የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሃገር ህልውና እና ሉዐላዊነት ላይ የተደቀነን አደጋ ለመከላከል የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 5/2014 እንዲነሳ ወሰነ።
ከጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በስራ ላይ የዋለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነው የሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲነሳ የወሰነው።
“የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማውጣት የግድ አስፈላጊ እንዲሆን አድርጎ የነበረው ሁኔታ የተቀየረ በመሆኑ እና ስጋቱን በመደበኛው የሕግ ማስከበር ስራ መከላከልና መቆጣጠር የሚቻልበት ደረጃ ላይ በመደረሱ ለስድስት ወራት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተፈፃሚነት ጊዜ ማሳጠር አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።” ሲል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ገልጿል።
በመሆኑም የአዋጁን ተፈጻሚነት ቀሪ እንዲያደርገው የሚጠይቅ የውሳኔ ሃሳብ ቀርቦ በውሳኔ ሃሳቡ ላይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በጥልቀት ተወያይቶ በማጽደቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሚኒስትሮች ምክር ቤት 2ተኛ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ወስኗል፡፡
በአዋጅ ቁጥር 1264/2014 አንቀጽ 11(2) በተደነገገው መሰረት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስድስት ወራት የጊዜ ገደቡ ከመጠናቀቁ በፊት ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጅ ምክንያት የሆኑ ሁኔታዎች ከተቀየሩ እና በመደበኛው የሕግ ማስከበር ስርዓት ሊከሰቱ የሚችሉ ጉዳዮችን መቆጣጠር ይቻላል ብሎ ካመነ የስድስት ወር ጊዜው ሳይጠናቀቅ ጊዜውን የማሳጠር ስልጣን አለው።
አሁን በመተግበር ላይ የሚገኘውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ያስገደደው ሁኔታ በመቀየሩ እና ስጋቱን በመደበኛዉ የህግ ማስከበር ስራ መከላከልና መቆጣጠር የሚቻልበት ደረጃ ላይ በመድረሱ ለ6 ወራት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተፈጻሚነት ጊዜ ማሳጠር አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ብሏል የሚኒስትሮች ምክር ቤት።