ነሐሴ 27 ፣ 2012

ሁለት ሴትና አንድ ወንድ ኢትዮጵያዊ አትሌቶችን የሚያሳትፈው የፕራጉ የግማሽ ማራቶን ውድድር

ወቅታዊ ጉዳዮችዜናዎች

አስር ወንድና ዘጠኝ ሴት አትሌቶችን የሚያሳትፈው የፕራጉ የግማሽ ማራቶን ውድድር ሁለት ሴትና አንድ ወንድ አትሌቶችን በማሳተፍ በፊታችን ቅዳሜ ነሐሴ 30,…

ሁለት ሴትና አንድ ወንድ ኢትዮጵያዊ አትሌቶችን የሚያሳትፈው የፕራጉ የግማሽ ማራቶን ውድድር
አስር ወንድና ዘጠኝ ሴት አትሌቶችን የሚያሳትፈው የፕራጉ የግማሽ ማራቶን ውድድር ሁለት ሴትና አንድ ወንድ አትሌቶችን በማሳተፍ በፊታችን ቅዳሜ ነሐሴ 30, 2012 ዓ.ም ለየት ባለ ይዘት እንደሚካሄድ የውድድሩ አዘጋጆች ተናገሩ። ራን ቼክ (RunCzech) በተሰኘው ድርጅት የሚዘጋጀው የግማሽ ማራቶን ውድድር ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያንና በኬንያውያን አትሌቶች መካከል የሚደረግ ሲሆን ይህንን ለማድረግ የተመረጠበት ምክንያት የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ አትሌቶችን ማወዳደር ባለመቻሉ እንደሆነ ከድርጅቱ ድህረ ገፅ መረዳት ይቻላል። በውድድሩ ኢትዮጵያን በመወከል አትሌት ነፃነት ጉደታና አትሌት ሰንደሬ ተፈሪ በሴቶች የሩጫ ዘርፍየሚወዳደሩ ሲሆን በወንዶች ደግሞ በብቸኝነት ኢትዮጵያን የሚወክለው አትሌት አንዱአምላክ በሀይሉ በርታ እንደሆነ የተለያዩ በውድድሩ አዘጋጆች ድህረ ገፅ ላይ የሚገኙ መረጃዎች ያሳያሉ። ውድድሩ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ጋር በተያያዘ ተሰርዞ የነበረ ቢሆንም ከውድድሩ ተወዳጅነት የተነሳ የሩጫ ውድድሩን ከመሰረዝ ይልቅ በተለየ መልኩ ለማካሄድ እንደተወሰነ የውድድሩ አዘጋጆች ተናግረዋል። ውድድሩ 1,200 ሜትር ርቀት ባለው አካባቢ የሚደረግ ሲሆን አትሌቶቹ ይህን ርቀት 16.5 ጊዜ በመዞር የሩጫ ውድድሩን እንደሚያደርጉ ዘገባው አክሎ አስቀምጧል። ኔድያን ራኒንግ ማጋዚን (Canadian Running Magazine) በትላንትናው እለት እንዳስነበበው ከሆነ የፕራግ ግማሽ ማራቶን ሬከርድ በወቅቱ በኢትዮጵያዊቷ አትሌት ነፃነት ጉደታ የተያዘ ሲሆን አትሌቷ ቅዳሜ በሚደረገው ውድድር ላይ ይህን ሬከርድ ያሻሽላሉ ተብለው ከሚጠበቁ አትሌቶች መካከል አንዷ ነች። አትሌቷ የግል ምርጥ ሰዓቷ 1 ሰዓት ከ5 ደቂቃ ከ45 ሴኮንድ ሲሆን ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊ አትሌት ሰንደሬ ተፈሪ ከተወዳዳሪዎቹ አምስተኛው ምርጥ ሰዓት እንዳላት ዘገባው ያስረዳል። ከሁለቱ አትሌቶች በተጨማሪ ጆዋን ቺሌሞንና ቪብያን ቺፕኪሩይ ጨምሮ ሰባት ኬንያውያን አትሌቶች በውድድሩ ላይ እንደሚሳተፉ መረጃው ያስረዳል።በወንዶች ዘርፍ በሚካሄደው የግማሽ ማራቶን ውድድር ኢትዮጵያን በብቸኝነት የሚወክለው አትሌት አንዱአምላክ በሀይሉ የግል ምርጥ ሰዓቱ 59 ደቂቃ ከ10 ሴኮንድ ሲሆን በፊታችን ቅዳሜ ከሚወዳደሩት አስር አትሌቶች መካከል አራተኛው ምርጥ ሰዓት እንዳለው ከኔድያን ራኒንግ ያወጣው መረጃ ያስረዳል። ከአትሌት አንዱአምላክ ጋር ስቲፈን ኪፕሮፕ፣ ኪቢዎት ካንዲና በርናርድ ኪሜሊን ጨምሮ አስር ኬንያውያን አትሌቶች በቅዳሜው ውድድር ላይ እንደሚሳተፉም ከመረጃው መገንዘብ ይቻላል። ውድድሩ በሴቶች ዘርፍ ቅዳሜ ነሐሴ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ከጠዋቱ 3፡30 የሚካሄድ ሲሆን የወንዶቹ የግማሽ ማራቶን ውድድር ደግሞ ከቀኑ 7፡20 እንደሚካሄድ የውድድሩ አዘጋጆች የገለፁ ሲሆን አክለውም ውድድሩ በአዘጋጆቹ የዩትዩብ (YouTube) ቻናል ላይ መከታተል እንደሚቻል ገልፀዋል። የስፖርቱ አለም የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝን ተከትሎ በብዙ መልኩ አቀራረቡ ለመቀየሩ ትልቅ ማሳያ የሆነው በፊታችን ቅዳሜ የሚካሄደው የፕራጉ የግማሽ ማራቶን ውድድር ላለፉት 21 አመታት በሺዎች የሚቆጠሩ አትሌቶችን በማሳተፍ በየአመቱ የሚካሄድ ውድድር ነበር ። በ2011ና 2010 በተካሄዱት የፕራግ ግማሽ ማራቶን ውድድሮች ላይ ኬንያዊው በርናርድ ካሜሊ ለሁለት ተከታታይ አመታት ማሸነፍ የቻለ ሲሆን በ2009 ዓ.ም ኢትዮጵያዊው አትሌት ታምራት ሞላ ማሸነፉ ይታወሳል። በተጨማሪ በሴቶች የግማሽ ማራቶን የሩጫ ውድድር ላይ ያሸነፈች ኢትዮጵያዊ አትሌትን ለማግኘት ወደ 2007 ዓ.ም መመለስ የሚያሻ ሲሆን በወቅቱ አንድ ሰዓት ከሰባት ደቂቃ ከአስራ አራት ሴኮንድ በመግባት ያሸነፈችው አትሌት ወርቅነሽ ደገፋ ነበረች። ላለፉት አራት አመታት ኬንያ የፕራግ የሴቶች ግማሽ ማራቶን መቆጣጠር እንደቻሉ የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ።የፕራግ የወንዶች የግማሽ ማራቶች ውድድር ክብረወሰን ከ2004 ዓ.ም አንስቶ በኢትዮጵያዊው አትሌት አፀዱ ፀጋይ የተያዘ ሲሆን በወቅቱ አትሌቱ የሮጠበት ሰዓት 58 ደቂቃ ከ47 ሴኮንድ ነበረ። በሴቶች መካከል በሚደረገው የፕራጉ የግማሽ ማራቶን ውድድር ላይ በአንፃሩ ኬንያዊቷ የ27 አመት አትሌት ጆይሲሊን ጄፖስጌይ የተያዘ ሲሆን አትሌቷ ርቀቱን በአንድ ሰዓት ከአራት ደቂቃ እና ከአምሳ ሁለት ሴኮንድ ውስጥ በማጠናቀቅ የክብረወሰኑ ባለቤት እንደሆነች ከዝግጅቱ አዘጋጆች ድህረ ገፅ መረዳት ይቻላል። 

አስተያየት