ፈረስ ከኢትዮጵያውያን የእለት ተእለት ኑሮ ጋር የተቆራኘ የረዥም ዘመን ታሪክ አለው። በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ብቻ ሳይሆን በጦርነት አውድማ ተሰልፈው ለአርበኞች ጀብዱ የማይናቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ በርካታ ፈረሶች አሉ። ፈረስ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የክብር መገለጫ ሆኖ አገልግሏል። እንደ አዊ ዞን ባሉ የመኖርያ አካባቢዎች ደግሞ ፈረስ አሁንም ድረስ ከማኅበረሰቡ ጋር የተቆራኘ ታሪክ አለው። በዓመታዊ የንግሥ በዓላት ወቅት ታቦታትን ለመሸኘት፣ የተጣላን ለማስታረቅ፣ የቀብር ስርአትን ለማጀብ፣ ትዕይንተ ህዝቦችን ለማድመቅ፣ ለእርሻ ሥራ፣ ለጭነትና ለመጓጓዣ ፈረስ ጥቅም ላይ ይውላል።
“አገው የፈረሰኞች ማኅበር” የብሔረሰቡ መገለጫ ከሆነ ሰነባብቷል። ረዥም እድሜ ያስቆጠረው ማኅበር በ1932 ዓ.ም. ከ30 ባልበለጡ አባላት እንደተመሰረተ ይነገራል። ከጣልያን ወረራ ማግስት በጥቂት አባላት የተመሰረተው ማኅበር ዛሬ ከ48,000 ሺህ በላይ አባላት አሉት። ማኅበሩ ከቀበሌ እስከ ዞን አደረጃጃት አንዳለው ከዞኑ ባህል እና ቱሪዝም መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል። እንደ ብሪታኒያ የፈረስ ስፖርት ኪስ የሚገባ ጥቅም ባያስገኝም፣ እንደ ቴቢት የፈረስ ድግስ ዓለምን ባያንጋጋም፣ እንደ ቱርክሜኒስታን የፈረስ ፌስቲቫል ባይደምቅም ወደ82 ዓመታት አስቆጥሯል።
አቶ ለይኩን ሲሳይ በአዊ ብሄረሰብ ዞን ባህልና ቱሪዘም ቢሮ የወጣቶች እና ስፖርት የመምሪያ ኃላፊ ናቸው። በአካባቢው ባህል ፈረሱም ፈረሰኛውም በጌጣጌጦች አምረው እንደሚቀርቡ ይናገራሉ።
“የተለያዩ ዝግጅቶች በሚኖሩበት ጊዜ ፈረሶቻቸውን በጌጣጌጦችና በአልባሳት ያደምቃሉ። በዚህም መጣምር (ከቆርቆሮና ከቆዳ የተሰራ ብር ቅብ የሆነ ጌጥ)፣ ፋርኔሳ (የፈረሱ የአንገትና ከጆሮ በላይ ጌጥ)፣ ውዴላ (ኮርቻውን በኋላ በኩል ሚይዘው)፣ እምቢያ ጉስም (ደረቱ ላይ የኮረቻው ቀዳዳ የሚይዘው) እና በኮርቻው ላይ መቀነቻ (ቀበቶ) ይደረግላቸዋል። በተጨማሪም ለኮ (የፈረሱ መሳቢያ)፣ ልጓም (የፈረሱ መሪ) እና ፈረሰኛው ሲቀመጥ ግራና ቀኝ እንዳይንሸራተት በእግሩ የሚረግጠው እርካብ ይጠቀሳሉ”
በተጨማሪም አንደ መምሪያ ኃላፊው ገለፃ በዞኑ ባህል ፈረሱን ያስጌጠው ፈረሰኛ ፊሳ (ለምድ ከዱር እንስሳት የሚገኝ ቆዳ)፣ ጀበርና (ፈረሰኛው ወገቡን የሚታጠቀው)፣ ገምባሌ (ለእግሩ/ባቱ መካላከያ)፣ የጉሽ ባርኔጣ፣ በጉግስ ውድድር ጊዜ ጋሻና አብሮት የሚገጥመው ሁለት መውጊያ ዘንጎችና ለፈረሱ ማባረሪያ ጉማሬ አለንጋ በመያዝ እንደሚዋብ ነግረውናል።
የአገው ፈረሰኞች ማኅበር የተለያዩ ማኅበራዊ ሁነቶችን በማጀብ በየዓመቱ በፌስቲቫል ይከበራል። ማኅበሩ በየዓመቱ ጥር 23 ዓመታዊ ብዓሉን በተለያዩ ዝግጅቶች ያከበራል። ዘንድሮም ለ82ኛ ግዜ በተለያዩ ክንዋኔዎች በድምቀት አንደሚከበር አቶ ለይኩን ነግረውናል።
በዚህ ዓመታዊ በዓል (ፊስቲቫል) ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የፈረስ ጉግስ እና ሽርጥ ውድድር ትዕይንት አንዱ ነው። ፈረሰኞች በፈረስ ጉግስ ወቅት ጋሻ በዘንግ እየሰበቁ በፈረስ ላይ ሆነው ይፎክረሉ። ስነ-ስርዓቱን የሚያስተባብሩት አጋፋሪዎች (የፈረስ አለቆች) ደግሞ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በመያዝ ስነ-ስርዓቱን ይመራሉ። ሲመሩም “አይሞሎ፣ የዳማ ጌታ፣ የቦራ ጌታ፣ የጥሪኝ ጌታ፣ እያሉ ፈረሱን እያሞገሱ በማቀንቀን መሆኑን ባህላዊ ክዋኔውን ያስረዱን በመምሪያ ኃላፊው ግልፀውልናል።
በስነ-ስርዓቱ ላይ ባህላዊ ምግቦችና መጠጦች በዓይነቱ ለታዳሚወች ይቀርባሉ። የማኅበሩ ዓባላት የሆኑት ሴቶች በፈረስ ጉግስና በሽርጥ ውድድር ጊዜ ብዙም በአይሳተፉም። በመስተንግዶው ከፍተኛውን ድርሻ አላቸው። የመስትንግዶው አቀራረብም እንደየመጡበት ቀበሌና ወረዳ በአካባቢው አጠራር በአቆልቋይ (አስተናጋጅ) አማካኝነት መሆኑን ከዞኑ መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።
አቶ እንግዳ ዳኛው የአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ ናቸው። ይህን ታሪካዊ ሁነት ምክንያት በማድረግ በመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ ማኅበሩ በዩኔስኮ አንዲመዘገብ እየጣሩ አንደሆነ ግለፀዋል። በሌላ መልኩ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በዘመናዊ መልኩ እየተከበረ አንደሚገኝ በመግለጫቸው አንስተዋል። ጥር 23 ቀን 2014 ዓ.ም. በእንጅባራ ከተማ 82ኛ ጊዜ ለሚከበረው ታሪካዊ የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ፊስቲቫል ሁሉም አንዲሳተፍ ጥሪ አቀርበዋል።
የአንጋፈው የአገው ፈረሰኞች ታሪካዊ ማኅበር አለቃ ጥላየ አየነው አንደተናገሩት ማኅበሩ በአሉን ለማክበር ዝግጅቱን አጠናቋል። (አለቃ ለማኅበሩ መሪ የሚሰጥ የክብር ስም ነው) በአካባቢው የሚገኘው የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ በዓሉን አስመልክቶ በተሰጠው መግለጫ የፈረሰኞች ማኅበር እና ሌሎች የአካባቢውን የቱሪዝም ፀጋዎች ለማልማት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግሯል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት እንደተናገሩት ማህበሩ በ2013 ዓ.ም. በሀገር አቀፍ ደረጃ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የማይዳሰስ ቅርስ ተብሎ መመዝገቡን አስታውሰው የዓለም ቅርስ ሆኖ በዩኔስኮ እንዲመዘገብ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በ1986 ዓ.ም. የተመሰረተው የአዊ ብሔረሰብ ዞን በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ከሚገኙት የብሄረሰብ ዞኖች አንዱ ነው። መልካም-ምድራዊ አቀማመጡ ከባህር ወለል በላይ ከ700-2920 ሜትር ከፍታ ያለው ሲሆን የቆዳ ስፋቱም 857,886 ሄክታር ነው። የአካባቢው ነዋሪዎች ኢኮኖሚ በግብርና ላይ የተመሰረተ ነው። በተለይ በማርና ቅቤ ምርት ይታወቃል። የአዊ ህዝብ በተለይ በደጋማ አካባቢዎች በፈረስ የማረስ ባህሉ የቆየ እና አሁንም ድረስ ከፈረስ ጋር ያለው ቁርኝት በእጅጉ የጠበቀ ነው። የዞኑ መናገሻ ከተማ አንጅባራ ከአዲስ አበባ በ445 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ የምትገኝ ሲሆን ከክልሉ ዋና ከተማ ባህር ዳር በ118 ኪ.ሜ. ትርቃለች።