ሰኔ 7 ፣ 2014

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያገለገሉ የጤና ባለሙያዎች መንግስት የገባላቸውን ቃል ማጠፉን ገለጹ

City: Addis Ababaጤናኮቪድ 19ዜናወቅታዊ ጉዳዮች

በአማራ ክልል እስካሁን በማገልገል ላይ የሚገኙት የጤና ባለሙያዎች ከሰኔ 30 ጀምሮ የቅጥር ኮንትራታቸው እንደሚቋረጥ የሚገልፅ ደብዳቤ ደርሷቸዋል።

Avatar: Nigist Berta
ንግስት በርታ

ንግስት የአዲስ ዘይቤ ከፍተኛ ዘጋቢ እና የይዘት ፈጣሪ ስትሆን ፅሁፎችን የማጠናቀር ልምዷን በመጠቀም ተነባቢ ይዘት ያላቸውን ጽሁፎች ታሰናዳለች

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያገለገሉ የጤና ባለሙያዎች መንግስት የገባላቸውን ቃል ማጠፉን ገለጹ
Camera Icon

Credit: The Guardian

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ አስከፊ ነበረ በሚባልበት ወቅት ማለትም ከመጋቢት 2012 ጀምሮ በአማራ ክልል በኮንትራት ተቀጥረው ሲያገለግሉ የነበሩ የጤና ባለሙያዎች ላደረጉት አስተዋፅኦ በቋሚነት የቅጥር ሁኔታ እንደሚመቻችላቸው የተገባላቸው ቃል አለመፈፀሙን አሳወቁ። 

ቅሬታቸውን ያሰሙት አንዳንድ ባለሙያዎች ኮቪድ ከጀመረ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ በተለያዩ ሆስፒታሎች ሲያገለግሉ መቆየታቸውን በመግለጽ ፣ ከአንድ አመት በፊት የጤና ሚኒስቴር እና ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በቋሚነት ቅጥር እንደሚፈጸምላቸው በደብዳቤ ገልጸውላቸው እንደነበር አስታውሰዋል። 

ነገር ግን ከሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ የእነዚህ ሰራተኞች የኮንትራት ቅጥር እንደሚቋረጥ የሚገልፅ ደብዳቤ ከአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የጤና ጥበቃ ቢሮ በኩል እንደደደረሳቸው ገልፀዋል።

ንጉስ ሰለሞን የተባለ እና በደቡብ ወሎ ዞን በኮምቦልቻ አጠቃላይ ሆስፒታል በነርስነት እያገለገለ የሚገኝ ወጣት “የተደረገብን ነገር ግፍ ነው፣ የጤና ስራ ላይ የሚገኘውን ጥቅማጥቅም ሳንጠይቅ ለሁለት አመት ያህል ያገለገልነው ቢያንስ ቅጥሩ ይሟላልናል በሚል ተስፋ ነበር” በማለት ቅሬታውን ለአዲስ ዘይቤ አሰምቷል።

እንደንጉስ ገለጻ ከሆነ ባለሙያዎቹ በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ህዝብን ከማገልገል ባለፈ በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል በነበረው ጦርነት የጦር ቁስለኞችን በማከም ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን አልፈዋል። “ይሁን እንጂ ይሄ ምስጋና እንኳን ባያሰጠን እንዴት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ያስበትነናል” ሲልም ምሬቱን ይገልፃል። 

“በበሽታው አስከፊነት ምክንያት ከሰው ተገልለን፣ ከቤተሰብ ተለይተን ያለምንም ማወላወል ሕዝብ በምናገለግልበት ወቅት ነበር ጦርነቱ የተከሰተው፣ በዛ ሁኔታ ውስጥ የነበርንበትን አስቸጋሪ ሁኔታ መገመት አይከብድም፣ በብዙ ነገር ተጎድተናል ያገኘነው ምላሽ ደግሞ አንገት የሚያስደፋ ነው” የሚለው ንጉስ መፍትሄውን ከየት ማግኘት እንደሚቻል እሱም ሆነ ባልደረባዎቹ ግራ መጋባታቸውን ተናግሯል::

ሀምሌ 21 ቀን 2013 ዓ.ም የጤና ሚኒስቴር ለሁሉም የክልል መንግስታት ባስተላለፈው ደብዳቤ በፌደራል ደረጃ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በኮንትራት የተቀጠሩ ባለሙያዎችን ወደ ቋሚነት ለማዛወር የሚያዝ መመሪያ አያይዞ ልኮ ነበር።

በደብዳቤው ባለሙያዎቹ ለሀገር ባለውለታ መሆናቸውን በመጥቀስ በ2014 የበጀት አመት በፌደራል ደረጃ በየተቋማቱ ባለው ክፍት ቦታ እንዲመደቡ ለሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጥያቄ አቅርቦ፣ ባለሙያዎቹ ከሀምሌ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ቋሚ እንዲሆኑ መወሰኑን ገልጾ ነበር።

የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንም በበኩሉ በዛው ወቅት ሀምሌ 06 ቀን 2013 ዓ.ም በጤና ሚኒስቴር በኩል የቀረበለትን የቋሚ ቅጥር ጥያቄ አሳማኝ ሆኖ አግኝቼዋለሁ በማለት በተለያዩ የጤና ስራ መደቦች ላይ በኮንትራት ተቀጥረው እያገለገሉ ያሉ ባለሙያዎች በቋሚነት ቅጥር እንዲፈጸምላቸው ወስኖ አስተላልፏል። 

ይሁን እንጂ በአማራ ክልል የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች አመቱን በሙሉ ቅጥሩ ሳይፈጸም መቆየቱን አስመልክቶ ጉዳዩን ወደ ህግ ለመውሰድ እየተንቀሳቀሱ በነበሩበት ሰዓት የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የጤና ጥበቃ ቢሮ የኮንትራት መቋረጥን የሚያመላክት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ግንቦት 25 ቀን 2014 ዓ.ም ማውጣቱ ታውቋል።

ቢሮው በደብዳቤው እንዳያያዘው ወደ ፊት ከፌደራል ጤና ሚኒስቴር እና ከአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ የሚሰጠውን መልስ ታሳቢ በማድረግ ተለዋጭ ሁኔታ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል በመጥቀስ እስከዛው ግን ባለሙያዎቹ ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉ አሳስቧል።

ቅሬታችንን ህዝብ እንዲሰማልን እንፈልጋለን የሚሉት ጤና ባለሙያዎቹ “ላለፉት 11 ወራት ወደ ቋሚ ቅጥር አለመዘዋወራችን በራሱ ካሳ የሚያስፈልገው ጉዳይ ሆኖ ሳለ ይሄ መደገሙ ያሳዝናል” ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

በባህርዳር ፈለገ ዮርዳኖስ ሆስፒታል በጤና መኮንንነት በማገልገል ላይ የምትገኝ ስሟ እንዳይጠቀስ የፈለገች ባለሙያ በበኩሏ “ላለፉት ስድስት ወራት ገደማ ይሄን ቅሬታ ይዘን ያልረገጥነው ቢሮ የለም፣ ነገር ግን ዞን ስንሄድ ወደ ክልል ሂዱ ይሉናል ክልል ስንሄድ ወደ ዞናችሁ ሂዱ ይሉናል፣ ይሄ ይሄ ነው ብሎ በቀናነት የሚያስረዳ አካል እንኳን የለም” ትላለች።

እንደ ባለሙያዋ ገለፃ የተገባው ቃል ሊፈጸም ያልቻለበት ምክንያት ከበጀት እጥረት ጋር በተያያዘ መሆኑን በጭምጭምታ ይሰማል። ነገር ግን ይፋዊ የሆነ ምክንያት የሰጣቸው አካል የለም። “የበጀት ጉዳይ ቢሆን ራሱ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል እንጂ እኛን መበተኑ አማራጭ ሊሆን አይገባም፣ አመት ሙሉ ታግሰናል ይበቃናል” ብላለች። 

ይህ የጤና ባለሙያዎች ቋሚ ቅጥር ያለመፈጸም ችግር የሚስተዋለው በመላ ሀገሪቱ ሲሆን፣ በሌሎች ክልሎች ከኮንትራት መቋረጥ ጋር በተያያዘ ባለሙያዎቹ የደረሳቸው መረጃ አለመኖሩ ታውቋል። ይሁን እንጂ በቋሚነት ቅጥር ያለመፈጸሙ መፍትሄ እስካላገኘ ድረስ ባለሙያዎቹ ጉዳዩን ወደ ህግ እንደሚወስዱት ተናግረዋል።

ይሄ ዘገባ እስከወጣበት ሰዓት ድረስ ከዚህ ቅሬታ ጋር በተያያዘ የጤና ሚኒስቴር እና የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የጤና ጥበቃ ቢሮ ምላሽን ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ ያልተሳካ ሲሆን፣ ምላሹን እንዳገኘን ከማብራሪያ ጋር የምናቀርብ መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን።

አስተያየት