ጳጉሜ 1 ፣ 2010

ረጅሙ ዓመት

ወቅታዊ ጉዳዮችዜናዎች

እንግሊዛዊው ማርክሲስት የታሪክ ባለሙያና ደራሲ ኢሪክ ሆብስዋም 19ኛውን ክፍለ ዘመን ረጅሙ ክፍለ ዘመን ሲል ይጠራዋል፡፡ ለሆብስዋም ክፍለ ዘመኑ በክስተት…

ረጅሙ ዓመት
እንግሊዛዊው ማርክሲስት የታሪክ ባለሙያና ደራሲ ኢሪክ ሆብስዋም 19ኛውን ክፍለ ዘመን ረጅሙ ክፍለ ዘመን ሲል ይጠራዋል፡፡ ለሆብስዋም ክፍለ ዘመኑ በክስተት የተሞላ ነበር፡፡ የአውሮፓ ታላለቅና ተከታታይ አብዮቶችና ታላቅ የፖለቲካ ኹነቶች አንስቶ እስከ የጀርመንና የጣልያን ውህደቶች፤ እንዲሁም የዓለም ኢኮኖሚ መስፋፋት የተከወኑት በዚህ ክፍለ ዘመን ነበር፡፡በኢትዮጵያም 2010 ዓ.ም. አንድ ዓመት አይመስልም ነበር፡፡ ይህ ዓመት በውስጡ የያዛቸውን በርካታ ለማመን የሚያስቸግሩ ክስተቶች የተመለከተ ሁሉ ዓመቱ በውስጡ ሌላ አስር ዓመታትን የያዘ ጉድ ነው ቢል አይፈረድበትም፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ 2010 ዓ.ም. ልክ እንደ 1966ቱ አብዮትና እንደ 1983ቱ የመንግስት ለዉጥ በታሪካዊነቱ ሲዋሳ ሊኖር የሚችል ዓመት መሆኑን ብዙዎችን ያስማማል፡፡አዲስ ዘይቤ/ጎበና መንገድ በዓመቱ ዉስጥ ከተሰሙ ዜናዎች አንኳር የሆኑትን አባይን በጭልፋ ቢሆንበትም እያለፈ እያለፈ በ12 ወራት ውስጥ የተከናወኑ ዐበይት ተግባራትን ለመመልከት ሞክሯል፡፡መስከረም፡- በአገሩ መጤ የተባለው የኦሮሞ ማኀበረሰብ
  • የመስከረም ወርን የመፋናቀል ወር ብንለው አያንስበትም፡፡ ዓመቱ የተጀመረዉ በግድያና መፈናቀል ዜና ነዉ፡፡ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሃረርጌ ዞን፤ አወዳይ ከተማ፤ 18 የሶማሌ ተወላጆች ባልታወቁ ሰዎቸ መገደላቸዉን ተከትሎ ከሶማሌ ክልል ዋና ከተማ ጅግጅጋና ሌሎች ከተሞች እንዲሁም ከሶማሊላንድ ከ600 ሺህ በላይ የሆኑ የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ ኢትዮጵያዉያን ተፈናቅለው በጭናቅሰን፣ በባቢሌና ሐረር ከተሞች ውስጥ ከነቤተሰባቸው በአገራቸው መጻተኛ እንዲሆኑ ተገደዋል፡፡
ጥቅምት፡- የታላቁ  ሠለሞን ደሬሳ ስንበት፤ ኦቦ ለማ መገርሳ ሱስ
  • በኢትዮጵያ ስነ ጽሑፍ ዉሰጥ የገዘፈ ሰም ያለዉ ገጣሚ፣ መምህርና ጋዜጠኛ ሰሎሞን ዴሬሳ ጥቅምት 23/2010 ዓ.ም. በሰማንያ ዓመት ዕድሜው አረፈ። ሰሎሞን ዴሬሳ በአሜሪካን አገር ሚኔሶታ ዉሰጥ ይኖር ነበር፡፡ የዚህ ታላቅ የጥበብ ሰዉ አስከሬን በሃበሻ ወግ አፈር አልቀመሰም፡፡ ይልቁንም በኑዛዜዉ መሰረት አስከሬኑ ተቃጥሎ ለሰሜን ንፋስ ተሰጥቷዋል፡፡
  • በባህር ዳር ከተማ በተካሄደው የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች የምክክር መድረክ አቶ ለማ መገርሳ ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው አሉ፡፡ “በባድመ፤ በአድዋና በሌሎችም ቦታዎች የሞትነው ቅጥረኛ ሆነን ሳይሆን ለዚህች አገር ስንል ነው” በማለት የዓመቱን ታላቅ ንግግር አድረጉ፡፡
  • በእንቦጭ ይሉት አረም አደጋ ያንዣበበትን የጣና ሐይቅ ለመታደግ በሚል ከኦሮሚያ ክልል የተዉጣጡ 200 ወጣቶች ወደ አማራ ክልል ተጉዘው "ጣና ኬኛ"  ጣና የኛ ነው በማለት አረሙን በማጥፋት ስራ ተሳተፉ።
  • አቶ በረከት ስምዖን ከኃላፊነታቸው ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸው ተነገረ። በወቅቱ አነጋጋሪ የነበረዉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ዜናውን እኛም የሰማነዉ ከሚዲያ ነዉ ማለታቸዉ ነበር፡፡
ሕዳር:- ሼሁ ታሰሩ፤ እንደ ኣንዳችንም ሆኑ
  •  ‘ከመቃብር እና ከእስር የሚያመልጥ የለም’ እንዲል የቅሊንጦ እስረኛ ዓለም አቀፍ ቢሊየነሩ፤ አፍቃሪ ኢህአዴጉ፤ ቱጃሩ ሼክ ሞሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ሳውዲ ዓረቢያ በከፈተችው ጥልቅ የጸረ ሙስና ዘመቻ ሳቢያ ተፈላጊ ሆነዉ ዘብጥያ ወረዱ። ሼኩን ጨምሮ ሌሎች የሳዉዲ ዜጋ የሆኑት ቢሊኒየሮች የታሰሩት ቅንጡ በሆነው ሆቴል ሪትዝ-ካርሊተን መሆኑና የአሜሪካው ቅጥረኛ ብላክ ዋተር ቶርቸር ፈጸሞባቸዋል መባሉ ትኩረትን የሳበ ጉዳይ ነበር፡፡
  • ሕዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ (ሕወሃት) ማዕከላዊ ኮሚቴ ለአንድ ወር የረዘመ ዝግ ስብሰባ በመቀሌ ከተማ አካሄደ። ከስበሰባዉ በኋላም ሊቀመንበሩን አቶ አባይ ወልዱን ከሥልጣን በማንሳት በምትካቸዉ ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የሕወሃት ሊቀመንበር፣ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔርን ደግሞ ምክትል ሊቀመንበር ከማደረጉም በላይ ክልሉን በምክትል ፕሬዝደንት ማዕረግ እንዲመራ ለመወሰን ተገደደ፡፡ በዚሁ ስብሰባ የፓርቲው የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የነበሩት የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ባለቤት የነበሩት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት እንዲታገዱ ተደረገ፡፡
ታህሳስ፡- የኢህአዴግ ንስሃ፤ የማዕከላዊ ሙዚየምነት፤ የኢብራሂም ሻፊ ሞት
  •  የኢህአዲግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ለ17 ቀናት የቆየ ጥልቅ ግምገማ ካካሄደበት ባህር ሲዋጣ ባወጣዉ መግለጫ፤ የኢህአዴግን ሀጢያት ተናዘዘ፤እንደተለመደው ህዝቡንም ይቅርታ ጠየቀ፡፡
  • ማዕከላዊ ይዘጋል ወደ ሙዝየምነትም ይቀየራል፤ በእሥር ላይ የሚገኙ የፖለቲካ እሥረኞች ይፈታሉ፡፡ የዓቃቤ ሕግ ክስም ይቋረጣል ሲሉ የወቅቱ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ፡፡ ይህን ማደረግ ያስፈለገዉም “የዴሞክራሲያዊ ምኅዳሩን ለሁሉም ሰፊ ለማድረግ” ታስቦ እንደሆነ ተናገሩ፡፡
  • የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም በተመለከተ የተዘጋጀን የዐዋጅ ረቂቅ ውይይት ለማድረግ በሕግና ፍትሕ ጉዳዮችና በከተማ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተጠርቶ የነበረው የሕዝብ አስተያየት መቀበያ ስብሰባ ላይ ብዙዎች የኦሮሚያ ተወካዮች  “በሀገሪቱ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ አንገብጋቢ ጉዳይ እያለ በዚህ ላይ አንወያይም” በማለታቸው ውይይቱ ተቋርጦ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዘመ፡፡
  • ተወዳጁ የስፖርት ጋዜጠኛ ጋዜጠኛ ኢብራሂም ሻፊ በስደት ይኖርበት በነበረዉ ናይሮቢ ታህሳስ 25/2010 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ ፡፡ ኢብራሂም ሻፊ ነሃሴ 2006 ዓ.ም. አዲስ ጉዳይ የተሰኘችው መጽኄት ስትዘጋና ስትከሰስ ከሌሎች ባልደረቦቹ ጋር የተሰደደ ሲሆን የሞቱ ዜና ብዙዎችን ያስደነገጠ ነበር፡፡
ጥር፡- የመረራ መፈታት፤ የወልድያው ግድያ
  • የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግሬስ /ኦፌኮ/ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና የተመሰረተባቸው ክስ ተቋርጦ ከሌሎች 528 ተጠርጣሪዎች ጋር ተፈቱ፡፡
  • በአማራ ክልል ወልድያ ከተማ ሲካሄድ በነበረው ሀይማኖታዊ ክብረ በዓል በተፈጠረ ግጭት ሰባት ሰዎች እንደተገደሉ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች እንደቆሰሉ ተገለፀ፡፡
የካቲት፡- ኃይለማርያም ስልጣኑን ተረከቡኝ አሉ፤ እስክንድርም ተፈታ
  • በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣውና ለኢትዮጵያ ፓርላማ የቀረበው የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ፣ ባልተለመደ ሁኔታ ከሰፊ ተቃውሞ ጋር ጸድቋል፡፡የኦሮምያን ክልል የሚወክሉ ዘጠና አምስት የፓርላማ አባላት የዐዋጁን መፅደቅ አልደገፉም፡፡ አቶ አባዱላ ገመዳ በመሩት በዚህ የፓርላማ ስብሰባ የውሳኔው ድምጽ ላይ የቁጥር ማጭበርበር እንደነበረ ብዙዎች ሲከሱም ሲገረሙም ከረሙ፡፡
  • የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ዶ/ር ዐቢይ አህመድን ሊቀመንበር፣ ሊቀመንበር የነበሩትን አቶ ለማ መገርሳን ደግሞ ምክትል አድርጎ የኃላፊነት ሽግሽግ አደረገ
  • ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከድርጅት የመሪነት መንበራቸውና ከጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣናቸው ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸውን ይፋ አደረጉ፡፡ ከድርጀት መሪነትና ከሥልጣናቸው ለመልቀቅ ጥያቄ ያቀረቡት የሀገሪቱ ችግር መፍትሄ አካል ለመሆን ስለፈለጉ መሆኑንም ገለጸዋል፡፡
  • ረዥም ዓመት ተፈርዶባቸው በእስር ላይ የነበሩት እነ እስክንድር ነጋ፣ አንዷለም አራጌ፣ አሕመድ ሙስጠፋ፣ አሕመዲን ጀበልና ሌሎች እስረኞች ተፈቱ፡
መጋቢት፡- የዐቢይ ወደስልጣን መምጣት፤ የሞያሌ እልቂት
  • የኢህአዴግ ምክር ቤት የኦህዴዱን ዶ/ር ዐቢይ አህመድን ሊቀመንበር አድርጎ ሲመርጥ የግንባሩ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው የቆዩት አቶ ደመቀ መኮንን በያዙት ኃላፊነት እንዲቀጥሉ ወሰነ፡፡ ከዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ጋር በሊቀ መንበርነት የተወዳደሩት ከደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) አቶ ሽፈራው ሽጉጤና ከሕወሃት ዶ/ር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል ነበሩ፡፡ በኢህአዴግ ውስጥ ባልተለመደ መልኩ ሽኩቻ የበዛበት ምርጫ እንደነበር ተዘግቧል፡፡
  • ዶር ዐቢይ ታሪካዊ የተባለውን ንግግር በፓርላው ፊትና ለኢትዮጵያ ህዝብ አደረጉ፡፡ ለሃገሪቱ ታላቅነት ዋጋ ለከፈሉ ሰማዕታት ዕውቅና ሰጡ፡፡ መንግስታቸው ላደረሰው የሰብዓዊ መብት ረገጣ፣ ግድያ እና እስራት ጠየቁ፡፡
  • በሞያሌ ከተማ በርካታ ሰላማዊ ወገኖቻችን ምክንያቱ በውል ባልታወቀ ሁኔታ በመከላከያ ሰራዊት ተገደሉ፡፡ መንግስት ይህንን ክስተት በስህተት የተፈጸመ ብሎ የገለፀ ሲሆን እስካሁንም ማንም ኃላፊነቱን ያልወሰደበት አሳዛኝ ድርጊት እንደነበር ብዙዎች ያምናሉ፡፡ በርካቶችም ወደጎረቤት አገር ኬንያ ተሰደው ነበር፡፡
 ሚያዚያ፡- የአባዓለም ለምኔዎች ፍቺ፣ መፈናቀል በደቡብ ኢትዮጵያ ጌድኦ-ጉጂ
  • የዋልድባ ገዳም መነኮሳት ከእስር ተፈቱ፡፡ እነዚህ መነኮሳት አለምን ንቀው፤ ገዳማት ውስጥ ከሰው ተነጥለው ከሚኖሩበት ተይዘው መታሰራቸው የሥርዓቱን ጭካኔ የሚያሳይ ነው በማለት ብዙዎች መንግስት ላይ ውግዘት ሲያቀርቡ ከርመው ነበር፡፡
  • የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የሀገሪቱን ከፍተኛ የክብር ዲፕሎማ ተበረከተላችዉ፡፡ በብሔራዊ ቤተመንግሥት አሸኛኘት ተደርጎላቸዋል፡፡
  • የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን ከተረከቡ የመጀመሪያ የውጭ ጉዟቸውን ወደ ጂቡቲ አድርገዋል፡፡
  • በደቡብ  ኢትዮጵያ ምስራቅ ጉጂ ቀርቻ ወረዳ የተጀመረው በታጠቁ ወጣቶች የተጀመረው ማፈናቀል ሰፍቶ ከስምንት መቶ ሺህ የሚበልጡ ጌደዎች ጨርቄን ማቄን ሳይሉ ቤት ንብረታቸውን ጥለው እንዲወጡ ተገደዱ፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመፍራት የአከባቢው ባለስልጣናት የደረሰውን ሰብዓዊ ቀውስ ለሚዲያ ባለመግለጻቸው ሰብዓዊ እርዳታም በስፍራው የደረሰው ዘግየቶ ነው፡፡
ግንቦት፡- የማይነቃነቁ የሚመስሉት ተገነደሱ
  •  የሕወሃት መስራች የሆኑትና የድርጅቱን የፖለቲካ ጨዋታ ገና ከጅምሩ ከኃላ ሆነዉ ይዘዉሩታል እየተባለ በብዙዎች የሚነገርላቸዉ በቅፅል ስማቸዉ አቦይ ስብሃት ተብለዉ የሚታወቁት አዛዉንቱ ስብሃት ነጋ በጡረታ እንዲገለሉ ተወሰነ ፡፡ የጡረታ ዉሳኔዉ አቦይን ብቻ ሳይሆን ለረጅም ዓመታት በኢህአዲግ መንግስት በተለያየ ስልጣን እርከን ላይ የቆዩትን ዶ/ር ካሱ ኢላላ፣ አቶ ታደሰ ኃይሌ እና አቶ መኮንን ማንያዘዋልን ያካተተ ነበር፡፡
  •  ከፀደቀበት ጊዜ አንስቶ ከብዙ ወገኖች ተቃዉሞ ሲቀርብበት የከረመዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከሶስት ወራት ቆይታ በኃላ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጁ እንዲነሳ ተወሰነ፡፡
  • ከአራት ዓመታት በፊት በየመን ሰንዓ አውሮፕላን ማረፊያ በኢትዮጵያ የደህንነት ሃይሎች ተጠልፎ ይሙት በቃ ተፈርዶበት የነበረው የግንቦት ሰባት አመራሩ አንዳርጋቸው ጽጌ ከእስር ተለቀቀ፡፡ ከእሰር በመፈታቱ ሲደነቁ ለነበሩ በርካታ ደጋፊዎቹ አንዳርጋቸውን በቤተመንግስት ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር ያደረገው ውይይትና በማኀበራዊ ሚዲያ በስፋት የተሰራጨው ፎቶ ሌላ አስገራሚ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል፡፡
ሰኔ፡- የዶር ዐቢይ አህመድ የዘንባባ ዝንጣፊ፤ ኢሳያስ አፈወርቂ ምላሽ
  • የኢትዮጵያ መንግስት የአልጀርሱን ስምምነት ያለቅደመ ሁኔታ እንደሚቀበል መግለጹን ተከትሎ ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል ሲቀርብላቸዉ የነበሩ በርካታ የድርድር ጥያቄዎችን ዉድቅ ሲያደርጉ የቆዩት የኤርትራዉ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ የሰላም ጥሪዉን እንደሚቀበሉ መቀበልም ብቻ ሳይሆን በጉዳዩ ላይ የሚነጋገር የልዑካን ቡድን ወደ አዲሰ አበባ እንደሚልኩ አስታወቁ፡፡ በቃላቸዉ መሰረትም ከአንድ ሳምንት በኃላ የኤርትራዉ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳላህ እና የፕሬዝዳንቱን ልዩ አማካሪ የማነ ገብረዓብ የያዘ የልዑካን ቡድን ወደኢትዮጵያ በመምጣት ከጠቅላይ ሚ/ር ዐቢይ አህመድ ጋር ተወያየ፡፡ ለሃያ ዓመታት ተቋርጦ የነበረዉ የሁለቱ ሃገራት ግንኙነትም በዚህ መልኩ ተጀመረ ፡፡
  • ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ለጀመሩት ለውጥ ድጋፍ ለማሳየት ያለመ ሰላማዊ ሰልፍ በአዲሰ አበባ መስቀል አደባባይ ተካሄደ፡፡ ጠቅላይ ሚ/ሩ በሰልፉ ላይ በመገኘትም ንግግር ያደረጉ ሲሆን ንግግራቸዉን አጠናቀዉ ወደመቀመጫቸዉ ከተመለሱ ከጥቂት ደቂቃዎች በኃላ ቦንብ ተወርዉሮ ለሰልፍ በወጡ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የሞትና የመቁሰል አደጋ አስከተለ፡፡ በአደጋዉ 2 ሰዎች ህይወታቸወ ሲያልፍ 156ሰዎች ደግሞ ቀላልና ከባድ የመቁስል አደጋ ደርሰባቸዉ፡፡ የምርመራዉ ዉጤት እስካሁን ይፋ ባይደረግም በምርመራዉ ሂደት የአሜሪካ የብሔራዊ ምርመራ ባለሙያዎች እንደተሳተፉ ተገልጾ ነበር፡፡
  • ሰኔ 16 አዲሰ አበባ መሰቀል አደባባይ ከተደረገዉ ሰልፍ ጋር ተመሳሳይ ዓላማ ያለዉ ሰልፍ በባህር ዳር ተደረገ፡፡ በሰልፉ ላይ ተገኝተዉ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸዉ የለዉጥ ሂደቱን ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ ያሏቸውን ሃይሎች "ያልታደሰውና የአሮጌው ዘመን ቁማርተኞች” በማለት አዉግዘዋል፡፡ በሰልፉ ላይ አቶ ደመቀ መኮንንም ንግግር አድርገዋል፡፡ ሁለቱም በብዙዎች ዘንድ የሁለቱ ባለስልጣናት ንግግር ብአዴን ለለዉጡ ያለዉን ቁርጠኛነትና ብዙ ጊዜ ከሚወቀስበት የህወኃት ተጽእኖ እንደተላቀቀ ያሳየበት መድረክ ተደርጎ ተወስዷል፡፡
  • ኢትዮጵያ የድፍድፍ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሙከራ ምርትን በይፋ ጀመረች በቀን 450 በርሜል ድፍድፍ የተፈጥሮ ጋዝ ማዉጣት እንደሚቻል መንግስት አስታወቀ ፡፡
ሃምሌ፡- ጸጋዬና ፊያሜታ -ዳግም ፍቅር በፍቅር፤ የወገን ስቃይ በጅግጅጋ
  •  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኤርትራን ጎበኙ፡፡ በአስመራ ጎዳናዎች እጅግ ሞቅ ያለ አቀባበል ተደረገላቸዉ፡፡ በአስመራ ጎዳናዎች ላይ  ዐቢይ ዐቢይ ድምጾች እጅግ ጎለተው ሲሰሙ፤ አንዳንዶችም ከጥበቃ ሃይሎች እያመለጡና ወደ ጠቅላይ ሚ/ሩ መኪና አንገታቸውን በማስገባት ለጠቅላዩ የነበራቸውን ፍቅር በመሳምም ሲገልጹ ተስተውለዋል፡፡ ዶር ዐብይ ጉብኝታቸውን አጠናቀው በተሸኙበት ወቅት፤ፕት ኢሳያስና ታላላቅ የኢርትራ መንግስት ባለስልጣኖች ባልተለመደ መልኩ በአስመራ አውሮፕላን ማረፊያ ለብዙ ደቂቃዎች ስሜታዊ ሆነው ታይተዋል፡፡ የምስራቅ አፍሪካን ፖለቲካ የሚከታተሉ ዓለምአቀፍ የሚዲያና የዲፐሎማሲ ባለሙያዎች በቀጣናው አዲስ ተስፋ መፈንጠቁን ሲናገሩ ተሰምው ነበር፡፡
  • የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ኢትዮጵያን ሲጎበኙ የአዲስ አበባ ህዝብ ግልብጥ ብሎ በመውጣት አድናቆቱን ያሳየ ሲሆን፤ ፕሬዚደንት ኢሳያስም በተለይ በሚሊኒየም አዳራሽ በተደረገላቸው የህዝብ አቀባበል እጅጉን ተደንቀው ታይተዋል፡፡ ከረጅም ዓመታት (ብዙዎች ከ50 ዓመታት በሁዋላ ይሉታል) ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አዲስ አበባ ላይ ለተሰበሰበው ህዝብ በአማርኛ ንግግር አድርገዋል፡፡
  • ከ20 ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ አስመራ በረራ አደረገ። በዚህ የመጀመሪያ በረራም ለሃያ ዓመታት በኤርትራ ከሚገኙ ቤተሰቦቻቸዉ ጋር ተቆራርጠዉ የነበሩ በርካታ ሰዎች ከቤተሰቦቻቸዉ ጋር ሲቀላቀሉ መሬት እየሳሙ ሲያለቅሱ ታይተዋል፡፡ በተመሳሳይ የኤርትራ አየር መንገድም ወደ አዲስ አበባ በረራ ጀመረ።
  • አብዲ ሙሐመድ ዑመር(አብዲ ኢሌ) ያሰለጠናቸው ሄጎ የተባሉ የወጣቶች ቡድንና የክልሉ ልዩ ሃይል መጤ ወይም ደገኛ ባሉዋቸው ወገኖቻችን ላይ ከፍተኛ የሚባል ጉዳት አደረሱ፡፡ በዚህ ጥቃትና ግርግር በሶማሊ ክልል የሚገኙ በርካታ አብያተ ክርስትያናት ሲቃጠሉ፤ ብዙ ሰዎችም መሞታቸው ታወቀ፡፡
  • ኤርትራ በኢትዮጵያ የነበራትንና ከበርካታ ዓመታት በፊት የተዘጋ ኤምባሲዋን በመክፈት አቶ ሰመረ ርዕሶምን በኢትዮጵያ አምባሳደርነት ስትሾም ኢትዮጵያም በበኩሏ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴንን በኤርትራ የኢትዮጵያ አምባሳደር አድርጋ ሾመች።
  • ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደአሜሪካ ተጉዘው ከኢትዮጵያዊያን ጋር በሦስት ከተሞች ውይይት አደረጉ፡፡ በዋሽንግተን ዲሲ ለረጅም ዓመታት ተቀውሞውን በኤምባሲው ደጃፍ ሲገልጽ፤ ቁጣውንም በኢትዮጵያ ባለስልጣኖች ላይ ሲያሰማ የኖረው ሽመልስ ለገሰ የተባለውን ኢትዮጵያዊ ጠቅላይ ሚንስትሩ እጁን ይዘው ወደ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ቅጥር ውስጥ መግባታቸው ትኩረትን የሳበ ነበር፡፡ በቀጣይ በነበረውም የህዝብ ውይይት ላይም ጠቅላይ ሚንስትሩ ታዋቂውን የሰብኣዊ መብት ተሟጋች ታማኝ በየነን ንግግራቸውን አቋርጠው ወደመድረክ ጋብዘውታል፡፡ ታማኝም ኢትዮጵያዊ የሆነውን የክብር መግለጫ በታላቅ ስሜት ሆኖ እጅ በመንሳት ገለጸ፡፡ በንግግሩም ጠቅላይ ሚንስትሬ ሲል ያወደሰ ሲሆን በሚችለው ሁሉም ከጎናቸው እንደሚቆም ተናግሯል፡፡ በሚኒሶታው መድረክም አክቲቪስት ጃዋር መሐመድ ንግግር አድርጓል፡፡
  • በበርካታ ቴአትሮች፤ የሬዲዮና የቴሌሺዥን ድራማዎችና ፊልሞች ላይ ባሳየዉ ድንቅ የትወና ብቃት አድናቆትን ያተረፈዉ አንጋፋዉ ተዋናይ ፍቃዱ ተክለማሪያም ባደረበት የኩላሊት ሕመም በተወለደ በ62 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። ተዋናዩን ለማሳከም የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ ተቋቁሞ በሃገር ዉስጥም በዉጭ ሃገራትም ከፍተኛ የገቢ ማሰባሰብ ተደርጎ ነበር ፡፡ ቢሆንም የተሰበሰበውን ገንዘብ ሳይታከምበት የህይወቱን የመጨረሻዎቹን ቀናት ሰሜን ወሎ በሚገኝ ገዳም ጸበል ሲጠመቅ ቆይቶ አርፏል፡፡
  • ከኢህአዴግ አዲስ አበባን መቆጣጠር ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል ተፈጥሮ የነበረው መከፋፈል ተፈታ፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አራተኛ ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከ27 ዓመታት ስደት በኋላ ወደ ሃገራቸዉ ተመለሱ፡፡
  • ኢትዮጵያ የትልቁን ፕሮጀክቷን ትልቅ ሰዉ አጣች ፡፡የታላቁ ህዳሴ ግድብ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ መስቀል አደባባይ መኪናቸዉ ዉስጥ ሞተው ተገኙ፡፡ ፖሊስ ጠቋሚ መረጃዎች አሉኝ ቢልም እስካሁን ዝርዝር መረጃዎች ለህዝብ ይፋ አልተደረጉም፡፡
ነሃሴ፡- የታማኝ መምጣት፤ የመንጋ ፍርድና የጠ/ሚ/ሩ ጋዜጣዊ መግለጫ
  • ኦነግ ከትጥቅ ትግል ወደ ሰላማዊ ትግል ለመግባት የሚያስችለውን ሥምምነት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ተፈራርሟል፡፡ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳና የኢፌዴሪ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ አስመራ ውስጥ በኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ከሚመራው ልዑክ ጋር የእርቅ ውይይት ተካሂዷል።
  • የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) ልዑክ በግንባሩ ቃል አቀባይ አቶ አዳኒ አብዱልቃድር ሄርሞጌ የተመራው እና ፫ አባላትን ያለው ልዑክ አዲስ አበባ ገብቷል።ወደ ሀገር የገባውን ልዑክ የመሩት አቶ አዳኒ አብዱልቃድር ሄርሞጌ፥ ግንባሩ ወደ ሀገር ቤት ለመግባት የወሰነው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥሪን ተከትሎ መሆኑን አስታውቀዋል።
  • ጃዋር ሞሃመድ ወደኢትዮጵያ መጣ፡፡ አምቦ ላይ ባደረገው ጉብኝትም ቀደም ብሎ በገባው ቃል መሰረት፤በባዶ እግሩ ሲራመድ ታይቱል፡፡ በተመሳሳይ በሻሸመኔ በደረገው ጉብኝት ከፍተኛ የሆነ ህዝብ ሊቀበለው የወጣ ሲሆን በዚሁ ቀን አንድን ግለሰብ "ቦምብ ይዘሃል" በሚል ክስ በቦታው የተገኙ ወጣቶች ዘቅዝቀው በመግደል የስልክ እንጨት ላይ ሰቅለውት ታይቱል፡፡ ይህ ድርጊት በርካታ ኢትዮጵያንን ያስቆጣና ያሳዘነ ሲሆን፤የድርጊቱ ፈፃሚዎች ተይዘዋል ቢባልም እስካሁን የፍርድ ሂደቱ ምን እንደደረሰ አይታወቅም፡፡
  • የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ምክር ቤት የአቶ አብዲ መሐመድ ኡመርና የሌሎች ስድስት የምክር ቤቱ አባላትና የክልሉ ባለሥልጣናት ያለመከሰስ መብት ማንሳቱን ተከትሎ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ በብሔር ግጭት ቀስቃሽነት፣ በኃይማኖት መካከል ግጭት እንዲፈጠር አድርገዋል በሚል በቁጥጥር ስር ዉለዋል፡፡
  • ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የመጀመሪያው የሆነውን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጠተዋል፡፡ በጋዜጣዊ መግለጫዉ ቀጣዩን ምርጫ ነጻ ለማድረግ ያላቸዉን ቁርጠኝነት የገለጡ ሲሆን በሶማሊ ክልል የነበረዉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እጅግ አስከፊ እንደነበር መናገራቸው በዋነኛነት የሚጠቀሱ ናቸዉ፡፡
  • ኑሮዉን ለሀያ ሁለት ዓመታት በሃገረ አሜሪካ በማድረግ በኢትዮጵያ የነበረውን ጭቆና እና ሰብዓዊ መብት ረገጣን በመቃወም የሚታወቀው አክቲቪስት አርቲስት ታማኝ በየነ ወደ ሃገሩ ተመልሰ፡፡
 

አስተያየት