ጥቅምት 26 ፣ 2015

ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ የታሰሩት የአዳማ ከተማ የኦሮሚያ ጠ/ፍ/ቤት ዳኞች እስካሁን እንዳልተፈቱ ታወቀ

City: Adamaዜና

የፌዴራሉም ሆነ በኦሮሚያ ህገ-መንግስት ማንኛውም የፍርድ ቤት ዳኛ እጅ ከፍንጅ ካልሆነ በቀር ያለመከሰስ መብቱ በህጋዊ መንገድ ሳይነሳ መከሰስ እንደማይችል ይደነግጋል

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ የታሰሩት የአዳማ ከተማ የኦሮሚያ ጠ/ፍ/ቤት ዳኞች እስካሁን እንዳልተፈቱ ታወቀ

በትናንትናው እለት አርብ ጥቅምት 25 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ ገልማ አባ ገዳ አካባቢ ከሚገኘው የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምሥራቅ ምድብ ችሎት ዳኛ አብዲሳ ዋቅጅራ፣ ዳኛ ሙሀመድ ጅማ እና ዳኛ ደሳለኝ ለሚ የተባሉ ሶስት የወንጀል ችሎት ዳኞች ከስራ ገበታቸው ላይ በፖሊስ መታሰራቸው ተሰማ።

በቀን 24/02/2015ዓ/ም በአዳማ ከተማ ደንበላ ክ/ከተማ ፖሊስ ወንጀል ምርመራ በተጻፈለት እና የታሳሪዎቹን የስራ ሁኔታ በማይገልጸው ደብዳቤ  የዳኞቹን የእስር ትዛዝ አውጥቶ የነበረው የአዳማ ልዩ ወረዳ ፍ/ቤት የሰጠውን ትዕዛዝ ታሳሪዎቹ የከፍተኛ ፍ/ቤት ዳኞች መሆናቸው እንደታወቀ በቀን 25/02/2015 ዓ/ም ከቀኑ 8 ሰዓት ከ50 ላይ ትእዛዙን መሻሩን በፌስቡክ ገጹ ላይ አስነብቧል። 

የደብዳቤው ግልባጭም ለአዳማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ እና ለደምበላ ክ/ከተማ ፖሊስ መላኩን የአዳማ ልዩ ወረዳ ፍ/ቤት ቢገልፅም ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰአት ድረስ ዳኞቹ እንዳልተፈቱ ታውቋል። 

የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት ምስራቅ ምድብ አዳማ ባልደረባ የሆኑት እና ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ የፍ/ቤቱ ባልደረባ ስለሁኔታው ሲናገሩ ፖሊሶቹ “ከላይ የመጣ ትዕዛዝ ነው” ስለመባላቸው እንጂ ተጨማሪ መረጃ እንደሌላቸው መግለጻቸውን ይናገራሉ።"

“ለፖሊሶቹ ስለዳኞች አጠያየቅ እና አያያዝ ልናስረዳቸው ሙከራ ብናደርግምና ወደ በላይ አለቆቻችን ለመገናኘት ብንሞክርም መፍትሔ ባለመኖሩ ዳኞቹን አስረው ወስደዋቸዋል” በማለት የፍ/ቤቱ ባልደረባ ገልፀውልናል። 

በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው የህግ ባለሙያው አቶ አብዱራዛቅ ናስር የተፈጸመው ተግባር ህገ-ወጥ መሆኑን ያስረዳሉ። 

“ጉዳዩ ዳኞችን የሚመለከት በመሆኑ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዳንት እና የኦሮሚያ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ጉዳዩን በይፋ ማውገዝ ነበረባቸው” ሲሉ አቶ አብዱራዛቅ ተናግረዋል። በክልሉ የሚገኙ የዳኞች እና ጠበቆች ማህበራትም በጉዳዩ ላይ ከፍተኛ ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑንም የህግ ባለሙያው ይገልፃሉ።

በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 79 እና በኦሮሚያ ህገ-መንግስት አንቀጽ 61 እና 63 መሰረት ማንኛውም የፍርድ ቤት ዳኛ እጅ ከፍንጅ ካልሆነ በቀር ያለመከሰስ መብቱ በተገቢው ህጋዊ መንገድ ሳይነሳ መከሰስ እንደማይችል ይደነግጋል።

“የኢትዮጵያ የዳኞች ጉባዔ ዳኞች እጅ ከፍንጅ ሲያዙ አንኳን የሚያዙበት አካሄድ ግልጽ ድንጋጌና መመሪያ የለውም፣ ዳኞች የህግ መልክ (Public face of the judiciary) በመሆናቸው በሌሎች አለማት እንኳን ዳኞች ሲታሰሩ በሰንሰለት ያለማሰር እና የአያያዝ ሁኔታቸው በግልጽ የተደነገገ ነው” ሲል አቶ አብራዛቅ አስተያየቱን ይሰጣል።

የከፍተኛ የአስፈጻሚው አካላት ባለስልጣናትም በተለያየ ጊዜ ዳኞችን በተመለከተ የሚያደርቸው ንግግሮች ዳኞች ላይ ለሚፀሙ ይህን አይነት ህገ ወጥ ድርጊቶች ድርሻ እንዳላቸው የሚያምኑት የህግ ባለሞያው አቶ አብድራዛቅ አሁን የተፈፀመው ድርጊት በከፍተኛ ፍ/ቤት ዳኞች ላይ መሆኑን አንስተው “ነገ በሌሎች ራቅ ባሉ አካባቢዎች በሚገኙ እና ዝቅተኛ ደረጃ ላይ በሚገኙ ፍ/ቤት ዳኞች ላይ ይህን አይነት ድርጊት ሊፈፀም አይችልም ማለት አስቸጋሪ ነው” በማለት ስጋታቸውን ያጋራሉ። 

ትናንት ማምሻውን ኢሰመኮ ባወጣው መግለጫ የተፈጸመው ስህተት በቶሎ እንዲታረም እና እስረኞቹ ዳኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ጠይቋል።

የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ፍ/ቤት ህዝብ ግንኙነት እና የኦሮሚያ ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ተወካይን በስልክ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ ባለመሳካቱና አጭር መልእክት ብናስቀምጥም ምላሻቸውን ማግኘት ባለመቻላችን የተቋማቱን አስተያየት ማካተት አልቻልንም።

አዲስ ዘይቤ ይህንን መረጃ እስከሰራችበት ጊዜ ድረስ ዳኞቹ ከእስር ያልተፈቱ መሆኑንና በደንበላ ክ/ከተማ ፖሊስ ቁጥጥር ስር መሆናቸውን አዲስ ዘይቤ ለማወቅ ችላለች።

አስተያየት