መጋቢት 23 ፣ 2014

ከአማራ ክልል ባህርዳር የተጓዙ ተማሪዎች የግል ኮሌጆች ስለሞሉ መቸገራቸውን ተናገሩ

City: Bahir Darዜና

የግል ኮሌጆች ማህበር መረጃ እንደሚያመለክተው ልጆቻቸውን በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ወደሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ልከው የማስተማር ፍላጎት የሌላቸው ወላጆችም የግል ኮሌጆች በፍጥነት እንዲሞሉ አንድ አስተዋጽኦ አድርገዋል።

Avatar: Abinet Bihonegn
አብነት ቢሆነኝ

አብነት ቢሆነኝ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ምሩቅ ሲሆን። ዜና እና የተለያዩ ዘገባዎች የመፃፍ ልምድ አለው። አሁን በአዲስ ዘይቤ የባህር ዳር ሪፖርተር ነው

ከአማራ ክልል ባህርዳር የተጓዙ ተማሪዎች የግል ኮሌጆች ስለሞሉ መቸገራቸውን ተናገሩ
Camera Icon

ፎቶ፡ አብነት ቢሆነኝ

የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወስደው ውጤታቸው በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ያላስቻላቸው ተማሪዎች የግል ኮሌጆች በመሙላታቸው እንደተቸገሩ ተናገሩ። ከአምደ ወርቅ እና ከእንጅባራ ወደ ባህርዳር ተጉዘው በግል ኮሌጆች የመማር ተስፋ የሰነቁት ተማሪዎቹ የኮሌጆቹ የትምህርት መስክ አነስተኛ በመሆኑ የምርጫቸውን መስክ መማር አለማግኘታቸውን እና የተማሪው ቁጥር ከኮሌጆቹ የመቀበል አቅም በላይ በመሆኑ እንደተቸገሩ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

የግል ኮሌጆች ማኅበር መረጃ እንደሚያመለክተው ልጆቻቸውን በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ወደሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ልከው የማስተማር ፍላጎት የሌላቸው ወላጆችም የግል ኮሌጆች በፍጥነት እንዲሞሉ አንድ አስተዋጽኦ አድርገዋል።

ከዋግ ህምራ ብሔረሰብ ዞን ዳህና ወረዳ የመጣችው ተማሪ ትርንጎ ጌታሁን የዩኒቨርሲቲ የመግቢያ ውጤቷ 254 በመሆኑ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች መግባት አላስቻላትም። ከአባቷ አቶ ጌታሁን ታደሰ ጋር ወደ ባህርዳር ያቀናችው የግል ኮሌጅ ተመዝግባ ትምህርቷን ለመከታተል ነው። “መማር የምፈልገው ፋርማሲ ነበር። አብዛኛዎቹ የጤና ኮሌጆች ሞልተዋል። ምን መወሰን እንዳለብኝ ግራ ገብቶኛል” ብላናለች።

አባቷ አቶ ጌታሁን በበኩላቸው ልጃቸውን ለማስመዝገብ በተዘዋወሩበት ወቅት የዩኒቨርሲቲ የመግቢያ ውጤት አምጥተው በሌሎች ክልሎች የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ልንመደብ እንችላለን በሚል ስጋት ባህርዳር ከተማ በሚገኙ የግል ኮሌጆች ሲመዘገቡ መመልከታቸውን ነግረውናል።  

ሌላዋ የኮሌጅ ምዝገባ ወረፋ በመጠበቅ ላይ እያለች ያገኘናት አስተያየት ሰጪአችን ትእግስት አንዷለም የባህርዳር ከተማ ነዋሪ ነች። የማትሪከ ውጤቷ ዩኒቨርሲቲ መግባት የሚያስችላት ቢሆንም ወቅታዊውን ሁኔታ ፈርታ ባህርዳር ከተማ በሚገኙ የግል ኮሌጆች ለመማር መወሰኗን ትናገራለች። "አምና መቐለ ዩንቨርሲቲ ይማር የነበረው ታላቅ ወንድሜ በጣም ተንገላቷል። እኔ እንኳን እሺ ብል ቤተሰቦቼ ከአጠገባቸው እንድርቅ በፍጹም አይፈልጉም" ብላናለች።

ማጥናት የምትፈልገው ኬሚካል ኢንጅነሪንግ ወይም ሌሎች የምህንድስና ዘርፎችን ቢሆንም አብዛኛዎቹ ኮሌጆች የቢዝነስ ፊልዶችን  ብቻ የሚሰጡ በመሆናቸው መቸገሯንም ትናገራለች።

በባህርዳር ከተማ የዲግሪ ፕሮግራም እንዲያስተምሩ ፈቃድ የተሰጣቸው 12 የግል ኮሌጆች ይገኛሉ። ከክልሉ ስራና ስልጠና የተገኘው መረጃ እንደተቀመጠው ኮሌጆቹ ዘጠኝ ዓይነት ኮርሶችን የሚሰጡ ሲሆን ሁሉም ኮርሶች የጤና እና የቢዝነስ ኮርሶች መሆናቸው ተነግሯል። 

በአልካን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝዳንት አቶ አማረ ህሩይ "በአለፉት 4 ዓመታት የተማሪዎች ቁጥር አጅግ ጨምሯል” ያሉ ሲሆን “በዚህኛው ዓመት የጤና ዲፓርትመንቶችን ምዝገባ ያጠናቀቅነው በግማሽ ቀን ነው። የፋርማሲ እና ነርስ የትምህርት ክፍሎቻችን ሞልተዋል” ብለዋል። ከሌሎች ዓመታት በተለየ አብዛኛዎቹ የክልሉ ተማሪዎች የማለፊያ ነጥብ ያመጡትም ትምህርታቸውን በግል ተቋማት መከታተል መምረጣቸውን የታዘቡት አቶ አማረ የትምህርት መስክ አማራጩ ማነስ እና ቦታ አለመኖር ፈተናዎች እንደሆኑባቸው መመልከታቸውን አካፍለውናል። 

በአጠቃላይ በአማራ ክልል ከ60 በላይ የግል ኮሌጆች ፈቃድ ወስደው በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው። ኮሌጆቹ በየዓመቱ ከ70 ሺህ በላይ የሰው ኃይል እንደሚያስመርቁ ከግል ኮሌጆች ማኅበር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

አቶ ዓለማየሁ ይሁኔ በአማራ ክልል የግል ኮሌጆች ማኅበር ፕሬዝዳንት ናቸው። የትምህርት መስኮቹ ውሱን ናቸው የሚለውን የተማሪዎቹን ስጋት ይጋራሉ። “የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአቅም ውሱንነት አለባቸው። በዚህም ምክንያት ቀዳሚ ትኩረታቸው አዋጭነት ነው” የሚሉት አቶ ዓለማየሁ ኮሌጆች ከተፈቀደላቸው ቁጥር በላይ መቀበላቸው ከማስቀጣትም አልፎ የትምህርት ጥራቱን እንደሚቀንስ ነግረውናል።

በአማራ ክልል የሥራ እና ክህሎት ቢሮ የተቋማት ብቃት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሙላው አበበ “በድግሪ የሚሰለጥኑ ኮሌጆች እና ዩኒቨርሲቲዎች ግንኙነትታቸው ከፌድራሉ ከፍተኛ ትምህርት ጥራት አግባባት ኤጀንሲ ጋር ነው" ብለዋል።

በሀገር አቀፍ የፈተናዎች ኤጀንሲ ከ20ሺህ በላይ የተማሪዎች ቅሬታ ላይ ምላሽ መሰጠቱን ቢገልፅም በአማራ ክልል የተማሪዎችን ውጤት በተመለከተ የተነሳው ቅሬታ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ አልተፈታም።

በአማራ ክልል በ2014 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ 161 ሺህ 325 ተማሪዎች መካከል የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ያመጡት 18 በመቶ ያህሉ ብቻ መሆናቸው ተዘግቧል። የፌድራል ፈተናዎች ኤጀንሲ ደግሞ አጠቃላይ ፈተናውን ከወሰዱ ተማሪዎች ውስጥ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ያመጡት 25 በመቶ ብቻ መሆናቸውን ማሳወቁ ይታወሳል።

መግለጫው አያይዞ በሀገሪቱ ከሚገኙት ዩኒቨርሲቲዎች አራቱ ትግራይ ክልል በመሆናቸው በጦርነቱ ምክንያት አገልግሎት አይሰጡም። በያዝነው ዓመት ተማሪዎች እንደሚቀበሉ የሚጠበቀው 43 ያህሉ ብቻ ናቸው።