መጋቢት 24 ፣ 2014

H.R. 6600 እና S.3199 የሚባሉት ረቂቅ ህጎች ፀድቀዋል? ሩሲያ እና ቻይናስ ህጎቹ እንዳይፀድቁ በድምፃቸው መሻር ይችላሉ?

ወቅታዊ ጉዳዮች

ረቂቅ ህጎቹ ለመፅደቅ የተለያየ ሂደትን ማለፍ ያለባቸው ሲሆን በመጨረሻም በፕሬዝዳንቱ ውሳኔ ሲያገኙ ብቻ የሚፀድቁ ይሆናል

Avatar: Hagos Gebreamlak
ሓጎስ ገብረኣምላኽ

A fact-checker at HaqCheck, he has worked for Fortune as a reporter previously.

H.R. 6600 እና S.3199 የሚባሉት ረቂቅ ህጎች ፀድቀዋል? ሩሲያ እና ቻይናስ ህጎቹ እንዳይፀድቁ በድምፃቸው መሻር ይችላሉ?
Camera Icon

Credit: BBC

ከሰሞኑ በተለያዩ የሶሻል ሚድያ አውታሮች ላይ H.R.6600 እና S.3199 በተባሉ ረቂቅ ህጎች የአሜሪካው የህግ መወሰኛ ምክር ቤት የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ያለውን ግጭት እንዲያቆም ለማስገደድ ውሳኔ እንዲሰጥባቸው አቅርቧል። እነዚህን ረቂቅ ህጎች በተመለከተ በማህበራዊ ሚድያው ላይ በስፋት ሲዘዋወሩ የነበሩ ፖስቶች እና አሳሳች ሪፖርቶች ተስተውለዋል።

ሀቅቼክ ከነዚህ ህጎች ጋር በተያያዘ ሀሰተኛ እንዲሁም አሳሳች የሆኑ መረጃዎች እና ሪፖርቶችን ተመልክቷል። አንዳንድ የማህበራዊ ሚድያ ፖስቶችም S.3199 የተባለው ረቂቅ ህግ እንደፀደቀ አድርገው መረጃ ሲያስተላልፉና ሲያዘዋውሩ ሰንብተዋል።

ሌሎች ደግሞ H.R.6600 የተባለው ህግ በሩሲያ እና በቻይና ተቃውሞ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብታቸውን ተጠቅመው ውሳኔውን ሊያቋርጡት እንደቻሉ አስነብበዋል።  

እነዚህን ሀሰተኛ እና አወዛጋቢ መረጃዎችን በጥቂቱ ለማሳየት ያክል :- 

የረቂቅ ህጎቹ አላማ ምንድን ነው? 

የተለያዩ የማህበራዊ ሚድያ ገፆች ላይ የተንፀባረቁት ኃሳቦች ይህን የሚመስሉ ሲሆን በህጎቹ ዙሪያ የሚቀርቡ መረጃዎችን ትክክለኝነት ለመረዳት በአሜሪካ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት የቀረቡት እነዚህ ህጎች ምንድን ናቸው፣ ህግ ሆነው የሚፀድቁበት ሂደትስ ምን ይመስላል የሚለውን መገንዘብ አስፈላጊ ነው።

HR6600 ረቂቅ ህግ በኢትዮጵያ ውስጥ መረጋጋትን ፣ ሰላምን እና ዴሞክራሲን ለማምጣት ጥር 27 ቀን 2014 ዓ.ም ተዋወቀ። የአሜሪካ ሴኔት አባል በሆነው ቶም ማልኖውስኪ አነሳሽነት እንዲሁም የህግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል በሆኑት ማይክል ማኮውል እና ግሪጎሪ ሚክስ ደጋፊነት የቀረበው ይህ ረቂቅ ህግ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ግጭት ለማቆም በኢትዮጵያ መንግስትና በግጭቱ ተሳትፎ ያላቸው አካላት ላይ ጫና ማሳደርን እሳቤ ያደረገ የህግ ማዕቀፍ ነው።    

ይህ ረቂቅ ህግ ከፀደቀ ንብረቶችን ማገድ፣ የቪዛ ክልከላ እንዲሁም ከአሜሪካ እና አለም አቀፍ ከሆኑ ተቋማት የእርዳታ ክልከላ እንዲደረግ ያስችላል።  

ሌላኛው ረቂቅ ህግ S.3199  ጥቅምት 25 ቀን 2014 ዓ.ም በአሜሪካ የሴኔት አባል በሆነው ሮበርት ሜንዴዝ አነሳሽነት የተዋወቀ ነው።  ይህ ረቂቅ ህግ እንደ ህግ ከፀደቀ በሰሜን ኢትዮጵያ ባለው ግጭት ላይ ተሳታፊ የሆኑ ወገኖችን በገንዘብ እንዲሁም በጦር መሳሪያ የሚደግፉ አካላት ላይ ማዕቀቦችን  ለመጣል የሚያስችል ህግ ነው። 

S.3199 ህግ በዋነኝነት ለኢትዮጵያ እና ኤርትራ መንግስት ከአለም አቀፍ ተቋማት የሚሰጡ ማንኛውም አይነት የብድር እንዲሁም የብድር ማራዘሚያዎችም ሆነ የትኛውንም አይነት የፋይናንስ እና ቴክኒካል ድጋፎች ላይ ክልከላ የሚያደርግ ህግ ነው። 

የመንግስት አቋም

የነዚህ ረቂቅ ህጎች ጉዳይ በኢትዮጵያ የማህበራዊ ሚድያ አውታሮች ላይ በሰፊው አወዛጋቢ እና አወያይ ሀሳብ ሆኖ ቆይቷል። በአሜሪካና በተለያዩ የአለም ክፍሎችም ህጎቹን በመቃወም ሰልፎች የተደረጉ ሲሆን፣ በተቃራኒው ደግሞ የረቂቅ ህጎቹን መፅደቅ የሚያበረታቱ የተቃውሞ ሰልፎችም ተደርገዋል።

ረቂቅ ህጎቹን በማስመልከት መጋቢት 13 ቀን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ውጭ ጉዳይ አቶ ደመቀ መኮንን ውጭ ሀገራት ላሉ የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎች H.R.6600 እና S.3199 ረቂቅ ህጎችን በመቃወም ሰልፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።  

በተጨማሪም መጋቢት 15 ቀን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ዲና ሙፍቲ ውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ረቂቅ ሰነዶቹ እንዳይፀድቁ የሚያደርጉትን ተቃውሞ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።  

በቅርቡም በአሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ የHR6600 እና S3199 ረቂቅ ህጎችን በመቃወም የተቃውሞ ሰልፍ ተደርጎ ነበር።

ህጎቹ እውን ፀድቀዋል? አሜሪካና ቻይናስ ህጉን መሻር ይችላሉ?

ረቂቅ ህጎቹን በተመለከተ በማህበራዊ ሚድያ አውታሮች ሲዘዋወሩ ከነበሩት ኃሳቦች አንዱ ረቂቅ ህጎቹ እንዳይፀድቁ በሩሲያ እና ቻይና አማካኝነት ውድቅ መደረጉን የሚያሳዩ ነበሩ። 

ይሁን እንጂ እነዚህ ረቂቅ ህጎች በአሜሪካ መንግስት ምክር ቤቶች የቀረቡ በመሆናቸው በአሜሪካ በብሄራዊ ደረጃ ብቻ የሚፀድቁ ይሆናል። እነዚህ ረቂቅ ህጎች በተባበሩት መንግስታት ኤጀንሲዎች እና በአለም አቀፍ ስምምነቶች ደረጃ የሚወሰኑ ማዕቀቦች አይደሉም። 

ይህም በመሆኑ ሩሲያም ሆነ ቻይና ያላቸውን ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ሊጠቀሙ የሚችሉት በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ባላቸው መቀመጫና ስልጣን ብቻ ሲሆን፣ በአንፃሩ እነዚህ H.R.6600 እና S.3199 ረቂቅ ህጎች በአሜሪካ መንግስት ደረጃ የቀረቡ በመሆናቸው የህጎቹ መፅደቅ ላይ ምንም አይነት መብትና ስልጣን አይኖራቸውም። 

ሁለተኛው እና አወዛጋቢ ጉዳይ የነበረው የS3199 ረቂቅ ህግ በቅርቡ ህግ ሆኖ ፀድቋል የሚል ነበር።

እነዚህ ሁለቱ ረቂቅ ህጎች ህግ ሆ 5 የተለያዩ ደረጃዎችን ማለፍ ይኖርባቸዋል። እነዚህም ለውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ መተዋወቅ፣ በሴኔቱ መፅደቅ በመቀጠልም በምክር ቤቱ መፅደቅ ያለበት ሲሆን በመጨረሻም በፕሬዝዳንቱ ከፀደቀ በኋላ ህግ መሆን ይችላሉ። 

በሌላ መልኩ ረቂቁ በሴኔት አባል አማካኝነት የቀረበ ከሆነ በሴኔቱ የውጭ ግንኙነቶች ኮሚቴ አማካኝነት ድምፅ ተሰጥቶበት ወደ ሙሉ ሴኔት የሚተላለፍ ይሆናል። ነገር ግን ይህ ረቂቅ በተወካዮች ምክር ቤት አባል የቀረበ ከሆነ በውጭ ግንኙነቶች ኮሚቴ አማካኝነት ድምፅ ተሰጥቶበት ወደ ሙሉ የተወካዮች ምክር ቤት ይተላለፋል።

ከነዚህ በአሜሪካ ረቂቅ ህጎችን የማፅደቅ ሂደት አንፃር ስንመለከተው፣ S3199 ረቂቅ ህግ የቀረበው በሴናተር አማካኝነት ነው። በሴኔቱ የውጭ ግንኙነቶች ኮሚቴ አማካኝነት ረቂቁ መጋቢት 20 ቀን 2014 ዓ.ም በሴኔቱ ድምፅ እንዲሰጥበት ተላልፏል። ይህ ረቂቅ ህግ ሆኖ እንዲጸድቅ በሴኔቱ፣ በተወካዮች ምከር ቤት እና በአሜሪካው ፕሬዝደንት መፅደቅ አለበት። ይህ ረቂቅ ህግም ወደ ፕሬዝደንቱ ከማለፉ በፊት በሴኔቱ እና በተወካዮች ምክር ቤት አማካኝነት የሁለቱን ድምፅ ማግኘት አለበት።

በሌላ በኩል HR6600 የሚባለው ረቂቅ ህግ የተዘጋጀው በተወካዮች ምክር ቤት አማካኝነት ነው። ይህ ረቂቅም የካቲት 1 ቀን 2014 ዓ.ም በውጭ ጉዳይ ተወካዮች ምክር ቤት አማካኝነት ድምፅ ተሰቶበት ወደ አሜሪካ ተወካዮች ምክር ቤት ተላልፏል። በተመሳሳይ ሁኔታም ይህ ረቂቅ ህግ በተወካይ በሴናተሮች ፀድቆ በመጨረሻም በፕሬዝዳንቱ አማካኝነት ወደ ህግ መቀየር ይኖርበታል። 

ከዚህ መመልከት እንደምንችለው እነዚህ ሁለት ረቂቅ ህጎች እስካሁን ህግ ሆነው አልፀደቁም። በመሆኑም እነዚህ ረቂቅ ህጎች በሂደት ላይ ያሉ ሲሆኑ ህግ ሆነው እንዲፀድቁ ሶስት ሂደቶችን፤ ማለትም በሴኔቱ፣ በተወካዮች ምክር ቤ ፣ እና በመጨረሻም በፕሬዝደንቱ ሊፀድቅ ይገባዋል። 

አስተያየት