ግንቦት 23 ፣ 2013

የኢትዮጵያዊቷ ዲዛይነር ስኬት

ባለሙያነትወቅታዊ ጉዳዮች

አንድ ሺህ ሰዎች ተሳታፊ በነበሩበት ውድድር ምርጥ 50 ውስጥ የገባች ብቸኛዋ ኢትዮጵያዊት ዲዛይነር ከአዲስ ዘይቤ ጋር ቆይታ አድርጋለች።

የኢትዮጵያዊቷ ዲዛይነር ስኬት

ኢትዮጵያዊቷ ዲዛይነር ማህሌት አፈወርቅ (ማፊ) የቶሚ ሂልፊገር ድንበር ተሻጋሪ የፋሽን ውድድር (the Tommy Hilfiger Fashion Frontier Challenge) ላይ ከምርጥ 50 ተወዳዳሪዎች መካከል አንዷ ሆናለች፡፡ በውድድሩ ከዓለም ዙርያ የተውጣጡ አንድ ሺህ ተወዳዳሪዎች ተሳትፈውበታል፡፡ የዘንድሮው (2021 እ.ኤ.አ) ውድድር ጥቁር ሥራ ፈጣሪዎችን ማጉላት እና መደገፍን ዓላማ በማድረግ የተዘጋጀ ነው፡፡ ማኅበረሰቦቻቸውን ከዘመኑ ጋር ለማራመድ በመትጋት ላይ ለሚገኙና የፋሽን ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ የሚሰሩትን ከፍ ማድረግ ተቀዳሚ አላማዬ ነው ብሏል፡፡ ከተሳታፊ አገሮች መካከል ካናዳ እና ጣሊያን ይጠቀሳሉ፡፡ ከተወዳዳሪዎቹ መካከል ደግሞ ታዋቂዎቹ ዲዛይነሮች ጆሹዋ አታት እና አኔት ማዚኒ ተሳትፈዋል፡፡

ማፊ በድረ-ገጽ ምዝገባ አካሂዳ፣ አዳዲስ እና ነባር ሥራዎቿን አቅርባ በተወዳደረችበት የፋሽን ኢንዱስትሪው ሜዳ የራሷን እና የሐገሯን ስም የሚያስጠራ ነጥብ በዚህ ወር መጀመሪያ በተገለጸው ውጤት አስመዝግባለች፡፡ የውድድር ሂደቱ ተጠናቆ ዋናው አሸናፊ ባይለይም አንድ ሺህ ሰዎች ተሳታፊ በነበሩበት ውድድር ምርጥ 50 ውስጥ የገባች ብቸኛዋ ኢትዮጵያዊት ለመሆን በቅታለች ዲዛይነሯ የራሷን እና የሐገሯን ስም ከ50 ምርጥ ወጣት የዲዛይን ባለሙያዎች ተርታ ማሰለፏ ለራሷ እና ለሐገሯ የሚያስገኘውን ጠቀሜታ አስመልክቶ ከአዲስ ዘይቤ ጋር ቆይታ አድርጋለች።

“ይህ ውድድር ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ምርጥ 50 ውስጥ የገባ ኢትዮጵያዊ የለም፡፡ የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት በመሆኔ ደስ ብሎኛል፡፡ ውድድሩ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ አሸናፊ መሆን ባይቻል እንኳን 50 ውስጥ መግባት ቀላል ውጤት አይደለም” ስትል ለአዲስ ዘይቤ ተናግራለች፡፡

ቶሚ ሂልፈር ማን ነው?

በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር በ2018 የተጀመረው የቶሚ ሂልፊገር ድንበር ተሻጋሪ የፋሽን ውድድር (the Tommy Hilfiger Fashion Frontier Challenge) በዓለም ዙርያ ያሉ በፋሽን ዘርፍ ጠንካራ የፈጠራ አቅም እና ተፅእኖ ያላቸው የፋሽን ባለሙያዎችን አግኝቶ የሚያወዳድር እና የሚያበረታታ ዓመታዊ ፕሮግራም ነው። በውድድሩ ጥሩ ደረጃ ማግኘት የቻሉ ተወዳዳሪዎች ከስልጠና እስከ ገንዘብ ድጋፍ ያገኛሉ፡፡

የውድድሩ መስፈርት

በዚህ ውድድር ላይ የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎች ከተመረጡበት መስፈርት መካከል ልዩ ልዩ የሸማቾችን ፍላጎት የሚያሟላ እና ተደራሽ የሚሆን ምርቶችን ማቅረብ መቻልና ቀለል ላለ የአኗኗር ዘይቤ የሚመጥን ምርቶችን ማሳደግ የሚሉት ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ስራ ፈጣሪዎቹ የሚያምኑበትን ነገር አቅርበው ላቀረቡለት አካል ማሳመን የሚችሉ መሆን እንደሚጠበቅባቸውም አወዳዳሪ ድርጅቱ ይገልፃል።

የአሸናፊዎች ሽልማት

ወደመጨረሻው ዘር የሚያልፉ ተሳታፊዎች ውድድሩን ለመዳኘት በተመደቡት ዳኞች አብላጫውን ድምጽ ሲያገኙ የ2መቶ ሺህ ፓውንድ ሽልማት ያገኛሉ፡፡ በኢንተርኔት በሚካሄድ የድምጽ አሰጣጥ ስርአት የታዳሚዎችን ድምጽ የሚያገኙት ደግሞ 15ሺህ ፓውንድ ይሸለማሉ፡፡ አሸናፊ ተወዳዳሪዎች በገንዘብ ከሚያገኙት ሽልማት በተጨማሪ አወዳዳሪ ድርጅቱ የሚያዘጋጀውን የአንድ ዓመት ሙያዊ ስልጠና የመሳተፍ እድል ያገኛሉ፡፡ የቶሚ ሂልፈር የምርት ማኅበር ተደራሽ የሚሆንባቸው የንግድ ትስስሮች ውስጥ መግባታቸው ደግሞ ሌላኛው በውድድሩ የሚያገኙት ተጠቃሽ እድል ነው፡፡ በ Institut européen d'administration des affaires (INSEAD) ማኅበራዊ ሥራ ፈጠራ መርሃ-ግብር ላይ ቦታ የማግኘት እድሎችንም ያገኛሉ፡፡

በዚህ ትልቅ ዓለም አቀፍ የፋሽን ዲዛይነሮች ውድድር ላይ በመሳተፍ 50ዎቹ ውስጥ መግባት በመቻላችን ትልቅ ክብር ነው፡፡ ዲዛይነር ማሕሌት ድርጅቷን ማፊ-ኢቲን በመወከል በአዲስ ዘይቤ በኩል ባስተላለፈችው መልእክት “አሁንም ውድድሩ አላለቀም፡፡ ማበረታቻችሁ፣ መልካም ምኞታችሁና ድጋፋችሁ አይለየን” ብላለች፡፡ አዲስ ዘይቤ የመጨረሻዎቹ ምርጥ 6 ተወዳዳሪዎች ውስጥ ገብታ ለራሷና ለሐገሯ ውጡት እንድታስመዘግብ መልካም ምኞቷን ትገልጻለች፡፡

አስተያየት