ጥቅምት 23 ፣ 2015

በ1 ነጥብ 4 ቢልየን ብር እየተገነባ የሚገኘው የኢትዮጵያ ረጅም ድልድይ በእዚህ ዓመት እንደሚጠናቀቅ ተገለፀ

City: Bahir Darዜናወቅታዊ ጉዳዮች

ፕሮጀክቱ የዘገየባቸው ምክንያቶች የወንዝ ሙላት ለሥራ አመች አለመሆኑ፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና ድልድዩ ላይ የተደረገው የዲዛይን ማሻሻያ ናቸው

Avatar: Abinet Bihonegn
አብነት ቢሆነኝ

አብነት ቢሆነኝ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ምሩቅ ሲሆን። ዜና እና የተለያዩ ዘገባዎች የመፃፍ ልምድ አለው። አሁን በአዲስ ዘይቤ የባህር ዳር ሪፖርተር ነው

በ1 ነጥብ 4 ቢልየን ብር እየተገነባ የሚገኘው የኢትዮጵያ ረጅም ድልድይ በእዚህ ዓመት እንደሚጠናቀቅ ተገለፀ

ባሕር ዳር ከተማ ውስጥ እየተገነባው ያለው የአባይ ወንዝ ድልድይ በእዚህ ዓመት ሰኔ ወር ላይ እንደሚጠናቀቅ ተገለፀ። ሀምሌ 2011 ዓ.ም የተጀመረው ድልድዩ ከ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ በጀት ተይዞለት አየተሰራ የሚገኝ ሲሆን ሰኔ ወር 2015 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።

በሦስት ዓመታት ይጠናቀቃል ተብሎ ቢጠበቅም የነበረው ፕሮጀክቱ ከተሰጠው ጊዜ በላይ በመውሰድ እስካሁን መጠናቀቅ አልቻለም። ለእዚህ ምክንያቱ ደግሞ በክረምት ወቅት የሚፈጠረው የወንዝ ሙላት ለሥራ አመች አለመሆኑ፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና ድልድዩ ላይ የተደረገው የዲዛይን ማሻሻያ እንደሆኑ የፕሮጀክቱ ተጠሪ መሃንዲስ ኢንጂነር ፍቅረሥላሴ ወርቁ ገልፀዋል።

አሁን ላይ የድልድዩ ግንባታ ጥራቱን በጠበቀ መልኩ እየተፋጠነ እንደሚገኝ የተናገሩት ኢንጂነር ፍቅረስላሴ፤ ድልድዩ በአይነቱ እና በርዝመቱ በሀገሪቱ የመጀመሪያው እንደኾነ እና ለባሕር ዳር ከተማ ተጨማሪ ውበትን የሚያላብስ ይሆናል ብለዋል።

380 ሜትር ርዝመት እና 43 ሜትር የጎን ስፋት ወይም በአንድ ጊዜ ስድስት መኪኖችን ማሳለፍ የሚችል ሆኖ እየተገነባ የሚገኘው ድልድዩ የእግረኛ መንገድ እና የብስክሌት መተላለፊያ እንዳለው ማወቅ ተችሏል። እስካሁን ከዋናው የድልድዩ አካል ውስጥ 321 ሜትር የሚኾነው መጠናቀቁን ኢንጂነር ፍቅረሥላሴ ተናግረዋል።

የድልድዩ ግንባታ ተጨማሪ 111 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦ “ዓለም በደረሰበት ቴክኖሎጅ የታገዘ” እና ለድልድዩ ልዩ ውበት የሚያላብስ የመብራት ቴክኖሎጅም ጎን ለጎን እየተገጠመለት እንደኾነ የፕሮጀክቱ ተጠሪ ገልፀዋል።

ወደ ድልድዩ ለመውጣትና ለመውረድ የሚያገለግሉ አራት ማሳለጫዎችም እየተገነቡ የሚገኝ ሲሆን እንደ ኢንጂነር ፍቅረሥላሴ ገለፃ 4 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ወደ ድልድዩ መዳረሻ መንገድም ጎን ለጎን እየተገነባ ይገኛል።

አስተያየት