የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ወደ ሥልጣን መምጣት ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ ፖለቲከኞች መካከል አቶ ገላሳ ዲልቦ አንዱ ነበሩ። በ1983 ዓ.ም. በተካሄደው የሽግግር መንግሥት ተሳትፎ ከነበራቸው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አመራሮች እና የፖለቲካ ቢሮ አባላት ማለትም ሌንጮ ለታ፣ ጣሃ አብዲ፣ ታደሰ ኤባ (ዶ/ር)፣ ዲማ ነገዎ፣ ዱጋሳ በከኮ፣ ዳውድ ኢብሳ ውስጥ አንዱ ናቸው።
በፖለቲካው ዓለም የአንድ ጎልማሳ እድሜ ያሳለፉት አንጋፋ ፖለቲከኛ ባደረባቸው ድንገተኛ ህመም በሞት መለየታቸው እስከተሰማበት ቀን ድረስ በህዝብ ተወካዮች ምክር-ቤት የኢንዱስትሪ እና ማእድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ ሆነው አገልግለዋል።
ከ26 ዓመታት የስደት ትግል በኋላ ታህሳስ 20 ቀን 2011 ዓ.ም. አዲስ አበባ የገቡት ገላሳ ዲልቦ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል አዲስ አበባን ሲረግጡ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ “ይህ ትልቅ መስዋእትነት ተከፍሎ የተገኘውን ድል እና ኦሮሞን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ብሔሮች ያኮራ ለውጥ ወደ ኋላ እንዲመለስ አንፈልግም” በሚለው ንግግራቸው ብዙዎች ያስታውሷቸዋል።
በስደት ከሚኖሩበት ለንደን የጠ/ሚ ዐቢይ አህመድን ጥሪ ተከትለው አዲስ አበባ ከመሄዳቸው በፊት በጀርመን ፍራንክፈርት ከወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየው እና ከአምባሳደር ኩማ ደመቅሳ ጋር ስለመወያየታቸው በወቅቱ የወጡ መረጃዎች ያስረዳሉ።
አቶ ገላሳ የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ጎላኦዳ ቁምቢ መልካ በሎ ወረዳዎችን በመወከል በ2013 ዓ.ም. በተካሄደው 6ኛው ሐገራዊ ምርጫ በግል ተወዳዳሪነት ተሳትፈዋል። በህዝብ ተመርጠው የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባል መሆን ችለዋል።
በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት እንዳለው የሚነገርለት ኦነግ ከ1998 እኤአ ወዲህ በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራ፣ በጄነራል ከማል ገልቹ የሚመራ ተብሎ ሲከፈል አንዱን ኃይል ገላሳ ዲልቦ መርተውታል።
የትግል ቡድኑ በተበታተነ ሁኔታ ህቡእ የትግል ስልት ሲያካሄድ ረዥም ዓመታት ቢያልፉም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በሚል ስያሜ በይፋ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴውን የጀመረው በ1973 እ.ኤ.አ ነው። ግንባሩ ከ45 ዓመታት በላይ ባስቆጠረ ጉዞው የኦሮሞ ብሔርተኝነትን ትግል ወደ ላቀ ደረጃ አድርሷል በሚል ስሙ በበጎ ይነሳል።
ዋነኛ ዓላማዬ የብሔር ጭቆናን ማስቀረት ነው ብሎ የተነሳውን አንጋፋ ድርጅት ከ1989 – 1998 እኤአ አቶ ገላሳ ዲልቦ በሊቀመንበርነት መርተውታል።
ከገላሳ ዲልቦ በፊት ዲማ ነገዎ እና በሶማልያ መንግሥት እንደተገደሉ የሚነገረው ጃል መገርሳ በሪ በሊቀመንበርነት ግንባሩን መርተዋል። የኦነግ አመራሮችን ክፍፍል ተከትሎ "አባኦ ቃማ ጨኡምሳ" የሚል መጠሪያ ያለው ፓርቲ መስርተው በሊቀ-መንበርነት ለረዥም ዓመታት መምራታቸውን ከመገናኛ ብዙኃን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ለቢቢሲ በሰጡት ቆየት ያለ ቃለ መጠይቅ ተወልደው ያደጉት ምስራቅ ወለጋ መሆኑን ተናግረዋል። በተወለዱባት ነቀምቴ ከተማ የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ከተከታተሉ በኋለ በ1974 እኤአ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተዋል። የመጀመርያ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ሳያጠናቅቁ ወታደራዊው የደርግ መንግሥት ስልጣን መቆጣጠሩን ተከትሎ ወደ ሶማሊያ ቢያቀኑም የሶማልያ መንግሥት ወደመጡበት መልሷቸዋል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሐገር ውስጥ የነበረውን የትጥቅ ትግል ተቀላቅለዋል።
በ1984 ዓ.ም. ከሽግግር መንግሥቱ የመውጣት ውሳኔ ላይ ለመድረስ አባ ገዳዎችን ባማከሩበት ወቅት ‘የሽማግሌዎችን ምክር ወደ ጎን ትተው፣ የሽግግር መንግሥቱን ጥለው በመውጣት ያልተገባ መስዋእትነት አስከፍለዋል’ የሚለው ወቀሳ ከሚሰነዘሩባቸው ትችቶች መካከል አንዱ ነው።
የአቶ ገላሳ ዲልቦ ህልፈተ ህይወት እንደተሰማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ በርካታ ባለሥልጣናት እና የትግል አጋሮቻቸው በማኅበራዊ ሚድያ ሐዘናቸውን ገልጸዋል።
የቀብር ስነ-ስርአታቸውም ቅዳሜ መጋቢት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተክርስትያን ተፈፅሟል።