ኅዳር 13 ፣ 2011

ፕሬዝዳንታዊ ስርዓት ችግሩን ይፈታው ይሆን?

ፖለቲካ

የማኀበረሰባዊ ፖሊሲ አስተዳደርና ህግ ተማሪ የሆነው ዘሪሁን አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በፕሬዝዳንታዊ የመንግሥት አወቃቀር ላይ ብዙ ተስፋ…

ፕሬዝዳንታዊ ስርዓት ችግሩን ይፈታው ይሆን?
የማኀበረሰባዊ ፖሊሲ አስተዳደርና ህግ ተማሪ የሆነው ዘሪሁን አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በፕሬዝዳንታዊ የመንግሥት አወቃቀር ላይ ብዙ ተስፋ ማሳደራቸው እና እንደ ችግር ፈቺ መመልከታቸው ያለውን ስህተት ለማሳየት ይሞክራል፡፡የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተስፋጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ በተደጋጋሚ በሚያደርጓቸው ንግግሮችና ገለጻዎች የፓርላሜንታዊው ስርዓት ስራዎችን አላሰራ እንዳላቸውና የካቢኔ ምርጫቸው ላይ ጭምር ከፍተኛ ጫና በማድረጉ ፈጣን ለውጥ ለማምጣት እንዳላስቻላቸው ወይም እክል እንደሆነባቸው ይናገራሉ፡፡ ፕሬዘዳንታዊ ስርዓት ቢሆን የተሻለ ነፃነት ይኖራቸው እንደ ነበር ባለፈው ሳምንት ንግግራቸው ጭምር ገልጸዋል፡፡ ይህ እጅግ በጣም ስህተትና ከጥናታዊ ግኝቶች ጋር ብሎም ከዓለም አቀፍ ተሞክሮ ጋር የሚቃረን ነው፡፡ ቁም ነገሩ የፓርላሜንታው ስርዓት ሳይሆን የኢህአዴግ አሰራርና አወቃቀር ከሰፈነው የዘውግ/ብሔር ስርዓት ጋር የተያያዘ ጉዳይ በመሆኑ ነው፡፡ይህም በአራቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችና አጋር ፓርቲዎች የድርጅት ኮታንና የብሔር ስብጥርን ማዕከል ያደረገ የስልጣን አሰያየምና አመዳደብ ከፌደራዊው ስርዓት ጋር አቆራኝቶ የሚከተል በመሆኑ ነው፡፡ ማንም ኢህአዴግን የሚያውቅ እንደሚረዳው አራቱ ድርጅቶች በዋናነት ኮታ በመከፋፈል የተለያዪ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን የሚኒስቴርነትና ልዩ ልዩ የኃላፊነት እርከኖች እስከ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የቀበሌ መስተዳድር ድረስ ያሉ የካቢኔ ሹመቶችን በዚሁ አሰራር የሚወስን መሆኑ ነው፡፡ የጠ/ሚኒስትሩ አነጋገር ፕሬዘዳንታዊ ስርዓት ቢሆን የተሻለ ብቃት ያላቸውንና አላማዬን ያስፈፅሙልኛል የምላቸውን እመርጥ ነበር የሚል ሙግት ለመፍጠር የቀረበ አመክንዮ ይመስላል፡፡ ነገር ግን ፓርላሜንታዊው ስርዓት በራሱ የዚህ ችግር መንስኤ ሳይሆን ይባስ የዚሁ የኢህአዴግ አብዮታዊ ዴሞክራሲ እና የዴሞክራሲ ማዕከላዊነት ማስፈፀሚያ መሣሪያ ሰለባ በመሆኑ ሙሉ አሰራሩ ሊተገበር አለመቻሉ ነው፡፡ ይልቁንም በሌሎች ተመሳሳይ ስርዓትን በሚከተሉ ሀገራት ብቃትና ችሎታው ባላቸው የፓርቲ ሰዎች የኃላፊነት ቦታዎች ሲሸፈኑ በግልጽ የሚስተዋል ነው፡፡አሁን ባለው አሰራርና ስርዓት ፕሬዘዳንታዊ ስርዓትም ቢሆን እንኳ ከዚህ የተለየ ለውጥ መምጣቱ እጅግ አጠራጣሪ ነው፡፡ ግፋ ቢል ለውጡ ለፕሬዘዳንቱ የተወሰኑ ኃላፊነቶችን በህግ ያልተወሰኑ ነገር ግን እንዲኁ በባለስልጣኑ የሚደረጉ(discretionary) ስልጣን በመጠቀም ለመሰየም ያስችለው ይሆን ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ የፓርቲው አሰራርና የተዘረጋው የፌደራላዊ ስርዓት በስራ ላይ እስካለ ድረስ ብዙ የሚለወጥ ነገር አይኖርም፡፡ ይህ ማለት የብሔር ብሔረሰቦችና ልዩ ልዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች መካተት እጅግ አስፈላጊነት አጠያያቂነት የለውም፡፡የአሜሪካ ተሞክሮ በዘመነ ትራምፕይበልጥ ፓርላሜንታዊው ስርዓት ከፕሬዘዳንታዊ ይልቅ ስርዓትና ወጥነት የማስያዝ ባህሪ ስላለው ህገ ወጥ አሰራር የሚከተል ፕሬዘዳንት ስልጣን ላይ ሲመጣ ሊከሰት ከሚችለው ቀውስ በተሻለ ለማስተዳደር የሚቻል መሆኑ የተሻለ ያደረገዋል፡፡ አሜሪካዊያንም ቢሆን በዘመነ ትራምፕ የዚህ ክስተት ሰለባ መሆናቸውን ማስተዋል ይቻላል፡፡ እጅግ የዳበረ ሕገ መንግስታዊነት፣ ጠንካራ የሕግ አውጪ አካልና ከፍተኛ ስልጣን ያለው ፍርድ ቤት ብሎም ሕጋዊ የስልጣን ክፍፍልና እርስ በርስ ቁጥጥር ያላቸው ሦስቱ የመንግሥት አካላት ቢኖሩም የፕሬዘዳንቱን አሰራሮችና ድርጊቶች በሁለቱ ፓርቲዎቹ መካከል ባለው የኃይል ሚዛን ሽኩቻ ምክንያት ለማስቀረት ወይም ለማስቆም አልቻሉም፡፡ በዚህም ፓርቲ-ዘለል (non-partisan) በሆኑ ብሄራዊ ጉዳዮች ጭምር ለመስማማትና ውሳኔ ላይ ለመድረስ እየተቸገሩ ነው፡፡የፕሬዝዳንት ጎርባቾቭ ተሞክሮምንአልባት በፕሬዘዳንታዊ ስርዓት ተስፋ ማድረጉ ሁለት ዕድሎች ታሳቢ ያደረገ ሊሆን ይችላል ፡፡ አንደኛው የሶቪዬት ህብረትን የጎርባቾቭን ዘመን መነሻ ያደረገ ሊሆን ይችላል፡፡ እርግጥ ነው ጎርባቾቭ ወደ ስልጣን ከመጡ ማግስት ጀምሮ የፓርቲ ሴክረተሪያት የነበረው ስልጣን በአዲስ መልክ ተዋቅሮ ፕሬዘዳንታዊ ቅርጽ እንዲኖረው ተደርጓል፡፡ ይሁንና ይህም እጅግ ኮሚንስታዊ በሆነ አደረጃጀትና በተዋሃደ ድርጅት ውስጥ የተዋቀረ አሰራር ለፕሬዘዳንቱ ግዙፍ ስልጣን የሰጠ ነበር፡፡ ለዛም ነው በወቅቱ ጎርባቾቭ ማህበራዊ አውቶኖሚን/ነፃነትን ባጎናፀፈው ልክ ብዙ ስልጣን ተቆጣጥረዋል የሚል ስሞታ ይቀርብባቸው የነበረው፡፡ይህ ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ሲነጻጸር ቢያንስ ሁለት ልዩነቶች ጎልተው ይጠቀሳሉ፡፡ አንደኛ የኢትዮጲያው ኢህአዴግ የአራት ፓርቲዎች ጥምርና በብሄር የተዋቀረ መሆኑን መዘንጋት የለበትም፡፡ የፓርቲው ሊቀመንበርና የመንግስት የስራ አስፈጻሚው ኃላፊ ማለትም ጠ/ሚኒስትሩ ከፍተኛ ስልጣን ያለው ያህል ከፓርቲው አደረጃጀትና የብሄር ፖሊሲ ሊያፈነግጥ አይችልም፡፡ ይህም በመሆኑ ህገ መንግስቱ የሰጠውን ትልቅ ስልጣን በፓርቲ ርዕዮትና ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት አሰራሩ ሲገረስሰው ይታያል፡፡ የሶቪዬት ህብረቱ ኮሚዩኒስት ፓርቲ አንድ ዉህድ ፓርቲ በመሆኑ የዚህ አይነቱ ችግር አልበረበትም፡፡ ጎርባቾቭ ስልጣን ሲይዝ ህብረቱና አንድነቱ ለውጥ በሚሹትና ሌኒኒስት በሆኑት መካከል ልዩነት ተፈጥሮ የነበረ ቢሆንም፡፡ሁለተኛ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት በጎርባቾቭዋ ሶቪዬት ህብረት ፈጽሞ ያልነበረ ሲሆን የፉክክር ምርጫም የተፈቀደው በፓርቲው ውስጥ ከጎርባቾቭ ስልጣን መያዝ በኋላ ነበር፡፡ በአንጻሩ ኢትዮጲያ ምንም እንኳ ላለፉት ሃያ ሰባት አመታት ልምድ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት አለን ለማለት ባያስደፍርም በሕገ መንግስቱ የተደነገገ ስርዓት ነው፡:በዛሬይቱ ኢትዮጲያም እንደሚስተዋለው በነፃና ፍትሃዊ ውድድር የተሞላበት ምርጫ የተሰየመ የፓርቲዎች ስብጥር ያለበት የአብላጫ የሕግ አውጪ ምክር ቤት እስካልተመሠረተ ድረስ አደጋን ከመቀነስና ቀውስን ከመፍታት አኳያ ካልሆነ ፕሬዘዳንታዊም ሆነ ፓርላሜንታዊ ስርዓቱ መፍትሄ አይሆንም፡፡ ባለፉት የኢህአዴግ የአገዛዝ ዘመን እንደሚያሳየው ፓርላሜንታዊው ስርዓት በፓርቲው አወቃቀርና አሰራር ስርዓት ስር ነፃና ፍትሃዊ ምርጫዎች ባለመደረጋቸው የችግሮችን መፈጠር ሊታደግ አልቻለም፡፡ ምን አልባት ከፍተኛ መቃወስ እንዳይደርስ የራሱ የድርጅቱ ጠንካራ ዲሲፕሊናዊ አሰራርና የተማከለው አደረጃጀቱ በአንድ እዝ ስር መንቀሳቀሱ አስተዋፅኦ አበርክቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ችግሮቹን አፍኖ በመያዝና መፍትሄ እንዳያገኝ በማድረግ በህዝባዊ ቁጣ እራሱ የችግሩ ፈጣሪ መሆኑን በማመን ወደዚህ አይነት የጠ/ሚኒስትሩ ድምዳሜና አሁን ወዳለንበት ሁኔታ ሊያደርሰን ችሏል፡፡የቅቡልነት ቀውስሌላኛው መላ ምት የኢህአዴግ የሌጂትሜሲ ቀውስ ነው፡፡ እርሳቸውም ሆነ ድርጅታቸው በህዝብ ነፃ ምርጫ የተመረጡ ባለመሆናቸውና ከከፍተኛ የህዝብ ተቃውሞ ማግስት ወደ ስልጣን የመጡ እንደ መሆናቸው የወካይነት ስሜት ስለማይፈጥርባቸው ይሆናል፡፡ ይህም እንደፈለጉ ውሳኔዎችን ለመወሰን ግልፅ የሆነ ወደ ስልጣን ያመጣቸው አጀንዳ አለመኖሩ ነው፡፡ በተጨማሪም በሚቀጥለው ምርጫ በዛው በተለመደው ድርጅታዊ አሰራር ተጉዘው ዳግም ስልጣን ቢይዙ ይኸው ነባሩ ሂደት መቀጠሉ ይበልጥ ስራቸውን ሊያከብድባቸው እንደሚችል ገምተው ይሆናል፡፡ ከዚሁ ጋር የተያያዘው በመሪነት ደረጃ የሚጠበቅባቸው ይበልጥ እየጨመረ፣ እየተወሳሰበ ሲመጣ በነባሩ አሰራር በነፃነት ለመንቀሳቀስ ስለማያስችላቸውና ከድርጅቱ እራሳቸውን ነጥለው ቅቡልነታቸውን የማሳደግ አድርገን ልንወስደውም እንችላለን፡፡ ይህም በበጎ ከታየ በፕሬዘዳንቱ ዙሪያ በመሰባሰብ ከፓርቲ ባሻገር የሀገሪቱ ወካይነት ሚናንም በመወጣት አንድ የኢኮኖሚ እና ፖለቲካዊ ማኀበረሰብ የመገንባቱን ሂደት ሊያግዘው ይችላል፡፡ከአንዳንድ መግለጫዎቻቸው እንደምንረዳው የቀጥታ ምርጫን ብቻ እንደ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሂደት በመውሰድ ፓርላሜንታዊውን ስርዓት የማሳነስ ይሰተዋላል፡፡ ይህ ትክክለኛ አረዳድ አይደለም፡፡ ወይ ደግሞ በአሜሪካዊ የዴሞክራሲ ስርዓት ተማርከውና እርሱን ለሀገራቸው የመመኘት በጎ እሳቤ ይኖራቸዋል፡፡ በተለይ ለለውጥ በሚጥር ኃይል ሪፎርም ለማድረግና ፈጣን ለውጥ ለማምጣት በድርጅቱ ውስጥ የተሰገሰጉትን አባላትና አመራሮች ከኃላፊነትና ከስልጣን በማግለል በሌሎች አዳዲስ አባላት የመተካት ነጻነቱን ይሠጠኛል ብለው ይሆናል፡፡ ይህ በተወሰነ መልኩ ሊያስኬድ ቢችልም፤ ስጋታቸውም ተጨባጭ ቢሆንም፣ የድርጅቱ አሰራርና የብሔር ኮታ አሰራር ሳይቀየር የሚመጣው ለውጥ እምብዛም ብዙ ፈቅ የሚያደርግ አይዴለም፡፡ በህግ ያልተወሰነውን እንዲሁ ተመራጩ እንዲተገብረው የሚተወውን ስልጣኑን(discretionary) ቢጨምረውም የመጫወቻ ምህዳሩ ግን ብዙም የሚያወላዳና ነፃነትን የሚቸር አይደለም፡፡ ይህም በጠ/ሚኒስትሩና የለውጥ ቡድኑ ገፍቶ የድርጅቱን መርሆና አሰራር ገርስሶ እንደ ገረባቾቭ በአዲስ መልክ ለመቅረጽ የተዘጋጀና የወሰነ እንደሆነ ነው፡፡ ለዚህ በቂ ኃይል ማሰባሰብና ድጋፍ ማግኘት ከፖለቲካ ሥልጣን አመራርነት ከችግሮች ጋር ከመጋፈጥና ካሉት ነገሮችን የመቀየር ብቃትና ፍላጎት እየተማሩ በመሄድ የሚገኝ ክህሎት ነው፡፡ ለዚህም መቀየር ወይም ማደስ አሊያም ማፍረስ ያለባቸውን ለመለየት ጠ/ሚኒስትሩ ፈጣን ተማሪ መሆን አለባቸው፡፡የፓርላሜንታዊ ስርዓት ዴሞክራሲያዊነትብዙ ሀገራት ፓርላሜንታዊ ስርዓትን ይከተላሉ፡፡ ችግሩ የመነጨው ከነባራዊው የወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ እንጂ ፓርላሜንታዊ ስርዓት ከዴሞክራሲ ጋር በመሠረቱ የሚቃረን ሆኖ አይደለም፡፡ ይልቁኑም ይበልጥ ጠንካራና የዳበረ ዴሞክራሲ በመመስረት የተመሰከረላቸው ሀገራት የፓርላሜንታዊ ስርዓትን የሚከተሉ መሆናቸው ተደጋግሞ የተወሳ ነው፡፡ በ1970ዎቹ የስፔን ከአምባገነን ስርዓት ወደ ዴሞክራሲ የተደረገ ሽግግር የላቲን አሜሪካ ሀገራትን በእጅጉ ማርኮ የነበረና ለአገሪቱ የዴሞክራሲ ጉዞም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱ የተመሰከረለት ነበር፡፡ ይህም አስፈፃሚው አካል ስልጣኑ የሚመነጨው በህዝብ ከተመረጠው ከአብላጫው የህግ አውጪው አካል በመሆኑና በስልጣኑ ረግቶ ለመቆየት የዚህን የአብላጫ መቀመጫ የግድ ስለሚያስፈልገው ነው፡፡ ይህም መረጋጋትንና ተቋማዊ ቀጣይነትን የሚያረጋግጥ ነው፡፡በአንፃሩ ብቸኛው ሊባል የሚችል ዘመን ተሸጋሪ ሕገ መንግስታዊ የፕሬዘዳንታዊ ስርዓት መመስረት የቻለችው አሜሪካ ብቻ ነች፡፡ ከአሜሪካ ቀጥሎ ያልተቋረጠና ከመቶ አመት በላይ የቆየ ፕሬዘዳንታዊ ህገ መንግስታዊ ስርዓት መመስረት የቻለችው ቺሊ ብቻ ናት፡፡ እርሱም ቢሆን በ1970ዎቹ ሊገታ ችሏል፡፡መፍትሔው ምንድን ነው?መፍትሔው ተቋማዊነትን፣ የስልጣን ክፍፍልን እና ሕገ መንግስታዊነትን ማረጋገጥ ናቸው፡፡ በሦስቱ የመንግስት አካላት ማለትም ህግ አውጭ፣ አስፈፃሚና ተርጓሚ መካከል የተቀመጠው ስልጣን በግልፅ ልዩነትና ሳይጣረስ በህግ በተደነገገው መሠረት በመከፋፈል /separation of powers/ የመንግስትና የፓርቲን ልዩነት በአሰራር፣ በተቋምና ሕጎችን ተግባራዊ ማድረግ ድንበር ማበጀትን፣ ተጠያቂነትና ሚዛናዊነትን /checks and balances/ በመጠበቅ ነው፡፡ የሞንተስኪያን /Montesquieu/ መርሆን መከተልን ስልጣን አንድ ቦታ እንዳይከማችና አምባገነንነት እንዳይሰፍን ተግባራዊ ለውጥን ይጠይቃል፡፡ ይህም በነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ብቻ ወደ ስልጣን የሚመጣ መንግስት መኖሩን ማረጋገጥን በእጅጉ ይሻል፡፡ ይህም የቅቡልነትን ችግር በመሠረታዊነት መፍትሄ የሚሰጥ ነው፡፡ሌላኛው የፓርቲያቸውን የአብዮታዊ ዴሞክራሲና ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊ መርሆች እና አሰራርን በመቀየር ዴሞክራሲያዊና በሕገ መንግስቱ ለጠ/ሚኒስትሩ የተሰጡት ስልጣኖች ተግባራዊ እንዲደረጉ/እንዲተረጎሙ ማስቻል ነው፡፡ ከዚሁ ከድርጅቱ ጋር በተያያዘ የብሄር አደረጃጀቱና ተዋፅኦውን መከለስና ሕገ መንግስታዊው አፈፃፀም ሳይዛነፍ የብሔሮች ተሳትፎና ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ አወቃቀርና አሰራር መከተልን ይጠይቃል፡፡ አራቱ ድርጅቶች በብሔር እስከተደራጁና አንድ ወጥ ፓርቲ በመሆን ብሔራዊ አደረጃጀት እስካልተከተሉ ድረስ በዚሁ አደረጃጀቱ ፕሬዘዳታዊ ስርዓት ሀገሪቱ ብትከተል እንኳ ኢህአዴግ በተለመደው አሰራሩ መቀጠሉ ይበልጥ ቀውስን ሊያስከትል ይችላል፡፡ አንድ ፕሬዘዳንታዊ እጩ ለመምረጥ የብሄርና የድርጅቶቹን ተዋፅኦ የተከተለ ክርክር መነሳቱ አይቀርም፡፡ ከምርጫም በኋላ ፕሬዘዳንቱ ካቢኔውን ለማዋቀር ተመልሶ የዚሁ የድርጅቱ አሰራር አጥር ውስጥ መታሰሩ አየቀርም፤ ያም ከነጻና ፍትኃ ምርጫ እውን መሆን በኋላ፡:ይህ ማለት ፓርላሜንታዊ ስርዓት ከቀውስና ከችግር ፍፁም ነፃ ነው ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንም በአፍሪካ የተለያዩ ሀገራት እንደተስተዋለው የብሔርና የጎሳ ቡድኖች ግጭት ጎልቶ በሚስተዋልባቸው ሀገራት ፓርላሜንታዊ ስርዓትም ቢሆን ዋስትና እንዳልሆነ ነው፡፡ ይሁንና የህንድም ሆነ የሌሎች በካሪቢያን ያሉ አጅግ ሰፊ ብዝኃነትና የተካረሩ ልዩነቶች የሚስተዋልባቸው ሀገራት ተሞክሮ እንደሚነግረን ፓርላሜንታዊ ስርዓት የተሻለ አዋጭና ዘላቂነት ያለው መሆኑን ነው፡፡ በአንድ ፕሬዘዳንት ከስልጣን መወገድና መገለል ወይም ደግሞ በህዝብ ድምፅ አብላጫ ምርጫ ስልጣን ላይ ከሚወጣ አምባገነን ፕሬዘዳንት ምክንያት ከሚከሰት ከፍተኛ ሀገራዊ ቀውስ ይልቅ ወደ መንግስታዊ ቀውስነት የማይሸጋገር የፓርላሜንታዊ ቀውስ ይልቅ የተሻለ ለማስተዳደር ይቀላል፡፡ በተለይ እንደ ኢትዮጲያ ላሉ ስፍር ቁጥር ለሌለው የፓርቲዎች አሰላለፍ ለሚስተዋልባቸው ሀገሮች ፓርላመንታዊ ስርዓት የተሻለ ጥምረትና ህብረት እንዲፈጥሩ የሚያበረታታ ነው፡፡ ችግሩ ያለው ከፓርላሜንታዊው ስርዓት አይደለም፤ ፕሬዘዳንታዊ ስርዓትም አሁን ባለው የፌደራልና የኢህአዴግ ፓርቲ አሰራርና አወቃቀር ስር መፍትሄ አይሆንም፡፡ጠ/ሚኒስትሩ በሂደት አቅምና ኃይል በማሰባሰብ ወደ ለውጥ የሚያደርጉትን ጉዞ በሥልጣን ዘመናቸው ከዕለት ዕለት በመማር፣ ይበልጥ የስልጣን መሠረታቸውን በማረጋገጥና ይህንን የመጠቀምና ጫና የማሳደር ልምድ በመጨመር ሂደት ፓርቲያቸውንና አስተዳደራቸው የሚፈለገው ለውጥ እንዲመጣ የካፒቴኑን ስራ መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ እጅግ ፈጣን ተማሪና በጊዜ ሥልጣናቸውን በማደላደል በፓርቲያቸው ውስጥ የሚስተዋለውን የተካረረ አቋምና ፅንፍ የያዘ ተቃርኖ ማረቅ ይጠይቃል፡፡ ለዚህም ሦስት ዘርፍ ለውጦችን ይጠይቃል፡- የገዢውን ፓርቲ አሰራርና አወቃቀር፣ የመንግስት አስተዳደር እና አጠቃላይ የፖለቲካና ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን ማዕቀፍ አስመልክቶ የተሳኩ ለውጦችን ማብሰር ናቸው፡፡ በተጨባጭ ተግባራዊ የሕግና የዴሞክራሲ ተቋማትን በሁለት እግር ማቆምና ከተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ግልፅ ውይይት በመመስረት የሚፈለገውን ሽግግር ማሳካት ለነገ አይባልም፡፡ ሂደቱ የማይቀለበስበት ደረጃ መድረሱን ማረጋገጥ የተደላደለ ዴሞክራሲን በማስፈን ከአንድ ገዢ ፓርቲ በላይ ወደ ሆነች ሀገርን የመገንባትና የማስቀጠል ምዕራፍ መሻገር እውን ማድረግ ይበጃል፡፡ ከአምባገነን መንግስታት ማግስት የሚመጣ ለውጥ ይህንን ማሳካቱ ትልቁ ፈተናው ነው፡፡ በተለይ እጅግ የገዘፉና የሰፉ ልዩነቶችና ፍላጎቶች ባሉበት ሀገር ልዩነትን አቻችሎ የጋራ አጀንዳ በመመስረት የጋርዮሽ-ትግበራ ማሳካት ትልቅ የፖለቲካ ጥበብንና ድፍረትን ይጠይቃል፡፡ ያኔ ስርዓት መትከል መቻሉን ይረጋገጣል፡፡

አስተያየት