ጥቅምት 22 ፣ 2015

በጅግጅጋው ጥቃት ህይወቷ ያለፈው የዶ/ር ጁዌሪያ እህት እግሯ በህክምና እንዲቆረጥ ተደረገ

City: Addis Ababaዜናወቅታዊ ጉዳዮች

የፎዚያ ልጅ የሆነችው ሻዲያ አብዱላሂ በጎ ፈንድ ሚ ሂሳቡ ላይ እንደፃፈችው “የእናቴን የረጅም ጊዜ ህልም እውን ያደርጋል ብለን ያሰብነው ጉዞ በ72 ሰዓታት ውስጥ አስደንጋጭ ሆኗል”

Avatar: Ilyas Kifle
ኤልያስ ክፍሌ

ኢልያስ ክፍሌ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን የመፃፍ ልምድ አለው። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

በጅግጅጋው ጥቃት ህይወቷ ያለፈው የዶ/ር ጁዌሪያ እህት እግሯ በህክምና እንዲቆረጥ ተደረገ
Camera Icon

Credit: Addis Zeybe

ጥቅምት 15 ቀን 2015 ዓ.ም. ከሰዓት በጅግጅጋ ገራድ ዊልዋል አየር ማረፊያ በጥበቃ ስራ ላይ የነበረ የፖሊስ አባል በከፈተው ተኩስ የአንድ ሰው ህይወት ማለፉን የክልሉ ፓሊስ አስታወቆ ነበር። በጥቃቱ ህይወታቸው ያለፈው ዶ/ር ጃዌሪያ ሱብዒስ የተባሉ የክልሉ ምክር ቤት አባልና የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስ ፋኩልቲ ዲን የነበሩ ሴት ናቸው።

በጥቃቱ ከአንድ ሰው ሞት በተጨማሪ ሌሎች ሶስት ሰዎች መቁሰላቸውን የክልሉ ፖሊስ ያስታወቀ ሲሆን የቆሰሉት ሰዎች ቁጥር ወደ ዘጠኝ እንደሚደርስ አዲስ ዘይቤ ከምንጮቿ መረዳት ችላ ነበር። በጥቃቱ ተጎድተዋል ከተባሉ መካከል የሟች ጁዋሪያ ሱብዒስ እህት የሆነችው እና ከረጅም ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ቤተሰቦቿን ይዛ የመጣችው እህቷ ፎዚያ ሙሴና ቤተሰቦቿ የጥቃቱ ሰለባዎች ሆነዋል ተብሏል። 

የሶማሌ ክልል ምክር ቤት እና የብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆነችው የሁለት ልጆች እናቷ ዶክተር ጁዌሪያ ሱብዒስ በተከፈተው ተኩስ ወዲያው ህይወታቸው ሲያልፍ እህቷ ፎዚያ በህይወት ተርፋ ወደ ሆስፒታል ገብታ ነበር። 

የፎዚያ ህክምና እስካሁን ባለው ደረጃ በጥቃቱ ወቅት የተጎዳው አንድ እግሯ ከህክምና አቅም በላይ በመሆኑ እንዲቆረጥ በባለሙያዎች ተወስኗል። ለተሻለ ህክምና የተለያዩ ሆስፒታሎችን የጎበኘችው ፎዚያ ሙሴ የመጨረሻ ውሳኔው አካል ጉዳተኛ የሚያደርጋት ሆኗል። ከፎዚያ ጋር ከነበሩት ቤተሰቦቿም ወንድሟ እና አንድ ልጇ በጥቃቱ በጥይት ከተመቱት መካከል ነበሩ።የፎዚያ ልጅ የሆነችው ሻዲያ አብዱላሂ ለእናቷ የእርዳታ ማሰባሰቢያ በተከፈተው የ  Go Fund Me ገፅ ላይ “የእናቴን የረጅም ጊዜ ህልም እውን ያደርጋል ብለን ያሰብነው ጉዞ በ72 ሰዓታት ውስጥ አስደንጋጭ ሆኗል” ብላለች። 

በጥቃቱ ሁለት ጊዜ በጥይት የተመታችው ፎዚያ ሙሴ በአሜሪካ ሜይን በተባለ ስፍራ በማህበረሰብ አገልግሎቶች ክብር እና ዝና የተቸራት ናት። በ13 ዓመቷ ወደ አሜሪካ የተጓዘችው ፎዚያ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የመጣችው ጅግጅጋ የሚገኙትን እናቷን ለመጠየቅ የነበረ ቢሆንም በጅግጅጋ አየር ማረፊያ የተፈጠረው ክስተት እህቷን ነጥቋት እሷንም አካል ጉዳተኛ አድርጓታል። 

የጥቃቱ ሰለባዎችን ወደ አሜሪካ ለመመለስ እንዲሁም በጥቃቱ ህይወታቸው ያለፈውን የዶክተር ጅዌሪያ ልጆችን ኑሮ ለማገዝ የድጋፍ ማሰባሰቢያ ሂሳብ ተክፍቶ ከመላው ዓለም እርዳታ እየተሰበሰበ ይገኛል።

የተሻለ ህክምና የሚያስፈልጋት ፎዚያ ሙሴን በፍጥነት በአየር አምቡላንስ ወደ ጆን ሆፕኪንስ ሆስፒታል ለመውሰድ 178 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በማስፈለጉ 200 ሺህ ዶላር ለማሰባሰብ የታቀደ Go Fund Me ሂሳብ ተከፍቷል። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስም 82 ሺህ ያህል ዶላር መሰብሰብ እንደተቻለ ታውቋል።   

በአሜሪካ ሜይን ግዛት የሚገኙ ስደተኞችን ማቀራረብ እና ማስተባበር ላይ የሚሰራ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅትን የምታስተዳድረው ፎዚያ ሙሴ የደረሰባት ጉዳት በመኖሪያ አካባቢዋ ህብረተሰብ ዘንድ ከፍተኛ ድንጋጤ መፍጠሩን “ሜይን ቤከን” የተሰኘ ጋዜጣ አስነብቧል።

የሶማሌ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ድርጊቱን የፈፀመው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን እና የምርመራው ውጤት ይፋ እንደሚደረግ በጥቃቱ ወትት ገልፆ ነበር። አንድ ሳምንት ባስቆጠረው ጥቃት ዙሪያ እስካሁን ይፋ የተደረገ ውጤት የለም።

አስተያየት