ወ/ሪት ቅድስት ተፈራ የአዲስ አበባ ነዋሪ ስትሆን በተደጋጋሚ ወደ ድሬዳዋ የሚያመላልስ ጉዳይ አላት። ለጉዞዋ ሀገር አቋራጭ አውቶቡሶችን ትጠቀማለች። ከጉዞ ልምዷ በሐገር አቋራጩ ረዥም ጉዞ ለምሳ የሚመደበው ሰዓት አነስተኛ እንደሆነ ታዝባለች። በሰዓቱ ማጠር ምክንያት ጥቂት የማይባሉ ተጓዦች የሚጓዙበት አውቶብስ ጥሏቸው በመሄዱ ለእንግልት ሲዳረጉ ተመልክታለች። በ2012 ዓ.ም. በራሷ ላይ የደረሰውን ክፉ ገጠመኝ እንዲህ አብራርታለች። “ለሦስት ጓደኞቼ ጋር በ‘ኢትዮ ባስ’ ከድሬዳዋ ወደ አዲስ አበባ እየተጓዝን ነበር። መተሃራ ላይ ለምሳ አረፍን። በልተን ስንመለስ ግን አውቶብሱ መሄዱ ተነገረን። በወቅቱ ለሦስታችን በተጨማሪ ሌሎች ሁለት ሰዎችም ነበሩ። በቅርብ ርቀት ዕያየነው ስለነበር በባጃጅ ለመከተል ሞከርን። ፍጥነት ስለነበረው ልንደርስበት አልቻልንም። ሌላ የሞላ አውቶብስ ለምነን፣ ቆመን ተጉዘን፣ ተጨማሪ ወጪ አውጥተን ነበር አዲስ አበባ የደረስነው”
አቶ ሙሴ ባሳለፍነው ሳምንት ከአዲስ አበባ ወደ ድሬደዋ በ‘ኦዳ ባስ’ ጉዞ እንደጀመረና ለምሳ ባረፉበት አውቶብሱ ጥሎት መሄዱን ይናገራል። ከምሳ በኋላ የወረደበት ቦታ ሲመለስ የመጣበትን አውቶብስ በማጣቱ በተጨማሪ ወጪ ሌላ አውቶብስ ተሳፍሮ ያሰበበት ስለመድረሱ ገልጾአል። አውቶብሱ ላይ የጫነውን ምንም ሳይሆን ስለማግኘቱና ለተፈጠረው ችግር ይቅርታ የጠየቀው አካል አለመኖሩ ነገሩ ልክ ነው ተብሎ መታሰቡን እንዳስረዳው ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበረው ቆይታ ነናግሯል።
“ድርጅታችን ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ሕብረተሰቡን እያገለገለ ይገኛል” የሚለው የጎልደን ባስ የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ መስፍን አበበ ነው። በጉዞ መካከል ለምሳ የሚመደበው 30 ደቂቃ መሆኑንና ሰዓታቸውን በልዩ ልዩ ምክንያት ለማይጠብቁ ደንበኞች 15 ደቂቃ ተጨማሪ ሰዓት ይጣል ያሉ ሲሆን “ሹፌሮቻችን እና ረዳቶቻቸው መኪናው ከመንቀሳቀሱ በፊት መኪናው ያረፈበት አካባቢ እየተዘዋወሩ መኪናው ሊንቀሳቀስ መሆኑን ይናገራሉ” የሚል ማብራሪያ ሰጥተዋል።
አቶ መስፍን በቅርብ ጊዜ ያጋጠማቸውን ተያያዥ ገጠመኝ እንዲህ አስታውሰዋል። “በቅርቡ አንድ ደንበኛችን ለምሳ ወርዶ ዘገየብን። ትኬቱን ቀደም ብሎ ስላልገዛ ስልክ አላስመዘገበም። መጠበቅ ከምንችለው ሰዓት በላይ መቆየት ስለማንችል ለምሳ የቆምንበት ሆቴል መልእክት አስቀምጠንለት በሌላ ባስ እንዲመጣ አድርገናል” ብለዋል።
በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር አቶ አቤል ልዑልሰገድ አንድ መንገደኛ የአውቶብስ ትኬት (ደረሰኝ) ሲቆርጥ ከድርጅቱ ጋር ውል እንደገባ ይቆጠራል። ማንኛውም በግል ወይም በአክሲዮን የተቋቋሙ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶች የመንገደኛው ትኬት ላይ መነሻ እና መድረሻ ሰዓቱን በግልጽ ማስቀመጥ፣ ተሳፋሪው መጀመሪያ በተስማማበት ሰዓት ተገቢው ቦታ ማድረስ ግዴታ ገብቷል። ተሳፋሪውም በበኩሉ አስቀድሞ በድርጅቱ የወጣውን ፕሮግራም አክብሮ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል። የቁርስ፣ የምሳ ወይም የሻይ ሰዓት ካለ ይህንን የሚወስነው አጓጓዥ ድርጅቱ ነው። ተሳፋሪው ሕጉን የማክበር ግዴታ አለበት” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። እንደ ባለሙያው ሐሳብ ሁለቱ ወገኖች ስምምነታቸውን በግልጽ ተነጋግረው፣ ተማምነው ጉዟቸውን ከጀመሩ ከቀደመ ስምምነታቸው ያፈነገጠው አካል ተጠያቂ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ ሰፊ ነው።
በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ሚንስትር የህዝብና የጭነት ትራንስፖርት ዳሬክቶሬት ዳሬክተር አቶ ተፈራ ነጋ በተደጋጋሚ እንደዚህ ዓይነት ቅሬታዎች እንደሚቀርቡ አንስተዋል። “ማኅበረሰባችን መዘናጋት ይስተዋልበታል። የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ የምሳ ሰዓት መፍጀት የሚገባውን ደቂቃ የሚወሱኑት ሁሉንም ሰው ሊያማክል በሚችልና ይበቃል ብለው የሚያስቡትን ነው። መዳረሻቸውንም ታሳቢ ያደርጋሉ። በየቦታው የሚባክነው ደቂቃ የመዳረሻ ሰዓቱን አለመግፋቱ የሁለቱም ጥቅም ስለመሆኑም ተናግረዋል።
“በእርግጥ ተሳፋውን ከነእቃው ተገቢውን እንክብካቤ እያደረገ መውሰድ የድርጅቱ ኃላፊነት ነው። ይህ ሲባል ግን እነዚህ አውቶቡሶች ቁጥራቸው የበዛ ሰዎችን ስለሚያጓጉዙ ሁሌም የሚጠቀሙበት ሰዓት ስለሚመድቡ ተጠቃሚውም ያንን አምኖበት ትኬቱን ስለሚገዛ ሰዓቱን ማክበር ግዴታ ነው” ብለዋል።
በድሬደዋ ዩንቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ፣ የሕግና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሱራፌል ጌታሁን በጉዳዩ ለአዲስ ዘይቤ ማብራሪያ ሰጥተዋል። “በምሳ ሰዓት አንድ ሰው ቢዘገይ ያን ሰው የመጠበቅ እንዲሁም እቃውን የመጠበቅ ኃላፊነት የሐገር አቋራጭ የየብስ ትራንስፖርት ድርጅቱ ኃላፊነት ነው። ምክንያቱም ህመም ወይም ሌላ ግላዊ ችግር ገጥሞት ሊሆን ስለሚችል ጥሎ መሄድ አግባብነት የሌለው በሕጉም የሚያስጠይቅ ጉዳይ ነው።
በተጨማሪም ያሳፈረውን ግለሰብ አድራሻ፣ ስልክ ቁጥር የመያዝና የመጠየቅ ግዴታ አለበት። በእርግጥ ማኅበረሰባችን መብትና ግዴታውን ማጣራት ላይ ትኩረት አይሰጠውም። እንደዚህ ዓይነት ችግር ቢያጋጥመውም መጠየቅ ስላልለመደ ነው እንጂ በስነምግባር ጉድለት የሚያስጠይቅ ነገር ነው” ብለዋል። አቶ ሱራፉል መፍትሄ ያሉትን ሀሳብ ሲያቀርቡ አዋጅና ደንቦች ሲወጡ ለኅብረተሰቡ በማሳወቁ በኩል ሚዲያዎች ሰፊ ስራ ቢሰሩ እንዲሁም በትራንስፖርት ሴክተሩ ላይ የተሰማሩ የመንግስት ስራ አስፈፃሚዎች እንዲሁም ሕግ አስከባሪዎች ማለትም የትራንስፖርት ሚንስተሩና የትራፊክ ደህንነት ተናቦ መስራት ቢችል መልካም ነው ሲል ሀሳቡን ገልፁዋል።