በደሴ ከተማ የሚገኙ የሐይማኖት ተቋማት ትምህርት ሚኒስቴር ለ12ኛ ክፍል የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ያስቀመጠው ውጤት ፍትሐዊ አይደለም ሲሉ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። የእስልምና፣ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ፣ የካቶሊክ፣ የፕሮቴስታንት ሐይማኖት አባቶች በጋራ ባወጡት መግለጫ “ተማሪዎቹ ፈተናውን የወሰዱት በስነ-ልቦና በተጎዱበት ጊዜ ነበር” ብለዋል። የሐይማኖት አባቶቹ በትላንትናው ዕለት ከቀኑ 11 ሰዓት አካባቢ በደቡብ ወሎ መምህራን ማኅበር ጽ/ቤት ውስጥ በሰጡት መግለጫ “ለበርካታ ወራት ከትምህርት ገበታ እና ከጥናት ርቀው፣ በቂ የፈተና ዝግጅት ሳያደርጉ፣ አንዳንዶቹም ከዘመቱበት ጦር ግንባር ተመልሰው የወሰዱትን ፈተና የሰላም ቀጣና ውስጥ ከነበሩት ተማሪዎች እኩል እንዲመዘኑ መደረጉ አግባብነት የለውም” ብለዋል።
“ከተማችንና ዞናችን የወረራ ቀጣና ሆኖ ለበርካታ ወራት ቆይቷል። ክስተቱን የአማራ ክልል መንግሥት፣ የፌደራል መንግሥትም ሆነ ትምህርት ሚንስቴር ያውቁታል” የሚሉት ተወካዮቹ “የመማር ማስተማሩ ሂደት በተገቢው ሁኔታ አለመካሄዱ እየታወቀ ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ የተቀመጠው ነጥብ አግባብነት የለውም” ሲሉ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
የአራቱ ሐይማኖቶች ተወካዮች በጋራ በሰጡት መግለጫ ትምህርት ሚኒስቴር የከተማዋን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ሳያስገባ ያስቀመጠው የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ኢ-ፍትሐዊ ነው። ሚንስትር መስሪያ ቤቱ ወቅቱ ተማሪዎችና ወላጆች ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ የገቡበት መሆኑን በመገንዘብ የመግቢያ ውጤቱን በድጋሚ ሊመለከተው እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተያያዘ ዜና የሰሜን ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ “ትምህርት ሚኒስቴር ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ የወሰነው ማለፊያ ነጥብ በዞኑ ያለውን ሁኔታ ከግምት ያስገባ አይደለም” ብሏል።
በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና 42 ትምህርት ቤቶች ያስፈተኑ ሲሆን በ6 ትምህርት ቤቶች የተፈተኑት 679 ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት አለማምጣታቸው ተዘግቧል ትምህርት ቤቶቹ ጊራና፣ ቃሊም፣ ኩል መሰክ፣ ጉርጉር ደብረሮሀ፣ ሀናመኳት ደብረሲና እና ክበበው 2ተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መኾናቸው ተገልጿል።
የሰሜን ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ የፈተና ዝግጅትና አስተዳደር ባለሙያ ወይዘሮ ሙሉ አዳነ ዞኑ ከ5 ወራት በላይ ጦርነት ሲካሄድበት በመቆየቱና አሁንም ቀጣናው ሙሉ በሙሉ ሰላሙ ባልተረጋገጠበት ተማሪዎች ለፈተና በቂ ዝግጅት ሳያገኙ ፈተና መውሰዳቸውን አስረድተዋል።
ተማሪዎቹ በጦርነቱ ምክንያት ከደረሰው የሥነ ልቦና ጉዳት ሳያገግሙ ፈተና መውሰዳቸው ተገቢ እንዳልነበር የገለጹት ወይዘሮ ሙሉ ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ የወሰነው የማለፊያ ነጥብ ነባራዊ ሁኔታን ያላገናዘበ ነው ብለዋል።
በደቡብ ወሎ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ 14ሺ 697 ተማሪዎች መካከል የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ያመጡት 3694 ተማሪዎች ብቻ መሆናቸው ታውቋል። በደሴ ከተማ ብቻ 2ሺህ 799 ተማሪዎች ፈተና ላይ ቢቀመጡም የመግቢያ ነጥብ ያመጡት 760 ተማሪዎች መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። በሰሜን ወሎ ዞን 9 ሺህ 710 ተማሪዎች ፈተናውን ቢወስዱም የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ያመጡት 3 ሺህ 657 ተማሪዎች ብቻ ናቸው።