መጋቢት 9 ፣ 2014

የኢትዮ ቴሌኮምን በከፊል ወደግል ለማዛወር የተያዘውን እቅድ መንግስት ለጊዜው ማስተላለፉን አስታወቀ

ዜና

የኢትዮጵያ መንግስት የኢትዮ ቴሌኮምን 40 በመቶ ድርሻ ወደግል ለማዘዋወር ይዞት የነበረውን እቅድ ላልተወሰነ ጊዜ ማቋረጡን አስታወቀ።

Avatar: Addis Zeybe
አዲስ ዘይቤ

Addis Zeybe is a Digital News Media.

የኢትዮ ቴሌኮምን በከፊል ወደግል ለማዛወር የተያዘውን እቅድ መንግስት ለጊዜው ማስተላለፉን አስታወቀ

የኢትዮጵያ መንግስት የኢትዮ ቴሌኮምን 40 በመቶ ድርሻ ወደግል ለማዘዋወር ይዞት የነበረውን እቅድ ላልተወሰነ ጊዜ ማስተላለፉን አስታወቀ።

የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ “በዓለም አቀፍ ደረጃ እና በሀገር ውስጥ የሚታየውን ፈጣን የማክሮ ኢኮኖሚ ለውጥ ከግንዛቤ በማስገባት ኢትዮ ቴሌኮምን በከፊል ወደ ግል ለማዘዋወር የተያዘው እቅድ በተራዘመ ጊዜ ውስጥ እንዲደረግ በመንግስት ተወስኗል” ብሏል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስት የማክሮ ኢኮኖሚን ሁኔታ ማሻሻል እና የኢትዮ ቴሌኮምን የገንዘብ አቅም ማሳደግ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ መሆኑ ታምኖበታል ሲል መግለጫው አክሏል። “ይህ ውሳኔ የኢትዮጵያ ዜጎችን እና ወደ ግል በማዘዋወር ሂደቱ ፍላጎት ያላቸውን አካላት የሚጠቅም ነው” ተብሏል።

የኢትዮጵያ መንግስት ጨረታውን ለተወሰነ ጊዜ ቢያራዝመውም ወደ ያያዘውን ወደ ግል የማዘዋወር ሂደት በሚገባ ያጠናቅቃል ያለው መግለጫው እስካሁን ፍላጎት ካሳዩ እና ወደፊት ከሚመጡ አካላት ጋር ግንኙነቶች እንደሚቀጥሉ በመግለጫው ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ መንግስት የ‘ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ’ ፕሮግራም ይፋ ማድረጉን ተከትሎ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደግል ለማዘዋወር በአዋጅ ቁጥር 1206/2012 መወሰኑ ይታወሳል።

የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደግል የማዘዋወሩ ዋነኛ ዓላማ የተባሉት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ የግል ዘርፍ ሚናን ማሳደግ፣ የልማት ድርጅቶቹን ብቃት ማጎልበት፣ ተወዳዳሪነታቸውን ማስፋት፣ ካፒታላቸውን ማሳደግ እንዲሁም አገልግሎታቸውን ማሻሻል ናቸው።

በ2014 ዓ.ም. መስከረም ወር መንግስት የኢትዮ ቴለኢኮምን 40 በመቶ ድርሻ ወደግል ለማዘዋወር ጨረታ ማውጣቱን ተከትሎ በርካታ ፍላጎት ያላቸው አካላት የቀረቡ ሲሆን ተከታታይ ውይይቶች ሲደረጉበት እንደነበር መግለጫው አስታውሷል።

ከዚህ ቀደም በከፊል ወደግል ይዘዋወራሉ ከተባሉት የልማት ድርጅቶች አንዱ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ወቅትም ቢሆን ተወዳዳሪነቱን ያሳደገ በመሆኑ ሂደቱ የተቋረጠ ሲሆን፣ ኢትዮ ቴሌኮም ተከትሏል።