በአዳማ ከተማ የሞተር ሳይክል እንቅስቃሴ ላልተወደነ ጊዜ ታግዷል። እገዳው የጀመረው ካሳለፍነው ረቡዕ መጋቢት 7 ቀን 2014 ዓ.ም. መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ።
የሞተር ሳይክል እንቅስቃሴ መታገዱ በሥራቸው ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረ የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ። ሞተር ሳይክልን በመጠቀም ሥራቸውን የሚያቀላጥፉ የከተማዋ ነዋሪዎች ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገሩት እገዳው በእለታዊ ሥራቸው ላይ ከባድ ተጽእኖ አሳድሯል።
እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ ሞተር ሳይክል እንቅስቃሴ በየትኛውም የከተማዋ መንገዶች ላይ መታገዱ የማድረስ (ዴሊቨሪ) አገልግሎት ሰጪ እና ተጠቃሚዎች፣ ሬስቶራንቶች፣ የሞተር ሳይክል አሽከርካሪዎች እና ባለቤቶች፣ በግል ሥራ ላይ የተሰማሩ የከተማዋ ነዋሪዎች እና የኮንስትራክሽን ባለሙያዎች በተሻለ ቅልጥፍና ሥራቸውን እንዳይሰሩ እንቅፋት ሆኖባቸዋል።
የማድረስ (ዴሊቨሪ) አገልግሎታቸውን ከሞተር ሳይክል ወደ ሳይክል ቢቀይሩም ሂደቱ ከሞተሩ አንጻር ረዥም ሰዓት ይፈጃል። በተጨማሪም የአገልግሎት ጥራቱ ላይ እክል ይፈጥራል ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። የማድረስ (ዴሊቨሪ) አገልግሎት እንዲሰጡ ፈቃድ የሰጣቸው አካል ጋር በመሄድ ችግራቸውን ቢያመለክቱም “ኃላፊነት አንወድም” ስለመባላቸው አብራርተዋል።
አዲስ ዘይቤ ካነጋገራቸው የሞተር ሳይክል ባለቤቶች መካከል አንዱ የሆነው አቶ ሬድዋን ሚስባህ የሞተር ትራንስፖርት በመታገዱ ታክሲ ለመጠቀም መገደዱን ነግሮናል። “አሁን ወደ ቤቴም ሆነ ወደ ሥራዬ የምሄደው በታክሲ ነው። ከሰልፍ እና ከግፊያው እንግልት በተጨማሪ ጊዜዬን በአግባቡ እንዳልጠቀም አድርጎኛል” ብሎናል።
የክልከላውን ምክንያት የተጠየቁት የአዳማ መንገድ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ኃላፊ አቶ ታዬ ተሊላ “የሞተር ሳይክል አገልግሎት ለጊዜው የተቋረጠው በጨፌ ኦሮምያ ስብሰባ ምክንያት ነው” ብለዋል። እንደ ኃላፊው ገለጻ ከዛሬ 10 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ የሚካሄደው የጨፌው ስብሰባ ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ ቀድሞው እንቅስቃሴ ይመለሳል።
የጨፌ ኦሮሚያ 1ኛ ዓመት 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ከመጋቢት 10 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በአዳማ ከተማ እንደሚካሄድ ፕሮግራም ወጥቶለታል።