ኅዳር 13 ፣ 2011

የህዝብ ት/ቤቶች ወዴት አሉ ?

ወቅታዊ ጉዳዮች

የአዲስ ዘይቤ ባልደረባ የሆነው ዳዊት ዓለሙ ለተማሪዎች እንደ አንድ አማራጭ ሆነው ያገለግሉ የነበሩትን በመዲናዋ የተመናመኑትን የህዝብ ትምህርት ቤቶች ወዴት…

የህዝብ ት/ቤቶች ወዴት አሉ ?
የአዲስ ዘይቤ ባልደረባ የሆነው ዳዊት ዓለሙ ለተማሪዎች እንደ አንድ አማራጭ ሆነው ያገለግሉ የነበሩትን በመዲናዋ የተመናመኑትን የህዝብ ትምህርት ቤቶች ወዴት አሉ እያለ ይጠይቃል።በኢትዮጵያ እንዲህ እንዳሁኑ የግል ት/ቤቶች እንደአሸን ከመፍላታቸው በፊት የህዝብ ት/ቤቶች በዘርፉ የነበራቸው የማይተካ ሚና በቀላል የሚታይ አልነበረም። ካለፉት ጥቂት አመታት ወዲህ ግን የህዝብ ት/ቤቶች ቁጥር ማሽቆልቆልና ተገቢውን ትኩረት አለመሰጠታቸው አንደኛ ተወዳዳሪና ብቁ ተማሪዎች እንዲፈጠሩ ካለማድረጉ በላይ መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ወላጆች ከግምት ያላስገባ፤ ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር የሚችሉ ተቋማት እንዳይፈጠሩ እንዲሁም ከንግድ ትርፍ ይልቅ ብቁ ዜጋን ከማፍራት አንፃር የሚታየውን ክፍተት በመሙላት ደረጃ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ጥርጥር የለውም።ሐሙስ፣ ህዳር 6 2011 ዓ.ም የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት አግባብነት ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች በ2010 ያስመዘገቡት ውጤትና ደረጃቸውን ይፋ አድርጓል። በዚህም መሰረት ክትትልና ምርመራ ከተደረገባቸው 1407 ትምህርተ ተቋማት ውስጥ 1106 የሚሆኑት ደረጃ-1 እና ደረጃ- 2 መሆናቸውን አስታውቋል። ደረጃ-1 ከ 50 በመቶ በታች ውጤት ያስመዘገቡና ከደረጃ በታች የሆኑ ማለት ሲሆን ለምሳሌ ተቋማቱ ማሟላት የሚገባቸው መሰረተ ልማት፤ የመጫወቻ ሜዳዎች እንዲሁም የትምህርት መማሪያ ግብዓቶችን ያላሟሉ ናቸው። ደረጃ-2 የተሰጣቸው ከ50-69.9 በመቶ ያስመዘገቡና በአንድ አመት ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው፤ ድጋፍ ቢደረግላቸው ደግሞ መሻሻል የሚችሉ እንደሆነ ታምኖባቸው በጊዜ ገደብ ውስጥ ያሉት ናቸው ወይም በሂደት ራሳቸውን ማሻሻል የሚችሉ ተብሎ የታመነባቸው ።የምርመራ ሰነዱ እንደሚያመለክተው በአዲስ አበባ የተገኘው ውጤት 301 ትምህር ቤቶች ብቻ ደረጃ 3 (ከ70- 90) ውጤት ብቁ ተብለው የተመሰከረላቸው ናቸው። በከተማይቱ ውስጥ ካሉት 1407 ትምህርት ተቋመት ውጤታማ ናቸው የተባሉት እነዚህ ት/ቤቶች የተሟላ የቤተ ሙከራ ፤ ቤተ መጽሀፍትና ኮምፒውተሮች በሚፈለገው ደረጃ አለመሟላታቸው፤ ደረጃ-4 እንዳያስመዘግቡ በሀገሪቱ ለሚታየው የትምህርት ጥራት መጓደል፤የተማሪዎችና መምህራን ድክመት ማሳያ ነው።ሌላው ሊተኮርበት የሚገባው ጉዳይ ደረጃው ይፋ ሲደረግ ያካተተው የመንግስትና የግል የትምህርት ተቋማት ብቻ መሆኑ በህዝብ የሚተደዳደሩትን ከግምት ያላስገባና ምሉዕ እንዳልሆነ እንዲሁም በህዝብ ት/ቤቶች የሚታየውን የአሰራር ብልሹነት የሚያሳይ እንደሆነ ለመረዳት ይቻላል።የህዝብ ት/ቤቶችና የመንግስት ጣልቃ ገብነትከላይ ለተገለፀው ክፍተት ማሳያ እንዲሆን በአዲስ አበባ ከሚገኙትና በህዝብ ከሚተዳደሩት ተቋማት የአሳይ ት/ቤትን መጥቀስ ይቻላል። እንደሚታወቀው በ200 ዓ.ም ከአንድ መቶ የሚበልጡ የግል ትምህርት ቤቶች ራሳችን ማስተዳደር አልቻልንም በማለት በመንግስት ማእቀፍ ውስጥ እንሁን በማለት ጥያቄ አቅርበው ከአሳይ እና አባድር ት/ቤቶች በስተቀር ሁሉም በመንግስት እንዲተዳደሩ ተደንግጓል።እንደ ትምህርት ሚኒስተር አዋጅ ቁጥር 260/1984 መሰረት ማንኛውም የህዝብ ት/ቤት ከትምህርት ቁሳቁስ ውጪ አስተዳደርና ቅጥር ላይ የመንግስት ጣልቃ ገብነት እንደማይኖር ቢገልጽም ‹‹The rights and obligations of public schools, Committees established under Proclamation No. 260/1984 are pursuant to directives to be issued, transferred to the appropriate organs referred to in Article 3 of this Proclamation.>> በአሳይ ያሉት ከፍተኛ የአስተዳደር ሹማምት ግን በመንግስት እንደተሾሙ የት/ቤቱ መምህር ኃ/ ገብርኤል መላኩ ለመገናኛ ብዙሃን በላኩት ደብዳቤ ይገልፃሉ።አዲስ ዘይቤም ይሄን ጥያቄ ለት/ቤቱ ርእሰ መምህር ታደሰ አርአያ አቅርባ ነበር። “ሃላፊነቱን ያገኘሁት ባለኝ የትምህርት ዝግጅትና ብቃት እንጂ በመንግስት ሹመት አይደለም።” ቢሉም የአጠቃላይ የትምህርት ጥራትና አግባብነት ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ም/ዋና ዳይሬክተር ፍቅርተ አበራ አገላለጽ ሹመቱ በመንግስት እንደሆነ ይገልጻሉ። የምርመራ ቡድኑም ይሄን እንዳላረጋገጠና ወደፊት ግን እንደሚሰራበት የገለፁት ደግሞ ዋና ዳይሬክተሯ ብሩክነሽ አርጋው ናቸው። በዚህ አንጻር መምህሩ እንዳስቀመጡት ነፃና ገለልተኛ አይደለም ማለት ያስደፍራል።የመምህራንና ተማሪዎች ብቃትከተዘነጉት የህዝብ ት/ቤቶች በተጨማሪ በትምህርት ዘርፉ የሚታየው የመምህራንና የተማሪዎች ብቃት ማነስ ይጠቀሳል። የአጠቃላይ የትምህርት ጥራትና አግባብ ተቆጣጣሪ ከኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን የተሰራው ጥናት እንደሚያመለክተው የተማሪዎች ደካማነት ከቅድመ መደበኛ (ኬጂ) እየተጠራቀመ የመጣ ሲሆን መደበኛ ላይ የደረሱ ተማሪዎች በተለይ የ7ኛ እና 8ኛ ክፍል ተማሪዎች ባይማሩ ምንም ነገር እንደማያጡ አድርገው ማሰባቸው ለችግሮቹ መንስኤ እንደሆኑ የጥናቱ አስባባሪ ዶ/ር ኢላዛር ታደሰ ይናገራሉ።በአቃቂ አድቬንቲስት መሰናዶ ት/ቤት መምህር የሆኑት አበበ አባዲ በበኩላቸው በኬ-ጂ ደረጃ ያሉት መምህራን የማስተማር ክህሎታቸው ዝቅተኛ የሆነና ወደ መምህርነት ዘርፍ የሚገቡትም ውጤታቸው ዝቅተኛ የሆኑት በመሆናቸው፤ በስራቸው ያሉትም ተማሪዎች ደካማ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ምክንያት ናቸው ይላሉ።“እኛ ጥናቱን ማቅረብ እንጂ ማስፈጸም አንችልም፤ የስርአተ ትምህርቱ መፈተሸና መሻሻል አለበት። በጥናታችን አዲስ ችግር አግኝተናል። ይኸውም የ8ኛ ተማሪዎች ዝቅተኛ ውጤት ማስመዝገብ የሚመነጨው በስርዓተ ትምህረቱ ውስጥ የ7 እና 8ኛ ክፍልን መሰረት ያደረገ ስልጠና ባለመኖሩና ለነዚህ ክፍሎች የሚመደቡት የ9 እና 10ኛ ክፍል መምህራን በመሆናቸው በማህበራዊ ሳይንስ ወጤታማ ቢሆኑም በአካባቢ ሳይንስ (ኢንቫይሮመንታል ሳይንስ) ግን ዝቅተኛ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፤ በተጨማሪም ተማሪዎች የሚያገኙት እውቀት (የትምህርት አሰጣጡ) ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ ይከብዳቸዋል።” ሲሉ ዶ/ር ኢላዛር ይገልጻሉ።እንደ መምህር አበበ እና የስራ ባልደረቦቻቸው አገላለጽ ከሆነ ሌላው ጉዳይ ለመምህራን የሚከፈለው ገንዘብ ዝቅተኛ መሆን በኃላፊነት እንዳያስተምሩና ጥረት እንዳያደርጉ ማነቆ ሆኖባቸዋል። ተመጣጣኝ ክፍያ መኖሩ ሰዎች በሃላፊነት እንዲያስተምሩና ይሄን ዘርፍ በፍላጎት እንዲማሩ ይረዳቸዋል በማለት ጥናቱ የመምህራኑን ሀሳብ ያጠናክራል።አስተያየት ሰጪ ወላጆች በበኩላቸው የመንግስትና የግል ት/ቤቶች ብቻ መኖራቸው መካከለኛ ገቢ ያለውን የህብረተሰብ ክፍል ከግምት ያላስገባና ፤ ከአቅማቸው በላይ ለትምህርት ክፍያ በማውጣት እንደሚማረሩ ይገልፃሉ። ለዚህም ባለፈው የአዲስ ዘይቤ እትም ላይ ወላጆች የሚያወጡትን ከፍተኛ ወጪ መጥቀስ በቂ ነው። ( ህዳር 1/ 2011፤ ትምህር ቤት አምድ፤በታምሩ ሁሊሶ ፤የወላጅ አበሳ) ይመልከቱ።የእነዚህ ውጤቶች ድምር መምህራን ሀላፊነታቸውን እንዳይወጡ ሲያደርጋቸው ተማሪዎች ደግሞ ብልሹ ሥነ ምግባር እንዲያንጸባርቁ በር ይከፍታል። የትምህርት ተቋማቱ አስተዳደሮች በበኩላቸው ንግዳቸው ኪሳራ ላይ እንዳይወድቅ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚያመነቱ መምህራን ይናገራሉ። ነገር ግን ጠንካራ የሚባሉ ት/ቤቶች እንዳሉ ታሳቢ ማድረግ ይገባል ።ጠንካራ የሆነ ቁጥጥርና ክትትልበአጠቃላይ የትምህርት ጥራትና አግባብ ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ሃላፊነቶች ውስጥ ምርመራና ክትትል በማድረግ ላሳዩት ብቃት የሚገባቸውን ደረጃ መስጠት ነው። ከዚህ አንጻር ምርመራ የሚደረግባቸው በተለይ የግልና የህዝብ ትምህርት ቤቶች ላይ ተገቢውን ቁጥጥር እንደማይደረግ መምህራን ይናገራሉ።የኤጀንሲው ሰራተኞች ልጆች የሚማሩባቸው ተቋማት አስፈላጊውን መስፈርት ሳያማሉ አሊያም ከሌሎች ት/ቤቶች (ከመንግስት ት/ቤቶች ወይም ከሌላኛው ቅርንጫፍ) ሌሊት እየተጓጓዙ ምርመራውን እንደሚያልፉ ይናገራሉ። ዋና ዳይሬክተሯ ወ/ሮ ብሩክነሽ እንደዚሀ አይነት ሀሳቦች እንደሚነሱና ተደጋጋሚ ምርመራ ሲደረግ ያላሟሉትን በማስጠንቀቂያ እንዲሰሩ ለሚቀጥለው የት/ት ዘመን ማሻሸሻያ እንዲያደርጉ ትእዛዝ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።ኤጀንሲው ብቃትቸው የተመሰከረላቸው ትምህርት ቤቶችን ሲዘረዝር ደረጃ- 3 የተሰጣቸው የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 21.3 በመቶ እንደሚይዙ ወይም 299 መሆናቸውና 2 ሁለተኛ ደረጃ የግል ት/ቤቶች ብቻ ደረጃ -4 ማግኘታቸው ጠንካራ የሆነ ቁጥጥር ካለመኖሩ በተጨማሪ የተማሪዎች ብቃት ላይ ጥያቄ እንዲነሳ ያደርጋል።ወላጆች ልጆቻቸውን ከፍተኛ ክፍያ የሚጠይቁ ት/ቤቶች ማስገባታቸውን፤ አስጠኚ መቅጠራቸው በራሱ በቂ የሚመስላቸው ሲሆን ነገር ግን አስፈላጊውን ቁጥጥር አለማድረጋቸው በትምህርት ቤቱ ከሚታየው የጥራት ማነስ በተጨማሪ ተማሪዎቹ ላይ ለሚታየው ደካማነት ድርሻ እንዳለው መምህራን ይናገራሉ።በቅርቡ የትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ስልጠና ጥራትና ብቃት ለማሻሻል እንዲሁም ተወዳዳሪነትን ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ ከባለድርሻ አካላት ጋር ‹በትምህርት ፍኖተ ካርታው› ላይ ውይይት በማድረግ ላይ እንደሆነ ይታወቃል። ስለዚህ ከላይ የታዩትን ችግሮች ከግምት ያስገባ ከሆነ የትምህርት ጥራትን ስኬታማ ማድረግ ይቻላል።

አስተያየት