በከተማዋ እምብርት የነበረው የአዳማ ከተማ አገር አቋራጭ መናኸሪያ ለሁለት ተከፍሎ ወደ ሚጊራ (በተለምዶ አሰላ መነኸሪያ) እና ፒኮክ (በተለምዶ አዲስ አበባ መነኻሪያ) ከተቀየረ በኋላ ለተወሰኑ ወራት የከተማው የትራፊክ መጨናነቅ ጋብ ያለ ቢሆንም ከሚኒባስ ታክሲዎች፣ ከባለሦስት እግር ተሽርካሪ (ባጃጅ)፣ የቤት መኪኖች እና ሌሎችም የተሽከርካሪ ዓይነቶች መጨመር ጋር በተያያዘ የትራፊክ መጨናነቁ በተለይም በስራ መግቢያና መውጫ ሰዓቶች ላይ ዕየታየ ነው።
በከተማዋ 3 የሚኒባስ ታክሲ ባለንብረቶችና 28 የባለሦስት እግር ተሽከርካሪ ባለንብረቶች ማኅበራት ይገኛሉ። የኮንፍረንስ ቱሪዝም መነኸሪያነቷ እንዲሁም በትራንስፖርት መተላለፊያነቷ ምክንያት በብዙ ጎበኚዎች የምትጎበኘው አዳማ በመንደሮቿ ጥበት ምክንያት የፓርኪንግ የእግረኛ መንገድ ችግር ይስተዋልባታል። ከጥቂት ወራት በፊት ከከተማዋ እምብርት ፖስታ ቤት እስከ ገልማ አባገዳ መሰብሰቢያ ድረስ የእግረኛ መንገድ ተገንብቷል።
ይህ የእግረኛ መንገድ ከዚህ ቀደም ይስተዋል የነበረውን ከአስፓልት ግራ እና ቀኝ እግረኛ ማለፊያ በቆሙ መኪኖች መዘጋት፣ ታክሲዎች እግረኛ መንገድ ላይ ገብቶ መጫንና ማውረድ፣ የተለያዩ እንደ ሬስትዎራንት፣ ስጋ ቤቶች እና ካፌዎች እግረኛ መንገድ ዘግቶ አገልግሎት መስጠት ችግርን በሚገባ ፈትቷል። የታክሲ መጫኛ እና ማውረጃ ቦታ ማጣት በታክሲ ሹፌሮች፣ የፓርኪንግ ቦታ በግል እና አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪ አሽከርካሪዎች ዘንድ ይሰማል። ሌላው በአዲሱ የእግረኛ መንገድ ላይ የተቀመጡት የአትክልት ማስቀመጫዎች እና የመቀመጫ አግዳሚዎች የህዝብ ማረፊያ ቦታ የላትም ለምትባለው እጅግ አበረታች ጅምር ሆኗል።
"መሄጃ እስከምናጣ ነበር መንገዱ የሚዘጋው" ስትል የችግሩን ጥልቀት የነገረችን የአዳማ ነዋሪዋ መሰረት ለታ አሁን ግን የእግረኛ መንገዱ በአዲስ መልክ በመገንባቱ የተሻለ ደህንነት ለእግረኞች እንደፈጠረና ለከተማዋም የተሻለ ውበት እንዳጎናጸፈ ለሪፖርተራችን ገልጻለች።
በአዳማ ከተማ በሆቴል ስራ ላይ ተሰማርቶ የሚገኘው የኤክስክዩቲቭ ሆቴል አስተዳደር የሆኑት አቶ ለገሰ እንደነገሩን፣ጥር 2013 ዓ.ም. ከከተማ አስተዳደሩ በደረሳቸው ጥሪ በአሁን ወቅት በግንባታ ላይ ያለውን ሁለተኛ ቅርንጫፍ ጨምሮ ብር 450 ሺህ ወጪ በማድረግ የእግረኛ መንገዱን በተሻለ ጥራት ማስገንባታቸውን ይናገራሉ። በዚህም ለከተማው በጨመረው ውበት እና ንጽህና እጅግ ደስተኞች ነን። በየቀኑ በአማካኝ እስከ 200 እንግዶች እንደሚያስተናግዱና እነሱም እጅግ ደስተኞች መሆናቸው ገልጸዋል።
ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የሚኒባስ ታክሲ አሽከርካሪ የሆነው ወጣት እንደሚለው ከሆነ የችግሩ ስር የከተማዋ መንገድ ጠብቦ መሰራቱ እንደሆነ ነው። መፍትሔው ህንጻዎቹን አፍርሶ ማስፋት ካልሆነ ሌላ ነገር እንደማይሆንና እሱን ማድረግ ከባድ ስለሆነ ጉዳዩ መፍትሔ አልባ እንደሆነ ይናገራል። ከአዲሱ የእግረኛ መንገድ ጋር በተገናኘ መሰራቱ ለከተማው ውበት እንደሰጠ ይናገራል። የታክሲ መጫኛ እና ማውረጃ ጋር በተያያዘ ግን ታስቦ አለመሰራቱ መኪና ደርቦ ሲጭን ወይም ሲያወርድ ለተደጋጋሚ ቅጣት መዳረጉን ይናገራል።
“ትልቁ ችግር ህንጸዎች መጀመሪያ ሲሰሩ ለተጠቃሚዎቻቸው የሚሆን የፓርኪንግ ቦታ ባለማዘጋጀታቸው ነው ችግሩ“ ይላሉ የንብ ሚኒባስ ታክሲ ባለንብረቶች አክሲዮን ማህበር ሊቀ-መንበር አቶ አህመድ መሀመድ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከተማዋ በ3 ማህበር ለተደራጁ ከ900 በላይ ለሆኑ ሚኒባስ ታክሲዎች እና በውስጣቸው 300 የባለሶስት እግር ተሽከርካሪ ባለንብረቶች ለያዙ 28 ማህበራት የሚሆን በቂ የሆነ የፌርማታም ሆነ ለፓርኪንግ የተወሰነ ቦታ አለመኖሩን ይናገራል፡፡
ከታክሲ ፌርማዎች አንጻር አሁን ባለው ሁኔታ ያለውን በቤት መኪኖች እንዲሁም በጭነት መኪኖች መዘጋት ችግር ለመቅረፍ ከትራንስፖር ባለስልጣን ጋር በመነጋገር ከታክሲ በስተቀር መቆም ክልክል ነው የሚል ታፔላ ቢቆምም ከጥቂት ቀናት መፍትሄ እና ከዘመቻ ስራ ያለፈ የቀየረው ስራ የለም ይላሉ፡፡ ይህ የመንዶች ፓርክ በተደረጉ መኪኖች መሞላት እና መጨናነቅ የታክሲ አገልግሎት ሰጪዎች ላይ ተሳፋሪ ካሰበው እና ከፈለገው ቦታ ውጪ በማውረድ የተጠቃሚን ሮሮ አሰስከትሏል፤ አሽከርካሪዎችን ደግሞ ለተደጋጋሚ ቅጣት ዳርጓል ይላሉ፡፡
እነኚህ እና ሌሎችንም ሀሳቦች ይዞ የአዲስ ዘይቤ አዳማ ሪፖርተር ወደ አዳማ ከተማ የትራንስፖር ባለሥልጣን ኃላፊ አቶ አብዲሳ ደደፎ አቅንቶ ነበር፡፡ በአዳማ ፓርኪንግ ችግር እና በአዲሱ የእግረኛ መንገድ ጉዳይ ሲናገሩ የፓርኪንግ ችግሩ መሰረታዊ መነሻ ከከተማ ፕላን ጋር የተያያዘ የመንገድ ጥበት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በአሁን ወቅት አንድም የፓርኪንግ ቦታ አለመኖሩ በከተማው የትራፊክ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጫና እንዳሳደረ እንደሚገኝ ነግረውናል፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ በቅርቡ ለታክሲዎች የሚሆን የፓርኪንግ ቦታ ከኤልሞ ቂልጡ ህንጻ ጀርባ ያለን ቦታ፣ ፖስታ ቤት አካባቢ የድሮ አሰብ ሆቴል ግቢን በአጭር ጊዜ መፍትሔነት እያዘጋጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከረጅም ጊዜ አንጻር ደግሞ ከማዘጋጃ ቤቱ ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን ነግረውናል፡፡ አዲሱ የእግረኛ መንገድ ከትራፊክ አደጋ እና ከፓርኪንግ ጋር ያለውን ችግር ያቃልል ዘንድ በትራንስፖር ባለስልጣን አስተባባሪነት 76 የትራፊክ ምልክቶች መተከላቸውን ይናገራሉ፡፡
በዓመት እስከ 30 ሚሊዮን ብር በትራፊክ ቅጣት የምትሰበስበው አዳማ ከፓርኪንግ ጋር የተያያዘው ምን ያህሉ እንደሆነ ባይታወቅም ችግሩ ግን አስቸኳይ መፍትሄ እነደሚሻ ብዙዎች ይጠቁማሉ።