የእስራኤል መንግስት የትንሳኤ በዓልን በሚያከብሩ ሃይማኖት ተጓዦች ላይ የጣለችውን እገዳ ማንሳቱን በእስራኤል የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታወቀ።
የሀገሪቱ መንግስት የቀደመውን የክልከላ ውሳኔ የሰረዘው በኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ በእየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ገዳም አባቶች እና የእስራኤል የፓርላማ አባል በሆኑት ጋዲ ይባርከን ጥረት መሆኑ ተጠቅሷል።
በእስራኤል የኢትዮጵያ ኤምባሲ በይፋዊ የማኀበራዊ ትስስር ገፁ (ፌስቡክ) እንዳስታወቀው “በእየሩሳሌም የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን ገዳም አባቶች ባቀረቡት አቤቱታ መሠረት፣ ኤምባሲያችን ከእስራኤል ጠቅላይ ሚ/ር ጽ/ቤት፣ ከእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚ/ር፣ ከሕዝብና ኢሚግሬሽን ጉዳይ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ከተለያዩ አካላት ጋር በተደረገው ተደጋጋሚ ምክክር ውሳኔው የሁለቱን አገራት ወዳጅነት አንጻር ተገቢ አለመሆኑን አስታውቀናል” ብሏል።
በጥረቱ የተሳተፉት አካላት ውሳኔው በመሻሩ የተሰማቸውን ደስታ እና ለእስራኤል መንግስትም ምስጋናቸውን ገልፀዋል።
መጋቢት 6 ቀን 2014 ዓ.ም. የእስራኤል የህዝብ እና የስደት ጉዳዮች ባለስልጣን ኢትዮጵያውያን በመንፈሳዊ ጉዞም ቢሆን ወደ እስራኤል እንዳይገቡ መወሰኑ በአዲስ ዘይቤ ተዘግቧል።
እገዳው ኢትዮጵያዊያኑን ተጓዦች ብቻ የሚመለከት ሲሆን የእገዳው ዋነኛ መንሳኤ በኢትዮጵያ ያለው “የእርስ በእርስ ጦርነት” ነው መባሉን በወቅቱ መቀመጫውን እየሩሳሌም ያደረገው ‘ታይምስ ኦፍ እስራኤል’ ዲጂታል ጋዜጣ አስነብቧል።
በተጨማሪም ወደ እስራኤል የሚገቡ ተጓዦችን የሚቀበሉ የአስጎብኚዎች ማኅበር ከውሳኔው በኋላ ለሀገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በፃፈው ይፋዊ ደብዳቤ “እስራኤል የምትከተለው የጉዞ ፖሊሲ በርካታ መገለሎችን እያደረሰ መሆኑን” ተችቷል። የአስጎብኚዎች ማኅበሩ አክሎም ውሳኔውን የተቃወሙ በኢትዮጵያ የሚገኙ በርካታ ሰዎች የመንግስት ባለስልጣናትን እየተቹ ነው ብሎም ነበር።
ውሳኔው በተላለፈበት ወቅት የእስራኤል የህዝብ እና የስደት ጉዳዮች ባለስልጣን ለእስራኤል አስጎብኚዎች ማኅበር በፃፈው ደብዳቤ እንዳስታወቀው “በኢትዮጵያ ያለውን የእስር በእርስ ጦርነት ተከትሎ ኢትዮጵያዊያን ወደ እስራኤል ከመጡ ወደ ሐገራቸው አይመለሱም የሚል ስጋት በመኖሩ” ለሀይማኖታዊ ጉዞዎች እንዳይገቡ ብሎ ነበር።
የዐብይ ፆም ማጠናቀቂያ የሆነው የትንሳኤ በዓል ጥቂት የማይባሉ የኢትዮጵያ እና የእስራኤል የጉዞ ወኪሎች ወደ እየሩሳሌም የሚደረጉ መንፈሳዊ ጉዞዎችን ያመቻቻሉ፡፡ በርካታ ኢትዮጵያዊያን የኦርቶክስ እምነት ተከታዮችም ወደ እስራኤል ይጓዛሉ።