ግንቦት 18 ፣ 2013

ቅድስት ማርያም አካባቢ ትላንት የሆነው ምንድነው?

ወቅታዊ ጉዳዮችዜናዎች

ግንቦት 17 ቀን 2013 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ዓመታዊ ጉባኤ የመክፈቻ መርሀ ግብር ላይ ማኅበሩ ሃሳቡን ለማቅረብ እንደተገኘ በአከባቢው የተገኙ ምእመናን ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

ቅድስት ማርያም አካባቢ ትላንት የሆነው ምንድነው?

በትላንትናው እለት በመንበረ ፓትሪያሪክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ውስጥ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊያን ወጣቶች እና ጎልማሶች ማኅበራት ሕብረት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አስር ጥያቄዎች ተጠይቀዋል። 

ግንቦት 17 ቀን 2013 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ዓመታዊ ጉባኤ የመክፈቻ መርሀ ግብር ላይ ማኅበሩ ሃሳቡን ለማቅረብ እንደተገኘ በአከባቢው የተገኙ ምእመናን ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። የእምነቱ ተከታዮች ጥያቄያቸውን ለማቅረብ እና ድጋፍ ለመስጠት ወደ ቤተ ክርስቲያኗ ቅጥር ግቢ ከረፋድ ጀምሮ መሰብሰባቸውን ጠቅሰው ከተወሰኑ የማኅበሩ አባላት ውጪ ምእመኑ በጸጥታ ኃይሎች ለመግባት ክልከላ ስለተደረገበት ከደጃፍ ለመቆም መገደዳቸውን ሰምተናል፡፡

''ከስራ ወጥቼ ከቀትር በኋላ ስለመጣው መግባት አልቻልኩም፤ ለምን እንደተከለከልኩ አላወኩም፤ ነገር ግን ጉባኤው እስከሚገባደድ እጠብቃለው'' ያሉን ከቤተ ክርስቲያኒቱ አጥር ግቢ ፊትለፊት ለንግድ ቤቶች መወጣጫ የተሰራ ደረጃ ላይ ነጠላቸውን ለብሰው የተቀመጡ እናት ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት በማኅበራቱ የሚጠየቁትን ሀሳቦች ለመደገፍ ከሌሎች ሰዎች ጋር ሰብሰብ ብለው በማኅበር መምጣታቸውን፣ መግባት እንደማይችሉ ሲነገራቸው መንፈሳዊ ዝማሬ እየዘመሩ እንደነበር እና በጸጥታ ኃይሎች መበተናቸውን ነው። 

''አብረውኝ የመጡት ሰዎች የት እንዳሉ አላውቅም፤ ሁላችንም ከጸጥታ አካላት ለማምለጥ እየሮጥን ስለነበር ተበታትነናል፤ እኔም ነገሩ ሲበርድ ተመልሼ መጣሁ፤ ይህን የማደርገው ለሀይማኖቴ እና ለሀይማኖቴ መሪ ይጠቅማል ብዬ ስለማስብ ነው'' ብለዋል።

በቤተክርስቲያኑ ዙሪያ የጸጥታ ኃይሎች፣ የተለያዩ ጽሑፎች የተጻፈበት ባነር የያዙ ቀሳውስት እና ነጠላ የለበሱ ሰዎች እስከ አመሻሹ 11 ሰዓት የመኪና እንቅስቃሴ በሌለበት መንገድ ላይ ገሚሱ ቆሞ ውስጥ የሚካሄደውን የጸሎት መርሃግብር እየተከታተለ የተቀረው አከባቢው በሚገኝ ስፍራ ላይ ወገቡን አሳርፎ ይጠባበቅ ጀመር።

ከአመሻሹ 11 ሰዓት በኋላ የተለመደው የመኪና እና የእግረኛ እንቅስቃሴ ተስተዋለ፤ የጸሎቱ ሂደት እና የጥያቄ አቅራቢዎቹ መጠባበቅም ቀጠለ። ለሰዓታት ያህል የእምነቱ ተከታዮች የቆዩበት ''ውሳኔ እንዲሰጥበት'' ያሉት ሀሳብ እና ጥያቄ ከአመሻሹ 12 ሰአት አከባቢ ከቤተክርስቲያኗ ቅጥር ጊቢ አልፎ በደጃፉ ዙሪያ ላለው ሕብረተሰብ በሚሰማ መልኩ ከፍ ባለ ድምጽ ቀረበ።    

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊያን ወጣቶች እና ጎልማሶች ማኅበራት ሕብረት 10 ጥያቄዎች ቀረቡ፤ ጥያቄዎቹ መካከል፡-

  • ቅዱስ ፓትሪያሪክ ብጹእ አቡነ ማቲያስ ላይ ክብረ-ነክ ንግግሮች የሚናገሩ አካላት፣ በእርሳቸው ላይ የሚደረግ ፖለቲካዊ እና አስተዳደራዊ ጫና፣ ፓትሪያሪኩን ከመንበረ ሥልጣናቸው ለማንሳት እና ቤተክርስቲያንን ዳግም ለመሰንጠቅ የሚሞክሩ አካላት በቅዱስ ሲኖዶስ እርምጃ እንዲወሰድ እንዲሁም መንግሥት እጁን ከቤተክርስቲያን ላይ እንዲያነሳ፤
  • የሲኖዶስ ጸሐፊ ብጹእ አቡነ ዮሴፍ ከቤተ ክርስቲያን ከተሰጣቸው ሥልጣን እና ኃላፊነት በመተላለፍ ሊቃነ ጳጳሱን በመቃወማቸው ኢ-ቀኖናዊ ድርጊታቸውን በማውገዝ ከጸሐፊነት እንዲነሱ፤
  • በመላው ሃገሪቱ በእምነቱ ተከታዮች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ችግር የሚያጣራ ኮሚቴ ተቋቁሞ እንዲታይ፣ መንግሥትም ጥቃቱን እንዲያስቆም፣ ይቅርታ እንዲጠይቅ፣ ካሳ እንዲከፍል እና መንግሥት ይህን የማያከብር ከሆነ ከዓለም አቀፍ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተሟጋቾች ጋር በመቆም ማኅበሩ መብቱን እንደሚጠይቅ እንዲሁም በሀይማኖታቸው ምክንያት ለሞቱ ሰማዕታት ሐውልት እንዲቆምላቸው፤
  • በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ፣ ጃንሜዳ እና በክልሎች ቤተ ክርስቲያኗ በይዞታነት የምትገለገልባቸውን ቦታዎች የይዞታ ማረጋገጫ እንዲሰጥ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ለመንግሥት ጥያቄውን በይፋ እንዲያቀርብ፤
  • ከመስቀል አደባባይ ጋር በተያያዘ ብጹእ አቡነ ያሬድ ለከንቲባ ጽ/ቤት የጻፉትን ደብዳቤ በመጻረር የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ዋና ስራ አስኪያጅ እና የካህናት መምሪያ ኃላፊ ለፈጸሙት ተግባር ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ እና ምርመራ እንዲደረግባቸው፤ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት 'መስቀል አደባባይ' የሚለውን ስያሜ 'አቢዮት አደባባይ' በሚል ለመቀየር የተደረገው አካሄድ ምክር ቤቱ ተገቢውን እርምት እንዲያደርግ ሲኖዶሱ እንዲያወግዝ ማኅበሩ አሳስቧል።
  • እንዲሁም ኢቢኤስ የቴሌቪዥን ጣቢያ ኦርቶዶክሳዊ ዶግማ፣ ቀኖና፣ ትውፊት፣ እሴት እና ማንነት ላይ የተቃረነ ሥራ በመስራቱ ከዚህ ቀደምም ይቅርታ እንዲጠቅ ተጠይቆ ፍቃደኛ ባለመሆኑ ቤተክርስቲያኗ ያላትን ግንኙነት እንድታቆም፣ በመጨረሻም የምእመናን ድርሻ እና መብት እንዲከበር ጥያቄ ቀርቧል።

ከ15 ቀናት በፊት ብጹእ አቡነ ማቲያስ ''ሀሳቤን እንዳላስተላልፍ ድምጼ ታፍኗል'' ብለው ሀሳባቸውን በቪድዮ መተላለፉን ተከትሎ የሲኖዶሱ ጸሐፊ ብጹእ አቡነ ዮሴፍ የፓትሪያሪኩ ንግግር ቤተክርስቲያኒቱን እንደማይወክል እንዲሁም ሀሳቡ የግላቸው መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል።

አስተያየት