቡክታ፤ ጋግራ ሌላ አዲስ የከተማ ባሕልን ፈጥራ የምታቀርብ መሶብ ነች፡፡ ይሄ አዲስ ባሕል ከብዙ ባሕሎች መስተጋብርነትም አልፎ ከዘመናዊነት፤ ከትምህርት ማዕከልነት፤ ከንግድ ማሳለጫነት ወዘተ የሚመነጭ የከተሜ ባሕል (urban culture) ነው፡፡ የከተማ ባህል ከአንድ ማንነት፤ ከአንድ ባሕል፤ ከአንድ ብሔር፤ ከአንድ ሃይማኖት በላይ የሆነ የውህደት እና የማሕበራዊ ድርድር (negotiation) ውጤት ነው፡፡ ዳኛቸው አሰፋ (ፒ.ኤች.ዲ) በአዲስ ዘይቤ ጋዜጣ ምርቃት ሥነ-ሥርዓት ላይ ባቀረቡት ንግግር የአዲስ አበባ ባሕል የድርድር ባሕል እንደሆነ ገልፀው፤ በተቃራኒው ደግሞ የገጠር ባሕል በጉልበት የማሸነፍ ልማድ እንዳለው አውስተው ነበር፡፡ ይሄ በጉልበት የማሸነፍ የገጠር ባሕል ፖለቲካውም ላይ እንዳጠላ ጠቆም አድርገው አልፈዋል፡፡ መቼም ይሄ ምልከታ ፖለቲካችንን ብቻ ሳይሆን ብዙ መስኮችንና ተቋማትን በድርድር ወ ድብድብ እሳቤ እንድንመረምር ይጋብዘናል፡፡ አዲስ አበባ ትንሽዋ ኢትዮጵያ ነች ስንል ግን በባሕል ብቻ እንዳልሆነ ግልፅ ነው፡፡ እንደዋና ከተማነቷ እንድምታቸው ግዙፍ የሆኑና የዘመናዊት ኢትየጵያን ዕጣ-ፈንታዎችን የወሰኑ አውራ ፖለቲካዊ ክስተቶችንም አስተናግዳለች፡፡ የነበላይ ዘለቀ የሞት ቅጣት፤ የነግርማሜ ነዋይ የመፈንቀለ-መንግስት ሙከራ፤ የታሕሳስ ግርግር፤ የ66ቱ አብዮትና የንጉሱ መወረድ፤ ቀይ ሽብር፤ ነጭ ሽብር፤ የኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት መፅድቅ፤ የድህረ-ምርጫ 97 አመፅና ግድያዎች…ሁሉ በአዲስ አበባ የሆኑ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው አውቶሞቢል በይፋ የተሸከረከረው አዲስ አበባ ላይ ነው፤ የመጀመሪያው ሲኒማ በአዲስ አበባ ነው የታየው፤ የመጀመሪያው ዩኒቨርሲቲ በአዲስ አበባ ነው የተከፈተው፡፡አዲስ አበባ የሳይንሱ፤ የምርምሩ፤ የንግዱ፤ የፖለቲካው፤ የዲፕሎማሲው ማዕከል ነች፡፡ የአትሌቲክሱ፤ የእግር ኳሱ፤ የሲኒማው፤ የቴአትሩ፤ የሙዚቃው፤ የስዕሉ፤ የጋዜጣው ማዕከል ነች፡፡ ይሄ ሁሉ የሆነው አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያውያን መሸሻ፤ ማደጊያ፤ መማሪያ፤ መሞከሪያ የተስፋ ከተማ ስለሆነች ነው፡፡ የትውልድና ማደጊያ ስፍራው ያልተመቸው፤ ያስጨነቀው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ሸሽቶ መጥቶ የሚያርፍባት፤ የሚሸሸግባት ከተማ ነች፡፡ ሕልሙ ትልቅ ሆኖ የተወለደባት ቦታ የጠበበችው፤ ያልበቃችው ሁሉ ተምሞ ሕልሙን የሚያሳካባት ከተማም ነች፡፡ አዲስ አበባ ሃዲስ አለማየሁን ከጎጃም፤ ፀጋዬ ገ/መድኀንን ከአምቦ፤ ስብሃት ገ/እግዚአብሔርን ከአድዋ፤ አሰፋ ጫቦን ከጋሞ፤ እሸቱ ጮሌን ከቦረና፤ ጥላሁን ገሰሰን ከወሊሶ…አሰባስባ ለኢትዮጵያ በሞላ እንዲተርፉ ያስቻለች ከተማ ነች፡፡አዲስ አበባ ለባላገሩ የምታስፈራራ (intimidating) ከተማ ነች፡፡ አዲስ አበባ ላይ ሕልሙን ያሳካው እንዳለ ሁሉ፤ አዲስ አበባ ላይ ተውጦ የተረሳ ብዙ ነው፡፡ አዲስ አበባ ላይ ሰርቶ ያተረፈ እንዳለ ሁሉ፤ አዲስ አበባ ላይ ሙልጭ ተደርጎ የተዘረፈ ብዙ ነው፡፡ አዲስ አበባ ላይ ፈክቶ ያብረቀረቀ እንዳለ ሁሉ፤ አዲስ አበባ ላይ የተሳቀበትም ብዙ ነው፡፡ ይኼም የትልቅ ከተማ ባህሪ ነው፡፡ አዲስ አበባ እንደመጣበት የገጠር ቀበሌ ስላልሆነችለት ቂም የያዘባት፤ ጥላቻ ያረገዘባት ብዙ ነው፡፡ እንደማንኛውም ትልቅ ከተማ አዲስ አበባም በባይተዋርነትና አለፍ ሲልም ደራሲ፤ ፖለቲከኛ፤ ነጋዴ፤ ምሁር፤ ወይም ጋዜጠኛ አትሆንም፡፡በማንኛውም መስክ የአዲስ አበባን ልብ ካላሸነፉ መላው ኢትዮጵያን ማሸነፍ በፍፁም አይቻልም፡፡ ፖለቲከኛም ሆነ ዘፋኝ፤ ጋዜጠኛም ሆነ ባለቅኔ የአዲስ አበባን ልብ ካልረታ አንድን አካባቢ፤ አንድን ብሔር፤ የአንድ ቋንቋ ተናጋሪዎችን ቢያሰልፍ እንጂ መላው ኢትዮጵያን ማሸነፍ አይችልም፡፡ እንዴትም ብናዟዙረው ምክንያቱ ግልፅ ነው፤ በሁሉም የማንነት ሰበዞች አዲስ አበባ የሁሉም ሕብርና የኢትዮጵያ ናሙና በመሆኗ ነው፡፡አዲስ አበባ ስለዋጠችው፤ ወይም ስላልተቀበለችው “ረጋግጫት አልፋለሁ” የሚል ኢትዮጵያንም እንደዛው አደርጋለሁ ማለቱ እንደሆነም ግልፅ ነው፡፡ የሚሳካም አይደለም፡፡ ወትውቶ ለመመረጥ መታገል፤ በሀሳብ ተከራክሮ በማሳመን ለመምራት መፍጨርጨር፤ ተናግሮ ለመማረክ መጣጣር፤ ፅፎ ለመነበብ መውተርተር፤ አስተዋውቆ ለመሸጥ መታተር የከተማ ግዴታዎች ናቸው፡፡ዳኛቸው አሰፋ እንዳሉት አዲስ አበቤ ለመሆን የመደራደር ዝግጁነት ያስፈልጋል፡፡ ስብሃት ገ/እግዚአብሔር አድዋን አምጥቼ አዲስ አበባ ውስጥ ካልተከልኩ ቢል አዲስ አበቤ አይሆንም ነበር፡፡ ፀጋዬ ገ/መድኅን አምቦን አዲስ አበባ ላይ ካላቆምኩ ቢል አዲስ አበቤ፤ ብሎም የኢትዮጵያ ልጅ አይሆንም ነበር፡፡ በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታላላቆቹ ኢትዮጵያውያን የያዙትን ሳይጥሉ የባሕል፤ የጥበብ፤ የፖለቲካ፤ የስነ-ልቦና፤ የኢኮኖሚ፤ የማሕበራዊ ድርድር አድርገው የኢትዮጵያ ጣዕም ላይ የራሳቸውን መጨመር፤ በኢትዮጵያ ገፅታ ላይ የራሳቸውን አሻራ ማኖር ችለዋል፡፡ የዚህ ልቡ ደግሞ አዲስ አበባ ነው፤ መንገዱም ረቂቅ ድርድር ነው፡፡