ጥር 19 ፣ 2014

የአዳማ መናኸሪያ እድሳት መጓተት ተጓዦችን ለተጨማሪ ወጪ ዳርጓል

City: Adamaመልካም አስተዳደር

መናኸሪያው የራሱ አጥር የሌለው በመሆኑ ለቁጥጥር አስቸጋሪ ነው።

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

የአዳማ መናኸሪያ እድሳት መጓተት ተጓዦችን ለተጨማሪ ወጪ ዳርጓል
Camera Icon

Credit: Tesfalidet Bizuwork

በኦሮሚያ መንገድ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ባለቤትነት እየተገነባ የሚገኘው የአዳማ ከተማ አገር አቋራጭ ትራንስፖርት መናኸሪያ ስለመጓተቱ ተደጋግሞ ተነስቷል። ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ከተማዋ የሚገቡና ከከተማዋ የሚወጡ ተጓዦችን የሚያስተናግደው “ፍራንኮ” መናኸሪያ በእድሳት ላይ በመሆኑ “ሚግራ” እና “ፒኮክ” የአውቶቡስ መናኸሪያዎች በጊዜያዊነት አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ። በመስተዳድሩ በተለዋጭነት የተመደቡት ሕጋዊ የትራንስፖርት ማሰማሪያዎች ከሚሰጡት አገልግሎት በተጨማሪ ሌሎች ሕገ-ወጥ መናኸሪያዎች ስለመኖራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ይናገራሉ። ከመደበኛው የትራንስፖርት መናኸሪያ ውጭ አገልግሎት የሚሰጡት ተሽከርካሪዎች ድርጊቱን የሚፈጽሙት በሕጋዊው መናኸሪያ ቢገለገሉ የማያገኙትን ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ስለመሆኑ ሰምተናል። አዲስ ዘይቤ ያነጋገራቸው ተጠቃሚዎች እንደሚሉት ከመናኸሪያ ውጭ የሚጭኑት ተሽከርካሪዎች ከታሪፍ በላይ የሚያስከፍሉ፣ ባልተፈቀደ ሰዓት የሚጓዙ ናቸው።

ወንጂ ከአዳማ በስተደቡብ 15 ኪ.ሜ. ላይ የምትገኝ ከተማ ናት። በየእለቱ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆነ ተጓዦች በልዩ ልዩ ምክንያት ወደ አዳማ ይጓዛሉ። ለስራ፣ ለትምህርት፣ ለግብይት እና ለሌሎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ማለዳ ገብተው ምሽት የሚመለሱት የወንጂ ተሳፋሪዎች ሕጋዊውን መነኸሪያ ሳይሆን ለደህንነት አስጊ የሆነውን ነው። 

"ቦታው መንደር ውስጥ ያለ መንገድ ነው። በተለይ በክረምት ደግሞ ውሃ ስለሚይዝ ለመሳፈር አይመችም" ስትል በሕገወጥ መንገድ የወንጂ መስመር መኪኖች የሚጭኑበትን ቦታ የምትገልጸው ዳግማዊት ሰለሞን ናት። ተወልዳ ያደገችው በወንጂ ሸዋ ከተማ ነው። በአሁኑ ወቅት በአዳማ የኮሌጅ ትምህርቷን ትከታተላለች። ከታሪፍ በላይ ማስከፈል፣ የተሳፋሪ እንግልት፣ ጾታዊ ጥቃት እና ስድብ ከጭነት ልክ በላይ መጫን እና የመሳሰሉት ችግሮች እንዳሉበት የምትናገረው ዳግማዊት ሰለሞን መፍትሔ ቢበጅለት መልካም ነው ትላለች።

በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም ሮማን ሽሮ አካባቢ ወደ አሰላ፣ ዴራ እና አዋሽ መልካሳ ከንጋቱ 12 ሰዓት በኋላ ተሳፋሪ ሲጭኑ መመልከት እንግዳ ጉዳይ አይደለም። ይህ ቦታ አንዱ በተለምዶ ወደ መናኸሪያነት የተቀየረ “ሕገ-ወጥ” ቦታ ነው።

የአዳማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪው በኃይሉ ኢቲቻ ነዋሪነቱ አዋሽ መልካሳ ከተማ ነው። ማታ 2 ሰዓት ከትምህርት ሲመለስ ስለሚመሽ መናኸሪያ ይዘጋል። በዚህ ምክንያት ስታድየም አካባቢ የሚጭኑትን ተሽከርካሪዎች ይጠቀማል።

"በዚህ ቦታ መጫኑ ለእኛ የታክሲ ወጪ አቅልሎልኛል። ማታ መናኸሪያ ስለሚዘጋ እነኚህ መኪኖች በዚህ ቦታ ኖረው ባይጭኑ ተመላልሶ መማር የማይታሰብ ነው" ይላል። በሕገ-ወጥ መናኸሪያዎች ከታሪፍ በላይ በማስከፈል፣ መጉላላት እና ዝርፊያ ይከሰታል በሚል ተደጋጋሚ ቅሬታ ይሰማል ያልነው በኃይሉ ኢቲቻ" ይህ ችግር በመናኸሪያ ውስጥም ያለ ጉዳይ ነው። መናኸሪያ ውስጥም ከታሪፉ 12 ብር በላይ 15ብር ነው ምንከፍለው" ሲል የሕገ-ወጥነት ተግባሩ በሕገ-ወጥ መናኸሪያዎች ብቻ እንዳልሆነ ያስረዳል።

ሌላዋ በመናኸሪያዎች አገልግሎት ላይ ያወራናት በእምነት በለጠ በተደጋጋሚ ከአዳማ ወደ አሰላ ለቤተሰብ ጥየቃ እንደምትመላለስ ትናገራለች። በመደበኛ መናኸሪያዎች ላይ ያለው የአስተዳደር ብልሽት ለችግሩ መንስኤ ነው ትላለች። "ቀን ላይ መኪኖቹ ከመናኸሪያ ውጪ ተደብቀው ውለው ማታ ላይ ይመጡና ዋጋ ጨምረው ይጭናሉ" ብናላናለች። ረዥም ሰልፍ፣ ከታሪፉ 50 ብር  በላይ እስከ ሦስት እጥፍ 150 ብር ድረስ ያለ ክፍያ ማስከፈል፣ እንግልት ያጋጥማል የምትለው በእምነት በሕገ-ወጥ መንገድ የሚጭኑት ከመናኸሪያ ውጪ የሚጭኑት መኪኖች ከመደበኛው ታሪፍ 50 ብር ጨምረው እስከ 80ብር ቢያስከፍሉም እነርሱን ለመጠቀም እንደሚሻላት ትናገራለች። ምክንያቷንም ስታስረዳ "ከፍተኛ ክፍያ ከፍዬ አምሽቼም ከምጉላላ ውጪ ላይ ተሳፍሬ ብሄድ ቶሎ ወደ ቤቴ ገባለሁ"

ከአዲስ አበባ እና ሀዋሳ መስመር ህዝብ ጭነው የሚመጡ ተሽከርካሪዎች መናኸሪያ ሳይደርሱ ፖስታ ቤትን እንደመዳረሻ ይጠቀሙበታል። በዚህ ቦታ ቆመው "ድሬ-ደዋ ሐረር" እያሉ የሚጠሩ በተለምዶ “ጆካ” የሚባሉ ወጣቶችን መመልከት አዲስ አይደለም። ሐኒ ኬክ አካባቢ በመንገድ ላይ፣ በሆቴሎች እና በግለሰብ ቤቶች መጫን የተለመደ ነው።

"ድሬዳዋ ሆቴል አካባቢ በቀንም በማታም ወደ ድሬዳዋ፣ በዴሳ፣ ሐረር ሲጫን ዓያለሁ" የሚለው የታክሲ ሹፌሩ አህመድ መሃመድ  ነው። ማታ የሚጫነው ትራፊክም ስለሌለ ፒካፖች እና የቤት መኪኖችም ይጭናሉ። ቀን ቀን ግን ሚኒባሶች እንደፓርኪንግ ቆመው በጆካ ይጭናሉ ሲል ይናገራል። የቦታውን የመኪኖች እና የተጠቃሚዎቹ ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የሚናገረው አህመድ መሃመድ "አሁን ሕጋዊ እየመሰለ ነው የሚቆጣጠራቸው አካል ያለ አይመስልም” ሲል ትዝብቱን ነግሮናል።

በዋርካ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የታክሲ መጫኛ እና ማውረጃ  ቦታ ይገኛል። በዚህ ስፍራ ናማልድ እና ዱቄት ወደ ሚባል የከተማ ክፍል የሚሄዱ ሚኒባስ ታክሲዎች እንደ ፌርማታ ይጠቀሙታል። ከዚህ አካባቢ በተጨማሪ ወደ ሞጆ እና ቢሾፍቱ  ከተማ የሚሄዱ መኪኖችም እንደፌርማታ ይጠቀሙታል።

ከምሽት 11 ሰዓት በኋላ ማንኛውም ወደ አዲስ አበባ የሚሄድ ተሳፋሪ መኪና የሚጠብቀው ከፖስታ ቤት እስከ ዋርካ ባለው መንገድ ላይ ነው። በተለይም ከበደ ጭቋላ ህንጻ አካባቢ ገባ ብለው በሚቆሙ መኪኖች እንደመደበኛ መናኸሪያ ተከታትለው ቆመው ወረፋ ጠብቀው ወደ አዲስ አበባ ይጭናሉ።

በእነኚህ ቦታዎች የሚስተባብሩ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ወጣቶች ይታያሉ። በዚህ ቦታ ላይ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት የማይችሉ ኮድ 2 የቤት መኪኖች፣ ንብረትነታቸው የመንግስት የሆነ  ኮዶ 4 መኪኖች እንዲሁም አልፎ አልፎ ዓለም አቀፍ ድርጅት ኮድ ታርጋ የለጠፉ ተሽከርካሪዎችን መመልከት እንግዳ ጉዳይ አይደለም።

ዓለማየሁ ጎሳ ከአዲስ አበባ አዳማ መስመር ተሳፋሪዎች የሚያመላልስ አሽከርካሪ ነው። አሽከርካሪው እየደረሰበት ያለው ጫና ትኩረት አግኝቷል ብሎ እንደማያምን ይናገራል። "ለአንድ ጉዞ ከአዳማ አዲስ አበባ እስከ 200 ብር በመውጫ፣ የተራ አስከባሪ  እና የፍጥነት መንገድ ወጪዎች እናወጣለን" የሚለው ዓለማየሁ በመናኸሪያው ውስጥ ከፍተኛ መጉላላት እንደሚደርስባቸው ይናገራል። በመናኸሪያው አስተዳደር ተደጋጋሚ ቅጣቶች በአሽከርካሪው ላይ መጣሉ ተራ አስከባሪ ተብለው ማኅበራት የተደራጁ ወጣቶች የሚያደርሱባቸው ጫናዎች አሽከርካሪው ወጥቶ መጫን ቅጣት እንዳለው ቢያውቅም ወደዚህ አሰራር እንደሚገፉት ይናገራል። ሌላው የመናኸሪያ አስተዳደር ሰራተኞች ጠዋት በጊዜ ገብተው ስራ ቢጀምሩ ማታም ህዝብ እስካለ ድረስ ቢሰሩ ሕገ-ወጥ አስራሩ ሊቀር ይችላል ሲል ሀሳቡን ይደመድማል።

“በአሁን ወቅት የመለዋወጫ ዋጋ መናር፣ የነዳጅ ጭማሪ እና ሌሎችም ወጪዎች ለአሽከርካሪው ወጥቶ መጫን እና የታሪፍ ማሻሻያ አለመደረጉ አንድ ገፊ ምክንያት ነው” የሚለው ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ ከአዳማ አዲስ አበባ የሚሰራ አሽከርካሪ "ወጥቶ ሲጭን የሚያገኘው ትርፍ  ለአሽከርካሪው የሚጨምርለት ነገር ብዙም ባይኖርም እንደተራ እና የመውጫ ክፍያ ያሉ ክፍያዎችን ይሸፍንለታል" ሲል ይናገራል። አሽከርካሪው እንደሚለው ጨምረን ብንጭንም ገንዘቡ ለተራ አስከባሪ የሚውል ነው። “በሕገ-ወጥ መናኸሪያዎች ተራ አስከባሪዎቹ እስከ 250 ብር ድረስ ይቀበሉናል። የእኛ ጥቅም እጅግ አነስተኛ ነው። ከዚህ ይልቅ መናኸሪያዎች ውስጥ ያለው ወደ ውጪ የሚገፋ አሰራር ቢሻሻል መልካም ነው” ያለ ሲሆን የታሪፍ ማሻሻያ ተደርጎ በሕጋዊ መንገድ ቢሰሩ ለእነርሱም ጥሩ ነው ባይ ነው።

በጉዳዩ ዙርያ ያነጋገርናቸው የአዳማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የትራፊክ ኃላፊ ኮማንደር ዓለማየሁ በቀለ ችግሩ መኖሩን እንደሚያውቁና ተደጋጋሚ እርምጃ እየተወሰደ እንደሆነ ነግረውናል። የቀድሞው ፍራንኮ የሚገኘው መናኸሪያ ለእድሳት መዘጋት እና ወደ አዲስ አበባ እና ሌሎች ከተሞች የሚሰሩ መኪኖች ወደ ፒኮክ መናኸሪያ ከተዘዋወሩ በኋላ  ችግሩ እንደተስፋፋ ይናገራሉ።

"መናኸሪያው የራሱ አጥር የሌለው በመሆኑ ለቁጥጥር አስቸጋሪ ነው" የሚሉት ኮማንደር ዓለማየሁ የወንጂ ተራ በልዩ ሁኔታ ዕንደሚታይ ይናገራሉ። 

"የወንጂ ተራ ጉዳይ ከዚህ ቀደም ከተነሳው የፒኮክ መናኸሪያ ተራ አስከባሪዎች እና የወንጂ ሹፌሮች ጸብ እና በሕብረተሰቡ ጥያቄ ምክንያት የቀድሞ መናኸሪያ አካባቢ እንዲሰሩ ተፈቅዷል" ይበሉ እንጂ የመናኸሪያው እድሳት ሲጠናቀቅ ይህ እንደማይኖር ነግረውናል።

"ከመናኸሪያ ውጪ ሲጭን የተገኘ አሽከርካሪ እስከ 1000 ብር ድረስ ይቀጣል" የሚሉት ኮማንደሩ መኪኖች በጋራጆች መደበደቅ እና የትራንስፖርት ዋጋ ጭማሪ ሙከራ በሚያደርጉ ላይ አሽከርከሪው ብቻ ሳይሆን የአሽከርካሪ ማኅበራቱም ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ ነግረውናል። ሕብረተሰቡም ወደ መሰል ሕገ-ወጥ ስፍራዎች ከመሄድ መቆጠብ እና ከታሪፍ በላይ የሚያስከፍሉትን አሽከርካሪዎች ማጋለጥ ይገባዋል ሲሉ ፖሊስ የሕብረተሰቡን ድጋፍ እንደሚሻ ይናገራሉ።

"በግንባታ ላይ ያለው መናኸሪያ መጓተት የከተማውን የትራንስፖርት ዘርፍ አዛብቷል" የሚሉት የአዳማ ከተማ ትራንስፖርት ባለስልጣን ኃላፊ አቶ ታዬ ተሊላ ናቸው። ኃላፊው በአሁን ሰዓት የህገ-ወጥ መናኸሪያዎችን ለመከላከል የትራንስፖርት ስምሪት ከሚሰጠው የምስራቅ ሸዋ ትራንስፖርት ባለስልጣን ጋር በቅንጅት መዘገብ ተዘጋጅቶ በስምሪት ውስጥ ያሉትን በመለየት እርምጃ እየተወሰደ እንደሆነ ነግረውናል።

የመናኸሪያዎች በጊዜ መዘጋት ለዚህ አስተዋጽኦ አለው በሚል ለተነሳው የአሽከርካሪው አስተያየት ሲመልሱም "በተቀመጠው መመሪያ 

የእኛ ግዴታ ከንጋት 12 እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ነው። በሁለት ፈረቃ የሚሰሩት 30 ሰራተኞች ጠዋት 11 ሰዓት ገብተው ማታ እስከ 12:30 ድረስ ግፋ ሲልም እስከ1:30 ይሰራሉ” የሚሉት ኃላፊው ከዚያ በኋላ ያለው ኃላፊነት የከተማው ትራፊክ ፖሊስ ጽ/ቤት ነው። የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ከተሳፋሪዎች የሚነሱ የቅሬታዎችን በተመለከተ የትራንስፖርት ማሻሻያ ሪፎርም እየተተገበረ መሆኑን አንስተው አንዱ ነጥብ ተሳፋሪዎች የትራንስፖርት ክፍያን በመናኸሪያዎች ከፍለው እንዲወጡ ማድረግ ስለመሆኑ ነግረውናል።

በመናኸሪያ ግቢዎች ውስጥ ለሚነሳ ስርዓት አልበኝነትን ለመከላከል እና በአሽከርካሪዎች የተነሱትን ከተራ አስከባሪዎች ጋር ያለ አለመግባባትና የደህንነት ስጋት ባለስልጣኑ ለመከላከል ከከተማው አስተዳደር ጋር ተነጋግሮ ሁለት ሁለት የፖሊስ አባላት መመደባቸውን ነግረውናል።

“አዲሱ መናኸሪያ እስከሚጠናቅ እና ስራ እስኪጀምር ድረስ የአገልግሎቱን በማሻሻል እና ቁጥጥር በማድረግ ከሕጋዊ መናኸሪያዎች ውጪ ያለ አሰራርን ለማስቀረት እየሰራን ነው” በማለት ሀሳባቸውን ያጠቃልላሉ።

አስተያየት