በጎረቤት ሶማሌ ላንድ የተሳውን የእሳት ቃጠሎ ለማጥፋት 25 የእሳት አደጋ ተሽከርካሪዎች ሀርጌሳ ገብተዋል። ተሽከርካሪዎቹ የተላኩት ከትላንት በስተያ ምሽት 3 ሰዓት አካባቢ ‘ዋሄን’ ገበያ ላይ የተነሳውን የእሳት ቃጠሎ ለማጥፋት መሆኑን የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ከስፍራው ዘግቧል።
ሀርጌሳ ከተማ ዋሄን ገበያ በሚገኘው ግዙፍ የገበያ ማእከል ላይ የተነሳውን ቃጠሎ ለማጥፋት የእሳት እና ድንገተኛ አደጋዎች ሰራተኞችን ጨምሮ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ተሳትፈዋል።
የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ አደጋውን አስመልክተው እንደገለጹት መንስኤው ያልታወቀው የእሳት አደጋ 5ሚልዮን ዶላር የሚገመት ሐብት አውድሟል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ በሶማልኛ ቋንቋ ባስተላለፉት የትዊተር መልእክታቸው “በዚህ በታላቁና በተቀደሰው ረመዳን ወቅት በተነሳው የእሳት ጉዳትና ኪሳራ ልባችን ተሰብሯል” ብለዋል።
በሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፋ መሀመድ ዑመር የሚመራ የሶማሌ ክልል የልዑካን ቡድን ትላንት ከሰዓት በኋላ ሶማሌ ላንድ ተጉዞ የአደጋውን መጠን ተመልክቷል።
የፋይናንስ ሚንስትሩ አህመድ ሼዴ መሀመድ፣ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ሚንስትሯ ዳግማዊት ሞገስ፣ የሶማሌ ክልል ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ሙበሽር ድበድ ራጌ እና ሌሎችም የፌደራል እና የክልል ባለሥልጣናት በስፍራው በመገኘት ሀዘናቸውን ገልጸዋል።