ጥቅምት 24 ፣ 2015

የባከኑት ሙያተኞች

City: Addis Ababaማህበራዊ ጉዳዮችወቅታዊ ጉዳዮች

አብዛኞቹ ሙያተኞች በሰለጠኑበት ሙያ ለመስራት ፍላጎቱ አይታይባቸውም፤ ወደ ሌሎች ስራዎችና ሙያዎች ሲሰማሩም የባከነው ሙያተኝነታቸውንም ሆነ የጠፋውን ጊዜና ሃብት አያስተውሉትም

Avatar: Kalayou Hagose
ኻልኣዩ ሓጎሰ

ኻልኣዩ ሓጎሰ የህግ ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን ይፅፋል። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

የባከኑት ሙያተኞች
Camera Icon

ፎቶ፡ ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ

ተምረው ከተመረቁበት የሙያ ዘርፍ ውጪ ተሰማርተው የሚሠሩ ባለሙያዎችን ማግኘት የተለመደ እየሆነ መጥቷል። 

ለዚህም ባለሙያዎቹ የተለያዩ ምክንያቶች ሲያቀርቡ ይደመጣሉ። አንዳንዶች መንስኤው እኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና አካባቢያዊ ችግሮች እንደሆኑ ሲናገሩ ሌሎቹ ደግሞ ከሙያተኞች ከራሳቸው ከሚመነጭ ችግር፣ ከሥራ ቅጥር ሁኔታ እና ሀገሪቱ ካላት የስራ ዕድል ማነስ እንደሆነ ይገልጻሉ። 

የሚሰጠው ምክንያት የትኛውም ይሁን ሀገርና ቤተሰብ ጊዜያቸውን እንዲሁም አንጡራ ኃብታቸውን አፍስሰውና አስተምረው የተለያዩ ሙያዎች ባለቤት ያደረጓቸው እነዚህ ሙያተኞች ገና በተመረቁ ማግስት በሰለጠኑበት ሙያ ላይ ትኩረት ለማድረግና ለመስራት ፍላጎቱ አይታይባቸውም። ሙያተኞቹ ወደ ሌሎች ስራዎችና ሙያዎች ሲሰማሩም የባከነው ሙያተኝነታቸውንም ሆነ የጠፋውን ጊዜና ሃብት አያስተውሉትም። 

ዝቅተኛ የሙያ ክፍያ

ናሆም አበራ ከዓመታት በፊት ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በሲቪል ኢንጂነሪንግ የተመረቀ ሲሆን በሙያው ለተወሰነ ጊዜ ከሰራ በኋላ ብዙ ጊዜ፣ ጉልበት እና ገንዘብ ያወጣበትን የእንጂነሪንግ ሙያውን ትቶ በማርኬቲንግ የስራ ዘርፍ ተሰማርቶ ኑሮውን እየገፋ እንደሚገኝ ይናገራል። 

ናሆም ከሙያው የወጣበትን ዋና ምክንያት ሲያስረዳ “ዋናው ምክንያቴ በሙያው የሚገባኝ ክፍያ ስለማላገኝ እና ስራው ለአዲስ ነገር ፈጠራና ምርምር የሚጋብዝ ባለመሆኑ ነው” ይላል። 

አብዛኛውን ጊዜ ጀማሪ የሲቪል ኢንጂነሪንግ ምሩቃን ሳይት ጠባቂ ሆነው እንደሚቀጠሩ እና የሚከፈላቸው ገንዘብ በአማካኝ እስከ 3500 ብር ብቻ እንደሆነ የሚናገረው ናሆም “በዚህ ክፍያ እና አሁን ባለው ከፍተኛ የኑሮ ውድነት በህይወት ለመኖር ራሱ ከባድ ነው” ሲል ያስረዳል። 

በኢትዮጵያ ያለውን የደሞዝ ሁኔታ የሚዘረዝረው salary explore እንደሚያሳየው ከሆነ በኢትዮጵያ በሲቪል መሀንዲስነት የሚሰራ ሰው የመኖሪያ ቤት፣ የመጓጓዣ እና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን ጨምሮ በወር እስከ 7,840 ብር በአማካኝ ያገኛል። በዚህ የሙያ ዘርፍ ከ20 አመት በላይ ልምድ ያካበቱ ባለሙያዎች እስከ 12ሺህ ብር ብቻ የሚያገኙ ሲሆን 2 አመት የስራ ልምድ ያላቸው ደግሞ እስከ 4 ሺህ ስማንያ ብር ብቻ ያገኛሉ። 

ይህን የደሞዝ የክፍያ ማነስን ተከትሎ የተለያዩ ባለሙያዎች ከግል ኮሌጆች ዲግሪ እየገዙ ያልተማሩትንና ያላጠኑትን የሙያ ዘርፍ በመቀላቀል ሥራ እየሰሩ እንደሆነ ይነገራል። 

አንድ ስሙ እንዳይገለጽ የፈለገ የሜካኒካል እንጂነሪንግ ባለሙያ አንዳንድ ሰዎች በሙያቸው የሚያገኙት ገንዘብ ዝቅተኛ በመሆኑ ከግል ኮሌጆች በሚፈልጉት መስክ የትምህርት ማስረጃዎችን እስከ 15 ሺህ ብር አውጥተው በመግዛት በተለያዩ ድርጅቶች ተቀጥረው የሚሰሩ እንዳሉ ይናገራል። 

ዶክተር ደራርቱ በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የጤና ኮሌጅ በመምህርነት እያገለገሉ የሚገኙ ሲሆን አሁን አሁን ከተለያዩ የጤና ኮሌጆች ተመርቀው የሚወጡ ሙያተኞች ከሙያቸው ውጪ ተሰማርተው እንዲሰሩ እየተገደዱ እንደሆነ ይገልፃሉ።

ዶክተሯ ለዚህ መንስኤ ያሏቸውን የተለያዩ  ምክንያቶች ያስቀምጣሉ። በግንባር ቀደም የሚያስቀምጡት ምክንያት የስራ አጥነት ችግር ነው። “ከዚህ ቀደም ከተለያዩ የጤና ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ የጤና ሙያተኞች በመንግስት የሚመደቡበት ሁኔታ እንደነበረና ከ2011 እና 2012 ዓ.ም በኋላ ግን ቀርቷል” ይላሉ። ይህም ሙያተኞቹን ለስራ አጥነት ተጋላጭ እንዳደረጋቸው እና ከሙያቸው ውጪ እንዲሰማሩ እየተገደዱ እንደሆኑ ያስረዳሉ። 

በተጨማሪም የክፍያ ማነስ፣ የአስተዳደር ችግር እና የመውጫ ፈተና ውጤት መዘግየት በጤና ባለሙያዎቹ ላይ እጅግ ከፍተኛ ተፅእኖ ከመፍጠሩ ባሻገር ሙያተኞቹ የሰለጠኑበትን የሙያ ዘርፍ እንዳይወዱ እና በእርሱም እንዳይሰሩ ከሚያደርጉ ምክንያቶች ውስጥ እንደሆኑ ዶክተሯ ያብራራሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ እና እስያ ጥናቶች እና ምርምር ማዕከል ረዳት ፕሮፌሰር የሆነው ዶክተር ሳሙኤል ተፈራ አስተያየቱን ሲሰጥ “ዜጎች በተማሩበት የትምህርት ዘርፍ ተሰማርተው ኑሯቸውን ማስቀጠል ስለማይችሉ ያጠኑትን የሙያ ዘርፍ ወደጎን በመተው የተሻለ ገቢ ወደሚገኝበት የሙያ ዘርፍ እንዲቀላቀሉ ይገደዳሉ” ይላል።

የህክምና ዶክትሬት አጥንቶ አሁን የራይድ ሹፌር የሆነ ሰው እንደገጠመው የሚናገረው ዶክተር ሳሙኤል “7 ዓመትና ከዚያ በላይ ጊዜያቸው፣ ጉልበታቸው እንዲሁም የቤተሰብ እና የህዝብ ሀብት የፈሰሰበትን የሙያ ዘርፍ ባለሙያዎች እንዲተዉ መሆኑ የሙያተኞችን ብክነት የሚያሳይ ነው” በማለት ኃሳቡን ይገልፃል። 

“እነዚህ ባለሙያዎች ህዝባቸውን ለማገልገል አቅሙና ችሎታው እያላቸው ለሙያቸው የተቀመጠው ክፍያ ዝቅተኛ በመሆኑ ከሙያቸው ውጪ መስራትን እንደ አማራጭ ይጠቀማሉ” እንደ ዶ/ር ሳሙኤል አስተያየት። 

በኢትዮጵያ አንድ የህክምና ዶክተር የሚሰጠው አገልግሎት ለሃያ ሺህ ዜጎች እንደሚደርስ በቅርብ የተደረገ ጥናት ያስረዳል። ይህም በዓለም ጤና ድርጅት መሰረት 2.3 ዶክተሮች ለአንድ ሺህ ሰዎች መድረስ እንዳለበት ከተቀመጠው መለኪያ እጅግ ያነሰ ነው።

ባለሙያዎች የሚጠብቁትና መሬት ላይ ያለው እውነታ

ያሬድ በ2012 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኤሌክትሪካል እንጂነሪንግ የተመረቀ ሲሆን አሁን በጋዜጠኝነት እየሰራ ይገኛል። ያሬድ ስለሚነሳው የሙያተኞች ብክነት ሲናገር “ለዚህ ችግር ቅድሚያ ተጠያቂ የማደርገው መንግስትን ነው። ምክንያቱም መንግስት ለወጣቱ የስራ ዕድል የመፍጠር ግዴታውን እየተወጣ አይደለም” ይላል።  

አሁን ከሚሰራበት የተሻለ ክፍያ ካላገኘ በስተቀር በኢንጂነሪንግ የሙያ ዘርፍ የመስራት ፍላጎት እንደሌለው የሚናገረው ያሬድ “ከመንግስት በተጨማሪ ከሙያተኞቹ ከራሳቸው የሚመጣ ችግር አለ። ይህም በዩኒቨርሲቲም ሆነ በኮሌጅ ወደ አንድ የሙያ ዘርፍ ከመቀላቀላቸው በፊት ስለሚመርጡት የሙያ ዘርፍ በቂ ግንዛቤ የላቸውም፤ ከገቡም በኋላ ሙያውን ይጠሉታል፣ ውጤታማም አይሆኑም” በማለት ይገልጻል።

ሌላኛው ከአዲስ ዘይቤ ጋር ቆይታ ያደረገው የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ባለሙያው አብርሃም ሲናገር “ያላቸውን ቅሬታ ሲገልጹ፣ 'ኢንጅነሪንግ ኩራት እንጂ እራት አይሆንም' የሚሉት የኢንጅነሪንግ ባለሙያዎች ስራ ቢያገኙ እንኳን የሚያገኙት ገቢ ከሚሰሩት ስራ ጋር ስለማይመጣጠን በሰለጠኑበት ሙያ ላይ ያላቸው እምነትና ተስፋ እየደበዘዘ ይሄዳል” ይላል።

እንደ ዶክተር ሳሙኤል ገለፃ  “አንዳንድ ሰዎች አንድን የሙያ ዘርፍ ገንዘብ እናገኝበታለን ብለው ከገቡ በኋላ እንደጠበቁት ስለማያገኙት ሙያውን ትተው ይወጣሉ፤ ይህም ለሀገርም ሆነ ለባለሙያው ትልቅ ብክነት ነው” ይላሉ። በተጨማሪም ሙያተኞቹ ባጠኑት የሙያ ዘርፍ የመስራት ፍላጎት ቢኖራቸዉም የመሰረተ ልማት እጥረት፣ጦርነት እና አለመረጋጋት ሰዎች በተማሩት የሙያ ዘርፍ እንዳይሰሩ እንቅፋት ይሆናሉ። 

የቅጥር መስፈርት

“አሁን አሁን ሙያዊ እውቀትና ዝግጁነት አስፈላጊነቱ እየቀረ የመጣ ይመስላል” የሚለው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በህግ ተመርቆ ከሙያው ውጪ በሆነ ስራ ተሰማርቶ የሚገኘው ኩራባቸው ተገኝ (ስሙ የተቀየረ) ነው። 

ሁሉንም ተወዳዳሪ ሙያተኞች እኩል የመወዳደር እድል እንዲያገኙ ከሚያስችሏቸው መንገዶች መሀከል አንዱ ግልጽ ማስታወቅያ በማውጣት አቅምን መሰረት ያደረገ የውድድር ስነ-ስርአት መዘርጋት መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም። 

የስራ ቅጥር ሁኔታው የሀገርና የቤተሰብ ሀብት አባክኖ፣ ግለሰቡ የተመረቀበትን ሙያና የግለሰቡን ወቅታዊ ብቃት ከቁብ የማይቆጥር እንደሆነ የሚናገረው ኩራባቸው “ዛሬ ስራ የሚገኘው ባለህ የግንኙነት መስመር ልክ ነው። አቅም ብዙም አይታይም። በስንት አሳር የሚሰበሰበው እውቀት ዋጋ የሚያገኘው ከቀጣሪው ጋር በሚኖርህ ዝምድና ወይም ቅርርብ ልክ ነው” ይላል። 

ሆኖም በአንዳንድ የመንግስትም ሆነ የግል ተቋማት ተቀጣሪዎች የመጀመርያ ዲግሪ ተመራቂ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ዶክመንት ከተማሩበት ተቋም ገና ሳይወስዱ ከቀጣሪዎቻቸው ጋር ባላቸው የግንኙነት መረብ ብቻ ያለፈተና የሚገቡበት አጋጣሚ እንዳለ ሰዎች ሲናገሩ ይደመጣሉ። 

በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየቱን ያጋራን ኩራባቸው በበኩሉ “ሰዎች ከቀጣሪዎቻቸው ጋር ባላቸው የግንኙነት መረብ ብቻ ስራ እንዲገቡ እየተደረገ ስለሆነ በሙያችን ተወዳድረን ለመስራት አልቻልንም፤ በዚህም ምክንያት በሌላ ሙያ ተሰማርተን እንዲንሰራ እየተገደድን ነው” በማለት ባለሙያዎች የሚገጥማቸውን ሌላኛውን ተግዳሮት ያስረዳል። 

በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ከአዲስ ዘይቤ ጋር ቆይታ ያደረጉ ባለሙያዎች አብዛኞቹ በዚህ እውነታ ላይ ይስማማሉ። ግለሰቦች ባላቸው የግንኙነት መረብ ስራ የመቅጠር አድሏዊ ከመሆኑ በላይ ለሙያዎችም ሆነ ለሀገር የሚፈይደው ነገር እንደሌለም አፅዕኖት ሰጥተው ይሞግታሉ።

የትምህርት ፖሊሲ

የትምህርት ፖሊሲያችን ከተለያዩ የውጭ ሀገራት የተቀዳ እና የሀገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያላስገባ እንደሆነ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣሉ። 

በዚህ ጉዳይ ላይ ዶክተር ሳሙኤል ኃሳቡን ሲገልፅ “ የትምህርት ፖሊሲን ጨምሮ ፖሊሲዎቻችን የተኮረጁ በመሆናቸው በሀገሪቱ በትምህርት ስርዓት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ከማስከተላቸውም ባሻገር ሰዎች በሙያቸው ስራ እንዲያጡ እና ከሙያቸው ውጭ ተሰማርተው እንዲሰሩ የራሱ የሆነ አስተዋጽዖ ያደርጋል” ይላል። 

አቶ ቢኒያም ከዲላ ዩኒቨርሲቲ በአንትሮፖሎጂ የትምህርት መስክ ተመርቆ በግል ትምህርት ቤት ውስጥ በሳይንስ መምህርነት እየሰራ የሚገኝ ወጣት ነው። እንደ ቢኒያም አገላለጽ የትምህርት ፖሊሲው በየትኛው የስራ መስክ ምን ያህል የተማረ የሰው ኃይል እንደሚያስፈልግ ታስቦ የተዘጋጀ ባለመሆኑ የባለሙያ ብክነት ፈጥሯል። “እኔና ጓደኞቼ ከተመረቅን አራት ዓመት ቢሆነንም በአንትሮፖሎጂ ስራ ማግኘት አልቻልንም። የስራ ዕድል በሌለበት የትምህርት መስክ ለምን አስተማሩን?” በማለት ይጠይቃል። 

“ዩኒቨርሲቲው መድቦኝ ነው እንጂ የጂኦግራፊ ትምህርት ምርጫዬ አልነበረም። ነገር ግን ለወላጆቼ ስል ተመርቄያው” የምትለው ወ/ት መዲና ሐሰን በአሁኑ ሰዓት የሜክአፕ ባለሙያ ናት። “ፍላጎቴ ቴአትር መማር ነበር። በተመደብኩበት የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱ ሰለማይሰጥ ያለ ፍላጎቴ በሙያው ተማርኩ” በማለት እንደሷ ብዙዎች በማይፈልጉት የሙያ መስክ እንዲሰለጥኑ መገደዳቸው የፖሊሲው ችግር እንደሆነ እንደምታምን መዲና ትገልጻለች።

ከዓመታት በፊት 'የስራ ዕድል ፈጠራ' በሚል የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች በዩኒቨርሲቲዎች በመገኘት ለተመራቂ ተማሪዎች ስለ ድንጋይ ንጣፍ (ኮብል ስቶን)፣ ስለ ዶሮ እርባታና መሰል የስራ ዓይነቶች ያደረጉት ንግግር በወቅቱ ብዙ ትችት ማስከተሉ ይታወሳል። እንዲያውም “የተማረ ይጥረበኝ አለች ኮብል ስቶን” እየተባለ እስከመተረትም ተደርሷል።

ዛሬ ላይ ባለው ከፍተኛ የስራ ማጣት ችግር የተነሳ አንዳንዶች በሙያቸው እስከሚቀጠሩ ድረስ “ስራ መፈለጊያ ይሆነኛል” በማለት ሌሎች ደግሞ የተሻለ ደሞዝና ጥቅማጥቅም ፍለጋ የሰለጠኑበትን ሙያ ትተዋል። በዚህም የተማሪ፣ የወላጅና የሀገር ጊዜ፣ ተስፋ፣ ኃብትና ጉልበት የወጣበት እውቀትና ስልጠና ባክኖ እየቀረ ነው።     

መፍትሄዎችስ ምንድን ናቸው? 

ዶክተር ሳሙኤል እንደ መፍትሄ የሚጠቁመው የኢትዮጵያ የትምህርት ፖሊሲ ከስራ እና የሙያተኞች ብክነት ጋር ተያይዞ ለሚነሳበት ችግር እልባት ለመስጠት የትምህርት ስርዓቱን ማስተካከል ያለበት ሲሆን በመሰረተ ልማት አጥረት ሙያቸውን ትተው ወደሌላ የሙያ ዘርፍ እንዲገቡ ለሚገደዱ ሙያተኞች ደግሞ መንግስት በተቻለው መጠን እነዚህን አቅርቦቶች ሊያሟላ ይገባል። 

“የሙያተኞች ብክነት የሚመነጨው ተማሪዎች በአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቆይታቸው የትኛውን የሙያ ዘርፍ መቀላቀል እንዳለባቸው አያውቁም፤ የትምህርት ስርዓቱም ይህንን ችግር እንዲቀርፉ አይረዳቸዉም። ስለሆነም የትምህርት ስርዓቱን ከማስተካከል ባሻገር ወላጆች ልጆቻቸው በምን የሙያ ዘርፍ መሰማራት እንደሚፈልጉ መከታተል አለባቸው” የሚለው ደግሞ  የኢንጅነሪንግ ባለሙያው ያሬድ ነው። 

ያሬድ አክሎም ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲ ከመግባታቸው በፊትም ሆነ ከገቡ በኋላ በምን አይነት የሙያ ዘርፍ መሰልጠን እንዳለባቸው ከዘርፉ ባለሙያዎች ምክር ያስፈልጋቸዋል፤ ይህም ወደ ሚፈልጉትና ወደፊት ዉጤታማ ሊያደርጋቸው ወደሚችል የሙያ ዘርፍ እንዲገቡ ያግዛቸዋል በማለት መፍትሄ ያለውን አስቀምጧል። 

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተለይም ዩኒቨርሲቲዎች የመፍትሄው አካል መሆን እንዳለባቸው ብዙዎች የሚስማሙበት ኃሳብ ነው። ዩኒቨርሲቲዎች ሙያተኞቻቸው ባጠኑት የሙያ ዘርፍ ተሰማርተው ራሳቸዉን፣ ወገናቸውን እንዲሁም ሀገራቸውን ለመጥቀም ከተለያዩ ቀጣሪ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት በመፍጠር የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ ማድረግ ያለባቸው ጥረትም ሌላው የሚነሳ የመፍትሄ አቅጣጫ ነው።

አስተያየት