ጥቅምት 24 ፣ 2015

በሲዳማ ክልል በመንግስት ሆስፒታሎች የሚሰሩ ሃኪሞች ከነሐሴ ወር ጀምሮ ደመወዝ አልተከፈለንም አሉ

City: Hawassaጤናማህበራዊ ጉዳዮች

በሲዳማ ክልል በሚገኙ የመንግስት ሆስፒታሎች ውስጥ በወጪ መጋራት አስራር (Matching Fund) አማካኝነት በተሰጣቸው ኮታ መሰረት 100 ሀኪሞች ተቀጥረው በመስራት ላይ ይገኛሉ

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

በሲዳማ ክልል በመንግስት ሆስፒታሎች የሚሰሩ ሃኪሞች ከነሐሴ ወር ጀምሮ ደመወዝ አልተከፈለንም አሉ
Camera Icon

ፎቶ፡ ከማህበራዊ ሚዲያ የተገኘ (ቅሬታ አቅራቢዎቹ ሃኪሞች ከሚያገለግሉባቸው ተቋማት አንዱ አዳሬ አጠቃላይ ሆስፒታል)

ሐዋሳ ከተማን ጨምሮ በሲዳማ ክልል በሚገኙ ወረዳዎች ውስጥ በመንግስት ሆስፒታሎች እየሰሩ የሚገኙ የህክምና ባለሞያዎች ከነሐሴ ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ መከፈል የነበረበት ደመወዝ ባለመከፈሉ ለችግር ተጋልጠናል ብለዋል።

ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ መንግስት ተመራቂ ሐኪሞችን ምደባ በማቆሙ እና በዚህ ምትክ ደግሞ ክልሎች የህክምና ባለሞያውን አወዳድረው እንዲቀጥሩ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው እንደነበር ይታወቃል። ነገር ግን ክልሎች በበጀት እጥረት እና በሌሎች ምክንያቶች የህክምና ባለሞያዎችን መቅጠር አልቻሉም። በዚህ ምክንያት ስራ አጥ ሀኪሞች ሰላማዊ ሰልፍ እስከመውጣት መድረሳቸዉ ይታወሳል። 

ይህንን ችግር ለመፍታት እንዲቻል የጤና ሚኒስትር ከአጋር ድርጅቶች እና ከክልሎች ጋር በመቀናጀት ተመርቀው የተቀመጡ የህክምና ባለሞያዎችን በሚገኙበት ክልል ለመቅጠር የመፍትሔ ሀሳብ አቅርቧል። ይህም “Matching Fund” (ወጪ መጋራት) ይባላል። 

ይህ አሰራር የሃኪሞችን የስራ ማጣት ለተወሰነ ዓመታት ሊቀርፍ ይችላል የተባለ ሲሆን ለሶስት ዓመትም የሚዘልቅ ነው። 

ከዛሬ ስድስት ወር ገደማ በሲዳማ ክልል በሚገኙ የመንግስት ሆስፒታሎች በዚሁ የወጪ መጋራት አስራር (Matching Fund) አማካኝነት በተሰጣቸው ኮታ መሰረት 100 ሃኪሞች ተቀጥረው በመስራት ላይ ይገኛሉ። 

በሲዳማ ክልል በሚገኙ ማለትም በአዳሬ፣ ይርጋዓለም፣ ለኩ፣ ሀዌላ ቱላ፣ ቡርሳ እንዲሁም ዳዬ የመጀመሪያ እና አጠቃላይ ሆስፒታሎች፤ ሃኪሞቹ ተቀጥረው የሚሰሩባቸው የህክምና ተቋማት ናቸው። 

ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸዉ እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሃኪሞች በተለይ ለአዲስ ዘይቤ እንደሚናገሩት ከነሐሴ 2014 ዓ.ም ጀምሮ ደሞዝ እንዳልተከፈላቸዉ እና ለሚመለከተው አካል በጉዳዩ ላይ ጥያቄ ቢያቀርቡም “ታገሱ” የሚል ምላሽ እንደሚሰጣቸዉ ገልፀዋል።

ከ 7 ወር በፊት የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ አዳዲስ ሀኪሞችን ለመቅጠር ባወጣዉ ማስታወቂያ መሰረት 120 ሀኪሞች በክልል ደረጃ ውጪ መጋራት (Matching Fund) በሚል ደመወዝ እንዲከፈል እንዲሁም ሌሎች ጥቅማጥቅሞች በሚሰሩባቸው ሆስፒታሎች እንዲሸፈን ተስማምተው ወደ ስራ መግባታቸውን ቅሬታ አቅራቢዎቹ ተናግረዋል።

በተከታታይ ለ5 ወራቶች ደሞዛቸው ሲከፈላቸዉ ቆይቶ ከሐምሌ 2014 ዓ.ም ጀምሮ ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጥቅምት 22 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ደመወዛቸው አለመከፈሉን ያስረዳሉ። 

በዚህ ምክንያት “ከትርፍ ሰዓት ክፍያ ውጪ ተጨማሪ ገቢ ባለመኖሩ እንዲሁም የኑሮ ዉድነቱ በየጊዜው እየጨመረ በመምጣቱ ስራና ህይወታችንን ከባድ አድርጎታል” ይላሉ። 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ለትርፍ ሰዓት ስራ የማይከፈልባቸዉ የህክምና ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ሀኪሞች በብድር ኑራቸውን እንዲገፉ መገደዳቸዉን ገልፀውልናል።

የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሰላማዊት መንገሻ በተለይ ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገሩት “ከፌዴራል ጤና ሚኒስትር ጋር በተገባው በወጪ መጋራት (matching fund) ውል መሰረት የተቀጠሩ ሀኪሞች እስከ ሐምሌ ወር ድረስ ያለዉ ክፍያ መከፈላቸውን ገልፀዉ ነገር ግን ከነሐሴ ወር ወዲህ ያለውን ክፍያ በጀት ባለመኖሩ ምክንያት ሊዘገይ ችሏል” ብለዋል።

“እንደ ሲዳማ ክልል ኮታ የተሰጠን 126 ሀኪሞችን እንድንቀጥር ነዉ። ነገር ግን ሊቀጠር የቻለዉ 100 ብቻ ነው። ምክንያቱም እንደ ስራ ፈላጊው ይወሰናል” የሚሉት ዶክተር ሰላማዊት “የጤና ሚኒስትር ኮታ ለሰጣቸዉ ሀኪሞች በጀት ይመድባል። በዚህ ምክንያት እስከ ሐምሌ ድረስ ክፍያ ፈፅመናል” ብለዋል።

ይህ ችግር የተፈጠረዉ በሲዳማ እና በድሬዳዋ በሚገኙ የጤና ተቋማት ላይ ሲሆን በሌሎች ክልሎች የበጀት እጥረቱ አልተከሰተም። ምክንያቱ ደግሞ ክልሎች በጤና ሚኒስትር እንዲቀጥሩ የሚቀመጥ ኮታ ያለ ሲሆን ይህንን ቁጥር ታሳቢ ያደረገ በጀት እንዲመደብ ይደረጋል። በሌሎች ክልሎች ላይ ችግሩ ያልተፈጠረበት ምክንያት ከኮታቸዉ በታች ስለቀጠሩ ክፍያዉን በዚያው ማካካስ ስለቻሉ እንደሆነ ይነገራል።

“በመሃከል የተቋረጠዉን በጀት በሚመለከት ለሰራተኞቹ ደመወዝ እንዲከፈላቸው እንደ ክልሉ ጤና ቢሮ ስራ እየሰራን ነው። ከፌዴራል ወደ ፋይናስ ገንዘብ ስለተላከ በጥቂት ቀናት ዉስጥ እንዲከፈላቸው ይደረጋል” ሲሉ የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሰላማዊት መንገሻ ለአዲስ ዘይቤ ገልጸዋል።

አስተያየት