ጥር 17 ፣ 2014

ድሬዳዋ ያፈራቻቸው የስፖርት ሰዎች

City: Dire Dawaማህበራዊ ጉዳዮች

በድሬደዋ ከተማ በርካታ የእግር ኳስ ክለቦች መገኛ ነበረች።

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራው

ዝናሽ ሽፈራው በድሬዳዋ የሚትገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነች።

ድሬዳዋ ያፈራቻቸው የስፖርት ሰዎች
Camera Icon

Photo Caption: Social Media

በድሬደዋ ከተማ በርካታ የእግር ኳስ ክለቦች መገኛ ነበረች። በተለይ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት በከተማዋ በሚገኙ የመኖርያ ሰፈሮች መካከል የሚካሄዱ ጨዋታዎች ከከተማዋ አልፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ያገለገሉ ተጨዋቾችን ለማፍራት ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ነበራቸው።  በከተማዋ የሚገኙ ትልልቅ ፋብሪካዎች የእግር ኳስ ክለቦች እያቋቋሙ ትልቅ መነቃቃት በመፍጠር በኩል ድርሻቸው የጎላ ነበር። ለምሳሌ ድሬደዋ ጨርቃ ጨርቅ፣ ኮካ ኮላ፣ ምድር ባቡር ስፖርት ክለቦች ይጠቀሳሉ። በዚህ ጽሑፍ ድሬዳዋ ያፈራቻቸውን ስመ ጥር የእግር ኳስ ተጫዋቾች በጥቂቱ እንመለከታለን።

Ì አስግድ ተስፋዬ

በብዙዎች ዘንድ “ፔሌ” በሚለው ቅጽል ስሙ ይታወቃል። የጨዋታ ዘመኑን ድሬዳዋ ኮካኮላ ክለብ በመጫወት የእግር ኳሱን ዓለም በይፋ ተቀላቅሏል።  የሦስት ክለቦችን ማልያ ለብሶ ለ16 ዓመታት ተጫውቷል።  ለቅዱስ ጊዮርጊስ አምስት ዓመት፣ ለመድን አምስት ዓመት እንዲሁም ለቡና ገበያ ለስድስት ዓመታት በድምሩ ለ16 ዓመታት እግር ኳስን በሀገሪቱ ታላላቅ ክለቦች በመጫወት ድንቅ የሚባል የማይዘነጋ የእግር ኳስ ጊዜ አሳልፏል።

ጋዜጠኛ ሰዒድ ኪያር የአሰግድ ተስፋዬን ህልፈት አስመልክቶ ሲዘግብ፡-

“እውነተኛ የኳስ ጀግና፣ የደቻቱ ፍሬ፣ የአሸዋው ሜዳ አብዶኛ፣ አጭሩ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ባለሟል፣ ቀንደኛው የጎል ሰው፣ ለድሬደዋ “ፔሌ” ለቅዱስ ጎርጊስ እና መድን “አለንዥሬስ”፣ ለኢትዮጵያ ቡና “ሮማርዮ” የነበረው የጎል ማሽን አሰግድ ተስፋዬ በሚወደው እግር ኳስ ህይወቱን ባሳለፈበት ሜዳ ጀምሮ እዛው እስትንፋሱን ጨረሰ” ማለቱ ይታወሳል።

“በእርሱ ዘመን ከተፈጠሩ አጥቂዎች በፍጥነት ዝግ ያለ ቢሆንም በአስተሳሰብ ፍጥነቱ ኮከብነቱን ደጋግሟል” ሲሉ ብዙዎች ይመሰክሩለታል። ከምስራቅ ኢትዮጵያ ኮከብነት አንስቶ እስከ ምስራቅ አፍሪካ ኮከብነት አንፀባራቂ የእግር ኳስ ህይወት አሳልፏል።

የሀያ ሦስተኛው የዩጋንዳ የምስራቅ አፍሪካ ዋንጫ የውድድሩ ኮከብ ግብ አግቢ ነበር። በሴካፋ ክለቦች ታሪክ ኢትዮጵያዊው ቀዳሚ ኮከብ ግብ አስቆጣሪም ነበር። በ1988 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ቻምፒዮንስ ሊግ ጥምር ግብ አስቆጣሪ እና የአዲስ አበባ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ጭምር ነበር።

የአርባ አንድ ዓመቱ ኢትዮጵያ ቡና የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ ዋንጫ ባለቤት ዋነኛ መንስኤ እሱ ነበር። የስልሳ ስምተኛው ደቂቃ የአዲስ አበባ ስታዲየም ድንቅ ግብ በማስቆጠር ክለቡን በአፍሪካ ደረጃ ለመጀመርያ ጊዜ ለቻምፒዮንስ ሊግ ክብር አብቅቷል። እንዲሁም በቀድሞ አጠራር ቡና ገበያ በአንድ ጨዋታ 5 ጎሎችን የሲሼልሱ ሴንት ሚሼልስ ላይ በኢንተርናሽናል ጨዋታ ያስቆጠራቸው ግቦች የማይዘነጉ ናቸው። በዚህም ኢትዮጵያዊው ሮማርዮ የሚል የአድናቆት መለያ ተሰጥቶት ነበር። በደቡብ አፍሪካ ክለቦች የመጫወት እድል አጋጥሞት በወቅቱ ከሀገሩ ውጪ መጫወት እንደማይፈልግ ገልፆ ነበር።

የአንዲት ሴት ልጅ አባት የነበረው አሰግድ ዘወትር ቅዳሜ እንደሚያደርገው የጤና ቡድን የእግር ኳስ ጨዋታ (ልምምድ) ካደረገ በኋላ መታጠቢያ ቤት ውስጥ እያለ በድንገት የመውደቅ አደጋ አጋጥሞት ህይወቱ አለፈ። የአሰግድን በድንገት መታጠቢያ ቤት ውስጥ መውደቅ ተከትሎ የገጠመውን አደጋ ለመታደግና ህይወቱን ለማትረፍ ወደ ሀያት ሆስፒታል ቢወሰድም ህይወቱን መታደግ ሳይቻል አሰግድ ተስፋዬ ትዝታውንና መልካም ስራዎቹን ብቻ ትቶልን በድንገት አሸልቧል።

በ1990ዎቹ በተለይ በቡና ገበያ ስፖርት ክለብ በሚያደርጋቸው ድንቅ እንቅስቃሴዎች፣ በግብ አይምሬነቱ የብዙዎችን ቀልብ የገዛው አሰግድ ተስፋዬ የጨዋታ ዘመኑ ከተጠናቀቀ በኋላም ከእግር ኳሱ ላለመራቅና በሙያው ለሀገሩ መልካም ነገር ሠርቶ ለማለፍ በማሰብ “አሰጌ ስፖርት አካዳሚ”ን በመክፈት የነገ የሀገር ተረካቢ ታዳጊዎችን እስከ ህልፈተ ህይወቱ ድረስ በማሰልጠን በእግር ኳሱ የራሱን አሻራ ለማስቀመጥ በብርቱ ጥሯል።

Ì አሸናፊ ግርማ

ተፈጥሮ እግርኳስ ጥበብን አትረፍርፋ ስጥታዋለች ይባልለታል።  ኢትዮጵያ ውስጥ ደምቀው ካበሩ የእግርኳስ ከዋክብት መካከል በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳል። ኢትዮጵያ ቡናንም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንንም በአምበልነት መርቷል። በአርጀንቲና በተካሄደው የወጣቶች ዓለም ዋንጫ የአሸናፊ ግርማን ያህል ደምቆ የታየ የለም እየተባለ ይነገርለታል።

በ1993 እና 1995 የኢትዮጵያ ፕርምየር ሊግ ኮከብ ተጨዋችነትን ክብር ተቀናጅቷል። አሸናፊ በአጭርም ረጅም ኳስም ደብልፓስ ለቡድን ጓደኞቹ ያለቀላቸው ኳሶችን በማቀበል፣ ከፈለገው አቅጣጫ ግብ በማስቆጠር፣ ያለምንም ድካም ሙሉ ሜዳ አካልሎ በመጫወትም ስም ያለው ተጨዋች ስለመሆኑ የእግር ኳስ ተከታታዮች ይመሰክሩለታል። አሸናፊ ከኮርና ቀጥታ ግብ አስቆጥሮ ያውቃል።  ምድር ባቡር ላይ ፌር ፕሌይ ይሰጠናል ብለው ሲጠብቁ የበረኛውን መውጣት ተመልክቶ ያስቆጠራት ጎልም አትረሳም።  የኢትዮጵያን የተጨዋቾች ሪከርድ በመስበር በ65ሺ ብር ቅዱስ ጊዮርጊስን ለአጭር ግዜ ቢቀላቀልም ወደ ቡና ገበያ ከ3 ወር በኋላ ተመልሷል። አሸናፊ ከቡና ገበያ እና  ከጊዮርጊስ ውጪ ለመብራት ኃይል፣ ለድሬደዋ ጨርቃጨርቅ፣ ለመድን፣ ለአየር ኃይል ስፖርት ክለቦች ተጫውቷል። በእግርኳሱ በግልም በቡድንም ትልልቅ ስኬቶችን አስመዝግቧል።

እግር ኳስን በክለብ ደረጃ መጫወት ባቆመበት ወቅት በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ደማቅ የሽኝት ፕሮግራም ተዘጋጅቶለት ነበር። የሽኝት ስነ-ስርዓቱ ላይም የመጽሐፍ እና የዘጋቢ ፊልም ዝግጅትን ጨምሮ የጎዳና ላይ ሩጫ እና በቀድሞ ክለቦቹ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ኢትዮጵያ ቡና መካከል የሚደረግ ጨዋታንም ያካተተ ነበር።

የአሸናፊ ግርማን የእግር ኳስ ታሪክ የሚዳስስ “ከአሸዋ ሜዳ እስከ አርጀንቲና” ፊልም ለዕይታ በቅቷል። በወቅቱ ፊልሙ በኢትዮጵያ በእግር ኳስ ተጫዋቾች ታሪክ ዙሪያ ከተሰሩ ስራዎች በዓይነቱ የመጀመሪያ ነው ተብሎለታል።  ፊልሙ ለሌሎች ስፖርተኞችም ታሪክን መዝግቦ የማስቀመጥ ልምድ እንዲቀስሙ በአርአያነት ሊወሰድ የሚገባው እንደሆነ ሲነገርለት ቆይቷል። ፊልሙ የአንድ ሰአት ከ14 ደቂቃ ርዝማኔ ያለው ሲሆን በዝግጅቱ ለተገኙ ታዳሚዎች አንድ የመግቢያ ትኬት በ100ብር ለሽያጭ ቀርቧል።  አሸናፊ ግርማ በአሁን ሰዓት የአበበ ቢቂላን የጤና ቡድን ያሰለጥናል።

  Ì ዮርዳኖስ ዓባይ

በድሬዳዋ ተወልዶ እስከ የመን ድረስ በደረሰው የእግር ኳስ ህይወቱ ከድሬዳዋ ጨርቃጨርቅ፣ መብራት ኃይል፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ በየመኑ አልሳክር እና ለኢትዮጵያ ታዳጊ እና ወጣት ብሔራዊ ቡድን በመጫወት ደማቅ ታሪክን ማፃፍ ችሏል። በ1993 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ኘሪሜየር ሊግ ውድድር በ26 ጨዋታዎች 24 ጎሎችን በማስቆጠር ለ16 ዓመታት ሪከርዱን በመያዝ ለብዙ ኢትዮጵያን ወጣት እግር ኳስ ተጫዋቾች እንደ ተምሳሌት የታየ እግርኳሰኛ ነበር።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከታዳጊዎች ጀምሮ በተለያዩ እርከኖች የተጫወተው ዮርዳኖስ በአርጀንቲና በተደረገው የወጣቶች ዓለም ዋንጫ ላይ የብሔራዊ ቡድኑን ማልያ ለብሰው ታሪክ ከሰሩ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነበር።

በየመን ሊግ ከአስር ዓመታት በላይ የጠጫወተው ዮርዳኖስ ዓባይ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኋላ ለተለያዩ ክለቦች ለጥቂት ጊዜ የተጫወተ ሲሆን የአሠልጣኝነት ስራንም ጀምሮ እንደነበር ይታወሳል። የናሽናል ሲሜንት እግር ኳስ ክለብ የቡድን መሪ ነበር።

Ì ተካበ ዘውዴ

ድሬደዋ ያፈራችው አንጋፋውና ተወዳጁ ተካበ ዘውዴ በኢትዮጵያ የበረኝነት ዘመን ከድሬደዋ የካቲት 66፣ ድሬደዋ ከነማ፣ ድሬደዋ ጨርቃ ጨርቅ እና ሐረርጌ ምርጥ እስከ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመጫወት ለሀገሩ ትልቅ አስተዋፆ አበርክቷል።

በ1980 ዓ.ም. በምስራቅና በመካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ ሁለት የፍፁም ቅጣት በማዳን፣ ሦስተኛውን ደግሞ የዙንባቤን ተጫዋች አርበትብቶ እንዲስት በማድረግ ኢትዮጵያን የዋንጫ ባለቤት ያደረገበት ጨዋታ ሁሌም ይታወሳል።

ተካበ ዘውዴ ወደ አሜሪካ ከተጓዘበት ከ1984 ዓ.ም. ጀምሮ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ስፖርት ፌደሬሽን በተጨዋችነት፣ አሰልጣኝነት፣ በቦርድ አባልነት እና ስራ አመራርነት ላለፉት 28 ዓመታት እያገለገለ ይገኛል።

አስተያየት