ጥቅምት 25 ፣ 2015

ድብቁ ሀይቅ፦ ሀረ ሸይጣን

City: Hawassaኢኮኖሚማህበራዊ ጉዳዮችቱሪዝም

“ሀረ ሸይጣን” ማለት የሰይጣን ሀይቅ ወይም የሰይጣን ውሃ ማለት እንደሆነ በአፈታሪክ ሲነገር ቆይቷል። ዛሬም ብዙዎቹ የአካባቢው ነዋሪዎች ሀይቁን በሩቁ ያዩታል እንጂ አይቀርቡትም

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ድብቁ ሀይቅ፦ ሀረ ሸይጣን
Camera Icon

ፎቶ፡ ከስልጤ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ (ሀረ ሸይጣን ሀይቅ ከፊል ገጽታ)

“ስለ ሀረ ሸይጣን ሀይቅ ትርጓሜ የተለያዩ መላምቶች ቢሰጥም በስልጥኛ ቃል ሐረ-አሽ-እጣን ማለት 'እጣን አጭስ' እንደ ማለት ነው” ይላሉ የስልጤ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የቱሪዝም ባለሙያ የሆኑት አቶ መሐመድ ደርገባ።

በሀይቁ አካባቢ ተወልዶ እንዳደገ የሚናገረው ጀማል ሀሰን፤ በልጅነቱ ወላጆቹ በሀይቁ ዙሪያ ሰይጣን እንዳለ በመንገር ወደ ሀይቁ እንዳይቀርብ ያስጠቅቁት እንደነበር ያስታውሳል።    

የአዲስ ዘይቤ የሐዋሳ ሪፖርተር በስልጤ አፈ ታሪክ ብዙ ስለሚነገርለት ሀረ ሸይጣን ሀይቅ ዳሰሳ አድርጓል። ከአዲስ አበባ በስተደቡብ አቅጣጫ 174 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የስልጤ ዞን፤ በውስጡ ከሚገኙት በርካታ የቱሪዝም መስህብ ስፍራዎች መካከል አንዱ በአካባቢው ማህበረሰብ አጠራር “ሀረ ሸይጣን” የሚባለው ሀይቅ ነው።  

ሀረ ሸይጣን በስልጤ ዞን ከቅበት ከተማ 3.4 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በአጎዴ ሎብሬራ ቀበሌ ውስጥ ይገኛል። በሀይቁ ተፈጥሮ እና በሚነገሩበት አፈ ታሪኮች በመሳብ በርካታ ጎብኚዎች ሀይቁን ለማየት ወደ ስፍራው ይመጣሉ። 

የሀይቁ አቀማመጥ የገበቴ ወይም የክብ ጎድጓዳ ሰሃን ቅርጽ ያለው ሲሆን ከጉድጓዱ አፋፍ አንስቶ ቁልቁል ውሃው እስካለበት ለመድረስ በአማካኝ የ30 ሜትር ርቀት ባለው ገደላማ የመሬት አቀማመጥ ተከቧል። ከዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ በተገኘው መረጃ መሰረት የሀይቁ የጎን ስፋት 2400 ሜትር የሚደርስ ሲሆን ስለሀይቁ ጥልቀት ግን እስካሁን የተረጋገጠ መረጃ የለም።  

የአካባቢው ወጣቶች እንደሚገልጹት ከሀይቁ ጫፍ ዳገት ላይ ሆኖ ድንጋይ ቢወረወርም ውሃው ላይ ሲወድቅ ሊታይ አለመቻሉ አስገራሚ ነገር እንደሆን በአድናቆት ይናገራሉ። በተጨማሪም የሀይቁ የውሃ ቀለም በየወቅቱ መቀያየር፣ የሀይቁ ምንጭ አለመታወቁ እና የውሃ መጠኑ ክረምት ከበጋ ተመሳሳይ መሆኑ አስገራሚ እንደሆነም ነዋሪዎች ይገልጻሉ።

በስልጤ ዞን የባህልና ቱሪዝም መምሪያ የቱሪዝም ፕሮሞሽንና ግብይት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ መሐመድ ደርገባ እንደሚናገሩት “የሀረ ሸይጣን ሀይቅ የውሃ ቀለም እና መጠኑም እንደሌሎች የውሃ አካላት ክረምት ወይም በጋ ወራት ሳይሆን የራሱ የመጨመሪያ ጊዜ አለው። ለዚህ ምክንያት ተብሎ የሚነገረው ያለማቋረጥ ከስር የሚመነጭ በመሆኑ ነው” ይላሉ።

“የሀይቁ አፈጣጠር ከሳይንሳዊ ምልከታ አንፃር ከተፈጥሮ ውስጣዊ ሀይል አንዱ በሆነው እሳተ ገሞራ ፍንዳታ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ይገመታል” ሲሉ አቶ መሐመድ ስለሀይቁ አፈጣጠር ያስረዳሉ።

“ሀይቁ ከመሬት ገጽታ በታች መገኘት፣ በአካባቢው የሚገኙ ሌሎች መልካዓ ምድራዊ ገጽታዎች ማለትም አነስተኛ ኮረብታዎች፣ ተፈጥሯዊ ዋሻዎች፣ ፍል ውሃዎች እና እንደሌሎቹ ሀይቁ በስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ በእሳተ ጎሞራ የተፈጠረ ስለመሆኑ መገመት ይቻላል” በማለት የቱሪዝም ባለሙያው አቶ መሐመድ መረጃቸውን ያጠናክራሉ።

ፎቶ፡ ከስልጤ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ (ሀረ ሸይጣን ሀይቅ ከፊል ገጽታ)

የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት የሀይቁ ቀለም ቶሎ ቶሎ ይቀያየራል። አልፎ አልፎ የተቃጠለ ዘይት ዓይነት ሽታ እንደሚፈጥርም ይናገራሉ።

የሀይቁ የውሃ ቀለም መቀያየርን በተመለከተ አቶ መሃመድ ሲናገሩ “በውሃውና በጉድጓዱ አፋፍ መካከል ያለው ቀይ አፈር እና አረንጓዴ ደን ለቀለሙ መቀያየር ዋነኛው ምክንያቶች ናቸው” ይላሉ። የውሃው ቀለም በየሳምንቱ ወይም በየ15 ቀናት ወደ ሰማያዊ፣ አረንጓዴ እንዲሁም ወተታማ መልክ እንደሚቀያየር ይነገራል። 

ሀረ ሸይጣን መቼ እና እንዴት እንደተፈጠረ በትክክል የተቀመጠ ሳይንሳዊ መረጃ ባይኖርም ከጥንት ጀምሮ በማህበረሰቡ ዘንድ ስለ ሀይቁ አፈጣጠር የተለያዩ መላምቶች ይነገራሉ። 

የአከባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ከሚነገሩ አፈ ታሪኮች መካከል አንደኛው እንዲህ ይላል፤ “የሀረ ሸይጣን ሀይቅ የተፈጠረበት ቦታ እንዲህ ከመሆኑ አስቀድሞ ለጥ ያለ ሜዳ ነበር። ከዕለታት ባንዱ ቀን ሸህ ኑር ሁሴን የተባሉ የሃይማኖት አባት ወደ አካባቢው መጡ። በጊዜው የነበሩ ነዋሪዎች እንግዳውን ባለመቀበላቸው ሸህ ኑር ሁሴን ተራገሙ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ቀስ በቀስ ሜዳዉ እየሰመጠ በመሄድ ትንሽ ውሃ ፈጠረ በሂደት ደግሞ ሀረ ሼይጣን ሀይቅ ሊፈጠር ቻለ” ተብሎ ይነገራል።

ሌላኛው ደግሞ “ሀረ ሸይጣን ማለት ከሴጣን የተነሳ አልያም የሴይጣን ሀይቅ ነው” የሚል አፈታሪክ አለ። “ስፍራው ዳገት ነበር በዚያን ቦታ ዳር ዳር ላይ ሼይጣን ይኖርበት ነበር። አንድ የእልምና እምነት አባት በዳገቱ ላይ እየሰገዱ ሳሉ ሼይጣኖች (እርኩስ መናፍስት) ሰደቧቸው። ያኔ ዳገቱም ሼይጣኖቹም ሊሰምጡ ችለዋል” በማለት የአካባቢው ማህበረሰብ ይነገራል።

በእነዚህ እና መሰል አፈ ታሪኮች ምክንያት “እርኩስ መናፍስቱን” በመፍራት የአካባቢው ነዋሪዎች ሀይቁን በርቀት ያዩታል እንጂ አይቀርቡትም፣ ለመዋኘትም ሆነ አሳ ለማጥመድ እንደማይጠቀሙት ይነገራል።   

ጀማል ሀሰን ትውልድ እና እድገቱ በሀይቁ አቅራቢያ በመሆኑ በተደጋጋሚ ወደ ሀይቁ ይሄዳል። ጀማል እንደሚለዉ “በፊት ወደ ሀይቁ መጠጋት እንዳንችል በቤተሰቦቻችን ጫና ይደረግብን ስለነበር በጣም እንፈራዉ ነበር። ምክንያቱም 'የሰይጣን ውሃ ነው ትሞታላችሁ' ስለሚሉን ነው። አሁን ወደ ሀረ ሸይጣን ሀይቅ ዳር ላይ ከጓደኞቼ ጋር ቆመን እንመለከተዋለን ድንጋይ ይዘን ወደ ታች ስንወረውር ውሃዉ ላይ ሲያርፍ ግን መምልከት አንችልም” በማለት ይናገራል።

ሌላው የቅበት ከተማ ነዋሪ የሆነው ፋሪስ “ወደ ታች ሀይቁ ጋር ለመድረስ አዳጋች በመሆኑ በጥግ ቆሞ ከመመልከት ውጪ ሌላ አማራጭ የለም” ይላል። ፋሪስ እንደሚለው ሀይቁ ለጎብኚዎች ምቹ መሆን እንዲችል ቢያንስ መግቢያ መንገድ መሰራት ቢቻል ጥሩ እንደሆነ ገልጿል። 

የቱሪስት መስህቡን ለማልማት በከተማ አስተዳደሩ በኩል የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ቢገኙም በሚፈለገው ልክ ማስተዋወቅ ባለመቻሉ ከዘርፉ ተገቢውን ጥቅም እየተገኘ እንዳልሆነ ለማውቅ ተችሏል። ይህን የተፈጥሮ መስህብ አልምቶ ከዘርፉ ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት እየተሰራ እንደሆነ ከዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ተገልጿል።

ሀረ ሸጣን እስካሁን በገቢ ደረጃ ያስገኘው ነገር እንደሌለ እና ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በህገወጥ መልኩ የተደራጁ ማህበራት መሆናቸዉ የሚገልጹት የቱሪዝም ባለሞያው አቶ መሐመድ “እንደ ባህልና ቱሪዝም እስካሁን እየተሰራ የሚገኘው የጎብኚዎችን ቁጥር መጨመር ላይ ሲሆን በ2015 ዓ.ም በህገወጥ መንገድ የተደራጁ ማህበራትን ወደ ህጋዊ መንገድ በማምጣት ትኬት ተዘጋጅቶ ገቢ ለማግኘት እየተሰራ ነው” ብለዋል።

የስልጤ ዞን ከሀረ ሸይጣን ሀይቅ በተጨማሪም የአባያ (ቱፋ) ሀይቅ፣ ላሞሮ ፏፏቴ፣ ለቦ ፏፏቴ፣ ፍል ውሃ እና ሌሎች የተፈጥሮ መስህቦችን በውስጡ ይዟል። ጥንታዊ መስጂዶች፤ መድረሳዋች (የእስላማዊ ሃይማኖት ትምህርት ቤቶች)፣ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ዋሻዎች በዞኑ ይገኛሉ። እንዲሁም የዞን መዲና በሆነቸው ወራቤ ከተማ የተገነባው የስልጤን ባህልና ታሪክ ሙዝየም ሌላው የቱሪዝም መዳረሻ ነው።   

አስተያየት